በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ አደጋዎች እንደነበሩ፤ እንዳሉና ለወደፊቱም ሊኖሩ እንደሚችሉ በቀደሙት ሁለት ተከታታይ ዝግጅቶች ተገልጿል:: ኢትዮጵያውያን በእንዲህ ዓይነት የአደጋ ጊዜያት ከእርስ በእርስ ጋር እንዴት እንደሚቆሙ ባለፈው ዝግጅት ባጭሩ አይተናል:: በዚህ ዝግጅት የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ሲከሰት የታዩ ክፋቶችን፤ ባንጻሩ የተከናወኑ የደግነት ሥራዎችንና ለወደፊቱ የሚጠበቁብን ነገሮችን በጥቅሉ እናነሳለን::
ኮሮና ቫይረስ ያመጣውን አደጋ እንደ ዕድል በመጠቀም በቤት ኪራይ ዙሪያ ችግር የፈጠሩ፤ ሸቀጦችንና የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ የሰቀሉ፤ ተፈላጊና መሠረታዊ ሸቀጦችን የደበቁ፤ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመደባለቅ ያቀረቡ፤ የመጠቀሚያ ጊዜ የተላለፈባቸውን ነገሮች የሸጡ፣ የሚሸጡና ሌሎች መሰል እኩይ ድርጊቶችን የፈፀሙ ዜጎች ተስተውለዋል:: እነዚህ በግልጽ የታዩ ናቸው:: ያልታዩና በድብቅ እየተፈፀሙ ያሉም ይኖራሉ:: በቤት ኪራይ ዙሪያ የተነሳውን ብቻ ለማሳያ እናንሳ::
አንዳንድ ሰዎችና ቤተሰቦች “ኮሮና ቫይረስን ታመጡ ብናላችሁ” ብለው ተከራዮችን ቤት እንዲለቁላቸው ጠይቀዋል የሚል ዜና በተለያዩ ሚዲያዎች በቅብብሎሽ ተላልፎአል:: ይህ ለብዙዎች አስደንጋጭ ነበር:: ከመቸውም ይበልጥ በጋራ በመቆም የወረርሸኑን አቅም መስበር በሚገባበት ጊዜ ተከራዮችን ሂዱልን ማለት ከሕግ፤ ከሞራል፤ ከሃይማኖትና ከዜግነት አንጻር ያሳስባል:: የሰው ልጆችን የተፈታተኑና የሚፈታተኑ ብዙ ነገሮች ነበሩ፤ ሊኖሩም ይችላሉ:: በአንዲህ ዓይነት ጊዜ በራስ ወዳድነት ሌላ ያልታሰበ ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች ይኖራሉ:: ሰው ራሱን ይወዳል:: ራስን በአግባቡ መውደድ ክፋት የለውም:: ድንበሩን የሚያወቅ ራስወዳድነት የሌላውን መብትና ነጻነት አይጋፋም፤ ክብርና ፍላጎት አይደፍርም፤ ሰላምና ደህንነት አይነሳም:: ገደብ የሌለው ራስ ወዳድነት ግን “እኔ ወይም የእኔ ብቻ” ስለሚል የሌሎችን መብትና ጥቅም፤ ክብርና ፍላጎት፤ ሰላምና ነፃነት ይፈታተናል:: ለተጠቀሰው ችግር ምክንያት ሊሆን የሚችለው ራስ ወዳድነት ይህ ዓይነቱ ነው::
ፍርሃትም ሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል:: ኮሮና ቫይረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን አሽመደመዳት:: ይህ የዓለምን ሕዝብ ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ከቶታል:: ሕይወት ነውና መፍራት አግባብ ነው:: ከምንም በላይ ለራሳቸው የሚፈሩ ሰዎች ይኖራሉ:: ለቤተሰባቸው፤ ለልጆቻቸውና ለዘመዶቻቸው የሚጨነቁም አሉ:: ለሀገር፤ ለሕዝብና ለዓለማችን ሲሉ የሚሰጉም እንዲሁ:: ይህ ተገቢ ፍርሃት ነው:: ተገቢ ያልሆነው ፍርሃት ግን “ጉዳት ይደርስብኛል” ብሎ ወገንን ወደ አደጋ የሚገፋ ነው::
