በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ 77 ቀናት ተቆጥረዋል:: በነዚህ ቀናት አጠቃላይ 92 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ምርመራ የተካሄደ ሲሆን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ750 በላይ ሆኗል፤ የስድስት ሰዎች ህይወትም አልፏል::
አገራችን ችግሩ መከሰቱን ተከትሎ በወሰደችው እርምጃ ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች፤ በርካታ የመንግስት ተቋማትም ሰራተኞቻቸው በፈረቃ አልያም በከፊል ስራ ላይ እንዲሆኑ በማድረግ በቤት እንዲቆዩ አድርጋለች፤ የትራስፖርት አገልግሎቱ መራራቅን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲከናወን የተሳፋሪ ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጓል:: በአጠቃላይ በርካታ እቅስቃሴዎች ተገድበዋል::
መንግስት ችግሩን ለመግታትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ እየሰራ ይገኛል:: በሌላ በኩልም እነዚህ እገዳዎች በመተግበራቸው ከእጅ ወደአፍ ኑሮ ያላቸው በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጎዱ ይታወቃል:: ሆኖም ይህን ችግር ለመከላከል መንግስት የህብረተሰቡ የመረዳዳት ባህል እንዲጎለብት በማስተማርና ሀብትን በማሰባሰብ የኢኮኖሚ ችግሩ እንዳይባባስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል::
በአንፃሩ ግን በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋትና ለበሽታው የተሰጠው ትኩረት በቂ እንዳልሆነ አጠቃላይ ያለውን እንቅስቃሴና ግርግር ተመልክቶ መገንዘብ ይቻላል:: በተለይ በመጀመሪያው አካባቢ የነበረው እጅን የመታጠብና፣ አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ እንዲሁም በቤት ውስጥ የመቆየት እርምጃ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እየተዘነጋ ወደ ቀደመው እንቅስቃሴ የመመለስ ሁኔታ ይስተዋላል::
መንግስት በአንድ በኩል አልፎ አልፎ እርምጃዎችን እየወሰደና በየጊዜውም ትምህርት እየሰጠ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥረት ቢያደርግም ቫይረሱን በሚፈለገው ደረጃ መቆጠጠር አልቻለም:: በዚህ የተነሳ በመካከሉ በነበረው መዘናጋት የተነሳ በዚህ ሳምንት አስደንጋጭ ስርጭት እየተከሰተ ይገኛል::
በዚህ የተነሳም በዚህ ሳምንት ብቻ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር በ70 ቀናት ከታየው ስርጭት ጋር ተመጣጣኝ መሆኑ ምን ያህል ስርጭቱ እየተስፋፋ መምጣቱን ያሳያል:: በአንድ በኩል በእንቅስቃሴዎች መታገድ የተነሳ የኢኮኖሚ መቃወሱ መፈጠሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ስርጭቱንም ለመግታት አለመቻላችን ከሁለት ያጣን ያደርገናል::
የህክምና ዘርፍ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አምስት ደረጃዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የመጨረሻ ደረጃ የሚባለው አምስተኛው ደረጃ በሽታው ከፍተኛ ቀውስ የሚያስከትልበትና ህዝብና መንግስትም በሽታውን መከላከል ላይ የሚረባረቡበት ደረጃ ነው:: አሁን አገራችን ያለችበት ደረጃ ደግሞ ለዚህ የቀረበው አራተኛ ደረጃ ነው:: ይህ ደረጃ ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ የሚችልበት እድል መኖሩን ያሳያል::
በመሆኑም በሽታው የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስም ሆነ በኢኮኖሚው መዳከም የሚከሰተውን ጉዳት ለመቀነስ እነዚህን ሁለት ችግሮች አቻችሎ መጓዝ ይገባል:: ለዚህ ዋነኛው መፍትሄ ደግሞ የቅድመ መከላከል ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ነው::
በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል በህክምና ባለሙያዎችና ጉዳዩ በሚመለከታው የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡ ምክሮችና የሚወጡ ህጎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ዋነኛው የመከላከያ መንገድ ነው:: ከዚህ አንፃር በተለይ የበሽታው መተላፊያ ዋነኛ መንገዶችን ማለትም ማስክን በመጠቀም አፍና አፍንጫን መሸፈን፣ ከማንኛውም ንኪኪ በኋላ እጅን በሳሙናና በውሃ ለ20 ሰከንድ በአግባቡ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን ጠብቆ መጓዝ፣ የግድ አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በስተቀር ከቤት አለመውጣት እና የመሳሰሉ ተግባራትን በአግባቡ መተግበር ተገቢ ነው::
በተለይ ቀደም ሲል ቀንሶ የነበረው የሰዎች እቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየጨመረ ሄዶ በአሁኑ ወቅት ወደቀደመው ሁኔታ እየተመለሰ ይገኛል:: በአንዳንድ ቦታዎችም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚቃረን መልኩ ከሶስት በላይ ሆኖ አንድ ላይ የመቀመጥና የመንቀሳቀስ፣ ሰብሰብ ብሎ ጫት መቃም፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ መጓዝ፣ መጨባበጥና በየሰፈሩም ኳስ መጫወት ይታያል::
በተለይ በመካከሉ አነስተኛ መሆን እና ከቫይረሱ ነፃ የነበረበት ቀን መኖሩ በርካቶች እንዲዘናጉ አድርጓል:: ከበዓላት ጋር ተያይዞም የሚደረጉ እቅስቃሴዎች ብዙዎች ለቫይረሱ እንዲጋለጡ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደነበር የሚታወስ ነው:: እነዚህና መሰል የመዘናጋት ውጤቶች ደግሞ ውጤታቸው አደገኛ ሊሆን ይችላል::
በመሆኑም የኮሮና ቫይረስ ስህተትን ፈፅሞ የማይታገስ በሽታ እንደመሆኑ የአንድ ቀን ስህተት ህይወትን እስከማሳጣት የሚያደርስ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ፈጽሞ ባለመዘናጋት በሽታውን መከላከል የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም