የሳይንስ ፈጠራ ሥራ በተለይም በሥነ ጽሑፍና በእሱው ጥላ ሥር ባሉት ሥራዎች ውስጥ ምን ማለት ነው፤ ምንስ ፋይዳ አለው፤ በማንና ምንስ ላይ ያጠነጥናል? እና የመሳሰሉት ብዙ ጊዜ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ ለውይይት የሚቀርቡና የሚያጨቃጭቁ ጉዳዮች ናቸው። ማጨቃጨቃቸው ሊያወዛግብ አይገባም። ለምን? በፈጠራ ዓለም ሁል ጊዜ ውይይት፣ ሁል ጊዜ ፈጠራ፣ ሁል ጊዜ ንባብ፤ ሁል ጊዜ ምርምር ወዘተ እንጂ ስለአንድ ጉዳይ የመጨረሻ ማጠቃለያ ሰጥቶ ቁጭ ብሎ ነገር የለም። ያ ከሆነ ውጤቱም ተያይዞ ቁጭ ነው።
ምንም እንኳን በሁለት (“Hard sci-fi” እና “Soft sci-fi”) የሚከፈል ቢሆንም፤ “ሳይ-ፊክ” በሁለተኛው ክፍለ ዘመን (AD) በሶሪያዊው ስላቅ ጸሐፊ ሉሺያን “A True Story” አማካኝነት ወደ እዚህ ምድር የመጣ መሆኑ ቢነገርለትም ከዘመናዊነት አኳያ ደግሞ ማዕረጉን ሌላ ወስዶት እናገኘዋለን። በተለይ የሳይ-ፊክ ወርቃማ ዘመን ወደ ተባለው አብርሆት ዘመን ስንመጣ የዘርፉን መመንደግ የምንመለከት ሲሆን የወቅቱ ተጠቃሽ ጸሐፍትና ሥራዎቻቸውም New Atlantis በፍራንሲስ ቤከን (1627)፣ Somnium በዮሐንስ ከፕለር (1634)፣ እና Comical History of the States and Empires of the Moon በሲራኖ ዴ ቤርጌራክ (1657) ሆነው የምናገኛቸው ሲሆን የሁሉም ትንበያና ህልም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለፀገች፣ ሰዎች ከችግር የተላቀቁባት ዓለም ተፈጥራ ማየት ነበር፤ Utopia።
የሳይንሳዊ ልቦለድ አባት ተብሎ በሚታወቀው H.G. Wells በመካከለኛው ዘመን ብቅ ስላለው ሳይንሳዊ ልቦለድ -”Science fiction”- ሲነሳ ለማንኛውም ሰው ጥያቄ ሆነው የሚቀርቡት “ምንድን ነው እሱ?”፤ “ስለምንድን የሚያስተምር /የሚተርክ ሥራ ነው?”፤ “ከሌሎቹ በምን ይለያል?” የሚሉ ናቸው። ትክክል ነው።
በዘርፉ አንቱ የተባሉ ኔይል ጌይማ፣ ዴቪድ ዌበር እና የመሳሰሉትን ያፈራው ይህ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ለጽንሰሀሳቡ በርካታ ብያኔዎች ተሰጥተውት እናገኛለን።
እስከዛሬ ባሉት አዋቂዎች ስምምነት ላይ የተደረሰበት ብያኔና ማብራሪያ ቢኖር የሳይንስ ልቦለድ /ጽሑፍ ከሌሎቹ ልዩ መሆኑ፤ ሁለት ነገሮችን በአንድ ጊዜ ማስኬድ/ ማከናወን ማስቻሉ፤ ወሳኝ ወቅታዊ ጉዳዮችን በቀጥታና ጥበባዊ ስልት ማቅረቡ፣ በገድል የተሞላ፣ ሲፈልግ ሰማየ ሰማያት፣ ሲፈልግ ደግሞ እንጦሮጦስ የመውረድ አቅም ያለው፤ በሁለንተናዊ ጭብጥ ላይ መመስረቱ፣ በዘይቤ የታሸና የተዋዛ፣ አጠቃላይ ይዘቱ ሰብአዊ መሆኑ… ልዩ ሲያደርገው፤ በተለይ ወጣቶችን አሁን ላይ ቆመው የወደፊቱን እንዲያማትሩ፣ አማትረውም ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ምን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያስቡ ማድረጉ፣ አዕምሯቸውን ለፈጠራ ማነቃቃቱ፣ ከአሁኑ የተሻለ ዓለም እንዲመለከቱና እንዲመኙ (Utopia)፣ ለዚያም ተግተው እንዲሠሩ ማድረጉ፤ ከጠባብ ክብ ወጣ ብለው ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን እንዲመለከቱና በዚያው ልክም እንዲያስቡ፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዲመራመሩና ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽ እንዲያፈላልጉ፣ መፍትሄዎችን እንዲያፈልቁ፣ ክንውኖቹ በእውኑ ዓለም የሌሉና የራሳቸውን ዓለም ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው፤ የህዋ እና ጊዜ ትኩረቱን መሳቡ ሁሉ ልዩ ያደርገዋል።
የሳይንሳዊ ፈጠራ፤ በተለይም የፊልሙ ዓለም ሥራ ተንባይ ነው፤ ተንባይነቱም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀት ላይ የተጠመደ ሲሆን ይህም በዚህ መስክ የወደፊቷን ዓለማችንን መምጠቅ /መዝቀጥ፤ በተለይም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ከፍና ዝቆችን ለማሳየት ይጠቀምበታል። የዚህ አላማውም ሰዎች አሁን የሏቸውን ክፍተቶች እንዲደፍኑ፣ እነሱም ሆኑ ማህበረሰቡ፤ ባጠቃላይም ዓለም ወዴት እየሄደች እንደሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡና እራሳቸውን እንዲያስተካክሉ ማስተማሩ፤ ገፀባህሪያቱ ከቴክኖሎጂ ጋር ሲባዛ የተፋቀሩና ከሱው ውጭ ህይወት ያለ የማይመስላቸው ወዘተ መሆኑ ከሁሉም የፈልም /ሙቪ ፆታዎች ይለየዋል።
በአሁኑ ዘመን የጥበብ ዓለም ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ተወዳጅነትን እያገኘ በመሄድ ላይ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ የትኩረት አቅጣጫው ማለትም በፍቅር፣ አየር ንብረት ለውጥ፣ መፃኢ ዕድልን መተንበይ /ማመላከት፣ ጓደኝነት፣ ህብረተሰባዊነት፣ አብሮ መሥራት፣ ጥሩ እና መጥፎን ለይቶ ማመልከት ላይ እና ሌሎች በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወዘተ ማጠንጠኑ ተጠቃሽ ነው። በተለይ ነገሮችን፣ ክስተቶችን ምንም አይነት ዝንፈትም ሆነ የተጠያቃዊነት ችግር ሳይታይባቸው ማቅረቡ፤ የአቀራረቡ አማላይነት፣ ያለንና ጥቅም ላይ ያልዋለን የተፈጥሮ ሀብት ፈልፍሎ በማውጣት ማሳየቱና እንዴት ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ማስረዳቱ ነው። መብራሪያውን እናብቃና ወደ “በሳይ-ፊክ የፈጠራ ሥራዎች አማካኝነት ምን ምን ተተነበየ?” ወደ እሚለው እንሂድ። (በነገራችን ላይ ሆን ተብሎ አስቀድመው በፊልም እንዲወጡ በማድረግና ዘግየት ብለው ወደ ሥራ የሚተረጎሙትን፤ የሴራ ንድፈ ሀሳብ አካል የሆኑትን እዚህ ላይ አደባልቆ መመልከት ስህተት ነው፤ ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። ለይቶ ለማየት ደግሞ ከፍተኛ ፍተሻን ይጠይቃል።)
በወቅቱ የወደፊቱን ያመላከተው የዳይሬክተር ስታንሌይ ኩብሪክ “Stanley Kubrick 2001: A Space Odyssey” (1968) ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ስለመዋሉ (እውን ስለመሆኑ) የተመሰከረለት ሲሆን እነ”iPad”ና የመሳሰሉትን አስቀድሞ የተነበየው ይሄው ፊልም ነበር። የጆርጅ ሉካስ “Star Wars” (1977)ም ወደ እውነት ከተቀየሩት አሜሪካዊ ሳይንስ ፊልሞች አንዱ ነው።
ዊሊያም ጊብሰን በሳይ-ፊክ አማካኝነት የወደፊቱን በመተንበይ በኩል ከተዋጣላቸው ሁሉ በቀዳሚነትና የላይነቱ የተመሰከረለት ሲሆን፤ በፊልሙ ዓለም፤ በተለይ የመጪውን ዘመን ቴክኖሎጂ መተንበይ በኩልም “Back to The Future Trilogy” (1985)፣ “Star Trek Series” (1966)፣ “Star Wars Series” (1977)፣ “Minority Report” (2002)፣ “The Smart House” (1999)፣ “Total Recall” (1990)፣ “The Terminator” (1984)፣ “The Running Man,” (1987)፣ እና ሌሎች በርካቶችም በዕለት ተዕለት የዘርፉ ውይይት ወቅት ፈጥነው የሚጠቀሱ የዚያ ማዶ ፊልም ሥራዎች ናቸው።
በዓለማችን በተንባይነቱ የሚታወቀው ፈረንሳዊው አስትሮሎጀር Michel de Nostredame (December 1503–July 1566) ሲሆን የወደፊቱን የተነበየባቸው፤ 942 አርኬዎችን የያዘው “Les Prophéties” መጽሐፉ ተጠቃሽ፤ ተወዳሽ ነው።
ከማጠቃለላችን በፊት ትንበያ በሰው ልጅ ሥራ ውስጥ በተለያዩ መስኮች ያለ ሲሆን፤ ሊሆንም ላይሆንም የሚችል እንጂ እንደ መጽሐፍ ቅዱሶቹ ነቢያት (ትንቢተ ኤርሚያስ፣ ትንቢተ …) ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። እርግጥ ነው፤ አንዳንዱን ሲያዩት ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚተናነስ አይመስልም። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ከከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊና የአስተሳሰብ ጥልቀት፤ ብቃትና ልቀት ነውና ያስደምማል። ለዚህ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ የሀገራችንን ብላቴን ጌታ እንጥቀስና በዛው እንውጣ። ልብ እንበል ግጥሙ (“አቅ” (የወላድ ሮሮ))ን የፃፈው በ1969 ዓ.ም ነው። እንዲህ ይላል:
የሰው ትንንሽ ሰው ብዬ
አዳኝ እንዳስወረዳት ወፍ፣ ስንቱን ግም እንቁላል ጥዬ
ሀሳብ-ፈጠር የዘር ድርጭት፣ አያ ድብልብል ደብልዬ
እንደቀልዱ እንቆቅልሽ ዚቅ፣ ዘጠኝ ስንዝሬ ፈልፍዬ
በዘጠኝ ትንንሽ አምባ፣ የተስፋ ቅሪት እየሳልኩ
በየቴሌቪዢኑ ላይ፣ አቅ! ሲሉ እኔም ጉድ! እያልኩ *
ለነገ ሰው ብሩህ ፋና አደረስኩ ስል አደረሰስኩ፤….
ይኸው ጉዴን የማርያም ልጅ፣ ዘጠኝ ፍርክስክስ አቅ! ወለድኩ።
(ፀጋዬ ገብረ መድህን)
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ግርማ መንግሥቴ