ፍርሃትን መቋቋም ከሰው ሰው ይለያል:: አንዳንዱ በጣም ይረበሻል፤ ይበሳጫል፤ ይጨናነቃል:: ይህ ሰው የፍርሃት ስሜቱን መቆጣጠር አይችልም:: አንዳንዱ ፍርሃቱን በምክንያት መቆጣጠር ይችላል:: ፍርሃቱን የሚቆጣጠር ራሱን ያረጋጋል:: ከውሳኔ የሚደርሰውና እርምጃ የሚወስደው አውጥቶና አውርዶ፤ ጥቅምና ጉዳትን፤ ትርፍና ኪሳራን፤ መልካምና መጥፎውን ለይቶ ነው:: ስለዚህ እርምጃው የተመዘነ ይሆናል:: በዚህ ጊዜ “ቤት ልቀቁልን” የሚሉ አከራዮች የፍርሃት ስሜታቸውን በምክንያት መቆጣጠር የማይችሉ ናቸው:: የተዛባ ውሳኔ አስተላልፈዋል:: ከሕግም ሆነ ከማሕበራዊ ደንቦች፤ ከግብረገብና ከሥነ-ምግባር መርህዎች አንጻር የተዛባ ውሳኔ ያስተላልፋሉ::
ችግሩ መታየት የሚኖርበት ከአካራዮች ራስወዳድነትና ፍርሃት አንጻር ብቻ መሆን የለበትም:: በተከራዮችም ዘንድ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ:: አንዳንዶቹ ዲስፒሊንና መልካም ስብዕና የሌላቸው፤ “እንዳስፈለገንና እንዳሰኘን መሆን እንችላለን” የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ:: በራሳቸው የግል ጉዳይ የተጠመዱ፤ ያለ ሰዓት ወጥተው የሚገቡ፤ ጠጥተውና ተሳክረው የሚያስቸግሩ፤ በተለያዩ ሱሶች የታሰሩና ሌሎች መሰል ጠባዮች ያሉባቸው ሊሆኑ ይችላሉ:: እነዚህ ለኮሮና ቫይረስ ራሳቸውንና ሌሎችን በቀላሉ የሚያጋልጡ ናቸው:: በዚህ ምክንያት ሰግተው ቤት ልቀቁልን ያሉ አከራዮች ቢኖሩ እውነት አላቸው::
መፍትሔው ግን “ቤት ልቀቁልን” ማለት አይደለም:: የጭንቅ ቀን ሁሉም ሰው ለእያንዳንዱ፤ እያንዳንዱም ሰው
ግር እንኳ ቢፈጠር በምክንያታዊ ንግግር መፍታት ይቻላል:: ሰው ለሰው መድኃኒት መሆኑ የሚታወቀው በመከራ ጊዜ ነው:: በተለይ በኮሮና ቫይረስ ባሕርይ አንጻር ለራስ ማሰብንና ለሌላ ማሰብን ለያይቶ ማየት አይቻልም:: ሰው በአካልም በመንፈስም አንድ የሆነበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው – በኮሮና ምክንያት:: ለራሱ ተገቢውን ጥንቃቄ ያደረገ ሌላውንም ሰው ሆነ ሀገርን ያድናል:: ፈታኝ ሁኔታ በማይኖርበት ጊዜ ሁሉም ሰው ያው ሰው ነው:: ጦርነት በሌለበት ቦታ ማን ጀግና፤ ማን ፈሪ እንደሆነ መለየት ያስቸግራል:: ፈተና ከሌለ የሰው መልካምነት ወይም መጥፎነት፤ ርህሩህነት ወይም ጨካኝነት አይታወቅም:: ሰብአዊ ባሕርይ ነጥሮ የሚወጣው የጭንቅ ቀን ነው:: “አለሁልህ፤ ከጎንህ ነኝ፤ አብረን ነን፤ ተጋግዘንና ተደማምጠን፤ ያለንን ተካፍለንና ተጋርተን ፈተናውን እናልፋለን” የሚባባሉበት ጊዜ ነው::
ከላይ የቀረቡት እኩይ ድርጊቶች በደግነቱ መክቶ ያጨናገፋቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው:: ምስጋና ይገበዋል:: ከላይ ድርጊቶቹን በመቃወም የሕዝብ፤ የመንግሥት፤ የሚዲያ፤ የበጎ ፈቃደኛና የቅን ዜጎች ድምፅ ከጫፍ እስከ ጫፍ አስተጋባ:: በጎ አድራጊ ዜጎች፤ ተቋሞች፤ ኩባኒያዎች፤ አክሲዮኖች፤ ባንኮች፤ ማሕበራት፤ የመከላከያ ሠራዊት፤ ባለሀብቶች፤ የከተማ ነዋሪዎች፤ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ባለሙያዎች፤ ወጣቶች ተረባርበው አረገቡት:: በሕዝባችን ውስጥ ያለው ግብረገብና ሥነምግባር አቁጥቁጠው ኢ-ግብረገብና ኢ-ሥነምግባር የደቀኑብንን መጥፎ አደጋዎች ገፈውልናል::
