ስለሳይክል ሲነሳ አብዛኛው ሰው ወደ ልጅነት ትውስታው ይመልሰዋል። በልጅነት ሰፈር በሚገኝ ሜዳ ወይም የአስፓልት መንገድ ላይ ሳይክል ሳይነዳ ያላደገ የለም። በዛውም ልክ ከሳይክል የወደቀና በመኪና የተገጨም አይጠፋም…። ታድያ እነዚህ ሁሉ አሁን ድረስ እንደቀጠሉ ናቸው….ለምን ብትሉ በአዲስ አበባ የሳይክል መንገዶች ባለመኖራቸው ነው።
የአዲስ አበባ አስተዳደርም ይህን ችግር ለመፍታት አስቦ ከጀሞ እስከ ለቡ ሁለት ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሸፈነ የሳይክል መንገድ ግንባታ ማከናወኑ ይታወሳል። ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ከተማ ያፀደቀው የ10 አመት የሞተር አልባ ትራንስፖርት አካል መሆኑንም በወቅቱ በመገናኛ ብዙሀን ሲነገር ቆይቷል። መንገዱም ሳይክል ብቻ እንዲንቀሳቀስበት ምልክት የተደረገበት ሲሆን መኪና ወደ መስመሩ እንዳይገባ የፕላስቲክ መከለያ ተደርጎበታል።
…ግን የተመረጠው ቦታ ለሳይክል ምቹ ነው? ምን ያክልስ ተንቀሳቃሽ ሳይክሎች በአካባቢው ይገኛሉ? እንዲሁም በአካባቢው ያለው የትራፊክ ሁኔታስ ምን ይመስላል? የሚለው የታየ አይመስልም። በተጨማሪም የብስክሌት መንገዱ የተሰራው ከዋና መንገዱ በመቁረጥ በመሆኑ መኪናዎች ሲጓዙበትም ይስተዋላል።
በአዲስ አበባ ከተማ የመኪና መንገድ እጥረት ምን ያክል የትራፊክ መጨናነቅ እንደፈጠረ ለሁላችንም ግልፅ ነው። እነዚህ መንገዶች ላይ ደግሞ የሳይክልና
የአውቶቡስ መንገድ ተብሎ ተቆርጦ በመከለሉ መጨናነቁን ከማባባስ ውጪ ምንም ያመጣው ለውጥ የለም…። ለአብነት የአውቶቡስ መሄጃ ተብለው የተሰመሩ መንገዶችን ብናይ ፈራርሰውና ሁሉም መኪናዎች ሲንቀሳቀሱባቸው ይስተዋላል።
በቅርቡ ደግሞ የሳይክል መንገድ ተብለው የተሰመሩት መንገዶች ላይ የሚሄድባቸው ሳይክሎች አይታዩም ለማለት ያስደፍራል። ለምን ቢባል በአዲስ አበባ ከተማ ሳይክል እንደ ትራንስፖርት አማራጭ ተደርጎ የተቀመጠ ባለመሆኑና የሳይክል ተጠቃሚዎች ቁጥር አስተኛ በመሆኑ ነው። በክልል ከተሞች ማለትም በባህርዳር፣ በሀዋሳ እና በመቀሌ ከተሞች ቀደም ብሎ የሳይክል እንቅስቃሴ ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት ግን ከመኪና መብዛት ጋር ተያይዞ በሞተር ሳይክል ተተክተዋል ማለት ይቻላል…።
በሌላ በኩልም በአዲስ አበባ ከተማ ሳይክል ለመንዳት የሚያስችል ሁኔታ ጠባብ በመሆኑ ህብረተሰቡ በብዛት ለመጠቀም አይደፍርም…። ያው እንጦጦ ፓርክ ሲመረቅ ህብረተሰቡ ሃሳቡን ካለወጠ በቀር…። ወላጆችም ለልጆቻቸው ሳይክል ቢገዙም ከግቢያቸው አለበለዚያም ከሰፈራቸው ወጥተው እንዲነዱ አይፈቅዱላቸውም። በስራም ምክንያት በሳይክል የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ቁጥር እንብዛም በመሆኑ ለሳይክል የተዘጋጀው መንገድ ለማነው? ያስብላል።
የሳይክል ስፖርትን ብንመለከት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፖርቱ የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች ግን የሚመጡት
