ስኬታማ ሰዎችን ከሌሎች ሰዎች ከሚለዩዋቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛውና ዋነኛው ነጥብ መጥፎ አጋጣሚዎችን አቅጣጫቸውን አስቀይረው ለመልካም ነገር የመጠቀም ችሎታቸው ነው:: እነዚህ ሰዎች የነገሮችን ተቃርኗዊ ሁለትዮሽ ተፈጥሮ(Paradoxical Duality Nature) በሚገባ የተረዱ ናቸው:: ሰውን ጨምሮ ህይወት ያላቸው አካላት ሴትና ወንድ ሆነው ነው የተፈጠሩት::
ከቶ አያሸንፈውም እንጅ ከብርሃንን በተቃራኒው ጨለማ አለ:: ቀንና ሌሊትም ብርሃንና የጨለማ ቅጥያዎች ናቸው:: ሙቅና ቀዝቃዛ፣ ክፉና በጎ፣ ሀብታምና ድሃ፣ አለቃና ምንዝር፣ ርኩሰትና ቅድስና፣ ኃጢአትና ጽድቅ፣ ሞትና ህይወት፣ ሰነፍና ጀግና፣ ለቅሶና ሳቅ፣ ችግርና መፍትሔ…:: እናም በአጠቃላይ ዓለም እንደ ሐበሻ ምሳሌ “ደስታና መከራን ከቀኝ ወደ ግራ” በተቃርኖ አሰናስላ ሁለት መልክ ይዛ ነው የተፈጠረችው::
ታዲያ ይህን የተፈጥሮ ህግ መረዳት ያቃተን ብዙዎቻችን ችግር ሲገጥመን “ለምን ሆነ?” በሚል ራሳችንን የበለጠ ችግር ውስጥ እንከታለን፤ የሳንቲሙ ሌላኛው ገጽታ ሲገለበጥ መፍትሔ መሆኑን ማወቅ ሲሳነን በስንፍና እንሸነፋለን:: ብልሆች ግን ሁሌም ቢሆን ከተራራው በስተጀርባ ይመለከታሉ፤ እዚህ ከጨፈነ እዚያ ብራ ነውና! ችግር ሲመጣም ከመቸገራቸው በፊት መፍትሔውን ያስባሉ፤ እንዲያውም ችግሮችንና የፈተና ጊዜያትን ከቀደሙ ችግሮቻቸው ለመውጣትና የበለጠ ስኬት ለማስመዝገብ እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀሙባቸዋል:: እናም በአልጋ ላይ ሳይሆን በችግር ላይ አልፈው ካሰቡት የሚደርሱት፤ በሁለቱ ዓይኖቻቸው ችግሮችን፣ በሌሎች ሁለቱ ዓይኖቻቸው ደግሞ ከችግሮቹ ጀርባ ያሉትን መፍትሔዎች የሚመለከቱበት አራት አይኖች ያሏቸው እነዚህ ጠቢቦች ስኬታማ ይባላሉ!
አሁን ደግሞ በእኛ የዘመን አቆጣጠር በሁለተኛው ሺህ ዓመት በአስራ ሁለተኛው ዓመት ከአራተኛው ወር መጨረሻ ጀምሮ የምድራችን ታላቁ ፍጡር ሰው ለየት ያለ ችግር ገጥሞታል:: ችግሩ የመነጨው ኮሮና በሚባል ረቂቅ ተህዋሲ በመላ ዓለም ላይ በተቀሰቀሰ በሽታ ሲሆን ለየት የሚያደርገው ደግሞ በሽታው የሰው ልጆችን ተፈጥሯዊ የመንቀሳቀስ ነጻነት የሚቀማ መሆኑ ላይ ነው:: በሽታው አደገኛና በዓለም ዙሪያ ሚሊዮኖችን እየለከፈና መቶ ሺዎችን እየገደለ የሚገኝ ቢሆንም ለጊዜው በቤት ውስጥ ከመቆየትና አካላዊና ማህበራዊ ርቀትን ከመጠበቅ ውጭ ሌላ መፍትሔ የሌለው መሆኑ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” የተባለውን የ“ማህበራዊውን እንስሳ” የሰውን ህይወት በእጅጉ እየፈተነው ይገኛል:: ይሁን እንጂ ይህ የሰው ልጆች የጋራ ጠላት በተባበረ ክንድ ከምድራችን እስኪጠፋ ድረስ ዛሬም ቢሆን ችግሩን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይረን ምናልባትም ኮሮና ካለፈ በኋላም በህይወታችን ሙሉ ልንጠቀምበት የምንችልበትን ወርቃማ የዕድሜ ልክ ልምድ ገንብተን የምናልፍበት ዕድል በእጃችን ላይ አለ:: እንዴትና በምን? የዛሬው ጽሑፋችን ምላሽ አለው::