ከወጣቶች እስከ አዛውንቶች፤ ከተራ ዜጎች እስከ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ ከግለሰብ እስከ ተቋማትኩባኒያዎች፤ ባንኮች፤ ድርጅቶችና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑትን ሁሉ ያካተቱ መጠነ-ሰፊ የበጎ ፍቃድና እርዳታ እንቅስቃሴዎች ተደረጉ፤ እየተደረጉም ነው:: እጅግ ብዙ የአልባሳትና የመጠለያ፤ የምግብና የገንዘብ፤ የአስቤዛና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለሚያስፈልጉአቸው ወገኖች ተበረከቱ:: በዚህ ርብርብ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለወገኖቻቸውና ለሀገራቸው የሚቆረቆሩ ደጋጎች መሆናቸውን አስመስክረዋል:: በወረርሽኙ ምክንያት ለጊዜው በአካል መራራቅ የግድ ቢሆንም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሞራልና መንፈስ፤ በገንዘብና በቁሳቁስ አንድ ላይ በመቅለጥ እኩይ ድርጊቶችን መክቶአል፤ እየመከተም ነው::
መልካም ትምህርቶችና ተሞክሮዎች
የኮሮና ቫይረስ ከሁለት ጎራዎች አንዱን ያስመርጠናል – የመፍትሔ ወይም የችግር አካል መሆን:: መምረጥ የሚኖርብን ሀገራችንና ሕዝባችንን የሚያድነውን ነው – ያም የመፍትሔ አካል መሆን ነው:: ይህ ቢቻል የሁላችን አሊያም የብዙዎቻችን ምርጫ ነው:: የችግሩ አካል መሆንን የመረጡና የሚመርጡ ጥቂቶችም ይኖራሉ:: ደግነቱ በቁጥር ጥቂት ናቸው:: የሚያደርሱት ችግር ቀላል ባይሆንም በብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካምነት የሚመከት ነው::
ፈተናውን ወደ ዕድል እንለውጥ:: የታዩ በጎ ተግባሮችና ፈቃደኝነት መቀጠል አለባቸው:: በሀገራችን በርካታ መልካም ነገሮች በሆነ ምክንያት ይፈጠራሉ:: መቀጠል ሲገባቸው ይቋረጣሉ:: ይህ ድክመት ነው – ከኛ ጋር መቀጠል የሌለበት ድክመት:: መልካም ተሞክሮዎች፤ ድርጊቶችና ባሕርያት ይበልጥ ተጠናክረውና ተቀናጅተው የበጎ ባሕል ማበልጸጊያ መሆን አለባቸው:: የተፈጠረው መልካም ነገር የሚጠፋው መልካምነትን የማንነት አካል ካለማድረግ ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ የመረዳዳት ፍላጎትም ሆነ አቅም አላጣም:: ያጣው ይህን በጎ ፈቃድ የሚመራ ሕጋዊና ተቋማዊ አካል ነው:: የፖለቲካ ሥርዓቶች የሕዝብን መረዳዳትና መተጋገዝን ስለሚፈሩ እምቅ ኃይሉን ለማደራጀት ፍቃድ አልነበራቸውም:: በዚህ ብቻ በቀላሉ የማይገኝ አቅምና ፀጋ ሲባክን ኖሯአል::
በየጎዳናው የአዛውንቶችና የእናቶች፤ የሕጻናትና የአቅመ-ደካሞች፤ የወጣቶችና የልጆችን መከራ ማየት ልብ ይሰብራል:: ሰዎች ለመርዳት ብለው ሳንቲሞች ሊሰጡአቸው ይችላሉ:: ይህ መሠረታዊ መፍትሔ አያመጣም:: ችግሩን ያባብስ እንደሆን እንጂ አይፈታም:: የእያንዳንዳችን ልብ እነዚህ ወገኖች በዚያ መልክ መኖር መቀጠላቸውን አይፈቅድም:: የሁሉም ፍላጎት በክብር እንዲነሱ ነው:: መሠረታዊ መፍትሔ የሚያመፕሮጄክት በሚያስተማምን መንገድ መቅረጽ ያስፈልጋል:: ሁሉም ዜጋ ለዚህ መልካም ተግባር በጽናት እንደሚቆም እምነታችን ነው:: ብዙዎች ለበጎ ስራ አስተዋጽኦ ማድረግ እየፈለጉ መንገዱ ጠፍቶአቸው ይቸገራሉ:: በባለቤትነት የሚመራ ሕጋዊና ሀገራዊ ተቋም መስርቶ ወገኖችን ትርጉም ባለው መንገድ ማቋቋም የእያንዳንዱ ዜጋ ግብረገባዊ፤ ሃይማኖታዊ፤ ዜግነታዊና ሰዋዊ ግዴታ ነው::
