በሰሜኑ የአገሪቱ አቅጣጫ እየተገነቡ ካሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ነው። በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከመትገኘው አዋሽ ሰባት ተነስቶ በአዋሽ አርባና በአማራ ክልል የሚገኙ እንደ ኮምቦልቻ፣ ሃይቅና መርሳ የመሳሰሉ ከተሞችን አቋርጦ እስከ ወልድያ/ሐራ ገበያ ይዘልቃል። ሁለት ክልሎችን፣ ስደስት ዞኖችን፣ አምስት የከተማ አስተዳደሮችን፣ አስራ ስድስት ወረዳዎችንና በርካታ ቀበሌዎችንም ያካትታል – የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሐራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት።
ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሐራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በየካቲት 18 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦለት ግንባታው ተጀምሯል። ፕሮጀክቱ በ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ በቱርኩ ያፒ መርከዚ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኢንኮርፖሬሽን /yapi merkezi constraction industry incorporation/ በተባለ የግንባታ ተቋራጭና በተወሀዱት የፈረንሳይ-ኢትዮጵያ ተቆጣጣሪ ድርጅት ሲስትራ-መልቲድ /systra-multid/ አማካሪነት በመገንባት ላይ ይገኛል።
የባቡር ፕርጀክቱ ጠቅላላ ርዝመት 390 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ አራት ዋና ዋና፣ ስድስት መለስተኛ ባቡር ጣቢያዎች፣ ጠቅላላ ርዝመታቸው 10 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 12 ዋሻዎች፣ 52 የተለያዩ ርዝመት ያላቸው ድልድዮች፣ 884 ካልቨርቶች፣ ስምንት የሃይል መቆጣጠሪያዎች /ሰብስቴሽን/፣ 12 የሬዲዮ ምሰሶዎች፣ 58 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የአፈር ቆረጣና ሙሌት፣ አንድ ወርክሾፕ /ጋራጅ/ 10 ቴክኒካል ህንፃዎችን እንደሚያካትትም መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
የባቡር ኮርፖሬሽኑ እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም ባጠናቀረው መረጃ መሠረትም ፕሮጀክቱ በርካታ የግንባታ ምዕራፎችን በማለፍ ከአዋሽ- ኮምቦልቻ የሚደርሰው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ከኮምቦልቻ እስከ ወልዲያ/ሐራ ገበያ የሚደርሰው ሁለተኛው ምዕራፍ
ግንባታ ደግሞ 70 ከመቶ ደርሷል። አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀምም 90 ከመቶ ሆኗል።
የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሐራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር አብዱልከሪም መሐመድ እንደሚገልፁት፤ በአሁኑ ወቅት ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ 270 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውና በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚገኘው ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል። ቀሪ ሥራዎችም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሚከናወኑ የሃይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ፣ ለጣቢያዎችና ጥገና ማዕከል ወርክሾፕ፣ የውሃ አቅርቦትና ማፋሰሻዎች ማጠናቀቅ ሥራዎች ናቸው። የባቡር መስመሩ ከአዲስ ጂቡቲ የባቡር መስመር የሚገናኙበት አገናኝ ሃዲድ ስቴሽንና ሌሎች የኦፕሬሽን ሥራዎችን እንዳይከለክል የማጠናቀቅ ሥራዎችም ይቀራሉ።
እንደ ፕሮጀክት ማናጀሩ ገለፃ፤ የሙከራ ሥራ ለመጀመር የሃይል አቅርቦት ወሳኝና አስፈላጊ ቢሆንም የባቡር መስመሩን የሃይል አቅርቦት መስመር ዝርጋታ የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እስካሁን ሥራውን ባለመጀመሩ የሲግናሊንግና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሙከራ ሥራዎችን መሥራት አልተቻለም። ይሁንና በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ወሳኝ ግንባታዎች ተከናውነዋል። ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ 12 ዋሻዎች ውስጥም ስደስቱ በዚህ ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።