በጥሬ ትርጉሙ ከአራቱ መሰረታዊ የቋንቋ ክህሎቶች አንዱ የሆነው ንባብ ዋጋው ከቀይ ዕንቁ የላቀ ነው:: ንባብ የቋንቋ ክህሎት ብቻ አይደለም:: ምክንያቱም በመደበኛው የትምህርት ሂደት ውስጥ ዋነኛው የመማሪያ መሳሪያ ከመሆኑም በላይ በሥራና በማናቸውም የሰው ልጆች ህይወት ውስጥ ራስን ለማሻሻልና ኑሮን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የዕውቀት ዓይነቶችም የሚገኙት በማንበብ አማካኝነት በመሆኑ ከመሰረታዊ የቋንቋ ክህሎትነትም ባሻገር በህይወት ዘመን ሁሉ የሚያገለግል የዕድሜ ልክ ባለሟልም ነው:: ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም የሚለው አባባል የሚሰራው ለሚያነቡ ሰዎች ነው:: በማንበብ አማካኝነት ሁሉን ነገር ማወቅ ከፍ ሲልም በንባብ ያገኙትን ዕውቀት ወደ ድርጊት በመቀየር ሁሉን ነገር ማድረግ ይችላሉ:: ዛሬ ዓለማችን አሁን ባለችበት መልኩ ሆና እንድትገኝ ያስቻሉ ታላላቅ የፈጠራ ሰዎች በንባብ እንጂ በመደበኛ ትምህርት ብዙም የገፉ አልነበሩም::
ከፈጣሪ ቀጥሎ ዓለማችን ብርሃናማ እንድትሆን ያስቻላትን የአምፑል ብርሃን ጨምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ፈጠራዎችን ለፕላኔታችን ያበረከተው ታላቁ የፈጠራ ሰው አሜሪካዊው ቶማስ ኤልቫ ኤዲሰን ትምህርት ቤት ገብቶ የተማረው እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ ነው:: እንደዚሁ ለኢንዱስትሪ አብዮት መፈጠር በዋነኛ ምክንያትነት የሚጠቀሰውንና በወሳኝነት የዓለምን ሁኔታ እንደቀየረ የሚታመነውን የአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታላቅ ፈጠራ በመባል የሚታወቀውን የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመጀመሪያ ጊዜ የፈለሰፈው ሌላኛው ታሪክ ቀያሪ ሳይንቲስት እንግሊዛዊው ሚካኤል ፋራዳይ ይህን ታላቅ ሥራ መስራት የቻለው ከመጽሐፍት ንባብ ባገኘው ዕውቀት ነበር:: ፋራዳይ ከድሃ ቤተሰብ የተገኘ ልጅ በመሆኑ የተነሳ መደበኛ ትምህርት መከታተል የቻለው እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ መሆኑንና በዚያ መንገድ እስከ ወዲያኛው ዓለምን መቀየር የቻለበትን ዕውቀት ያገኘው ግን የዕለት ጉርሱን ለመሸፈን ትምህርቱን አቋርጦ በአንድ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ በነበረበት ወቅት ካነበባቸው በርካታ መጽሐፍት ለረጅም ጊዜ ካካበተው የንባብ
ዕውቀቱ መሆኑን የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል::
ምን ይሄ ብቻ ማሳያ እንዲሆነን የሁለቱን ሰዎች ተሞክሮ አነሳን እንጂ በጥቅሉ በተለያዩ መስኮች የዓለማችንን ስልጣኔ ከፊት ሆነው በፊታውራሪነት የመሩ ሁሉም ታላላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስብዕናዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከመጻሕፍትና ከንባብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት የነበራቸው ሰዎች ናቸው:: በአንድ ወቅት መላ አውሮፓን ጠቅሎ መግዛት ከቻለው ከታላቁ ንጉስ ናፖሊዎን ቦናፖርቲ፣ እንግሊዛውያን ብሎም የመላ አውሮፓ የሥነ ጽሑፍ መኩሪያ ከሆነው ከዝነኛው ባለቅኔ ዊልያም ሸክስፒር እስከ ባልተለመደ መንገድ ሃይማኖትንና ፍልስፍናን አስማምቶ መተንተን እስከ ቻለው አስደናቂው የሃሳብ ሊቅ ሶረን ኪርክ ጋርድ ሁሉም የሚታወቁት በመጽሐፍት አፍቃሬነታቸው ነው::
ወደሃገራችን ስንመጣም “የታላቅ አገር መሰረቱ የሕዝብ አንድነት ነው” በሚል ፍልስፍናቸው የሚታወቁትና በግለኝነት አስተሳሰብ በዘቀጡ ዘመነ መሳፍንታውያን ተከፋፍላና ተዳክማ ለመፍረስ ጫፍ ላይ ደርሳ የነበረችውን ታሪካዊቷን ሃገር ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ አንድነቷ የመለሷት፤ ለታላቅነቷ ታላቅ ራዕይን ይዘው ህይወታቸውን እስከ መስጠት ድረስ የታገሉላት፣ የጀግንነትና የታላቅ ስብዕና ተምሳሌት የሆኑት ታላቁ ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሠት አፄ ቴዎድሮስም ለመጽሐፍት ልዩ ፍቅር ነበራቸው:: በዚህም ንጉሡ በህይወት ዘመናቸው ልዩ ልዩ ዕውቀትና ጥበብ የያዙ እስከ አንድ ሺ የሚደርሱ መጽሐፍትን በመቅደላ ጊዜያዊ ቤተ መንግስታቸው ሰብሰበው እንደነበር የአገር ውስጥና የውጭ የታሪክ ምሁራን የከተቧቸው ድርሳናት ያመላክታሉ::
በአጠቃላይ መጽሐፍት ተዝቀው የማያልቁ የዕውቀት ገበታዎች ናቸው:: ማንበብ ደግሞ ህይወትን አጥርቶ ለማየት የሚያስችል የዕውቀት ሻማ፣ ክፉና ደጉን ለመለየት የሚያግዝ የሃሳብ መመርመሪያና የእውነት ማንጠሪያ፣ የአዳዲስ አስተሳሰቦች መፍለቂያና የጠቃሚ ግኝቶች መፍጠሪያ፣ የመልካም ህይወት መምሪያና የማይናወጥ ደስታና የመንፈስ ርካታ መገኛ፣ የጥበብ መንገድና መግቢያ…የሁሉም ነገር መክፈቻ ነው:: እናም ርዕሰ ጉዳዩ ብቻውን ራሱን ችሎ አንድ ሺ አንድ መጽሐፍት ቢጻፉለት እንኳን ተዘርዝሮና ተመንዝሮ የማያልቀውን የመጽሐፍትንና የንባብን ጥቅም በዚች አጭር ጽሑፍ ለመግለጽ መሞከር “ዓባይን በጭልፋ” እንዳለው የሃገሬ ሰው የማይቻል ነውና ስለ ንባብ ፋይዳ ይህን ያህል በጥቂቱ አንዳች ስሜት ካጫርኩባችሁ ወደ ቀጣዩ ነጥቤ ልለፍ::
እንዲህ ከሆነ ቀጥለን ብንነጋገርበት ጠቃሚ የሚሆነው “ክህሎቱን እንዴት እናዳብረው? “እንዴትስ የሕይወታችን አንድ አካል የእንዳንዳችን የዕለት ተዕለት ልምድ ብሎም ባህል እናድርገው” የሚለው ይሆናል:: አንድን ክህሎት በከፍተኛ ደረጃ ለማዳበርና በክህሎቱ አማካኝነት የሚገኘውን ጥቅም አሟጦ ለመጠቀም ያለሰለሰ ልምምድ ያስፈልጋል:: ልምምዱ ሲደጋገም ልማድ ይሆናል፤ ልማዱ በበኩሉ ከስብዕናችን ጋር በደንብ ተዋህዶና በሚገባ ዳብሮ የሕይወታችን አንዱ አካል ይሆናል:: በመጨረሻም በእያንዳንዷ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንና የኑሮ ዘይቤያችን ውስጥ ሲገለጽ ከክህሎትነት ብሎም ከልማድነት አልፎ በህይወታችን ሙሉ አብሮን የሚኖር የእኛነታችን አንዱ መገለጫ ባህላችን ይሆናል:: በመሆኑም በህይወታችን እጅግ ወሳኝ የሆነው የንባብ ክህሎታችንም በዚህ መንገድ የእያንዳንዳችን አለፍ ሲልም የማህበረሰባችን ባህል እንዲሆን በግለሰብ ደረጃ በእለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ አበክረን ልንተገብረውና ልንለማመደው ግድ ይለናል::
በእርግጥ ክህሎት ልምድ ከዚያም ባህል እስኪሆን ድረስ የተወሰነ ጊዜ ይጠይቃል:: ለዚህ ደግሞ ከሰዎች ጋር በአካል እንድንራራቅና የግዴታ ካልሆነብን በስተቀር በቤታችን ውስጥ ተወስነን እንድንቆይ እያስገደደን የሚገኘው ሃገራችን ውስጥ ከገባ ስምንት ሳምንታትን ያስቆጠረው ጨቋኙ የኮሮና ወረርሽኝ ከላይ በመግቢያችን ላይ እንዳመላከትነው ከሁኔታው በተቃራኒ ገጽ ያለውን የችግሩን ሌላኛውን ገጽታ ከተመለከትነው በበሽታው ምክንያት የተፈጠረውን ከቤት ውስጥ የመቆየት ጊዜ የንባብ ባህላችንን ለማዳበር ልንጠቀምበት እንችላለን::
በኮሮና ምክንያት ቤት ውስጥ በመዋላችን እና በዚህም ነጋ ጠባ ችግሩን ብቻ እያብሰለሰልን እንደ ድብርትና ጭንቀት ለመሳሰሉ ተጨማሪ የአዕምሮና የሥነ ልቦና ችግሮች ከምንዳረግ እኛም እንደ ጠቢብ የነገሮችን ተቃርኗዊ ሁለትዮሽ ተፈጥሮ በመመርመርና ከችግሮቹ ባሻገር ያሉ ብሩህ ገጾችን መመልከት እንችላለን::
በዚህም መጥፎ አጋጣሚዎችን ወደ መልካም መለወጥና በአዎንታዊ መንገድ ተጠቅመን ማለፍ እንችላለን:: እናም ችግሩን ብቻ እያሰብን በቤት የምንውልባቸውን ጊዜያት የበለጠ እንዲረዝሙብንና እንዲሰለቹን በማድረግ ፋንታ በየቀኑ አራትም አምስትም ገጾችን ገለጥ እያደረግን በማንበብ አሁኑኑ የተዋጣለት አንባቢ መሆን ባንችል እንኳን የብዙ ሺ ኪሎ
ሜትሮች ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራልና ለነገው ዕድሜ ልክ አገልጋይ የንባብ ባህላችን መሰረት መጣል እንችላለን:: ፈጣሪ ብሎ በሽታው እስኪያልፍ ድረስ ባሉት ጊዜያት እንኳን በቤት ውስጥ በምናሳልፍበት ወቅት በየቀኑ ጥቂት ጥቂት ብንለማመድ በኮሮና ምክንያት ሳናስበው በህይወታችን ትልቁን ቁም ነገር ፈጽመን የምናልፍበት ወርቃማ ዕድል ከኮሮና ጋር ተዳብሎ ተሰጥቶን ቢሆንስ ማን ያውቃል?
አሁን በጀመርነው የንባብ ልምድ ችግሩ ካለፈ በኋላም የበለጠ ጠንክሮና ዳብሮ ራሳችንና ዓለምን ለመለወጥ የሚያስችል አዲስ ዕውቀት የምንገበይበት ቢሆንስ? እናም ቤት በምንቆይበት ሰሞን በአውሮፓና በአሜሪካ እንደምንሰማው በሴቶቻችን ላይ ጥቃት ከምንፈጽም(ነገሩ በእኛም ሃገር ቤት መዋል ከመጣ ወዲህ እህቶቻችን ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው የተከሰሱ መኖራቸውን ሰምቻለሁ) መጽሐፍትን ማንበብ እንለማመድ::
በዚያውም እኛ ኢትዮጵያውያን ያሉንን መልካም እሴቶችና አኩሪ ታሪኮች ያህል በተደጋጋሚ ከምንተችባቸውና ከምንታማባቸው ነገሮች መካከል ግንባር ቀደሙን ቦታ የሚይዘውን ደካማውን የንባብ ባህላችን በማሻሻል እንደ ግለሰብ ብሎም እንደ ህዝብና እንደ ሃገር ከምናገኘው ከፍተኛ ጥቅም ባሻገር መልካም ስምና ዝናችንንም የምንጨምርበትን ዕድልም እንፈጥራለን:: ሃሜት ብቻም ሳይሆን ከሁለት ዓመታት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገ አንድ ጥናት የንባብ ባህላችን በእጅጉ ደካማ መሆኑን አመላክቷል:: ዋና ከተሞቻቸውን እንደ ማሳያ በመውሰድ የዓለም ሃገራትን የንባብ ባህል የገመገመው ጥናት እንደ ጃፓንና ጀርመን የመሳሰሉትን አገራት በማንበብ ባህላቸው ከፍተኛ ደረጃ መድረሳቸውን የጠቆመ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለው የንባብ ባህል ግን በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን አመላክቷል::
የዓለም ሃገራት ዋና ዋና ከተሞችን የንባብ ባህል “ከፍተኛ”፣ “መካከለኛ” እና “ዝቅተኛ” በሚል በሦስት ምድብ ውስጥ በቅደም ተከተል ስማቸውን በደረጃ ያስቀመጠው ጥናቱ የእኛዋን አዲስ አበባ ግን ዝቅተኛም ቢሆን ከነጭራሹ ደረጃ ውስጥ ሳያስገባት “የማታነብ ከተማ” በማለት ተሳልቆባት አልፏል:: የንባብ ባህላችን በሚመለከት ሃቁ ቢመረንም ለእኛም ልካችንን ነግሮናል::
የማያነብ ህዝብ ደግሞ የብልጽግና ትንሳኤው ሩቅ ነውና ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ የንባብ ባህላችን ለማሻሻል እንደ ዜጋ እያንዳንዳችን የበኩላችንን መወጣት ይጠበቅብናል:: የዛሬው ዕይታዬ በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል:: ይሁን እንጂ የንባብ ባህል ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም:: ዛሬ ላይ በዳበረ የንባብ ባህላቸው የሚታወቁት ጀርመናውያን በአንድ ወቅት “በመጸዳጃ ቤቶቻችን የምናነበው ነገር ይቀመጥልን” በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው መንግስታቸውን መጠየቃቸውን ታሪክ ይነግረናል:: ሆኖም ታሪክ የእኛዎቹ ጥራዝ ነጠቆች እንደሚሉት ፋይዳ የሌለው ባዶ ተረት ተረት አይደለምና፤ ሰዎች በተግባር አድርገው ለትውልድ ያስተላለፉት ሰርቶ ማሳያ ቅርስ ነውና እኛም ከዚህ ታሪክ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር አለ:: ይህም ጀርመናውያኑ እንዲህ ዓይነቱን ድንቅ የንባብ ባህል እንዴት አዳበሩት፣ እኛስ የንባብ ባህላችንን ለማሻሻልና እነርሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ነው::
ይህ እንግዲህ ጀርመናውያኑ መጸዳጃ ቤት ውስጥም ሆነው ማንበብ ይፈልጋሉ ማለት እጅግ የሚደነቅ ከፍተኛ የሆነ የንባብ ባህል አላቸው ማለት ነው:: ለመሆኑ ጀርመናውያኑን መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሳይቀር እንዲያነቡ ያነሳሳቸው ምክንያት ምንድነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል:: እንዲህ ዓይነቱን አንባቢነትስ “የንባብ ባህል” የሚለው ብቻ ይገልጸዋልን? ደካማውን የንባብ ባህላችን ለማሻሻል እነዚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመርመርና መመለስ ይገባል:: ምክንያቱም የንባብ ባህላችን ለማሻሻል ትልቁ ሚስጥር ያለው በእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ነውና:: ታዲያ እነዚህን ወሳኝ ጥያቄዎች አንስተን ጉዳዩን በጥልቀት ስንመረምር የዳበረ የንባብ ባህልን ለመፍጠር በቅድሚያ “የንባብ ፍቅር” ሊኖር ይገባል የሚል መሰረታዊ ሃሳብ እናገኛለን:: አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር፤ እንደ ሃገር የዳበረ የንባብ ባህል በለቤት ለመሆን መፍትሄውም ይኸው ነው::
መጽሐፍትን ማፍቀር፣ ንባብን ማፍቀር ቁልፉ ጉዳይ ሆኖ እናገኛዋለን:: ምክንያቱም አንድን ነገር ሳንፈልገው፣ ሳንወደው እንዴት እንዲኖረን እናደርገዋለን? እናም በምንፈልገው ነገር ላይ ጥሩ ችሎታ እንዲኖረን ከፈለግን ከሁሉም በፊት ለዚያ ነገር ፍቅር ሊኖረን ይገባል:: ከላይ የተገለጸው የጀርመናውያኑ ሁኔታም የሚያሳየን ይህንኑ ነው:: እነሱ አይደለምና በመደበኛው ጊዜያቸው በዚያች የደቂቃ የመጸዳጃ ቤት ቆይታቸውም የሚነበብ ነገር ማጣት አይፈልጉም:: ለምን ቢሉ ንባብን ያፈቅሯታልና! ከማንበብ ፍቅር ይዟቸዋልና! ይህም የንባብ ፍቅራቸው በከፍተኛ ደረጃ የዳበረና የበለጸገ የንባብ ባህልን ፈጠረላቸው::
የእኛም አገር ትልቁ ችግር የንባብ ባህል አለማዳግ ሳይሆን የንባብ ፍቅር አለማደግ ነውና እዚህ ጋር ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል የሚል ዕምነት አለኝ:: ለመሆኑ ማንበብ እንወዳለን? ስንቶቻችን ነን ለመደበኛ ትምህርት ወይም የሆነ አስገዳጅ ነገር ተፈጥሮብን ካልሆነ በስተቀር ለንባብ ፍላጎት ኖሮን፣ ፍቅሩ ኖሮን የምናነበው? ማንበብን የምንስለውስ እንዴት ነው? እንደ አንድ አስጨናቂ ሥራ ወይስ እንደ አዝናኝ የአዕምሮ ምግብ? መልሱን ለእያንዳንዳችን ልተወው::
ከዚሁ ከንባብ ፍቅር ጋር በተያያዘ አንድ ወዳጄ ያወራልኝን ቀልድ የምትመስል ዕውነት ነግሬያችሁ ወደ ቀጣዩ ክፍል ልለፍ:: “ልጆች ያስቀመጥከውን ብር እያነሱ ካስቸገሩህ መጽሐፍ ውስጥ ደብቀው፣ ሌባ ይወስድብኛል የሚል ስጋት ካለህም ይህ ዘዴ ግሩም መፍትሄ ይሆንልሃል”:: አይገርምም? በእኛ አገር መጽሐፍት የሚፈለጉና የሚፈቀሩ ሳይሆኑ የሚያስፈሩና የሚያስጠሉ ናቸው ማለት ነው? ታዲያ እውነት መጽሐፍትን እየፈራናቸውና እየጠላናቸው፤ እንዲህ እየሰለቸናቸው ከሆነ እንዴት ነው የንባብ ባህላችን የሚያድገው? ስለሆነም በህይወት ዘመናችን ለዕድሜ ልክ ልንገለገልበትና ማናቸውንም የፈለግነውን ነገር ለማድረግና ለመሆን የስኬት በሮችን ሁሉ የሚከፍትልንን እጅግ አስፈላጊውን ባህል ለመገንባት እንችል ዘንድ ቤት ውስጥ ብዙ ጊዚያቶችን በምናሳልፍበት በዚህ በዘመነ ኮሮና መለማመድ ያለብን ንባብን ብቻ ሳይሆን የንባብ ፍቅርንም መሆን ይገባዋል በማለት ልሰናበታችሁ ወደድኩ::
ቤታችን ስንውል ዛሬውኑ ማንበብ እንጀምር፤ ኮሮና ከሚያመጣብን ጭንቀት ተገላግለን ለነገ ደግሞ ወሳኝ የሕይወት ዘመን ስንቅ እንቋጥር፣ እነርሱ ምን አደረጉን በአንድ ድንጋይ ወፎቻችንን ሳይሆን ኮሮናንና ደካማ ልምዳችንን እንምታ! ፈውስና ምህረት ለዓለማችን::
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
ይበል ካሳ