ከክልል ከተሞች መሆኑ ሲታይ አዲስ አበባ በሳይክል በኩል ምንም እንዳልሰራች ያሳያል። ከተማዋን ለማሳደግ የመንገድ ንድፎች ሲዘጋጁ የሳይክል መንገድ ጨምረው ያካትታሉ…..ነገር ግን መሬት ላይ በተግባር አይፈፀምም..። በዚህ ምክንያት በአዲስ አበባ የሳይክል እንቅስቃሴ የተዳከመ ነው ማለት ይቻላል።
በአንድ ወቅት የሳይክል ትራንስፖርት እንደሚጀመር ቢገለፅም ጉዳዩ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። የተገዙትም ሳይክሎች በመለዋወጫ እጥረት ምክንያት አንድ መጋዘን ውስጥ ታጉረዋል። የሳይክል ተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲቀንስ ካደረጉ ሌሎች ምክንያቶች መካከል ደግሞ የትራፊክ አደጋ መብዛት አንዱ ነው። ሳይክል የሚጠቀሙ ሰዎች በብዛት ለፍጥነት በሚል የመኪና ኋላ ይዘው መጓዝን ያዘወትራሉ። በዚህም ያልታሰቡ አደጋዎች ሲደርሱባቸው ይታያል።
በብዙ ሚሊዮን የሚገመት የህዝብ ገንዘብ በማውጣት የእግር መንገዶች እየተሰሩ ይገኛሉ። ለምሳሌ አሁን በቅርቡ የተጠናቀቀው ከመስቀል አደባባይ እስከ ስድስት ኪሎ ያለው የእግር መንገድ በጥሩ ሁኔታ ተሰርቷል። የከተማው ነዋሪዎችም በስነስርአት ሲገለገሉበት ይታያሉ:: ነገር ግን ለመኖሪያ አቅራቢያ የሚገኙ የእግረኛ መንገዶች ለሳይክል መጓጓዣነት ሲያገለግሉ ይስተዋላል። ይህን ብቻ አደለም ለሳይክል ተብሎ የተሰራው መንገድ አካባቢ የእግረኛ መንገድ ቢኖርም በህብረሰተቡ የተጨናነቀ ነው።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ በአዲስ አበባ የመንገድ ግንባታዎችም አቅጣጫን ያላማከለ ባለመሆኑ
ሰዎች እየተቸገሩ ነው። በከተሞች ላይ ምን አይነት የመንገድ ግንባታ መኖር አለበት ለሚለው የተለያዩ ጥናቶች የተሰሩ ቢሆንም ተግባር ላይ አልዋሉም። አብዛኛው መንገድ ለአደጋ የተጋለጡ ሲሆኑ የእግረኞችና የመኪና መንገዶች የተገጣጠሙ ናቸው። በሌላ በኩል ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ መንገዶች እስካሁን አልተገነቡም።
በከተሞች ላይ መኖር የሚገባቸው የመንገድ ዲዛይኖች መካከል ዋነኛው የውስጥ ለውስጥ መንገድ መቃረቢያ ነው። ህብረተሰቡ በቀላሉ ከቤቱ ወጥቶ የሚፈልግበት ቦታ ወይም ወደ ዋና መንገድ ማድረስ የሚያስችሉ አቋራጮች ከዲዛይን ስራ ጀምሮ መሰራት አለበት። ሌላው ደግሞ ለትራንስፖርት ፍሰት ጠቃሚ የሚሆኑ መንገዶች ዲዛይን ነው።
በከተሞች ላይ በትክክለኛ ዲዛይን መንገዶች ካልተሰሩ መጨናነቅና አንድ ቦታ መቆየትን ይፈጥራሉ። ለምሳሌ ያክል በመንገድ መራዘም የደከመ ሰው መስሪያ ቤቱ ገብቶ ውጤታማ ስራ ማከናወን አይችልም። በከተሞች ላይ ውጤታማ የመንገድ ዲዛይኖችን በመቀየስ ለመንገድ የሚውሉ መሬቶችን መቀነስ ያስፈልጋል። እንዴት ውጤታማ በሆነ መልኩ በአነስተኛ መሬት ስራን ማከናወን ይቻላል የሚለው መታየት አለበት። ውጤታማ የመንገድ ዲዛይን ሲኖር መዘጋት ያለባቸው መንገዶች እንዲዘጉ ያደርጋል። በአዲስ አበባ የተሰራውም የሳይክል መንገድ ትክክለኛ ዲዛይኑን ጠብቆ በሁሉም ቦታዎች መሰራት ካልተቻለ ትርፉ ኪሳራ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012
መርድ ክፍሉ