የአጋፋሪ እንዳሻው ወግ፤
ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር አንድ አይረሴ ገፀ ባህርይ አበርክቶልን አልፏል – አጋፋሪ እንዳሻውን:: የደራሲው ወዳጆች በአንቱታ የሚያስታውሷቸውና ታሪካቸውን ደጋግመው የሚያነቡላቸው እኒህ አዛውንት ገፀ ባህርይ የደራሲ ስብሐትን ያህል ይታወቃሉ ቢባል ከኩሸት የሚቆጠር አይሆኑም::ይህ ጸሐፊም የቅርብ ዘመድ ያህል የሚወዳቸውን እኒህን ገፀ ባህርይ መነሻ በማድረግ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በውጭ አገር ይታተም በነበረ አንድ የኢትዮጵያውያን ጋዜጣ ላይ “የአጋፋሪ እንዳሻው ሀገር” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ አስነብቦ ነበር፡፡
እኒህን ተወዳጅ ገፀ ባህርይ ደራሲ በዓሉ ግርማ ሳይቀር ስማቸውንና ግብራቸውን ተውሶ “ደራሲው” በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ቤተሰብ አድርጓቸዋል:: አጋፋሪ እንዳሻው የደራሲ ስብሐት የምናብ ፍጡር ብቻ ሳይሆኑ በአንባቢያን ዘንድም እንደ ሐውልት ተቀርፀው የቀሩ የብዕሩ ውላጅ ጭምር ናቸው:: ለምን ሊወደዱ እንደቻሉ ጥቂት ምናባዊ ድርጊታቸውን ፈነጣጥቄ ወደ ገሃዱ የዕለት ተዕለት የኑሯችን ትዝብት ብዕሬን አቀናለሁ።
አጋፋሪ እንዳሻው “ሞትን አጥብቀው የሚሸሹ” የሕይወት ወዳጅ ናቸው:: እንኳን የሞተ አስከሬን ካለበት ቀዬና መርዶ ከተሰማበት ቤት ድርሽ ሊሉ ቀርቶ ጉንፋንና ሣል፣ ማስነጠስና ራስ ምታት ታሟል የሚባል ሰው በሰፈር ውስጥ መኖሩ ከታወቀ ስንቅ ያስከተለችውን በቅሏቸውን መጭ እያሉ ከአካባቢው ፈጥነው ይሰወራሉ:: ዝርዝር ታሪካቸውን ሳይሆን ምጥን ትረካውን ከደራሲ ስብሐት “አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት” መጽሐፍ ውስጥ እንደሚከተለው ቆንጥሮ ማስነበቡ ይበልጥ ገላጭ ሊሆን ይችላል፡፡
“አጋፋሪ እንዳሻው የትም ቢሄዱ የሳምንት ስንቅ ተጭኖ የሚከተላቸው በቅሎ ነበራቸው:: ከአደባባይ፣ ከችሎት፣ ከቤተ ክርስቲያን ወይም ከጉዞ ሲመለሱ፤ ገና ከበቅሎ ሳይወርዱ አሽከሮቻቸውን “ሠፈር ደህና ነው?” ይሏቸዋል::“ደህና፣ ሁሉም ደህና?” ይላሉ ለማረጋገጥ:: “ደህና ነበር ብቻ የወይዘሮ ደብሪቱ ልጅ ራሴን አመመኝ ብላ ተኝታለች፡፡” “በሉ ደህና ቆዩኝ” ይሉና ውልቅ – አጋፋሪ እንዳሻው:: ወንድማቸው ግራዝማች አየለ ቤት ይሄዱና፣ አሁንም ከበቅሏቸው ሳይወርዱ፣ አሽከሮቹን “ሠፈር ደህና ነው?” ይሏቸዋል::“ደህና” “በሠፈሩ የሞተ ሰው የለም?”፣ “ኧረ የለም”፣ “የታመመ የለም?”፣ “ኧረ የለም”፣ “መርዶ የሰማም የለም?”፣ “ብቻ የልጅ ኃይሉ እህት ድሮ የፈቷቸው ባላቸው ሞተዋል ተብሎ ለቅሶ ተቀምጠዋል፡፡” “በሉ ደህና ሁኑ” ይሉና መንገዳቸውን ይቀጥላሉ:: እንዲህ እንዲህ እያሉ አጋፋሪ እንዳሻው ሞትን ሲሸሹ፣ ስድሳ ስድስት ዓመት ሞላቸው።”