ዜጎች የመንግሥት ግብር እንደሚከፍሉ ሁሉ በጎዳና ላይ ያሉትን ዜጎች ለማቋቋም ከእያንዳንዱ ፈቃደኛ ገቢ በቋሚነት በፐርሰንት ገንዘብ በመቁረጥ በቀላል መንገድ ታላቅ ሀገራዊና ትውልዳዊ ሥራ መስራት ይቻላል:: “ከእያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ብር ይሰብሰብ” እንኳ ቢባል ባንድ ጊዜ ከ100 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ፈንድ ይፈጠራል:: ጥቅሙ ወገኖችን ከማቋቋም ባሻገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፤ ማሕበራዊና ባሕላዊ አቅም ለሀገር የሚፈጥር መሆኑም ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተፈጠረውን መልካምነት፤ በጎ አድራጊነትና በጎ ፈቃደኝነት እንዲቀጥል ይፈልጋል:: ይህ ፍላጎቱን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ከሚተላለፉ መልእክቶችና አስተያየቶች ማረጋገጥ ይቻላል:: ይህ እድል መባከን የለበትም:: የመንግሥት ተቋማት፤ የሲቪክ ማሕበራትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል::
ኢትዮጵያ በጣም ግዙፍና ውስብስብ ችግሮች አሉባት:: በዚያው ልክ ግዙፍ የሰው ኃይል አላት:: አብዛኛው የሚገኘው በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ ነው:: ችግሮቹ በመደበኛ ሥራና እንቅስቃሴ ብቻ የሚቀረፉ፤ በተወሰኑ ወገኖችና ተቋማት አቅም ብቻ የሚገፉ አይደሉም:: ወጣቶች በቅድመ-ኮሮና ጀምረው የሚያሳዩት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተገቢ ቅርጽ፤ መዋቅርና እውቅና አግኝቶ መቀጠል አለበት:: በጎ ፈቃደኝነት የሚፈጠረው ፍቅርና ደግነት፤ አክብሮትና አስተዋይነት፤ የባለቤትነት ስሜትና የግዴታ መንፈስ ሲኖር ነው:: ለበጎ መርህዎችና ግቦች ራስን ማስገዛት የሚችል ዜጋ ለራሱ ሳይሰስት ሌላውን በነፃ ማገልገል ይመርጣል:: ስለዚህ ኢትዮጵያ በወጣቶችዋ በጎ ፈቃድና በሕዝብዋ በጎ አድራጎት እንድትታገዝ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው::
የሀገሪቱን የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ ለልማት ማዋል ከሚቻልባቸው፤ ችግሮች ከሚቀረፉባቸውና ሀገራዊ አቅም ከሚገነባባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ይህ ነው:: በጉልበት ሥራ ብቻ የሚፈቱ በርካታ ችግሮች አሉ:: በጎ አድራጎት ሲባል የገንዘብና የቁሳቁስ ብቻ አይደለም:: ጉልበትና ዕውቀት፤ ክህሎትና ጥበብ፤ መስራትና መገንባት፤ መንከባከብና ማፅዳት ሁሉን ያካትታል:: ከእነዚህ በአንዱ እንኳ መሳተፍ የማይችል ወገን ቢኖር ቢያንስ አንድ ማድረግ የሚችለው ነገር አለ – መጥፎ ነገር ከመሥራት መታቀብ:: ሆን ብሎ የችግር አካል ከመሆን መታቀብ በራሱ የመፍትሔ አካል መሆን ነው:: ለዚህ ግዙፍ ሀብት ሕጋዊና ተቋማዊ መዋቅር ፈጥሮ መንቀሳቀስ የግድ ይላል::
የድህረ-ኮሮና ገጽታችን ምን ሊመስል ይችላል?
