ውድ አንባቢዎች፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ቤት በየሳምንቱ በልዩ ልዩ የስነልቦና ጉዳዮች ዙሪያ አስተማሪ ፅሁፎችን ወደናንተ ሲያደርስ መቆየቱ ይታወሳል:: ይህንንም አጠናክሮ በማስቀጠል ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ለተከታታይ ጊዜያት የሚቆይ አስተማሪ ፅሁፍ ይዘንላችሁ የምንቀርብ ይሆናል:: መልካም ንባብ::
ስትረስ (ውጥረት) ምንድን ነው?
ክፍል አንድ
ስትረስ (ውጥረት) ማለት አንድ ግለሰብ ለአካባቢያዊ ወይም ከሰውነቱ ለሚመነጩ ሁነቶች ምላሽ ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት የሚፈጠር የስሜት ጫና ነው:: ይህ የስሜት ጫና የግለሰቡን የመቋቋም ብቃት በእጅጉ የሚፈትን ነው:: የውጥረትን ምንነት በአግባቡ ለመረዳት የተለያዩ የውጥረት መንስኤዎችን (Stressor) ማየት ግድ ይላል:: በአጠቃላይ የውጥረት መንስኤዎች (Stressor) በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባሉ እነሱም፡
.ውስጣዊ የውጥረት መንስኤዎች
ውስጣዊ የውጥረት መንስኤዎች ከሚባሉት መካከል ጤናዊና አካላዊ ህመሞች፣ እውነትን አምኖ መቀበል አለመቻል፣ የተስፋ ቢስነትና የጨለምተኝነት ስሜት፣ ለራስ የሚነገር አሉታዊ ንግግር፣ ከእውነታ ውጪ ማሰብ፣ መገመት፣ ሁሉም ነገር እንዲሳካ መጠበቅ፣ ዝቅተኛ የሆነ ለራስ ያለ ክብር ወይም በራስ አለ መተማመን…ወዘተ ናቸው:: እነዚህ ውስጣዊ የውጥረት አምጭ መንስኤዎች በአራት ንሁስ ክፍሎች ይመደባሉ::
1.አካላዊ እና ሥነ-ህይወታዊ የውጥረት መንስኤዎች (Physical and Biological factors in Stress)
2.ስሜታዊ የውጥረት መንስኤዎች (Emotional factors in Stress)
3.ስብዕና ነክ የውጥረት መንስኤዎች (Personality factors in Stress)
4.አእምሮአዊ (መረዳት/ መገንዘብ/ ህሳቤያዊ) የውጥረት መንስኤዎች (Cognitive factors in Stress) ናቸው::
ውጫዊ የውጥረት መንስኤዎች
ውጫዊ የውጥረት መንስኤዎች ከሚባሉት መካከል ድህነት፣ ሥራ ወይም የስራ ጫና፣ ትምህርት፣ የሰው ለሰው ግንኙነት፣ የአቻ ለአቻ ግፊት፣ የልጆችና ቤተሰብ ኃላፊነት፣ የገቢ እጥረት (የኢኮኖሚ ችግር)፣ ፖለቲካዊ ችግሮች፣ ኢፍትሀዊነት፣ የአየር ጠባይ/ንብረት፣ ሥራ አጥነት፣ የቤተሰብ ቁጥር መብዛት፣ ስደት፣ ዘረኝነት፣ ከመኖሪያ አካባቢ መፈናቀል፣ ርሀብ፣ ጦርነት፣ ተፈጥሮአዊና ሰብአዊ ጉዳት፣ አደጋ፣ የእረፍት ወይም መዝናኛ ጊዜ አለመኖር፣ የተደራጀ ኑሮ አለመምራት … ወዘተ ሲሆኑ በአጠቃላይ በሁለት ንዑስ ክፍሎች ይመደባሉ::
1. አካባቢያዊ የውጥረት መንስኤዎች (Environmental factors in Stress)
2.ማህበራዊ እና ባህላዊ የውጥረት መንስኤዎች (Sociocultural factors in stress) ናቸው:: ከዚህ በመቀጠል ከላይ የተገለፁትን የውስጥም ሆነ የውጭ ውጥረት መንስኤዎችን አንድ በአንድ እንመልከት:: .አካላዊ እና ሥነ-ህይወታዊ የውጥረት መንስኤዎች ከውጥረት መንስኤዎች አንዱ ሰውነታችን ሲሆን በአካላችን ውስጥ የተለያዩ ስነ-ህይወታዊ እንቅስቃሴዎች እና በሽታ ወይም አካላዊ ጉዳቶች ስትረስ (ውጥረት) ሊፈጥሩ ይቸላሉ:: ለምሳሌ አንድ ሰው ከበድ ያለ በሽታ በሚያጋጥመው ጊዜ ሰውነቱ ይህንን በሽታ አሸንፎ ወደ ጤናማ ሁኔታው ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ስትረስ (ውጥረት) ይፈጠራል:: እነዚህን ዓይነት ስትረስ አምጪዎችን በተሻለ ለመረዳት የሚከተሉትን የሰውነታችንን የውስጥ ክፍል ስርዓቶች መፈተሽ ግድ ይላል፡- ሀ. ኦቶኖሚክ ስርዓተ ነርቭ (Autonomic Nervous System) ለ. ኢንዶክራይን ስርዓት (Endocrine System) መ. በሽታ እና የበሽታ መከላከያ ስርዓት (Illness and Immune system) ሀ. የኦቶኖሚክ ስርዓተ ነርቭ (Autonomic Nervous System) ማንኛውም አይነት ውጥረት አምጭ ሁኔታ (stressful situation) ሲያጋጥመን የሰውነታችን ስርዓተ ነርቭ ይለወጣል::
በዚህም ምክንያት የአተነፋፈስ፣ የልብ አመታት እና የምግብ መዋሀድ ሂደት ላይ አሉታዊ (negative) እና አዎንታዊ (positive) ተፅዕኖ ያመጣል:: ይህ ሁኔታ የሚከሰተው ሁለቱ የስርዓተ-ነርቭ ክፍሎች ሲተባበሩ ሲሆን፣ ሲምፓታቲክ (sympathetic) ስርዓተ ነርቭ የተባለው የማነሳሳትና የመቀስቀስን (arousal) ስራ ሲያከናውን ፓራ-ሲምፓታቲክ (parasympathetic) ስርዓተ-ነርቭ የተባለው ደግሞ የማረጋጋትና የማቀዝቀዝ (calming) ስራን ይተገብራል:: የእነዚህ ሁለት ስርዓተ ነርቭ ክፍሎች ተባብሮ መስራት ስትረስ (ውጥረት) በሚኖርበት ጊዜ ሰውነት ለስትረሰሩ የሚኖረውን ምላሽ አስተባብሮ በማከናወን ሰውነት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ የመመለስን ስራ ይሰራል:: ለ.የኢንዶክራይን ስርዓት (Endocrine System) የኢንዶክራይን ስርዓት በሰውነታችን ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ እጢዎች በቀጥታ የሚያመነጩት ኬሚካላዊ ንጥረ ነገር (ሆርሞን) በደማችን በኩል ወደ ተለያዩ ሰውነታችን ክፍል ይሰራጫል:: ከእነዚህም ዕጢዎች መካከል በኩላሊታችን አናት ላይ የሚገኘው የአድሪናል ዕጢ (Adrenal gland) ውጥረትን የምንቋቋምበት አስፈላጊ ሚናን ይጫወታል:: የአድሪናል እጢ (Adrenal gland) ኤፒነፍሪን (Epinephrine) ወይም አድሪናሊን (Adrenaline) እና ኖርኤፒነፍሪን (Norepinephrine) ወይም ኖርአድሪናሊን /Noradrenaline/) እንዲሁም ኮርቲሶል የተባሉ ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች (ሆርሞን) በማመንጨት ነው
i.ኤፔነፍሪን /Epinephrine/ የተባለው ኬሚካላዊ ንጥረ ነገር (ሆርሞን) ግለሰቡ ላይ ለሚከሰት ማንኛውም አደጋ (ውጥረትን ጨምሮ) ምላሽ እንዲሰጥ ዝግጁ ያደርገዋል:: የዚህም መገለጫ የትልልቅ ጡንቻዎች መጠናከር፣ ፈጣን የልብ ምት፣ የደም ዝውውር መጨመር፣ ፈጣን የአተነፋፈስ ሁኔታ፣ የሰውነት ሙቀት መጨመር ናቸው:: እነዚህ ሁሉ የሰውነት ለውጦች ግለሰቡ ስትረስ አምጪ የሆነውን አደጋ ለመጋፈጥ ወይም ለማምለጥ ሰውነትን ያዘጋጃል::
ii.ኖርኤፒነፍሪን/Norepinephrine/የተባለው ኬሚካላዊ ንጥረ ነገር (ሆርሞን) አደጋ ወይም ስትረስ አምጭ የሆነው ሁኔታ ሲያልፍ ሰውነት ወደ መደበኛው ስርዓቱ ለመመለስ ያግዛል:: የዚህም መግለጫ ግለሰቡ የጡንቻዎች መላላት /ዘና ማለት ፣ የልብ ምትን ማረጋጋት፣ የደም ዝውውርን ማስተካከል፣ አተነፋፈስን መቀነስ፣ የሰውነት ሙቀትን መቀነስ፣… ወዘተ ናቸው:: ይህም የሰውነትን መነቃቃት በመቀነስ ወደ መደበኛ ስርዓቱ በመመለስ እና ጉልበትን በመቆጠብ ለሚቀጥለው ስትረስ /አደጋ ምላሽ የመስጠት አቅምን መቆጠብ ነው::
iii.ኮርቲሶል/Cortisol/ሰውነታችንስትረስ በሚያጋጥመው ወቅት የመከላከል አቅሙን አሰባስቦ ለስትረስ አምጪው ተገቢውን ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከሚጠቀምባቸው ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች (ሆርሞኖች) መካከል አንዱ ነው:: ይህ ሆርሞን ከአድሬናል እጢ መንጭቶ በቀጥታ ወደ ደም ስር ውስጥ በመግባት እና በደም ዝውውር ስርዓት ውስጥ ከደም ጋር አብሮ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በመጓዝ አካላዊ፣ ስነ-አእምሯዊ እና ስሜታዊ ለውጦችን ያሰከትላል:: በመሆኑም የተለያዩ የአካል ክፍሎችን በማነቃቃት (ለምሳሌ ልብ ምት መጨመር፣ አተነፋፈስን ማፍጠን፣…) ስትረስን ለመከላከል ያላቸውን ዝግጁነት ከመጨመር ባለፈ አእምሯችን ንቁ እና ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ እንዲሆን ያግዛል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ወርቅነህ ከበደ እና ሲሳይ የማነ (ዶ/ር) (ሳይኮሎጂ ት/ቤት – አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)