ለሞት እጄን አልሰጥም እያሉ በሽሽት ዕድሜያቸውን የገፉት አዛውንት ገፀ ባህርይ ለምን ሞትን እየፈሩ ሕይወትን የሙጥኝ እንዳሉ የሚከራከሩት እንዲህ በማለት ነው:: “ሕይወት ሲኖሩት ይጥማል፣ ማር ማር ይላል፣ ሽቶ ሽቶ ይላል፣ ሙቀት ሙቀት ይላል፣ ኑሮ ኑሮ ይላል:: በሕይወት ለመቆየት ያለኝን ሁሉ እከፍላለሁ:: እሚቀበለኝ ባገኝ የሌለኝንም እከፍላለሁ፡፡”
አጋፋሪ እንዳሻው በማስነጠስ ውስጥ የሞት መልአክ እየታያቸው፣ በጉንፋን ውስጥ ጣዕረ ሞት እየታወሳቸው፣ የጎረቤትና የወዳጅ መርዶ ሲሰሙ ሳጥናኤል እያስበረገጋቸው ከሕይወት ላለመፋታት እንደፈሩ ዕድሜያቸውን በሽሽት፣ ዘመናቸውን በብልሃት ማሳለፋቸውን የደራሲ ስብሐት የድርሰት ሥራ በውብ
ቋንቋና በአይረሴ የታሪክ ጥልፍልፍ ትረካ በአዕምሯችን ውስጥ ስሎልናል:: ታሪካቸው ከተጻፈ የአንድ ጎልማሳ ሰውን ዕድሜ ያህል ያስቆጠረ ቢሆንም ዛሬም ድረስ እንደ መልካም የወይን ጠጅ ብዙዎቹ እየተጎነጩ ያደንቁታል:: ደራሲው ስብሐት በአፀደ ሥጋ ከተለየንም ዓመታት ተቆጥረዋል:: ገፀ ባህርይው አጋፋሪ እንዳሻው ግን ለሞት አልረታም በማለት ዛሬም ድረስ በአዕምሯችን ውስጥ ግዘፍ ነስተው ህያው እንደሆኑ ከደራሲው በበለጠ ቤተኛ ሆነው ቀጥለዋል:: ከአንባቢያን ጋር እንዳላቸው ቁርኝት ለሁልግዜም የሚሞቱ አይመስለኝም፡፡
የዘመናችን የአጋፋሪ እንዳሻው መንፈስ፤
ዓለማችን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ አቅሏን ስታ ከወፈፈች ሰንብታለች:: ሕዝቦቿም በዚህ ክፉ የዘመናችን ደዌ እስትንፋሳቸው እንዳይነጠቅ በእጅጉ እየተጠነቀቁ ሰቀቀን በሞላበት ኑሮ ቀናቸውን እየገፉ ነው:: ተመራማሪዎች “ለመፍትሔ ሥራዩ” በትጋት እየደከሙ እንዳሉ እየሰማንም፣ እያስተዋልንም ነው:: “መፍትሔውን አግኝቻለሁ” ብሎ የሕክምናው ሳይንስ የምሥራቹን ከማብሰሩ አስቀድሞ ግን ቁጥራቸው ወደ ስድስት ሚሊዮን ሊቃረብ ጥቂት የቀረው የዓለም ዜጎች እስካሁን በደዌው ተለክፈው ለሆስፒታል ተዳርገዋል:: በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የሕዝበ አዳም ዝርያዎችም በዘርና በቀለም፣ በሃይማኖት በቋንቋ ልዩነት ሳይኖር እስትንፋሳቸው ተነጥቆ ለእንባና ለልብ ስብራት ዳርገውናል:: በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዕድለኞችም በፈጣሪ እርዳታና ቀን ከሌት በሚንከባከቧቸው የጤና ባለሙያዎች ያላሰለሰ ትጋት ከወረርሽኙ አገግመው ለወራት የተገላበጡበትን አልጋቸውን አንጥፈው በመነሳት ለቤታቸው በቅተዋል::
በደዌው ተጠቅተው ዛሬም ድረስ አልጋ ላይ ለዋሉ ምህረትን፣ ሥጋቸው አንቀላፍቶ ለተሰናበቱን ሰማያዊ እረፍትን፣ አገግመው ሕይወት ለተቀጠለላቸው ልባዊ ዕልልታችንን እንገልፃለን:: የቫይረሱ የገዳይነት መውጊያ በቅርቡ ተሰባብሮ በሽታው ራሱ በአዳዲስ የሕክምና መፈወሻ ግኝቶች ተዝለፍልፎ በታሪክ አልጋ ላይ በነበር እንደሚወድቅ ተስፋችን ጽኑ ነው:: አሜን ያድርግልን!
አገሬና ወረርሸኙ፤
የትልቋ ዓለማችን ንዑስ ክፋይ የሆነችው አገሬና ከምድራችን ሕዝቦች መካከል መቶ አሥር ሚሊዮን ቁጥር የሚጋራው ሕዝባችንም በዚህ ክፉ ወረርሽኝ መጠቃቱ አልቀረም:: ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር (ምንም አንኳ ንጽጽሩ ተገቢ ባይሆንም) እስካሁን የጥቂት ወገኖቻችን ሕይወት በወረርሽኙ መነጠቁ እውነት ነው:: በመቶዎች የሚቆጠሩም ለሕክምና ክትትል በአልጋ ላይ መዋላቸው ይታወቃል::ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩም “በሽልም ወጥተው” ለቤታቸው በቅተዋል:: አፍቅሮተ ወገን የታየበትን የሙያ ሥነ ምግባር በማክበር በደማቅ ብዕር አኩሪ ታሪክ እያጻፉ ላሉ የሕክምና ባለሙያዎቻችንና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች ክብርና ሞገስ ይሁንላቸው:: ወረርሽኙን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ቀን ከሌት እየተጉ ላሉት የሀገሬ ከፍተኛ ሹማምንትና በየተዋዕረዱ ለሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችም ምስጋናችንና አክብሮታችን ይድረሳቸው፡፡
እርግጥ ነው ወረርሽኙ ብዙዎቻችንን ከቤት ኮርኩዶ አውሎናል:: የዕለት እንጀራቸው ፋታ የማይሰጣቸውና የሥራ ጠባያቸው ተሰብስበው ከቤት እንዳይውሉ የሚያስገድዳቸው ዜጎችም ጎዳናውን፣ አደባባዩን፣ የሥራ አካባቢዎችንና ገበያዎችን ዛሬም እንዳጨናነቁ ነው:: የዕለት ጉሮሮ በዕለት ዳቦ ገርገብ ካላለ፣ የመንግሥት ሥራና የግዴታ ተግባራት ውሎዎች በአግባቡ ካልተከወኑ በስተቀር ዞሮ ዞሮ የችግሩ ሰንሰለት ስለሚራዘም ኑሯችንን አወሳስቦ የከፋ ጉስቁልና ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በርካታ ዜጎቻችን በዳተኝነትና በቸልተኝነት የበሽታውን አደገኛነት የተረዱ እስከ ማይመስል ድረስ “ኬሬዳሽ” በማለት በአጓጉል ተግባ ራትና በግዴለሽነት ንቀታቸውን ሲገልፁ እየታዘብን ነው:: ኧረ ጎበዝ ይሄ ጉዳይ ደግም አይደል! የጤና ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች የሚሠጡትን ትእዛዞችና ምክሮች እየጣስን አንገትን በማደንደን እምቢታን መግለጽ ዞሮ ዞሮ ችግሩ ከራስ አልፎ በሌሎች ላይ መፍረድ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ብዙ መመራመር ሳያስፈልግ ሕፃናት ልጆቻችንን እየመከርን እንዳሳደግናቸው ሁሉ እኛስ ራሳችን “ከሕፃናት ምክሮች” የማይተናነሱና የማይተልቁ እጅግ ቀላል የሆኑ ምክሮችን ተግባራዊ ብናደርግ ምን እንጎዳለን:: አታድርጉ የተባልነውን ላለማድረግ፣ አድርጉ
የተባለውን ለመፈፀም ለምን እንቢታ ይተናነቀናል:: ምሳሌ፡- የእጅን ንጽህና የመጠበቅ አስፈላጊነት፣ የተወሰነውን ርቀት ጠብቆ ግንኙነት ማድረግና ተግባርን መፈፀም፣ ሳልና ማስነጠስ ካለበት ሰው መጠንቀቅና ራስን የመጠበቅ ምክሮች ክፋታቸው ምኑ ላይ ነው:: አልገባንም እንጂ ሕፃናት ልጆቻችንን በምክርም ሆነ በቁንጥጫ እየገሰጽናቸው ያሳደግናቸውን መሰል ትዕዛዛት ዛሬ እኛ እንድናከብራቸው ስንጠየቅ ለምን በቸልታ ደንድነን ጉዳት ላይ እንወድቃለን? አዕምሮ ያለው ሰው አጥብቆ ሊያስብ የሚገባው “ይዋጣልን!” እያለ በንዝህላልነት ከበሽታው ጋር ግብግብ መፍጠር ሳይሆን እንደ አጋፋሪ እንዳሻው ሞትን መሸሽ ነው፡፡
“እንሽሽ” ማለት ግን በሞት ፍርሃት ሥር ወድቀን ምርኮኛ በመሆን እየበረገግን እንኑር ማለት አይደለም:: ኮቪድ 19 በቅርብ ወራት ተሸንፎ እጅ መስጠቱ አይቀሬ ነው:: የሞት ግልቢያውም ተገትቶ ልጓሙ በቁጥጥር ሥር መውደቁ እንደማይቀር ይታመናል:: የምሥራቹ ዜና ተረጋግጦ በሆታ እስክንዘምር ድረስ ግን በቸልተኝነት “ግባ በለው!” ይሉት ዓይነት ከሞት ጋር የሚደረግ ፍልሚያና ድሪያ ጅልነት እንጂ እንደ ጀብድ ሊቆጠር አይገባውም፡፡
ብዙ ሰዎች የወረርሽኙን ዓለም አቀፍ ስፋት፣ የሀገራችንን የአኗኗር ዘይቤ ጉስቁልናና ማኅበራዊ ቁርኝት እያነፃፀሩ ተስፋቸውን ሲጥሉ ይስተዋላል:: አንዳንዶችም በአስበርጋጊ ዜናዎች እምነታቸው ላሽቆ በቁዘማ ላይ እንዳሉ ይታወቃል:: ተገቢ አይደለም:: ኮቪድ በቁጥጥር ሥር ውሎ “ጉሮ ወሸባዬ” እያልን ደስታችንን የምንገልጽበት ቀን ሩቅ ባይሆንም እስከዚያው ድረስ ግን የሚያዋጣው የአጋፋሪ እንዳሻውን የሞት ሽሽት ዘዴ መተግበሩ ነው:: ደግመን ደጋግመን ልናጤነው የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ “በሞት ፍርሃት ሥር ወድቀን” እጅ እንስጥ ማለት እንዳይደለ አጥብቀን ልናስብ ይገባል:: ሞት ራሱ ሞቶ በቅርብ ቀን ለቀብር መውጣታችን እውነት መሆኑን ካመንን እስከዚያው ድረስ ራስን በመጠበቅና በመረጋጋት መኖሩ ብልህነት ነው፡፡
የምንግዜም ተጠቃሽ የጥበብ አምዳችን ደራሲ ጸጋዬ ገብረመድኅን “እሳት ወይ አበባ” በሚለው የግጥሞች ስብስብ መጽሐፉ ውስጥ “የት አባቱ! ሞትም ይሙት!” የሚል ርዕስ የሰጠው የጀግናን ቀረርቶ የሚያስታውስ አንድ ግጥም አለው::ይህ ግጥም ተራ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም:: ለብዙ ማኅበራዊና የግል ጉዳዮቻችን ወኔ ለመሰነቅ ትልቅ አቅም የሚሰጥ መልዕክት የታመቀበት ጭምር ነው:: ጥቂት ማሳያ ስንኞችን ልጥቀስ፡፡
“እባካችሁ ዘመዶቼ፣ ለሞት የልብ ልብ አትስጡት፣
ናቁት አጥላሉት አውግዙት፣
በሙሾ ግነን አትበሉት፤
በሞታችን አታስደስቱት፡፡
ማሳለፊያ መግቢያ ሲያጣ፣ ፍርሃት መግቢያው ሲራቆት፣
መቃረቢያ ፍንጭ ሲያጣ፣ በዕልልታ ሲወገር ብሶት፣
ብቻ ነው ሞት ራሱ እሚሞት፡፡
ግጥሙ የሚያስታውሰን ሞትን ራሱን ገለን እንድንፎክር እንጂ የሃሳብ በቅሏችንን ጭነን መጭ እያልን በፍርሃት እንድንጋልብ አይደለም:: ሞትን ራሱን ለመግደል መፋለሚያው ጠብመንጃችን በእጃችን ነው – በባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር መተግበር ብቻ:: በፍርሃት እየባነንን ተስፋችንን ከማሰልሰልና ከመጉዳት መጠበቅ ሌላው መፍትሔ ነው::የሚያንፁ መረጃዎችን ካልሆነ በስተቀር ክፉ ዜናዎችን ለመስማት ማነፍነፍም ከበሽታው የከፋ በሽታ ነው:: ራሳችን ለመኖር የምን ጓጓውን ያህል ሌሎችም እንዲኖሩ መፍቀድን የሕይወት መርህ ማድረግ በምድርም በሰማይም ያስመሰግናል፡፡
ከአጋፋሪ እንዳሻው አባባል አንድ ዘለላ ተውሼ ልሰናበት፤ “በሕይወት ለመቆየት ያለኝን ሁሉ እከፍላለሁ:: እሚቀበለኝ ባገኝ የሌለኝንም እከፍላለሁ።” ይሄው ነው:: እንዲህ ስናደርግ በመደማመጥ፣ የባለሙያዎችን ምክር በመስማትና በመከባበር ሞት ራሱ ይሸነፋል:: በግልጽ አናሟርትበት ካልንም ኮቪድ 19 ራሱ ከርሰ መቃብር ወርዶ “በጃሎ መገን” ቀረርቶ የመሸኘቱ ቀን ቅርብ ነው:: ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)