እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም የምኖርበት ባሻ ወልዴ ኮንዶሚኒየም የኮሚቴ አባላት አንዱ ስልክ ደወለልኝ፤ አነሳሁት:: ከፓስተር የጤና ባለሙያዎች ድንገተኛ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ መምጣቸውን ነገረኝና መገኘት እችል እንደሆን ጠየቀኝ:: ፍቃደኝነቴን ገልጬ ተገኘሁ:: ሌሎች ነዋሪዎችም እንዲሁ ያለምንም ችግር ሲመረመሩ ለማየት በቃኹ::
እዚያው እያለሁ ቀትር ላይ የሰማሁት ዜና እጅግ አስደንጋጭ ሆኖብኝ ነበር:: በዕለቱ 88 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የተረዳሁት ለምርመራ እንደተሰለፍኩኝ ነበር:: ከምንም በላይ ደግሞ ከዚህ ቁጥር ውስጥ 73 ያህል ገደማ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ፣ አብዛኛዎቹ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ካላቸው ሰዎች ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች መሆናቸው በድንጋጤ የልብ ምቴን እንደጨመረው መሸሸግ አይቻለኝም::
አዎ! ተደጋግሞ እንደሚነገረው ተዘናግተናል:: በዚህም ምክንያት የጤና ባለሙያዎች የጥንቃቄና የደህንነት መልዕክቶችን በሚገባ መተግበር ተስኖናል:: አንዳንድ ፖለቲከኞች እና የማህበራዊ ሚዲያ ተዋንያን ነገሩን ከፖለቲካ አጀንዳ ጋር በማጣፋት ለማሳየት ብዙ ርቀት መሄዳቸው በራሱ የኅብረተሰቡን የመዘናጋት ደረጃ ወደሽቅብ አጉነውታል:: ጥቂት የማይባሉ የሸገር ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሌለ ያህል በመቁጠር በሕግ የተከለከሉ አድራጎቶችን ወደመከወን ተሸጋግረዋል:: በአጭሩ በራሳችን የጤና ጥቅም ላይ አምጸናል:: እናም አሁን ወደማይቀረው ውሸባ (Lock down) ለመግባት የተገደድንበት ሁኔታ ከፊታችን ተደቅኗል::
በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ተጨናንቆ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው አብነት አካባቢ፣ የኮሮና ስርጭትን ለመግታት ሲባል ሙሉ በሙሉ አንድ መንደር ውሸባ (የቤት ውስጥ ኳራንታይን) እንዲገባ ተደርጎ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ ሰሞኑን መከልከሉ ተሰምቷል::
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ሰሞኑን የተናገሩት ይኸንኑ እርምጃ የሚደግፍ ነው:: እስካለፈው ቅዳሜ ዕለት ድረስ ብቻ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች 62 በመቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ነበሩ።
በተለይ በልደታ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የቫይረሱ ስርጭት ይበልጥ መስፋፋቱ ተገልጿል:: ልደታ ክፍለ ከተማ 104 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። ከአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ደግሞ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 28 ደርሷል ብለዋል:: እናም ሚኒስትሯ የቫይረሱ ስርጭት በተስፋፋባቸው ክ/ከተሞች የእንቅስቃሴ እገዳ ሊደረግ እንደሚችል በይፋ ተናግረዋል::
ተከታዩ የጣሊያን ልምድ የእኛን የዚህን ወቅት ተጨባጭ ሁኔታ ወለል አድርጎ የሚያሳይና ትምህርት ልንቀስምበት የሚገባ በመሆኑ ልጠቅሰው ወደድኩኝ::
የጣሊያን ልምድ እንደ አንድ አብነት
አንድ ጣሊያናዊ አገሩ ያለፈችበትን የኮሮና ቫይረስ ስድስት ደረጃዎች (Stages) እንደሚከተለው አስቀምጦታል::
የመጀመሪያ ደረጃ – ኮሮና ቫይረስ ምን እንደሆነ ሁሉም ይረዳል:: የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በሀገራችሁ ሪፖርት መደረግ ይጀምራል:: አብዛኛው ሕዝብ ከባድ ጉንፋን ነው ምንም የሚያሰጋኝ የለም የሚል ምላሽ ይሰጣል:: «ዕድሜዬ ከ75 በላይ አይደለም:: ስለዚህ ምንም የሚያሰጋኝ የለም» የሚሉ ድምፆች በብዛት ይሰማሉ:: በሽታው እኔን አያጠቃኝም፤ ለምን ሰዎች እንደሚያካብዱት አይገባኝም፤ ፖኒክ (Panic) እየፈጠሩ ነው፤ እንዲሁም የአፍ መሸፈኛና ሶፍት መጠቀም እንደ ማካበድ ይታያሉ:: ምንም የተለየ ነገር አልተፈጠረም፤ ዝም ብለን በለመድነው የኑሮ አኗኗር ዓይነት እንቀጥል ዓይነት ጩኸቶች በብዛት ይሰማሉ።
ሁለተኛ ደረጃ – የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ ይመጣል:: የመጀመሪያውን ተጠቂ ያገኙበትን አካባቢ «ቀይ ዞን» ብለው የተወሰኑ ቦታዎችን ለብቻ
የመለየትና የማግለል (Quarantined) ሥራ ይሰራል:: አሁንም መንግሥታት ምንም የሚያሰጋና የሚያስደነግጥ ነገር እንደሌለ ይናገራሉ:: (ይህም በጣሊያን እ.አ.አ. የካቲት 22/2020 የሆነው ማለት ነው)። የተወሰኑ ሰዎች መሞት ይጀምራሉ:: ነገር ግን አብዛኛው ሕዝብ ሚዲያዎችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተመልካችን ለመሳብ የሚፈጥሩት ፍርሃት (Panic) እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ዜጎች የተለመደ ሥራቸውን ይቀጥላሉ … ሥራ አይቆምም:: የሰዎች የእርስ-በእርስ ግንኙነታቸውን እንደቀድሞው ይቀጥላሉ:: ቫይረሱ እኔን አያጠቃም….. እና ምንም አዲስ ነገር የለም… ዓይነት ድምፆች በብዛት ይሰ ማሉ::
ሦስተኛ ደረጃ – የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ቁጥር ይጨምራል:: በአንድ ቀን የቫይረሱ ተጠቂ በእጥፍ እየጨመረ ይሄዳል:: ተጨማሪ ሞቶች ይመዘገባሉ:: ቫይረሱ የተመዘገቡባቸውን አራቱን ቦታዎች (በጣሊያን የሆነው ማለት ነው) ለብቻ በማግለል «ቀይ ዞን» ተብለው ይታወጃሉ:: በጣሊያን 25 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ቦታዎች እንዲገለሉ የተደረጉበት ወቅት ማለት ነው:: (መጋቢት 7/2020 እ.ኤ.አ. በጣሊያን የታወጀው):: በእነዚህ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲዘጉ ሲደረጉ ቡና ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶችና የሥራ ቦታዎች ግን ክፍት ሆነው ይቀጥላሉ።
75 በመቶ የሚሆነው የጣሊያን የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ክልከላ ባለመጣሉ ሌሊት ላይ ወደ 10 ሺ የሚጠጉ ሰዎች «ቀይ ዞን» ተብሎ ለብቻ ከተከለለውና ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ከተደረገው ቦታ አምልጠው ክልከላ ወዳልተጣለብት መኖሪያ ቦታቸው ይመለሳሉ (በኋላ ላይ ይህ ክስተት በጣም ወሳኝ ይሆናል):: ወደ 75 በመቶ የሚሆነው የተቀረው የጣሊያን ሕዝብ የተለመደ ሥራውን እንደቀጠለ ነው። አብዛኛው ሕዝብ በሽታው ምን ይህል ከባድ እንደሆነ እስካሁን አይገባቸውም:: መንግሥት በእያንዳንዳችሁ እንቅስቃሴ እጃችሁን ታጠቡ፣ አትጨባበጡ፣ አትውጡ፣ በጋራ መንቀሳቀስ ክልክል እንደሆነና ሌሎችንም ሕጎች በየቴሌቪዥኖቻችን በየ5 ደቂቃው ያስታውሱናል:: ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ከቁብ የሚቆጥራቸው የለም::
አራተኛ ደረጃ – የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እጅግ በጣም ይጨምራል። ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ይዘጋሉ፤ ብሔራዊ የጤና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃል:: ሆስፒታሎችና ጤና መስጫ ተቋማት በኮሮና ታማሚዎች ከአቅም በላይ ይሞላሉ:: በቂ የሕክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች እጥረት ይከሰትና ጡረተኞቹንና የመጨረሻ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲያግዙ ጥሪ ይተላለፋል። ለዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች በፈረቃ መስራት በማስቀረት የተቻላቸውን ያህል እንዲያግዙ ይደረጋል።
በዚህ ጊዜ ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መጠቃት እንዲሁም እነርሱም ለቤተሰቦቻቸው ቫይረሱን ማስተላለፍ ይጀምራሉ። ብዙ ታማሚዎችና ብዙ የጽኑ
ህሙማን ክፍል አይሲዩ (ICU) ፈላጊዎች የሚከሰትበት፤ ነገር ግን ሁሉንም ማስተናገድ የሚከብድበት ወቅት ይሆናል። በዚህ ወቅት ሁሉም ሰው ጦርነት ውስጥ ያለ እስኪመስለው ድረስ ነገሮች ይከብዱበታል::
ዶክተሮች የታማሚዎችን የመዳን ዕድል በማረጋገጥ ብቻ ሕክምና ይሰጣሉ:: ይህም ማለት በዕድሜ የገፉ፤ ስትሮክ ያለባቸውና የመሳሰሉት ሕክምና ይነፈጋሉ:: ለሁሉም የሚበቃ በቂ ግብዓት ባለመኖሩ በሽተኛን መምረጥ ግድ ይሆናል። ጣሊያን ላይ የሆነው ይኸው ነው። የቫይረሱን ተጠቂዎች ሆስፒታሎች ማስተናገድ ባለመቻላቸው ሰዎች እዚህም እዚያም ይሞታሉ። አንዱ ዶክተር ወዳጄ ዓይኑ እያየ ሦስት የቫይረሱ ተጠቂዎች በአንድ ቀን ሲሞቱበት ይህን ክስትት “Devastated” በማለት ነበር የገለፀው።
የቫይረሱ ተጠቂዎች ሲሞቱ ኦክስጅን ከማቅረብ ውጪ ምንም ማድረግ ያልቻሉት ነርሶች እንባቸውን መቆጣጠር እስኪከብዳቸው ድረስ በኀዘን ይዋጣሉ። የሕክምና ባለሙያዎች በትክክል እንክብካቤ ባለማድረጋቸው የወዳጄ ዘመድ ትናንት ሞተብኝ ዓይነት ድምፆች ጎልተው ይሰማሉ። እዚህም እዚያም ማጉረምረምና ሥርዓቱ ፈርሷል (The system is collapsed) ዓይነት ጩኸቶች በሰፊው ይሰማሉ። በሁሉም የዜና አውታሮች የኮሮና ቫይረስ ችግር በኢኮኖሚ ላይ ያለው ተፅዕኖ (The impact of Coronavirus on the economy) ዓይነት ዜናዎች በሰፊው ይሰማሉ።
አምስተኛ ደረጃ – “ቀይ ዞን” ተብሎ ከተከለለው 25 በመቶ ከሚሆነው ከጣሊያን ክፍል ወደ ተቀረው 75 በመቶ ወደሚሆነው ጣሊያን የገቡትን 10 ሺ ሰዎች ታስታውሳላችሁ? መላው የሀገሪቱ ቦታዎች ከማንም ጋር እንዳይገኙ (Quarantined) ይደረጋሉ (መጋቢት 9/2020 በጣሊያን የታወጀው ማለት ነው)። የዚህ ለይቶ ማቆያውም ዋና ዓላማ የቫይረሱን መተላለፍ መቀነስ እንደሆነ የሚመለከታቸው አካላት ይናገራሉ። ሰዎች ወደ ሥራ መሄድ፤ ሱፐርማርኬቶች እና ፋርማሲዎች ላይ መገበያየት እንዲሁም የተወሰኑ ቢዝነሶች ክፍት እንዲሆኑ ይታወጃል። ይህ ካልሆነ ኢኮኖሚው እንደሚጎዳ ባለሥልጣናት ይናገራሉ። በዚህ ወቅት አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ያልቻለ ሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም። በዚህ ወቅት ከፍተኛ ፍራቻ ይፈጠራል:: አብዛኛው ሰው በአፍና በእጅ መሸፈኛ ሲንቀሳቀስ ነገር ግን አሁንም ራሳቸውን በበሽታው የማይጠቁ አድርገው የሚቆጥሩ (The invincible) ሰዎች ያለመሸፈኛ እንዲሁም በቡድን ሆነው ወደ ምግብ ቤቶችና ምሽት ቤቶች ይንቀሳቀሳሉ።
ስድስተኛ ደረጃ – ከአምስተኛ ደረጃ ከሁለት ቀን በኋላ ሁሉም የሥራ ቦታዎች በሚባል መልኩ እንዲዘጉ ትዕዛዝ ይተላለፋል:: ከሱፐርማርኬትና ከፋርማሲዎች በስተቀር ሁሉም አገልግሎት እንዳይሰጡ ይደረጋል:: ወደ ሱፐርማርኬትና ፋርማሲዎች ለመንቀሳቀስም የፍቃድ ወረቀት ማሳየት የግድ ይሆናል:: ይህም ሰርተፍኬት በመንግሥት የሚሰጥ ይፋዊ ወረቀት ሲሆን በውስጡም ስማችሁን፤ ከየት እንደመጣችሁ፤ ወዴት እንደምትሄዱና ለምን ዓላማ እንደሆነ የሚዘረዝር ሰርተፍኬት ነው:: ይህንን ለማረጋገጥም በየቦታው ኬላዎች ይቋቋማሉ::
ያለበቂ ምክንያት ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ወይንም ቫይረሱ እንዳለብዎት እያወቁ ከተንቀሳቀሱ ደግሞ ሆን ብሎ ሰውን በመግደል በሚለው ሕግ ጠንካራ ቅጣት ይጣልብዎታል። (ዘ-ሐበሻ)
እንደማጠቃለያ – ምን ይደረግ?
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ከጊዜ ወደጊዜ ወጥነት ባለው መልኩ እየተሻሻለ ኮሮና ቫይረስን እንዳይስፋፋ የራሱን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ሰሞኑን ለሚዲያ አካላት ተናግረዋል። አያይዘውም «በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየታየ በመሆኑና የውጭ አገር የጉዞ ታሪክና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ የሌላቸው ዜጎች ቫይረሱ እየተገኘባቸው መሆኑ የተሰጠውን ትኩረት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ነው ካሉ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያወጣቸውን ዝርዝር ደንቦች በትክክል እንዲተገበሩ በጥብቅ መከታተል ያስፈልጋል።…. ለተጠያቂነት በሚያመች መልኩ አዋጁን ማየት እንዳለብን ተመልክተናል» ብለዋል።
አዎ!.. ጠበቅ ያለ፣ ቆንጣጭ ሕግ አስፈላጊነት አሁን ግልጽ እየሆነ መጥቷል:: ይህ ሁኔታ በእኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገራትም በትኩረት እየተሰራበት የሚገኝ ነው:: ለአብነት ያህል በአፍሪካ ደረጃ ቀደምት ተጠቂ ከሆኑት አገሮች አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ናት::
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከጁን 1/2020 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ወደ ኮሮና ቫይረስ ማንቂያ ደረጃ ሦስት እንደሚገባ ሰሞኑን አርድተዋል:: ፕሬዚዳንት ራማፎሳ አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ በመጠቃታቸው ምክንያት የተለየ አያያዝ ይኖራቸዋል ብለዋል።
አዎ! ወደአገራችን ኢትዮጵያ መለስ ስንል የመጀመሪያው ችግር አስቸኳይ አዋጁ ድንጋጌዎችን ሙሉ በሙሉ መተግበር አለመቻል ነው:: ለአብነት ያህል አዋጁ ለሃይማኖታዊ ወይም ማህበራዊ ዓላማ፣ ለመንግሥታዊ ወይም ፖለቲካዊ ሥራ ወይም ሌላ መሰል አላማ አምልኮ በሚደረግባቸው ቦታዎች፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በማናቸውም የመሰብሰቢያ አዳራሾችና በማናቸውም ቦታ አራትና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ ላይ መገኘት የተከለከለ ስለመሆኑ ደንግጓል:: ይህ ድንጋጌ የቱን ያህል ተግባራዊ ስለመሆኑ ማወቅ የሚፈልግ ሁሉ ከተማዋን ዘወርወር ብሎ መቃኘት ብቻ መልስ ያስገኝለታል::
ከቤቱም ሳይርቅ የየዕለቱን የመገናኛ ብዙኃን ወሬዎች ሲመለከት በሚያየው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ብቻ ተጨባጭ ሁኔታውን መገምገም ይችላል:: ሰሞኑን ሁለት የሃይማኖት መሪዎች የኢድ በዓልን አስመልክቶ በቀረቡበት የኢቢኤስ የቴሌቪዥን የበዓል ፕሮግራም ላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ በመካከላቸው በግምት አንድ ሜትር ባልሞላ ርቀት ልዩነት ተቀምጠው መመልከቴ ለዚህ አባባሌ አስረጂ ነው::
ተጨማሪ አብነት እንይ?!.. በጭፈራ ቤቶችና በመጠጥ ቤቶች ማናቸውንም የመጠጥና መዝናኛ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ስለመሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል:: በተጨማሪም በማናቸውም ቦታ የሺሻ ማስጨስና ጫት ማስቃም አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው:: እነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግን በእርግጥ ተግብረውታል ወይ? ተጠቃሚውም ክልከላውን አክብሯል ወይ የሚለውን ለመታዘብ የፈለገ ዓይኑን ከፈት አድርጎ አካባቢውን መቃኘት ብቻውን እውነታውን ለመረዳት ያስችለዋል:: በአጭሩ አዋጁ አለመተግበሩ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ አገልግሎት ሰጪዎች እንዲያውም ከወትሮው በባሰ ሁኔታ በደንበኞች የተጥለቀለቁበት ሁኔታ ማየት በእጅጉ ያስገርማል:: ሕግ አስፈጻሚው አካልም በይሉኝታ፣ አንዳንዴም በምንአገባኝ ስሜት፣ አንዳንዴም በሙስናና ብልሹ አሠራር እየተጠለፈ ሕጉን ማስከበር ሲሳነው ማየትም የየዕለቱ ትዕይንት ሆኗል::
እናም የሚመለከታቸው አካላት በቅድሚያ የአዋጁን አፈጻጸም ጥንካሬና ድክመት ይፈትሹ፣ ቀጥሎም ተጨማሪ አስገዳጅ ሁኔታዎች አስፈላጊነት ማየትን በሕጉ ለማካተት ይስሩ:: በእኔ እምነት በየዕለቱ የሚደረገውን ምርመራ ከማጠናከር ጎን ለጎን በአዲስአበባ ብዙ ሕዝብ የሚያስተናግዱ እንደመርካቶ እና እህል በረንዳ… ያሉ የገበያ ቦታዎች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ቡና ቤቶች… ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አገልግሎት እንዲያቆሙ ቢደረጉ ኮቪድ 19 በመታገል ሒደት አዎንታዊ ሚና ሊኖራቸው ይችላል ብዬ አስባለሁ:: በተጨማሪም የሰዎች ዝውውር በተጨናነቀ ሁኔታ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ለአብነት ያህል ሳሪስ፣ አዲሱ ሰፈር፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ኮልፌ አጠና ተራ እና የመሳሰሉ አካባቢዎች (መንገዶችን) ለእግረኞች ዝግ የማድረግ ጉዳይ ሊጤን ይገባል:: እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አጠቃቀም ወጥ መመሪያ በማውጣት ሰዎች በየትኛውም ቦታ መጠቀም እንደሚገደዱ፣ በየትኛው ቦታ እንደማይገደዱ ግልጽ ማድረግ ተገቢ ይሆናል:: የአዋጁ ግልጽነት የጸጥታ አካላት ያገኙትን ሰው ሁሉ ለእስር ከማጋዝ እና ከማንገላታት ያቅባቸዋል::
በመንግሥት በኩል የአዋጁን አፈጻጸም በቅርበት ሊከታተሉ የሚገባቸው የጸጥታ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የመደገፍና የመከታተል እንዲሁም በአሠራር ሒደት በማወቅም ባለማወቅም የሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ ጥብቅ ክትትል የማድረግ ሥራዎች በስፋት ማከናወን ይገባዋል:: መንግሥት ከምንም በላይ እነዚህን ከባድ ውሳኔዎች ሲያስፈጽም በቀጥታና በተዘዋዋሪ በኢኮኖሚ የሚጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በምን መልኩ መደገፍ እንደሚችል በጥናት በመመለስ ወደትግበራ መግባት ይጠበቅበታል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2012
ፍሬው አበበ