ታህሳስ 8 ቀን 1965 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ደረቅ ቼክ በመጻፍ “የመጀመሪያዋ አጭበርባሪ” ያላት ግለሰብ ስለመከሰሷ የሚገልጽ ዘገባ አስነብቦ ነበር::
ለመጀመሪያ ጊዜ በቼክ አጭበረበረች የተባለች ተከሰሰች
በባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ሳይኖራት ያላት በማስመሰል የባንክ ቼክ ጽፋና ፈርማ ሁለት ሺ ብር ወስዳለች የተባለችው እመት ሜሪጂ ካፋሲ ተከሳ ፍርድ ቤት ቀረበች:: ዕድሜዋ 45 ዓመት የሚሆናት ሴት ከሳጥን ገንዘብ የሌለውን የባንክ ቼክ ሰጠች የተባለችው እመት መሰለች ደስታ ለተባለችው ሴት ያለባትን ዕዳ ለመክፈል ምክንያት በማድረግ መሆኑ ታውቋል::
ተከሳሿ ሐሰተኛ ቼክ ሰጥታለች የተባለው አዲስ አበባ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቼክ ደረሰኝ በመስጠት መሆኑን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት የቀረበባት የዓቃቤ ህግ ክስ ይገልጻል:: እመት ሜሪ ወንጀሉን ፈጽማለች የተባለው አዲስ አበባ ገዳም ሰፈር ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን ከመኖሪያ ቤቷ እንዳለች መሆኑ ከፍርድ ቤቱ በተገኘው ዜና ታውቋል::
ተከሳሿ “ጥፋተኛ አይደለሁም” በማለት ክዳለች:: የችሎቱ ዓቃቤ ሕግ እንደክሱ አቀራረብ የሚያስረዱ የሰው ምስክሮችና የጽሁፍ ማስረጃዎች አሉ በማለት ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል:: ፍርድ ቤቱም ተከሳሿ በዋስ ቆይተው ክርክር እንዲቀጥል አዟል::
*****
ሰኔ አምስት ቀን 1955 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዶሮ አርቢዎች የተሻለ ምርት እንዲያገኙ የሚያስችል የዶሮዎች መነጽር መሰራቱን የሚገልጽ ዘገባ አስነብቦ ነበር::
ለርቢ ዶሮዎች የዓይን መነጽር
አንድ የካሊፎርኒያ ፈላስፋ የሆነ ሊቅ ጥሩ ዘርና ጥሩ እንቁላል ያላቸው ዶሮዎች ወይም ዶሮን የመሳሰሉ ወፎች ለማበርከት ከቀይ ፕላስቲክ የተሰራ የአይን መነጽር ሰርቷል:: ሚስተር ኤ ደብልዩ የተባለው ይህ ሊቅ ለቃል አቀባዮች እንደገለጸው መነጽሮቹ ዶሮዎቹ የሚያይቱን ሁሉ ቀይ በማድረግ ሁልጊዜ ቀይ የሆነን ነገር በማየት ተሯሩጠው ቆሻሻ ነገርን ሁሉ ከመብላት ያስታግሳቸዋል ሲል አስረድቷል:: መነጽሮቹ በዶሮዎቹ አይነ ጋጃ ላይ በቀላሉ ለመለጠፍ የሚችሉ መሆናቸውም ተገልጿል:: እነዚህ መነጽሮች ወደፊት በሌሎችም እንስሳቶች ላይ ይሞከራል ተብሏል::
*****
ሐምሌ ሦስት ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ውሃ በመስረቁ የሶስት ወር እስራት ስለተፈረደበት ዘበኛ ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር::
የውሃ ሌባ ሶስት ወር ተፈረደበት
ውሃ ሰርቆ ሸጧል ተብሎ የተከሰሰው በላይ ዘገየ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት በሶስት ወር እስራት እንዲቀጣ የደሴ ዙሪያ አውራጃ ፍርድ ቤት ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት ፈረደ::
የመጠጥ ውሃ ሰርቋል ተብሎ እስራት የተፈረደበት ይኸው ሰው በደሴ ከተማ በአቶ መሀመድ አሊ ቤት በዘበኝነት ተቀጥሮ በሚሰራበት ጊዜ በግቢው ውስጥ የሚገኘውን የቧንቧ ውሃ ሌሊት እየከፈተ ለሌሎች ሰዎች ሲሸጥ መገኘቱ ተረጋግጧል:: በዚህ ምክንያት ባለቤቶቹ ከፍ ያለ የገንዘብ ኪሳራ ያስከተለባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ቃል ገልጸዋል:: ተከሳሹ አንዱን በርሜል ውሃ በሃምሳ ሳንቲም እየሸጠ ይጠቀም እንደነበር ተረጋግጧል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
የትናየት ፈሩ