ግብርና ለዓለም ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡ ያለ ግብርና የሰው ልጅ ህልውና ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ በዚህም ምክንያት የዓለም ሀገራት ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው የግብርናውን ሴክተር ለማዘመንና ምርትን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ ከላይ እታች ይላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ጥቂት የማይባሉ ሀገራት ከራሳቸው ፍጆታ ተርፎ ምርታቸውን ለሌሎች በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን በውጭ ንግድ ይገነባሉ፡፡ ኢትዮጵያም ለግብርና ሥራ አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ብትሆንም የምርት አቅሟ ግን ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንኳን የሚበቃ አልሆነም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን ሳይጨምር 123 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የውሃ ሀብትና ከ36 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ሀገሪቱ የምትፈልገውን ሰብል በተለያዩ አካባቢዎች ለማምረት እንድትችል ዕድል ቢፈጥሩም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ግን በሰብል የለማው የአገሪቱ መሬት በጣም ጥቂት ነው፡፡
ለምሳሌ ስንዴ ለኢትዮጵያ ከጤፍ፣ ከበቆሎና ማሽላ ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ የሚመረት የሰብል ዓይነት ቢሆንም በስንዴ ምርት የሚለማው መሬት በጣም ውስን ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ አገሪቱ ለዜጎቿ የዕለት ተዕለት ፍጆታ የሚውል ስንዴን ከውጭ ለማስገባት ተገዳለች፡፡ በዓመትም ስንዴ ከሌሎች ሀገራት ለመግዛት የምታወጣው ወጪ በጣም ከፍተኛ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ይህንን የግብርና ሥራውን ኋላ ቀርነት ለመደገፍና ኢትዮጵያም በምግብ እህል እራሷን እንድትችል ለማድረግ መንግሥት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ነው:: ከነዚህ እንቅስቃሴዎቹ መካከል ደግሞ የምርምር ኢንስቲትዩቶችና ማዕከላት የሚያወጧቸውን የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ይገኝበታል::በዚህ ሥራም እስከ አሁን ጥሩ የሚባል ተሞክሮዎች ያሉ ቢሆንም አሁን መድረስ ካለበት ደረጃ አንጻር ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይናገራሉ::
እኛም በርካታ የግብርና ተመራማሪዎች ያሉትና ለግብርና ሥራው መዘመን ትልቅ ኃላፊነት ከተጣለበት ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ከዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ጋር እየተሰሩ ባሉ የምርምር ሥራዎች ግብርናውን የተሻለ ዘመናዊ ለማድረግና በምግብ እህል ራስን የመቻል ጉዞው ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ጠይቀናቸው መልስ ሰጥተውናል::
አዲስ ዘመን፦ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ሥራዎቹን በምን መልክ እየሰራ ነው:: ውጤታማነቱስ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት አላማ መካከል የግብርና ቴክኖሎጂ ማፍለቅ፣ ማባዛት እንዲሁም ማሰራጨት ይገኙበታል:: ቴክኖሎጂ የሚባሉት ለምሳሌ በሰብል በኩል የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮች ዲቃላና ዲቃላ ያልሆኑ ሰብሎች ናቸው :: በእንስሳት በኩል ደግሞ የተሻሻሉ ዝርያዎች ሲሆኑ በሜካናይዜሽን ዘርፍም የተሻሻለ የማረሻና የመዝሪያ እንዲሁም የመውቂያ መሣሪያዎችን ማቅረብ ነው:: በተመሳሳይ ባዮቴክኖሎጂ ላይ ለምሳሌ መሬት በምን መልኩ በምን ያህል ርቀት መታረስ አለበት:: እንዴት መዘራት አለበት? በመስመሮች መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት ምን ያህል ሊሆን ይገባል:: የሚሉና ሌሎች መረጃዎችም አሉ:: በሌላ በኩልም የሰብል ጥበቃ ሥራዎች ይሰራሉ:: በዚህም በሽታን፣ ተባይን፣ እንዲሁም አረምን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ምክረ ሀሳቦች ይወጣሉ:: ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 1ሺ300 ያህል ቴክኖሎጂዎችን አውጥቷል:: ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተያያዥ የሆኑ ምክረ ሀሳቦችንም አሰራጭቷል፤ እነዚህ ሁለቱ በአንድ ላይ ሲወጡም በፓኬጅ መልክ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ
በሚያደርግ መንገድ ነው::
አዲስ ዘመን ፦ እነዚህ ሥራዎች የግብርና ሴክተሩን ምን ያህል ቀይረውታል::
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የምግብ ዋስትና ከ20 እስከ 40 ሚሊዮን በነበርንበት ጊዜ ያለው የምግብ ዋስትና ሲታይ እነዚህ ሥራዎች ተከናውነው የግብርና ባለሙያዎቹ ተጨማሪ ምርት ማምረት ባይችሉ ኖሮ ችግሩ በጣም ይብስ ነበር:: በመሆኑም ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ግልጽ ነው:: እዚህ ላይ ግን አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች አሉ፤ የምርምር ውጤቶቹ በፓኬጅ መልክ ወይንም ደግሞ ከምርምር በተሰጠው አስተያየት መሠረት አርሶ አደሮቹ ጋ ሙሉ በሙሉ ደርሷል ለማለት አይቻልም::ለምሳሌ በሰብል በኩል የተሻሻለ ምርጥ ዘር የሚጠቀሙ ከ30 እስከ 40 በመቶ ቢሆኑ ነው::ነገር ግን 90 በመቶና ከዚያ በላይ አርሶ አደሮች ቢጠቀሙ እኛ ከራሳችን አልፈን ሌሎች አገሮችን መመገብ የምንችል፣ የግብርና ውጤቶቻችንን ለውጭ ገበያ የምናቀርብ፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ማቅረብ የምንችል እንሆን ነበር::
አዲስ ዘመን ፦ ይህ ከሆነ የምርምር ውጤቶቻችንን ለምንድን ነው ወደ አርሶ አደሮቹ ጋር ማውረድ ከባድ የሆነው::
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ ችግሮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ዋናው ነገር ቴክኖሎጂን በበቂ ሁኔታ የሚያባዛ አካል አለመኖር ነው:: ለምሳሌ ዘር የሚያባዛው የመንግሥትም ሆነ የግል ሴክተር ቢደመር አቅማቸው ከ28 እስከ 30 በመቶ ብቻ ነው::ይህ ሁኔታ ደግሞ በመንግሥትም በሴክተሩም በምርምር ደረጃም ይታወቃል::ከአምስት ወይም ስድስት ወራት በፊት አዲስ « ብሔራዊ የዘር (የሲድ ) ፖሊሲ» ቀርጸናል:: ይህ ደግሞ ስትራቴጂ ተሰርቶለት ወደ መሬት ሲወርድ ችግሮቹን ይፈታል:: በዚህም የግል ሴክተሩ አቅም እየተገነባ ይሄዳል::
በሌላ በኩል ሁሉም አርሶ አደር ስለ ግብርና ቴክኖሎጂ ያውቃል ለማለት ይከብዳል፤ በመሆኑም እውቀቱን ክህሎቱንና ልምዱን መገንባት ያስፈልጋል:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሰርቶ ማሳያዎችን ማብዛት በጣም ወሳኝ ነው:: ግን የእኛ የምርምር ማዕከላት 20 ናቸው፤ የክልሎችም ቢደመሩ 69 ቢደርሱ ነው ይህ ደግሞ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ወይንም ደግሞ 16 ሚሊዮን አርሶ አደር ላለባት አገር ምንም ነው:: ከቁጥሩ ማነስ የተነሳ ጥሩ ሰርቶ ማሳያዎች የሚታዩት ለማዕከላቱ ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ ነው:: በመሆኑም ወደ ገጠሩም ተመሳሳይ ጣቢያዎች ያስፈልጋሉ::
አዲስ ዘመን፦ ቁጥሩን ለማሳደግ እንደ ምርምር ኢንስቲትዩት የሄዳችሁት እርቀት ምን ያህል ነው::
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ይህንን ለማድረግ የሚገድበን በጀት ነው::ከመንግሥት የሚመደብልን በጀት በቂ ቢሆን ኖሮ እነዚህን የሳተላይት ጣቢያዎች በደንብ አስፋፍተን በዙሪያቸው ያሉ አርሶ አደሮችን የማነቃቃት ሥራ እንሰራ ነበር:: ከዚህ ቀደም እነዚህ ውስን ጣቢያዎች ያመረቱት የተሻሻለ ዘር የሚፈልገው በማጣት ያድር ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ ዘሩ ተርፎ ሳይሆን የት ቦታ ምን እንዳለን ባለመታወቁ ነው:: ስለዚህ ከላይ የገለጽነው ብሔራዊ የዘር (ሲድ) ፖሊስ በመላው አገሪቱ የተመረተውን ዘር በዓይነት በማስቀመጥ በክልል፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በዞን፣ በወረዳና ሌሎች የምርምር ማዕከላት ባሉበት አካባቢ እንዲሰራጭ ይደረጋል:: ይህ መሆኑ ደግሞ የት ቦታ ምን እንዳለ ሁሉም ያውቃል ማለት ነው::
አዲስ ዘመን ፦ ብሔራዊ የዘር ( ሲድ )ፖሊሲው በሥራ ላይ ውሏል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በአዋጅ ጸድቋል ወደ ስትራቴጂ ለመቀየር ስምንት ሰዎችን የያዘ ቡድን በማቋቋም እንዴት አድርገን መሬት እናስነካው የሚለውን እየሰራን ነው::የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባይመጣ ኖሮ በመስከረም ወር አካባቢ ይፋ ይደረግ ነበር :: እንግዲህ የወረርሽኙን ስርጭት ተቆጣጥረነው ወደቀድሞ ሁኔታችን ከተመለስን
በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ወደ ትግበራ እንገባለን:: አሁንም ግን ሥራውን አላቆምንም?
አዲስ ዘመን፦ ኢንስቲትዩቱ የሚያፈልቃቸውን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሁሉም አርሶ አደር ለማውረድ የበጀት እጥረት እንዳለበት ነግረውኛልና ከባለድርሻ አካላት ጋርስ መስራት አይቻልም?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ከሁለት ዓመት በፊት የግብርና ትምህርት ተቋማት፣ የግብርና ምርምር ማዕከላት፣ የግብርና ኤክስቴንሽንና የግብርና ግብይትን የያዘ ቁርኝት ፈጥረናል:: ይህ ደግሞ የምርምሩ፣ የኤክስቴንሽኑ እንዲሁም የግብይቱ ባለሙያዎች የሚወጡት ከትምህርት ቤት በመሆኑ ነው፤ ትምህርት ላይ ችግር ካለ ሁሉም ነገር ይበላሻል፤ ስለዚህ ትምህርቱ የሚጠናከርበትን መንገድ ለመፈለግ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ምርምር ካልተሰራ ግብይቱም ሆነ ኤክስቴንሽኑ ውጤታማ ስለማይሆን ምርምሩን ለማጠናከር፤ ምርምር ተሰርቶ ወደ አርሶ አደሩ የሚወስደው የኤክስቴንሽን ክንፍም በትክክል ካልሄደ ውጤቱ ምንም ስለሚሆን ለእሱም ተገቢው ትኩረት ለመስጠት፤ በዚህ መልኩ የተመረተው ምርት ደግሞ ገበያ ወጥቶ ገዥ ካላገኘ አሁንም ችግር በመሆኑ ነገሮችን በአንድ ላይ በማስተሳሰር
እየተሰራ ነው?
ከማስተሳሰር ባሻገር ደግሞ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በእውቀትም በልምድም የዳበረውንና በምርምር ተቋም ውስጥ ያለውን ባለሙያ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ እየሄዱ እንዲያስተምሩ በማድረግ ጠንካራ ሰዎችን የማውጣት፤ የትምህርት ተቋማቱ መምህራን ወደ ኢንስቲትዩቱ በመምጣት የምርምር ልምድ እንዲያዳብሩ የማድረግና የባለሙያ ልውውጥ ሥራ እየተሰራም ነው::
የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች የሚሰሯቸው ምርምሮች በደንብ የተቃኙ ባለመሆናቸው ሥራዎች ይደጋገማሉ፤ ይህንን ሊያስቀር የሚችል ትልቅ ይዘት ያለው የምርምር ሥራ ርዕስ እንሰጣቸዋለን:: ኤክስቴ ንሽንን በተመለከተ ማንኛውም የግብርና ውጤት ያለው ተቋም በአካባቢው የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት አለበት:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ በየዞኑ ቢቻል በየወረዳው የግብርና ልማት ማስተር ፕላን ስለሚያስፈልግ ያንንም እየሰራን ነው:: ምክንያቱም ግብረ ሰናይ ድርጅቱም፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሙም እንዲሁም ሌሎች በተለያየ መንገድ የተበጣጠሰ ነገር ይሰራሉና ይህ እንዳይሆን ሥራ ለመስራት የሚመጣ ሁሉ ለማስተር ፕላኑ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ለማድረግ እየሰራን ነው::
አዲስ ዘመን፦ ተቀናጅቶ መስራቱ ጥሩ ነው ግን ስምምነቱን በመጠበቅ በኩልስ ምን ያህል ውጤታማ ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ እኔና አንቺ የስምምነት ሰነድ ሊኖረን ይችላል ፤ በሕግ ፊትም ተቀባይነት አለው፤ ግን አንደኛው ወገን ይህንን ሁኔታ ሊጥስ ይችላል፤ ስምምነቱ ሲጣስ ተጠያቂ የሚያደርግ ማዕቀፍ ደግሞ የለውም:: ይህ እንዲኖር እየተሰራ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ከላይ የዘረዘርናቸው አሠራሮች ምናልባትም ዋል አደር ብለው ግብርናውን የሚያዘምኑ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ለግብርና ሥራ የምንጠቀምበትን ውስን መሬት ለማስፋት እየተሰራ ያለ ሥራ የለም?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በዚህ በኩል ላለፉት ሁለት ዓመታት ጥሩ ውጤት ያገኘንበት ሰፋፊ ሰርቶ ማሳያዎችን በማብዛት የአርሶ አደሩን አእምሮ በሚስብ መልኩ በሰፊው መስራት ነው::በዚህም አንድ ሰርቶ ማሳያ ከ10 ሄክታር ባላነሰ መሬት ላይ እንዲሰራ እየተደረገ ነው:: በአራቱ ትልልቅ ክልሎች ላይ ውጤትም አግኝተንበታል:: ይህ በደጋው አካባቢ የተሰራ ነው፤ በቆላው ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ሰፋፊ ሥራዎችን በሩዝ፣ በስንዴና በአኩሪ አተር ላይ ጀምረናል:: በዚህም ጥሩ ውጤት ተገኝቷል:: በሌላ በኩል ደግሞ መሬትን ከማስፋት ባሻገር በአንድ መሬት ላይ ሁለትና ሦስት ጊዜ መዝራት የሚለውን እንደ ትልቅ አማራጭ እየተጠቀምንበት ነው::
ለምሳሌ በቆላማው አካባቢ በክረምት ጥጥ ይመረታል፤ ምርቱ ከተነሳ በኋላ ስንዴ፤ ቀጥሎም አኩሪ አተር ይመረታል:: ይህ ማለት ደግሞ በአንድ መሬት ላይ ሦስት እጥፍ ትርፍ ማግኘት ማለት ነው::በእነዚህ ሦስት የሰብል ዓይነቶች ላይ ትኩረት ያደረግንበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ሁሉም ከውጭ የምናስገባቸው በመሆናቸው ነው፤ እነዚህ እንደ ትልቅ ሥራ ሲያዙ ደግሞ እነሱን ለማምጣት የሚጠፋውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በነበረን መሬት ላይ በዝቅተኛ ወጪ ማምረት ያስችላል:: በመሆኑም አምና በ3ሺ 500 ሄክታር መሬት ጀምረን ዘንድሮ ወደ 20 ሺ ሄክታር ለማሳደግ ችለናል፤ ለሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ከኮሮና መከላከል ሥራው ጋር በማያያዝ የተሻለ ሥራን ለመስራት በጀት በማስፈቀድና እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማስገምገምና ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲወያዩበት ሆኗል ፤ በቀጣይ ገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች የማስረዳትና በጀቱን በማስፈቀድ ወደ ሥራ መግባት ነው:: ይህንን ካደረግንና በክረምት ያቀድነውን ካሳካን ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል እናገኛለን::ይህ ደግሞ ሊገጥመን የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም ያግዛል::
ለምሳሌ አሁን ያለው ግምት 15 ሚሊዮን ተጨማሪ ሰዎች እርዳታ ሊፈልጉ ይችላሉ የሚል ነው፤ ይህ ደግሞ አሁን ላይ 8 ሚሊዮን በሴፍቲ ኔት የሚታገዙና 6 ሚሊዮን በቀጥታ የሚደገፉ አሉን፤ በዚህ ላይ 15 ሚሊዮን ሲደመር በጣም ከፍተኛ ነው ፤ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ ደግሞ ከውጭ ገዝተን ለማምጣት ገንዘብ የለንም ቢኖረንም ደግሞ አንችልም:: ምክንያቱ በወረርሽኙ ምክንያት አንዳንድ አገሮች ምርት ስላቋረጡ፤ አሁን ላይ ያለን አማራጭ በአገር ውስጥ ምርት ፍላጎታችንን ማሳካት ነው::
