አዲስ አበባ:- በኢትዮጵያ ሴቶች በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸው ውክልና እያደገ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን “ሴቶች በዲፕሎማሲው መስክ” በሚል መሪ ቃል ሴት ዲፕሎማቶች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ትናንት አካሂዷል። በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደገለጹት፤ በዓለም ታሪክ ሴቶች በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ አስተዋፅዖ አድርገዋል። ዲፕሎማሲ ሀገር የሚወከልበት የሥራ ዘርፍ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ።
ሴቶች በዲፕሎማሲው መስክ በሙሉ አቅም በመሥራት ለዓለም ትልቅ አስተዋፅዖ አድርገዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በኢትዮጵያ ሴቶች በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸው ውክልና እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሴቶች ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚው መስክ በስፋት በማሳተፍ የሴቶችን ሚና የማሳደግ ሥራ ስለመሠራቱ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያን ወክለው በሀገርና ከሀገር ውጭ በዲፐሎማሲው መስክ የሚሠሩ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም ይበልጥ ለማሳደግም እየተሠራ ነው፡፡ ይህም የፆታ እኩልነት ከማረጋገጥ በላይ አቅማቸውን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ አምባሳደር ብርቱኳን ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማቲክ ተቋሞቿ ውስጥ የሥርዓተ ፆታን ውክልና ለማሻሻል በርካታ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። ሴቶች የመሪነት ሚና እየተጫወቱና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ እየተሳተፉ ነው። ሆኖም ግን የታሪክ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ብዙ ሥራዎች አሉ፤ ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ትብብርን ይጠይቃል ፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ባለው ጊዜ ሴቶችን በዲፕሎማሲው መስክ በማሰማራት ጥሩ ልምድ እንዳላት አውስተው፤ አሁንም ተተኪ ወጣት ሴት ዲፕሎማቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ የሴቶችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ተናግረው፤ መሻሻሎች ቢኖሩም ያልተፈቱ ችግሮችን መኖራቸውን በመግለጽ፤ በዲፕሎማሲ ውስጥ የሥርዓተ-ፆታ ፍትሐዊነትን ለማስፈን ዓለም አቀፍ ጥረቶች እንዲጠናከሩ አሳስበዋል፡፡
በታሪክ ሴቶች በዲፕሎማሲ ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ አሁንም ወጣት ዲፕሎማቶች በዓለም መድረክ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው። ይህን ሚናቸውን ለማጠናከር የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሴቶች በአመራርነት፣ በግጭት አፈታት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ትግልና በሌሎች ዘርፎች ያላቸውን የጎላ ሚና ለማጠናከር በዲፕሎማሲው ዘርፍ በስፋት ማሳተፍ ይገባል ብለዋል።
ቀጣዩን ትውልድ በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ተሳትፎ እንዲኖረው ጠንካራ ሥራ መሥራት ይገባናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሴቶች በዓለም መድረክ ያላቸው ተሳትፎ በትውልድ ቅብብሎሽ እያደገ እንዲሄድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሞገስ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም