በልጅነቴ የታዘብኩትን ሁናቴ አሁን ላይ በማስተዋሌ ግርምት ፈጥሮብኛል:: ነገሩ እንዲህ ነው:: ከቀየው ርቆ ለሚሄድ ሰው ሰንቅ ይቋጠርለታል:: ስንቁም ከምግብ ዘሮች ብቻ አይምሰላችሁ፤ ከመድሐኒት ዘርም ጭምር እንጂ:: በስንቅነት ከሚቋጠረውም የወባ መድሃኒት ቅድሚያውን ይይዝ እንደነበር አስታውሳለሁ:: አሁን ላይም የወባ መድሃኒት ለስንቅነት እየተሸመተ እንደሆነ ይወራል:: ለዚያውም ለተሰራለት አላማ አይምሰላችሁ፤ ኮሮና ቫይረስን ይፈውሳል በሚል እንጂ::
ምክሩ ከዶናልድ ትራምፕ የተቀሰመ ይመስላል:: በዓለም የሆነውን ጉዳይ መጥቀስ ተገቢ ነው:: የኮሮና ቫይረስ የዓለም ኃያላን ነን ያሉትን ብርክ ያአስያዘ:: ዜጎቻቸው ከቅጠል እኩል ረገፉ:: በዚህ ሂደት ፖለቲካዊም ይሁን ሙያዊ ውሃ የሚያነሳ መፍትሄ ቢያማትሩ የሰማይ ያህል ራቀ:: በመሆኑም ለሕዝባቸው ለኮሮና ቫይረስ ፈውስነት የሚበጅ መፍትሄ አጣን ለማለት የደፈሩ መሪዎች የመኖራቸውን ያህል መፍትሄ አላገኘንም ማለት ከምን እንደቆጠሩት ግልጽ ባይሆንም ክሎሮኪልና ሐይድሮ ክሎሮኪል መሰል የወባ መድሃኒቶችን ውሰዱ ማለታቸው ይታወሳል::
የብራዚል ከፍተኛ ባለሥልጣናት እነዚህን የወባ መድሐኒቶች የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች እንዲወስዷቸው ይመክራሉ:: ለውጥም እንደማያስፈልጋቸው ያነሳሉ:: ነገር ግን ይሄን ጉዳይ የሚያጠናክር ሳይንሳዊ አመክንዮ የለም በሚል አልስማማበትም ያሉት የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ኔልሰንት ሼይሺ ከሥልጣናቸው ለቅቀዋል:: ከእርሳቸው በጥቂት ወራት ቀድመው የለቀቁት ሊውሴ ሪጌ ማንዴታ የሚባሉት የጤና ሚኒስትርም ከዚሁ ከወባ መድሃኒቱ ጋር በተያያዘ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት የተለየ አቋም በመያዛቸው ሥልጣናቸውን እንደለቀቁ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አትተዋል::
የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ “ክሎሮኪልና ሐይድሮ ክሎሮኪል መድሃኒቶችን መውሰድ ያለባቸው የወባ በሽታ ያለባቸው እንጂ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ግን ባይወስዷቸው ይመረጣል፤ አደገኛ ችግር ሊያስከትሉባቸው እንደሚችሉም ማሳያዎች አሉ” ይላል:: በመሆኑም የዓለም የጤና ድርጅት ይህንን እንደማያበረታታና ተቋሙ ሲያደርግ የነበረውን ሙከራ ማቆሙን ግንቦት 17 አስታውቋል::
እነዚህ ሁኔታዎች በዓለም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት በገዳይነቱ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው የወባ በሽታ አሁን ላይ እያገረሸ መምጣቱን ተከትሎ ችግሩን ‹‹በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ›› አያደርገው ይሆን? በኮሮና ወረርሽኙ ርብርብ በመጠመድ የወባ መከላከል ተግባሩ ችላ ተብሎ ይሆን ማገርሸቱ? በኢትዮጵያ ሥርጭቱ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?:: ምን መፍትሄዎች እየተወሰዱ ይሆን? የቅድመ መከላከል ሥራው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚሉትን ለመቃኘት ሞክረናል::
የሕብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት ሐኪምና የድሪም ኬር አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር መኮንን አይችሉህም ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከሚዲያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የመንግሥትም ሆነ የአብዛኛው ሕብረተሰብ ትኩረት ኮሮና ቫይረስ ላይ በመሆኑ የወባ በሽታ ትኩረት ተነፍጎታል ይላሉ::
የወባ በሽታ ምንነትና ኡደት
የወባ በሽታ በዓለም ላይ ከሚገኙ ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ነው:: በሴቷ ወባ ትንኝ አማካኝነት የሚተላለፍ በሽታ ነው:: የዓለም የጤና ድርጅት ከአምስት ዓመታት በፊት ባወጣው መረጃ መሠረት ከ198 ሚሊየን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል:: ከ584 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሕይታቸውን ማጣታቸው ተገልጿል:: በበሽታው ከሞቱት አራት አምስተኛ የሚሆኑት እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው:: በሽታው መቶ በሚጠጉ አገራት ውስጥ በሚኖሩ ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሰዎች ላይም ሥጋት እየፈጠረ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ::
የወባ በሽታ በዋናነት በጥገኛ ተህዋሲን ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው:: በሽታው ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል፡- ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማላብ፣ የራስ ምታት፣ የሰውነት መጓጎል፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪ አልፎ አልፎ ሁለትና ሦስት ቀናት እየቆየ ምልክቶቹ በድጋሚ የሚታዩባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ:: ይህ ሁኔታ በዋናነት የሚወሰነው ግለሰቡን ባጠቁት ተሕዋሲያን አይነትና በበሽታው ተይዞ የቆየበት ጊዜ ነው::
የወባ በሽታ ፕላስሞዲም ተብለው የሚጠሩ ባለአንድ ሕዋስ ፍጥረታት ሲሆኑ ወደ ሰው ደም ውስጥ የሚገቡት አኖፊልስ በምትባለው የሴቷ ትንኝ ንክሻ አማካኝነት ነው:: እነዚህ ተህዋሲያን በግለሰቡ የጉበት ሴሎች ውስጥ በመግባት ይራባሉ:: በጉበት ውስጥ ያሉ ህዋሶች ሲፈነዱ ይወጡና የግለሰቡን የደም ሴሎች ይወራሉ:: ከዚያም ተህዋሲያኑ በቀይ የደም ሴሎች ውስጥ መባዛታቸውን ይቀጥላሉ:: ቀይ የደም ሕዋሶችም በሚፈነዱበት ጊዜ ተህዋሲያኑ ይወጡና ሌሎች ቀይ የደም ሴሎችን ይወራሉ:: በቀይ የደም ሴሎች ውስጥ የሚካሄደው ይህ ኡደት ይቀጥላል:: በዚህም ቀይ የደም ሴሎቹ በፈነዱ ቁጥር በበሽታው የተያዘው ሰው የወባ በሽታ ምልክቶች ይታዩበታል::
ከወባ በሽታ መነሻ ምክንያቶች ዋናው የመራቢያ ቦታቸው መሆኑ ይነገራል:: ይህም ለወባ በሽታ መራቢያ ምቹ የሆኑ ውሃ የሚያቁሩ አካባቢዎች ለበሽታው ዋና የመራቢያ ቦታ በመሆን ያገለግላሉ:: እነዚህን በማፋሰስና በመድፈን ማስወገድ ከወባ በሽታ ለመከላከል ፍቱን መፍትሄ ተደርጎ የሚተገበር ነው::
የሥርጭቱ አሁናዊ ሁኔታ በወፍ በረር
በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት የወባ በሽታ ሥርጭት መኖሩ ይገለፃል:: በዋናነት ደግሞ ቆላማው የአገሪቱ ክፍል በስፋት በወረርሽኙ ተጋላጭ ነው:: በዚህ የተነሳም የአርሶአደሩን ጤና በማወክና ከአዋቂ እስከ ሕፃናት ድረስ ሕይወትን በመቅጠፍ ላይ የሚገኝ በሽታ ነው::
በአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ክፍል ባለሙያ የሆኑት አቶ አማረ ደስታ ለሚዲያዎች እንዳሉት፤ በዚህ ዓመት በክልሉ የሚስተዋለው የወባ ወረርሽኝ ሥርጭት ከአለፉት ሁለት ዓመታት በበለጠ መጨመሩን ገልፀዋል:: በተለይም በቋራ፣ ምሥራቅ ደምቢያ፣ ጎንደር ዙሪያ፣ ጃዊ፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ ደብረኤልያስ፣ ሸዋሮቢት፣ ራያ ቆቦ፣ ቃሉ፣ አበርገሌና የመሳሰሉት አካባቢዎችና ወረዳዎች በሽታው በስፋት ከጨመረባቸው አካባቢዎች ይጠቀሳሉ:: በምክንያትነትም ቀደም ሲል ወባን ለመከላከል ይወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች በመላላታቸው፣ የሕብረተሰቡ ጥንቃቄ አለማድረግ፣ ወባ ጠፍቷል የሚል የተሳሳተ አመለካከት መኖር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ትኩረቱ ወደ ኮቪድ 19 መዞር ይጠቀሳሉ:: ወረርሽኙን በጋራ መከላከል ይቻል ዘንድም የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር 260 ሺህ ኪሎ ፀረ ወባ ኬሚካል መላኩን አቶ አማረ መናገራቸው ተጠቅሷል:: አማራ ክልል 80 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ለወባ በሽታ መራቢያ ምቹ ሲሆን 68 በመቶ ነዋሪም ለበሽታው ተጋላጭ ነው ተብሏል::
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በተለይም በደቡብ ኦሞ አካባቢዎች፣ ጉራጌ ዞኖች የወባ ወረርሽኝ በስፋት መከሰቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በያዝነው ግንቦት ወር ገልፀው ነበር:: በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መሆኑን ገልፀው፣ የወባ ወረርሽኙ ችላ የተባለ ሥራ አለመሆኑንም አስምረውበታል:: በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከባለፉት ጊዜያት በሰፋ ሁኔታ መከሰቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጾ ነበር:: የክልሉ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ለወባ በሽታ መራቢያ ምቹ ነው:: በመሆኑም በሽታው በሕብረተሰቡ ጤና ላይ የከፋ ችግር ሳያስከትል መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ሰፊ ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ እንደሆነም ጤና ቢሮው አብራርቷል::
ከላይ የተጠቀሱት ለማሳያነት የተገለፁ እንጂ በአጠቃላይ የወባ ወረርሽኝ በሁሉም ክልሎች በስፋት የሚከሰት ነው:: በመሆኑም ከወቅቱ በሽታ ኮሮና በላይ ገዳይ የሆነው የወባ ወረርሽኝ መከላከል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: ሕብረተሰቡም ሆነ መንግሥት ለችግሩ መፍትሄ ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2012
ሙሐመድ ሁሴን