አዲስ ዘመን፦ በተለይም ስንዴ እስከ አሁን ከውጭ የምናመጣው ሰብል ነውና አሁን ላይ የተሻሻሉ ዝርያዎች ይኖሩ ይሆን?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎች በጣም ብዙ አሉን::ለቆላ ብቻ ይሆናሉ ብለን የለቀቅናቸው 7 ዝርያዎች፤ ለደጋ ደግሞ 41 ዝርያዎች አሉን:: ሰዎች ብዙ ጊዜ ለቆላ የሚሆን ስንዴ የለም ይላሉ፤ ግን ስንዴ ለቆላም ለደጋም ለወይናደጋም የሚሆን አለ::የሚፈለገው የአየር ጸባዩን ተስማሚ ማድረግ ብቻ ነው::አሁን ላይ ከአፋምቦ ከጅቡቲ ጠረፍ እስከ ጅማ ድረስ ሞክረናል ውጤትም አይተንበታል::ለምሳሌ ስንዴን በክረምት አፋር ወይም ሶማሌ ላይ ቢዘራ ሙቀቱ ከፍተኛ ስለሆነ አይሳካም። ግን በዚያው አካባቢ የጥጥ ምርቱ እንዳበቃ የአየር ጸባዩም እየቀዘቀዘ ስለሚሄድ በጥቅምት፣ ኅዳርና ታኅሣሥ ላይ ማምረቱ ውጤታማ ያደርጋል :: ቀጥሎ የሚመጣው የአየር ጸባይ ሙቀት ስለሚሆን ለአኩሪአተር ምቹ ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ አዳማን ይዘን ወደ አዋሳ አካባቢ ስንሄድ መሬቱ ለሦስት ወራት ያህል ጤፍ ተዘርቶበት ከተሰበሰበ በኋላ ባዶውን ነው የሚሆነው፡፡ ወዲያው ስንዴ ብንዘራበትስ ብለን ሞከርነው ተሳካልን፤ በመሆኑም በስንዴ ምርት ራሳችንን ለመቻል ይህንንና ሌሎች በርካታ ሙከራዎችን እያደረግን ተስፋ ሰጪ ውጤቶችንም እያየን ነው::
አዲስ ዘመን፦ እንደ ምርምር ተቋም የከተማ ግብርናን አስፋፍቶ ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ነገር ከጓሮው እንዲያገኝ በማድረግ በኩል የተሰራው ሥራ ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ የከተማ ግብርና ትልቅ አቅም ያለው ሴክተር ቢሆንም ምንም ትኩረት አልተሰጠውም::ትኩረት ለማጣቱ ደግሞ ዋናው ምክንያት
የግብርና ሴክተር አካል አለመሆኑ ነው?
አዲስ ዘመን፦ የግብርና ሴክተር ካልሆነ የምን ዘርፍ ነው ታዲያ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በአወቃቀር ደረጃ በከተማ አስተዳደሩ በንግድ ውስጥ እንደ አንድ ሂደት ተደርጎ የተቀመጠ ነው፤ አሁን ግን አዲስ አበባ ቢያንስ እራሷን ትቻል ሲባል ነው ወደ ከተማ ግብርና የተገባው::ዓለም ላይ እኮ ብዙ ከተሞች ለምሳሌ በወተት ምርት ራሳቸውን ይችላሉ፡፡ የእኛዋም አዲስ አበባ በዚህ መልኩ ራሷን የማትችልበት ምንም ምክንያት የለም::ከተማዋ ያላት የአየር ጸባይ ለወተት ከብቶች እጅግ ተስማሚ ነው::በሌላ በኩል ደግሞ አትክልት ማምረት ይቻላል::ምናልባት ሰዎች በከተማዋ ያሉ ወንዞች የተበከሉ ከመሆናቸው አንጻር ከቶክሲን ጋር ተያይዞ ይፈራሉ፤ ግን ደግሞ በንጹህ ውሃ አልያም ያንን ውሃ አጣርቶ መጠቀምም ይቻላል
ዋናው ችግር እቅዱ አለመኖሩ ነው::
በሌላ በኩልም የመሬት ችግር እንዳይነሳ አንድ ቦታ ላይ በተለያየ ደረጃ አትክልቶችን መትከል ይችላል፤ ሌላው አገር እኮ በኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቀር ሙቀት እየሰጡ ነው የሚያመርቱት፤ በመሆኑም ሥራ የሌላቸው ወጣቶችን በማደራጀት በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው::ሌላው በጣም በቀላሉ በትንሽ ቦታ ላይ ዶሮ ማርባት ይቻላል::በዚህ መልኩ ከተሰራ አዲስ አበባ በወተት፣በእንቁላልና በአትክልት ከ 70 እና 75 በመቶ በላይ ራሷን ትችላለች::
ብዙ ጊዜ በከተማና ከተማ ቀመስ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የግጭት መነሻው በኢኮኖሚ አለመተሳሰር ነው::በሁለቱ መካከል የኢኮኖሚ መስተጋብር ቢኖር ኖሮ የተረጋጋ አካባቢን መፍጠር ይቻላል::አንዳንዶች እንዲያውም በገጠር አፈር ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር በሙሉ ወደ ከተማ እየገባ ነው ይላሉ፤ ይህ ደግሞ የወደፊቱ ለም መሬት የሚኖረው በከተማ ውስጥ መሆኑን አመላካች ነው፤ በመሆኑም የከተማና የከተማ ቀመስ ሕዝቦች የልማት ትስስር በጣም ወሳኝ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ግብርናውን ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር እየተባለ በተደጋጋሚ የሚነሳ ነገር ነበርና በዚህ ላይ ትንሽ የተራመድንበት ነገር ይኖር ይሆን?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ እኔ የማውቀው ሰፊ ነገር የለም:: አንዳንድ ሰዎች ሁኔታውን እንደ እንቁላልና ዶሮ ያዩታል የትኛው ነው መቅደም ያለበት በማለትም ጥያቄ ያነሳሉ፤ የግብርና ሴክተሩ አድጎ ምርት ሲትረፈረፍና ወደ ኢንዱስትሪ የሚሄድ ነገር ሲኖር ኢንዱስትሪን መገንባት የሚልም አስተሳሰብ ያላቸውም አሉ::በሌላ በኩል ደግሞ የግብርና ሴክተሩን የሚያሳድገው ገበያ ነው፤ ገበያው ከሌለ አያድግምና አግሮ ኢንዱስትሪውን ፈጥረን ለዚያ ግብዓት እንዲያቀርብ በማድረግ ነው ማደግ ያለበት የሚሉ አሉ::
እንደ እኔ እምነት የተቋሜ ሀሳብ አይደለም::እኛ ከሁለቱም ወጣ ያልን ነን:: ብዙ ቦታ ኢንዱስትሪ፣ አግሮ ኢንዱስትሪ ብለን ከፍተናል፤ እነዚያ መሠረተ ልማቶች አሁን ላይ በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ ነው? አይደለም:: ስለዚህ ያን ያህል ገንዘብ አፍሰንባቸው አሁንም የባንክ ወለድ የሚከፈልባቸው ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ ካልሆኑ ለምን ቸኩለን ወደዚያ ሄድን:: ለእኔ ተመጋጋቢ የሆነ እድገት መኖር ነበረበት፡፡ ግብርናው አድጎ ብዙ ትርፍ ምርት ሲኖር ኢንዱስትሪው ደግሞ ተቀብሎ እሴት እንዲጨምርበት ብናደርግ ኖሮ የተሻለ ውጤታማ እንሆን ነበር ብዬ አስባለሁ::
ኢንዱስትሪ ብለን ያወጣነውን ወጪ ግብርናው ላይ አፍሰነው ቢሆን ኖሮ የት ያደርሰን ነበር::ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ኢንዱስትሪው ብንመጣ ኖሮ የምናገኘው ታክስ በራሱ ብዙ ሊሰራ ይችል ነበር የሚል ግንዛቤ ነው ያለኝ:: በመሆኑም ለኢንዱስትሪው ቸኮልን ግብርናው ላይ ደግሞ በጣም ዘገየን::
በነገራችን ላይ የገቢና ወጪ ንግዳችንም እንደዚሁ ነው የግብርና ምርት እንሸጣለን መልሰን እንገዛለን:: ግብርና ለአገሪቱ የጀርባ አጥነት ነው እያልን መልሰን የግብርና ምርት መግዛታችን በራሱ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች አለማወቃችንን ያሳያል:: ለምሳሌ ስንዴን፣ ሩዝንና ሌላውንም ለማብቀል ምን ያህል እናወጣለን ምናልባት እኮ እነዚህን ነገሮች ለመግዛት የምናወጣውን የአንድ ዓመት በጀት ብንመድብ ሴክተሩ ይመነደጋል::
አዲስ ዘመን፦ አንዳንዶች ከማምረት የተመረተውን ከውጭ ማስገባት አዋጭ ነው ይላሉ::እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ማስገባቱ አዋጭ አለመሆኑን በመረጃ አስደግፈን እናሳያቸው:: ምን ያህል ቢመረት ነው ውጤታማ የሚኮነው በሄክታር 18 ኩንታል ከተመረተ ከዚያ በላይ ያለው ትርፍ ነው ይህንን የምናሰላው ደግሞ ራሳችን ነን፤ በመሆኑም አዋጭ አይደለም እንላለን::ይሄንን እንዲሆን ደግሞ መንግሥት ከገዛ በኋላ አገር ውስጥ በማሰራጨት ወቅት ድጎማን ያደርጋል::ይህንን ድጎማውን ብቻ እንኳን ግብርናው ላይ ቢያውል በምግብ እህል እራሳችንን ለመቻል እንንደረደር ነበር ::
ሌላው ምግብ አምርቶ ራስን መቻል የሉአላዊነት መገለጫም ነው::ቅንጦት አይደለም::አሁን እኮ ኮሮና ቫይረስ ሲመጣ ነው ማምረት ቅንጦት አለመሆኑ የታወቀው::ምክንያቱም የማያመርቱ አገራት የገቡበት አጣብቂኝ እየታየ ስለሆነ:: ራሱን የማይችል አገር እኮ ሉአላዊ ነኝ ለማለት አይደፍርም፡፡ ምርት የሚሸጡ አገሮች ባኮረፉ ቁጥር መሸማቀቅ ነው፤ እንደዚህ እንዳይሆን የግብርናው ሴክተር የኢኮኖሚው ዋልታ ከሆነ በምግብ ሰብል ራሳችንን መቻል አለብን በዚህ ቁጭት ከሰራን ደግሞ ቀላል ነው::ግን አንዱ ወደሌላ፣
ሌላው ደግሞ ወደሚፈልገው የሚጎትት ከሆነ በጣም አስቸጋሪ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ኢንስቲትዩቱ ብዙ ልምድና እውቀት ያላቸው ተመራማሪዎች እንዳሉት ይታወቃልና በተለይም ለግብርናው ሥራ ሌላ ችግር የሆኑትን ጸረ ሰብል ተባዮች ለማስወገድ የሚሰሩ ምርምሮች አሉ:: ካሉስ ውጤታማነታቸው እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ በመደበኛነት ያሉ በሽታና ተባዮችን ለመቆጣጠር መፍትሔ እንዲሁም ቴክኖሎጂ አለ፤ ሆኖም በጣም አስቸጋሪ የሚሆኑት መደበኛ ያልሆኑትና ወቅትን ጠብቀው የሚመጡ እንደ በረሃ አምበጣና ሌሎች ናቸው::ሁሌም የሌሉ ነገሮች ላይ ደግሞ ኢንቨስት ማድረግ ምናልባት ሳይመጡ ከቀሩ ኪሳራ ነው:: ግን እዚህ ላይ መጠናከር አለበት ብዬ የምለው የትንበያ አቅማችን ነው:: የትና መቼ ነው የሚፈለፈሉት::የትኛው የአየር ጸባይ ነው የሚስማማቸው:: መቼ ነው የሚበሩት ኢትዮጵያስ ለመድረስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድባቸዋል:: የሚለውን የማወቅ አቅማችንን መገንባት ያስፈልጋል። አሁን አንድ ጂኦስፓሻል ዩኒት ተቋቁሟል፤ በዚህም ዝናብን፣ የፀሐይ ሙቀትን፣ ተባይንና ነፍሳትን ያሉበትን ሁኔታ መረጃ በመሰብሰብና በማጠናቀር ትንበያን ይሰጣል:: ከዚህ በመነሳት ደግሞ ተመራማሪዎች መፍትሔውን ይፈልጋሉ ማለት ነው:: ለምሳሌ በሚቀጥለው ዓመት በልግ አይኖርም ከተባለ የክረምቱን ዝናብ ብቻ ተጠቅሞ ሊመረቱ የሚችሉ ሰብሎችን አባዝቶ ወደ አርሶ አደሩ እንዲሄዱ የማድረግ ሥራም ይሰራል፤ መገንባትም ያለብን ይህንን ሥራ ነው፡፡
