ዜና ሐተታ
በጉብታማ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎች ይሰበሰባሉ፤ በጉብታማ አካባቢዎቹ ትይዩ በሚገኙት ረባዳማና ሜዳማ ቦታዎች ደግሞ የተንጣለለ የስንዴ ቡቃያ ይታያል። የጉድጓድ ውሃ የሚቆፍሩ ትልልቅ ማሽኖችም ቱምቢያቸውን ወደ መሬት ተክለው ውሃ ያስሳሉ። እነዚህ የጉድጓድ ውሃ ማውጫ መሣሪያዎች እስከ አሁንም 7 የውሃ ጉድጓዶችን ቆፍረው ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል።
በወርሐ ኅዳር በወልመራ ወረዳ የመኸር አዝመራን መሰብሰቡ የተለመደ ቢሆንም የስንዴ ቡቃያ ማየት ግን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሰውም እንግዳ ነገር ነው። ወልመራ፤ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኝ አነስተኛ ወረዳ ነች። ሕይወታቸውን በግብርና ሥራ የሚመሩ 17 የገጠር ቀበሌዎች አሏት። ከእነዚህ ውስጥ ገበያ ከምሳ እና ፋሌ ቱሉ ራዳን ቀበሌዎችን ጨምሮ በድምሩ አራት ቀበሌዎች በረባዳማውና የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ ይገኛሉ።
እነዚህ ቀበሌዎች በክረምት ወራት አብዛኛው የእርሻ ቦታቸው ውሃ ስለሚተኛበት የመኸር ሰብለን ለማምረት ሲቸገሩ ኖረዋል። አርሶ አደሮች ከመስከረም ወር በኋላ መሬታቸው ላይ የተኛው ውኃ ጠፈፍ ሲልላቸው እንደ ጓያ፣ ሽንብራ፣ ምስር የመሳሰሉትን በመዝራት ነበር ሕይወታቸውን የሚገፉት። የበጋ ስንዴ ንቅናቄ እንደ ሀገር ከተጀመረ በኋላ ግን የእነዚህ መንደር አርሶ አደሮች የአሠራር ዘይቤያቸውን ለውጠዋል።
የፋሌ ቱሉ ራዳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አበበ በቀለ ‹‹ለዘመናት ማሳችን ላይ ተኝቶ አላሳርስ ሲለን የነበረውን ውሃ አሁን በሁለት መንገድ እየተጠቀምንበት እንገኛለን። በመጀመሪያ ሰፋፊ የውሃ ማቆሪያ ጉድጓዶችን በመቆፈር ወደ አንድ ቦታ እንዲጠራቀም ካደረግን በኋላ እርሻችንን እንጀምራለን። የበጋ ስንዴን እየዘራን የተጠራቀመውን ውሃ እናጠጣለን። የተጠራቀመው ውሃ ሲያልቅ ደግሞ ክልሉ ያስቆፈረልንን የከርሰ ምድር ውሃ እየተጠቀምን በዓመት ሁለት ጊዜ እናመርታለን›› ይላሉ።
አቶ አበበ አራት ሄክታር መሬታቸውን ይዘው በፋሌ ቱሉ ራዳ አርሶ አደሮች ልማት ማኅበር አባል በመሆን ከ440 አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም እርሻ ስንዴን በማምረት ላይ ይገኛሉ። በዚህ የአስተራረስ ዘዴም ምርታማነታቸው እንደጨመረ ሕይወታቸውም እንደተለወጠ ይገልጻሉ።
አቶ ለታ ዳባ ሌላው የፋሌ ቱሉ ራዳ አርሶ አደሮች ልማት ማኅበር አባልና የበጋ ስንዴን አምራች ናቸው። ድሮ ወቅትን ጠብቀው የሚዘሯቸው እንደ ሽንብራ ጓያና ምስርን የመሳሰሉት ሰብሎች ብዙም ሕይወታቸውን እንዳልቀየሩላቸው ይናገራሉ። ስንዴን ማምረት ከጀመሩ በኋላ ግን ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ እንደመጣ ይገልጻሉ።
አካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል መኖሩ ውሃን ከጉድጓድ እየሳቡ ቡቃያቸውን ለማጠጣት ጭምር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናልም ይላሉ። በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲያመርቱም አድርጓቸዋል። የግብርና ባለሙያዎች የሚያደርጉላቸው ክትትልና እገዛም ለውጤታማነታቸው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተላቸው ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ።
የማዳበሪያ እጥረት ቢቀረፍላቸውና የመንገድ መሠረተ ልማት ቢጠናከርላቸው ከዚህም በላይ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።
የወልመራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጋሪ በወረዳዋ አንድ ሺህ 25 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን ለመዝራት እቅድ ተይዞ እስከ አሁን በአንድ ሺህ 24 ሄክታር መሬት ላይ መዘራቱን ይገልጻሉ። ከዚህም ውስጥ አብዛኛው የሚገኘው በዚሁ የፋሌ ቱሉ ራዳ የገጠር መንደር ነው። ለአርሶ አደሩ ሥልጠና እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመሠራቱ የስንዴ ምርትን ማሳደግ እየተቻለ ነው። ከድህነት ለመውጣትና በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እውን ለማድርግ ኩታ ገጠም እርሻን መተግበርና የባለሙያዎችን ምክር መፈጸም የአርሶ አደሩ የየእለት ተግባር ሊሆን ይገባል ይላሉ። አርሶ አደሩ ይህንን በማድረጉም የወረዳው ምርታማነት እያደገ መምጣቱን ያስረዳሉ።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም