ይህ ዓመት እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ቢሆን፤ በስፖርቱ ዓለም በተለይ በዚህ ወቅት በርካታ ውድድሮች፣ ጉባኤዎችና ሥልጠናዎች ሊካሄዱ ይችሉ ነበር። ነገር ግን ሳይታሰብ ተከስቶ ዓለምን ባዳረሰው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ19) ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች ብቻም ሳይሆኑ በርካታ ጉዳዮች በታቀደላቸው ሁኔታ እንዳይካሄዱ ማድረጉ ግልጽ ነው። ታዲያ የስፖርት ማህበራትና ሌሎች ተቋማት እቅዶቻቸው በዚህ መልኩ አቅጣጫቸውን ሲስቱ ምን ዓይነት አማራጮችን ተጠቀሙ? ከዓመት እስከ ዓመት በሩጫ ላይ ከሆኑና በሥራ ከሚወጠሩ ፌዴሬሽኖች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው። የፌዴሬሽኑ የሥልጠና ጥናትና ምርምር ዳይሬክተሩ አቶ ሳሙኤል ብርሃኑ የሚናገሩት አላቸው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ጨምሮ የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን፣ የወጣቶች ቻምፒዮና እንዲሁም ሌሎች ውድድሮች ፌዴሬሽኑ በዚህ ዓመት ያላካሄዳቸው የውድድር ዘርፍ እቅዶች ናቸው። በሥልጠና ጥናትና ምርምር ዘርፍ ደግሞ የዚህ ዓመት ዋነኛ እቅድ የነበረው ባለሙያዎችን ማብቃትና መመዘን መሆኑን ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። ዳኞችና አሰልጣኞች ዓለም አቀፍ ሥልጠናዎችን አግኝተው ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ባለበት ወቅት ግን የዓለም ትኩሳት የሆነው ጉዳይ በመከሰቱ እንደታሰበው ማስኬድ አልተቻለም ይላሉ። በተለይ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ወር ድረስ የሥራ ክፍሉ በዚህ ለማሳለፍ ያስቀመጠው እቅድ ወደ መሬት ሳይወርድ ቀርቷል።
በዓመቱ ኦሊምፒክና ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍና ብሔራዊ ቡድንን የማዘጋጀት እቅድም ተመሳሳይ ዕጣፈንታ ገጥሞታል። ለብሔራዊ ቡድን የተጠሩ አትሌቶችም ተበትነው ወደየ ቤታቸው ሄደዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ግን ሥራውን ከማቋረጥ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መጠቀምን መርጧል። ዋናው የአትሌቶች ጤንነትና በብቃት መቆየት በመሆኑም የተሻለ ያለውን ተግባር ሲከውን እንደቆየ ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
ፌዴሬሽኑ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ስፖርታዊ ክዋኔዎችን ማካሄድ አዳጋች መሆኑን በመገንዘቡ ቀደም ብሎ ወደ ዝግጅት መግባቱን ይጠቁማሉ። አትሌቶች ሥልጠና ማቋረጣቸውን ተከትሎ ከስፖርቱ እንዳይርቁ እንዲሁም አሰልጣኞችም ከአትሌቶቻቸው በጋራ ያላቸው ግንኙነት እንዳይቋረጥ ምን ማድረግ ይገባል? የሚለውን በማሰብም ነው በቴሌቪዥን ስርጭት በትምህርትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ፕሮግራሞች እንዲተላለፉ የተደረገው። በዚህም የስፖርቱ ባለሙያዎችን በማካተት በሦስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለስድስት ሳምንታት ለአትሌቶች ጠቃሚ የሆኑ መርሃ
ግብሮች ሲተላለፉ ቆይቷል። የመርሃ ግብሩ ይዘትም ሥነ-ልቦና፣ ሥነ-ምግብ፣ ሕክምና፣ ማህበራዊ ግንኙነት፣ የተምሳሌት አትሌቶች መልዕክት፣ የአሰልጣኞች ምክረ ሃሳብ እንዲሁም አትሌቶች በአጠቃላይ ምን ማድረግ ይገባቸዋል የሚለውን ያጠቃለለ ነበር። ከቴሌቪዥን ስርጭቱ ባሻገር በፌዴሬሽኑ ይፋዊ ማህበራዊ ገጽ (ፌስ ቡክ) እንዲሁም በድረገጹ አማካኝነትም አትሌቶችን ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህ ሂደትም ፌዴሬሽኑ ማድረግ የሚገባውን መልካም ተግባር ማከናወኑን ለመታዘብ ተችሏል። አትሌቶችና ሌሎች ባለሙያዎችም ለዚህ የሚሰጡት ግብረ መልስ ጥሩ ሥራ መሰራቱን የሚያሳይ ነው። አትሌቶች ቤታቸው በሚሆኑበት ወቅት ምን መስራት እንዳለባቸው ግራ ተጋብተው ነበር የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ አሰልጣኞች በሚሰጧቸው አቅጣጫ ተጠቃሚ ሆነዋል። በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙና እነዚህን አማራጮች የማያገኙ አትሌቶችን ደግሞ አሰልጣኞች በስልክና በሌሎች መንገዶች በተመሳሳይ እየረዷቸው ይገኛሉ። አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር ጥናት መስራትና አትሌቶችን ማግኘት ባይቻልም በተለያዩ መንገዶች ምስጋናቸውን
ያደርሳሉ። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክር የሚጠይቁ አትሌቶች ቁጥር መበራከትም ይህንኑ የሚያመላክት ነው። አሰልጣኞች በበኩላቸው ወትሮ ከነበረው ሁኔታ በተሻለ መልኩ ከፌዴሬሽኑ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያጠናከሩ ሲሆን፤ ግብረመልስ በመስጠትም አጋርነታቸውን እያሳዩ ነው።
ከዚህ በኋላም ፌዴሬሽኑ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት ጎን ለጎን መርሃ ግብሩን በአዲስ መልክ የሚያስቀጥልም ይሆናል። የሀገርን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስጠራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚደረገው ርብርብ ቅድሚያ ተሰላፊ መሆኑን በተግባር በማሳየት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም በግሉ፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር እንዲሁም በአትሌቶቹ አማካኝነት በገንዘብ እንዲሁም በቁሳቁስ የድርሻውን በማድረግ ላይ ይገኛል። አመራሩና ሌሎች ታዋቂ አትሌቶችም ለሕዝቡ መልዕክት በማስተላለፍ ላይ ናቸው። አሁንም ከዚህ በላቀ መልኩ ለመስራት የሚያስችል ተነሳሽነት አለ።
እንደሚታወቀው በዚህ ወቅት ውድድሮችና ሌሎች የሥልጠና መርሃ ግብሮች ተቋርጠዋል። በዚህ ምክንያት
ፌዴሬሽኑ ቀድሞ የያዛቸውን እቅዶች በመቀየር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች ላይ ለማተኮር ማቀዱን ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። በዚህም ከፌዴሬሽኑ ስፖንሰር ማልታ ጊነስ ጋር በመሆን በቴሌቪዥን የሚተላለፉ መርሃ ግብሮችን በመስራት ላይ ነው። በአንድ ወር ውስጥ ለ16 ቀናት ያህል የሚተላለፈው መርሃ ግብሩ እንደ ቀድሞ በምክረ ሃሳብ ላይ ሳይሆን በተግባር ላይ የተመሰረተ እንደሚሆንም ታውቋል። በአትሌቶች ዘንድ ተምሳሌት የሆኑና ዝነኛ አትሌቶች እንዲሁም ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ተከታታይነት ያላቸው እንቅስቃሴዎች በምን መልኩ እንደሚሰሩ የሚያሳይም ይሆናል። እንቅስቃሴው ከአትሌቶች ጋር ብቻ ሳይሆን ሌላውን ኅብረተሰብም የሚጠቅምም ነው የሚሆነው። ለዚህ የሚሆነው ዝግጅት በመጠናቀቁ በቅርቡ አየር ላይ የሚውልም ይሆናል።
በዚህ ወቅት አብዛኛው ኅብረተሰብ ትኩረቱ የመገናኛ ብዙኃን ላይ በመሆኑ፤ ትብብራቸውን እንዳያቋርጡ ይጠይቃሉ። ከቴሌቪዥን ባሻገር በርካቶችን ተደራሽ የሚያደርጉ የመገናኛ ብዙኃን አብሮነታቸውን እንዲያሳ ዩም ጠይቀዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
ብርሃን ፈይሳ