በሌላ በኩል ለዚህ ሥራ የሚጠቅሙ አውሮፕላኖች በማዘጋጀት አንድ አካባቢ ላይ ጸረ ተባይ በሽታ ተቀሰቀሰ ሲባል ያለምንም ቢሮክራሲ አስነስቶ ሄዶ መድኃኒት ረጭቶ መመለስ መቻልም ያስፈልጋል:: ሌሎች አገሮች ላይም የሚደረገው ባለሀብቶች አውሮፕላን ይገዛሉ፤ ለአርሶ አደሩ ያከራያሉ:: ለምሳሌ አረምን ለማጥፋት አውሮፕላን ይጠቀማሉ ግን ደግሞ አርሶ አደሩ ላገኘው አገልግሎት ተገቢው ክፍያ ይፈጽማል፤ እንግዲህ እኛም ወደዚያ ነው መሄድ ያለብን ::
አዲስ ዘመን ፦ በዚህ ልክ ሥራዎች ሊሰሩ የሚችሉ አቅም ያላቸው ባለሀብቶች እኮ አሉ ግን ዘርፉን ላለመቀላቀላቸው ምክንያቱ ምንድን ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ አብዛኛው ሰው ነጋዴ ነው፤ ሆቴል ይገነባና ወይ ሱቅ ሰርቶ ማከራየት ያንን መሰብሰብ ነው የሚፈልገው፤ በአንጻሩ ደግሞ በዚህ ዘርፍ ላይ አንድ ሁለት ባለሀብቶች ተሰማርተው ቢታይ ሁሉም ይሄዳሉ፤ ዘንድሮ እኮ ስንዴን ሰርተን ስላሳየን ወደ ሥራው ለመግባት የመጣው ማመልከቻ በጣም ብዙ ነው::በመሆኑም ልክ እንደ ስንዴው ሁሉ አንድ ሁለት ሞዴሎችን ማየት ያስፈልጋል::ስለዚህ ግንዛቤ ፈጠራው ላይ ሞዴሎችን በማዘጋጀት ላይ መስራት በጣም ወሳኝ ነው::
አዲስ ዘመን፦ ኢንስቲትዩቱ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዱ ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ አሁን እያደረግን ያለነው ኢንስቲትዩቱን ወደኮርፖሬሽን ማሳደግ ነው::ይህንንም ለማድረግ የመጀመሪያ ዙር ሥራዎች በሙከራ ደረጃ ተሰርቷል::ኢንስቲትዩቱ የተደራጀ የምርምር ተቋም ነው ግን ምርምር ብቻ ተሰርቶ ውጤት ከሌለውና አርብቶና አርሶ አደሩን ካልቀየረ የሚሰራው ሥራ የላብራቶሪ ሥራ ይሆናልና ይህ እንዳይሆን በምርምር ሥራ የሚባዛውንና የማስተዋወቅ ሥራውን ማመጣጠን ያስፈልጋል::አሁን ላይ 1ሺ 300 ዝርያ አለን ብሎ ተኩራርቶ መቀመጥ ያለፈበት ነገር ነው::በመሆኑም አትራፊ እንዲሆንና ሥራውም ለተጠቃሚው እንዲደርስ የሚያስችል አደረጃጀት መስራት ደግሞ የግድ በመሆኑ እሱን እየሰራን ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ ረጅም ጊዜ የሚፈጁብንን የምርምር ሥራዎች በአጭር ጊዜ ሰርቶ ለማጠናቀቅ በዘመናዊ መንገድ እንዲታቀፉ አድርገናል::ኢንስቲትዩቱን በጀት የሚመድብለት መንግሥት ቢሆንም አሁን ላይ ግን ራሱን በከፊል እንዲችል በማለት በራስ ገቢ የማመንጨት ሥራም ለመስራት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው፤ ምናልባት የረጅም ጊዜ እቅድ ልንለው እንችላለን::
የሰው ኃይል አቅማችንን የመገንባትና ሌሎች ለምሳሌ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገነቡትንም አቅም መጠቀም ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን::
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
እፀገነት አክሊሉ