አሁን ካለንበት ሁኔታ ተነስተን አዎንታዊ ትንበያ ማድረግ ይከብዳል:: ቁመናችን የሚያመላክተን በአብዛኛው አሉታዊ ነው:: ኃያላን መንግሥታትን በአጭር ወራት ውስጥ ያሽመደመው ወረርሽኝ ለኛ የተለየ ምሕረት ያደርጋል ብለን አንጃጃልም:: ስለዚህ ኢትዮጵያ በድህረኮሮና የሚኖራት ሁኔታ እጅግ ያሳስባል:: በተወሳሰቡ ችግሮች ታጅቦ የሚመጣውን ጊዜ “ረሃብና ቸነፈር ይዘሃልና አትምጣብን” ማለት አንችልም:: መምጣቱ የግድ ነው – አማራጭ ስለማይገኝለት:: ጥያቄው “ፈታኙ ድህረኮሮናን ተቀብሎ ለማስወገድ ዛሬ ምን ይደረግ?” የሚል ነው::
የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውታል – የጦርነት፤ የወረርሽኝ፤ የረሃብና የድርቅ ወዘተ:: ግዙፍ የሕይወት፤ የአካልና የሀብት መስዋዕትነት ከፍሎአል፤ በተለይ ጦርነቶችን በድል አድራጊነት ተረማምዶአቸዋል:: ያሁኑ ፈተና ግን የተለየ ነው:: ብዙና ውስብስብ ተፈጥሮአዊና ሰዋዊ ተግዳሮቶች በተለያዩ ግዝፈቶችና አቅጣጫዎች ባንድ ጊዜ በዓለምአቀፋዊ፤ ሀገራዊና አካባቢያዊ ስብጥር አፋጠውናል:: ችግሮቹ እርስ በእርስ እየተመጋገቡ አንዱ ለሌላው ጉልበት የሆነበት ሲናሪዮ ፈጥረዋል:: አሁን የሚኖረን አጀንዳ ፈተናውን ድል የሚነሳ ሀገራዊ አቅም መፍጠር እንችላለን ወይስ አንችልም፤ መልሱ በኢትዮጵያ ሕዝብ አእምሮና እጅ ውስጥ ነው፡፡
በዓለም ላይ ያሉ መልካም ነገሮችን ሁሉ ይዘን ባንድ ላይ ከቆምን ፈተናውን ሰብረን እናልፋለን እንጂ አንሰበርለትም:: የምንጠየቀው መስዋዕትነት ግን ከባድ ነው:: ከወዲሁ የምናደርገው ዝግጅት ለዚህ የሚመጥን መሆን አለበት:: የሚፈጠሩት ተግዳሮቶች ብዙ ቢሆኑም በኢኮኖሚና በፖለቲካ ረገድ ያሉትን በመጠኑ እንያቸው::
በኢኮኖሚ ረገድ የሚያስመካ አቅም የለንም:: ለዘመናት ያከማቸነው ሀብትን ሳይሆን ድህነትን ነው:: እንደ መልካም ነገር ትውልዶች ሲቀባበሉ የኖሩት ክፋትና ጥፋትን ነው:: ያለው ኢኮኖሚም ቢሆን በኋላቀርነትና ባለአዋቂነት፤ በጦርነትና በትርምስ፤ በቸልተኝነትና በደንታ ቢስነት፤ በስንፍናና በሙስና፤ በብክነትና በስደት ሲጠቃ ኖሮአል:: ግዙፍ የሆነ ስራ-አጥነት አለ:: ወረርሽኙ ደግሞ ዓይን ያረፈባቸውን ሴክተሮች እየተፈታተነ ነው:: ፈተናው ገና ያለበቃ በመሆኑ የሚያስከፍለንን ዋጋ መገመት ያስችግራል:: በጥቅሉ መጠነ-ሰፊ ረሃብና ከፍተኛ የመዋዕለ ነዋይ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል:: በተለይ በምግብ እጦት የከፋ አደጋ እንዳይደርስብን ብዙ መሠራት አለበት:: የሚባክን ሀብትና ጊዜ፤ ጉልበትና ዕውቀት መኖር የለበትም::
እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ግን የፖለቲካችን አቅምና አቋም ነው:: ሀገራችንና ሕዝባችን ቶሎ ማገገም የሚችሉት ፖለቲካችን ፍጹም እምርታዊ ለውጥ ካደረገ ነው:: እስካሁን ከነበሩበት ፊውዳላዊና ቡድናዊ፤ ግላዊና ስሜታዊ መንፈሶች መጽዳት ይኖርበታል:: ከጥንት ጀምሮ ጎልቶ የሚታይበት ሞትና ውድቀት፤ ጉዳትና ክፋት ነው:: ዋና ምክንያቱ የፖለቲካ ሥልጣን ይዞ “ማን ማንን ይመራል?”፤ “ማን በማን ይመራል?” የሚለው ጥያቄ በአግባቡ አለመመለሱ ነው:: ግለሰቦችና ቡድኖች ሰፈርን፤ ነገድን፤ ብሔር-ብሔረሰብን፤ ቋንቋን፤ እምነትን፤ ርዕዮተዓለምንና የመሳሰሉትን መሠረት አድርገው የፈጠሩአቸው የፖለቲካ ሥርዓቶች ለተጠቀሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት አልቻሉም:: ውጤቱም ውድቀት እንጂ ስኬት፤ ጉዳት እንጂ ጥቅም፤ ጥፋት እንጂ ልማት አልሆነም::
ከተደቀነብን ከባድ ፈተና አንጻር ፍጹም የሆነ የአስተሳሰብና የባሕርይ ለውጥ ከፖለቲከኞቻችን እንጠብቃለን:: ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብና ባሕርይ ይዘው እንደገና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት መቅረብ የለባቸውም:: በአስተሳሰብ የት እንዳሉ ለማወቅ ቆም ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው:: “ይህችን ሀገር አለማናት ወይስ አጠፋናት?” ፤ “የመራነውን ሕዝብ ከፍ አደርግነው ወይስ አወረድነው፤ አረካነው ወይስ አሰቃየነው?፤ “ስንቴና ለምን ያህል ጊዜ ነው ይኸን ሕዝብና ይህችን ሀገር የምናደማው፤ ስንቴና ለምን ያህል ጊዜ ነው ለሀገርና ለሕዝብ ካንሰር ሆነን የምንኖረው?”፤ “እኛስ በሰራነው የፖለቲካ ስራ ዘላቂ ጥቅምና ክብር አገኘን? ጥቅምም ክብርም ካላገኘን – ለምን? ለምን? ለምን?” ብለው ራሳቸውን ይጠይቁ:: ራሳቸውንና ውጤታቸውን የሚያዩበት መስታወት ይሆናቸዋል:: ራሳቸውን ካልዋሹ በቀር ለጥያቄዎቹ አዎንታዊ መልስ አያገኙም:: የተጎዳ እንጂ የተጠቀመ ማንም የለም::
ከተግባር የሚበልጥ ማረጋገጫ የለም:: ሀገርን ለመምራት ዕድል ያገኙ ነገር ግን ዕድሉን በምግባረብልሹነት ሀገርን ስለጎዱበት ሕዝብ በየጊዜው ገፍትሮ ጥሏቸዋል:: አሁንም በዚያው በአሮጌ ሴራና ጉራ እያቅራሩ ነው:: ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ ንቃተሕሊናው እንደቀደማቸው መረዳት አለባቸው:: እንደ በፊቱ አይጭበረበርላቸውም:: አሁን የሕዝብ መንግሥት መፍጠር የሚያስችል ሕሊናዊ ሁኔታ ተፈጥሯአል:: በፖለቲካው ዓለም የመቆየት ፍላጎት ካላቸው የሚበጃቸው ለሕዝብ መንግሥት መፈጠር አስተዋጽኦ ማድረግ ብቻ ነው:: ፖለቲካችን ተቀርቅሮ ከኖረበት አረንቋ የማውጣት ወይም ከባሰበት አረንቋ ውስጥ የመቀርቀር ዕድል አሁን በእጃችን ላይ ነው:: ከመጀመሪያው እንጂ ከሁለተኛው ምርጫ ማንም ምንም አያተርፍም:: ታሪካችን ይህን አረጋግጦልናል:: ቢቻል ሁላችንም አሊያም ብዙዎቻችን የመፍትሔ አካል እንሁን:: ይህን ካደረግን ኢትዮጵያ ፈርጀ-ብዙ ድል ትቀዳጃለች:: ወረርሽኙን እንደ ችግር ሳይሆን እንደ ዕድል እንየው:: ከፈተናው በላይ የሚውል ሀገራዊ ማንነት ለማነፅ ይረዳል:: ነጥረን ለመውጣት መደማመጥና መናበብ፤ መቀናጀትና መደራጀት፤ ክፋትና ሴራን ማስቀረት አለብን::
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ጠና ደዎ(ፒ.ኤች.ዲ