ፋይዳ መታወቂያ በዜጎች መካከል የመተማመኛ ማሕቀፍ በመሆን የኢኮኖሚ ትስስርን ያጠናክራል

አዲስ አበባ፡- የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በዜጎችና በተቋማት መካከል የመተማመኛ ማሕቀፍ በመሆን የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ዙሪያ ለሃይማኖት ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የፋይዳ መታወቂያ በሰዎችና ተቋማት መካከል መተማመንን በመፍጠር የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከርና ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል፡፡

መታወቂያው የተቀላጠፈ የንግድ አገልግሎት ለማግኘት፣ ከግል መረጃ ጥበቃና ከደኅንነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር እንደሀገር ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እስካሁን ለ10 ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም ከታቀደው አንጻር አፈጻጸሙ የሚፈለገውን ያህል እንዳልሆነ ገልጸው፤ ይህም በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የግንባዜ እጥረትና የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መታወቂያው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው በመገንዘብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ አቶ ዮዳሔ አንስተው፤ ለዚህም ግንዛቤ በመፍጠርና ሁሉም ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም የብሔራዊ መታወቂያ ግንዛቤን በኅብረተሰብ ውስጥ በማስረጽ የተመዝጋቢዎችን ቁጥር ከመጨመር ባሻገር የተቀላጠፈና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በማኅበረሰብ መካከል እርስ በእርስ መተማመን የሚፈጥርና ፍትሐዊነት የሚለውን ሃይማኖታዊ አስተምሮ የሚከተል ነው። ይህም የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ከሃይማኖት አስተምሮ ጋር ምንም አይነት ተቃርኖ የለውም ብለዋል፡፡

ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ በግንዛቤ እጥረትና የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ተደራሽነቱ አናሳ መሆኑን ገልጸው፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተዓማኒነት ባላቸው የሃይማኖት አባቶችን ምሳሌ በማድረግና በሚሰጡት አስተምሕሮ በመጠቀም ተደራሽነቱን ለማስፋት ያስችላል ብለዋል።

መታወቂያው ሀገራዊ ልማትን ለማሳደግ፣ ማጭበርበርንና ወንጀልን ለመከላከል እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት የሚረዳ መሆኑን አንስተው፤ የሃይማኖት አባቶችም ይህን ስኬታማ እንዲሆን ምሳሌ በመሆንና በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ ኅብረሰተቡም ይህንን አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

መድረኩ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት እና የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ ሼህ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ፣ የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ቸሩጌታ ገነነ ጨምሮ ከፍተኛ የሃይማኖት ተቋማት አመራሮች እና አባቶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ማሕሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ህዳር 18/2017 ዓ.ም

Recommended For You