ለትግራይ ዘላቂ ሠላም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል!

ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶሪያ በተካሄደው የሠላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ እልባት አግኝቷል፡፡ የተደረሰው ስምምነት ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም፣ ርዳታ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማስጀመርና የሀገሪቱን የግዛት አንድነት እንዲሁም ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት እንዲከበር የማድረግ ዓላማ ነበረው።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ከያዛቸው አንኳር ጉዳዮች አንዱ ‘ኢትዮጵያ አንድ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ብቻ ነው ያላት’ የሚለው ጉዳይ ነው። በዚሁ መሠረትም የኢትዮጵያ ፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች “በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም የፌደራሉን ተቋማትና አየር ማረፊያዎችንና አውራ ጎዳናዎችን ጨምሮ ዋነኛ መሠረተ ልማቶችን” ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር መብትን ያረጋግጣል።

ይህንኑ መነሻ በማድረግም በትግራይ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት እና የማቋቋም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ትግራይን ጨምሮ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታትም 371 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ይህም የፕሪቶሪያውን ስምምነት ወደ ተሟላ ትግበራ ለማስገባት ከማስቻሉም በላይ በትግራይ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ይታመናል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ዘላቂ ሠላም ለማስገኘት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል፡፡ በተለይም መንግሥት በጦርነቱ በእጅጉ የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና ጦርነቱ ያሳረፈበትን ሥነልቦና ለማከም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባዔው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልዑክ ነበር። ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሠላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል።

የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንዲጀመር ከማድረግ ባሻገር ከሁለት ዓመታት በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከራሱ በጀት ቀንሶ አያሌ ተግባራት አከናውኗል። የሠላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በመጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስመጀር ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል።

ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል የተደረገውን ጥረት ከግቡ ለማድረስ በተለይም ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚጠበቀው የፋይናንስ ድጋፍ በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ ታጣቂዎችን ወደ ሠላማዊ ሕይወት የመመለሱ ሥራ በሚጠበቀው ፍጥነት ሊፈጸም አልቻለም፡፡ ይህ ደግሞ የተጀመረው የሠላም ጥረት በሚፈለገው መልኩ ውጤት እንዳያመጣ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡

ሆኖም ይህ ሁኔታ ግን አንድ ቦታ ማብቃት አለበትና አሁን ላይ ታጣቂዎችን ወደ ሠላማዊ ሕይወት የመመለሱ ተግባር ተጀምሯል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በሠላም የመኖር እና የመልማት መብት እንዳለው በመገንዘብ ሁሉም ለዚሁ ስኬት ሊተባበር ያስፈልጋል፡፡ ብልጭ ድርግም የሚለው የሠላም ሁኔታ ተሻሽሎ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ የሠላም አየር በክልሉ ሊነፍስ ይገባል፡፡ ክልሉ ለበርካታ ዘመናት ያህል በጦርነት የተጎዳ በመሆኑ የመሠረተ ልማት እጥረት እና የምግብ ዋስትና ችግር የሚስተዋልበት ነው፡፡

ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ዘላቂ ሠላም ወሳኝ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በጦርነት እና በግጭት የሚጠፋ ጊዜ፤ ሀብት እና የሰው ሕይወት መኖር የለበትም፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፤ የሃይማኖት አባቶች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል!

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You