ፕሮጀክቱ ከሚይዛቸው አጠቃላይ 55 ድልድዮች መካከል ደግሞ 42ቱ በዚህ ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከኮምቦልቻ እስከ ወልድያ/ሐራ ገበያ 122 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የፕሮጀክቱ ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ አፈፃፀሙ በአሁኑ ወቅት 80 ከመቶ ደርሷል። በዚህ ምዕራፍ የሚገኙ ስድስት ዋሻዎች ውስጥ አራቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል። ረጅሙና ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ወልዲያ አካባቢ የሚገኘውን ጨምሮ ሌሎች የሁለት ዋሻዎች ግንባታም እንዲሁ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በጥቅሉ በፕሮጀክቱ የሚገኙ አስራ ሁለት ዋሻዎች ቁፋሮም አልቋል።
የፕሮጀክት ማናጀሩ እንደሚሉት፤ ለባቡር መሠረተ ልማት የሚያስፈልጉ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችም ከተወሰኑ ክፍሎች (ሴክሽኖች) በስተቀር በሁለቱ ምዕራፎች በአብዛኛው ተጠናቀዋል። ሆኖም በአንድ ሴክሽን ላይ ተወለደሬ በሚባል ወረዳ አካባቢ በህብረተሰቡ የካሳ ቅሬታ ምክንያት ሥራው ቆሟል። አሁን ባለው ሁኔታም በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ሲከናወን የቆየው ፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀሙ 92 ከመቶ ደርሷል። ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሃይል አቅርቦት እስካሁን ድረስ ባለመገኘቱና ከኮሮና ወረርኝ ጋር በተያያዘ ሥራዎች በመቆማቸው ለማጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰውን ፕሮጀክት
በሚፈለገው ፍጥነት ማስኬድ አልተቻለም።
በተለይ የፕሮጅቱ መጠናቀቅ ከሃይል አቅርቦት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ሲሆን፣ ይኸው የሃይል አቅርቦት መቼ እንደሚደርስ በትክክል የሚታወቅ ነገር የለም። በዚህም የተነሳ ፕሮጀክቱ በትክክል መቼ እንደሚጠናቀቅ አይታወቅም። ከሃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት በኮርፖሬሽኑና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መካከል ጊዜ የፈጀ ክርክር ሲካሄድም ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ለኤሌክተሪክ ሃይል አቅርቦቱ በጀት እንደሚበጅት በማስታወቁ ችግር ተፈቷል።
ሆኖም የኤሌክትሪክ ሃይል ወደ ፕሮጀክቱ ለማቅረብ የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት የግዢ ሂደቶች ፕሮጀክቱን እያጓተቱት ይገኛሉ። በፕሮጀክቱ ምዕራፍ አንድ 270 ኪሎ ሜትር የሃይል አቅርቦት እየተጠበቀ በመሆኑና በምዕራፍ ሁለት ደግሞ በተወልደሬ ወረዳ አንድ ሴክሽን ላይ ከመሬት ካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ችግሩ ስላልተፈታ በፕሮጀክቱ ላይ መጓተት ተፈጥሯል።
የፕሮጀክቱ ማናጀሩ እንደሚያብራሩት፤ የባቡር ፕሮጀክቱን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከአምስት ዓመታት በላይ ፈጅቷል። የፕሮጀክቱ ዋና ሥራም በታሰብው ጊዜ ተጠናቋል። ይሁንና የሥራው ውጤት የሚታየው ወደ ሥራ ሲገባ ነው። ፕሮጀክቱ በብድር የተሠራ ከመሆኑ አኳያም ብድሩን በቶሎ ለመክፈልና ለህብረተሰቡም የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት በቶሎ ወደ ሥራ እንዲገባ የኮርፖሬሽኑ ዋነኛ ፍላጎትና ጥረት ነው። በመሆኑም የዚህ የሃይል አቅርቦት ጉዳይ የሚፈታ ከሆነና የሚመለከተው ተቋም የሃይል አቅርቦቱን ካጠናቀቀ በኋላ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ሥራውን ይጀምራል።
ስልሳ ስድስት ወራት የተያዘለት የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ወልድያ/ሐራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ ገደብና በተመደበለት በጀት መሠረት እ.ኤ.አ በ2020 ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ቢጠበቅም በሃይል አቅርቦትና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሥራው መጓተቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012
አስናቀ ፀጋዬ