አባቷን በልጅነቷ ያጣችው ዝናሽ ተሾመ ተወልዳ ያደገችው ጅማ ነው። ልጅነቷን ያሳለፈችው በእናቷ ቤት በተንጣለለ ግቢ እንደፈለጋት ቦርቃ ነበር። ከእናቷ ጋር ያላት ግንኙነት እንደ እናት፣ ጓደኛ፣ እህትም ጭምር ጠንካራ ስለነበር በዚህ ሂደት ሆና ሳይታወቃት የወጣትነት ጊዜዋ አለፈ። ትዳር በመሠረተች ማግስት ደግሞ የእናቷ ህይወት አለፈ። ምንም እንኳ በግቢያቸው በርካታ ተከራዮች ቢኖሩም እናትና ልጅ በጣም ይዋደዱ ነበርና ዝናሽ ባዶነት ተሰማት። ግቢው ያለ እናቷ ኦና ሆነባት። ወደ አዲስ አበባ የሥራ ዝውውር ከጠየቀች በኋላ፤ ሙሉውን ግቢ አከራይታ ከባለቤቷ ጋር ጠቅልላ አዲስ አበባ ገባች። ቤት ስታከራይ የኖረችዋ ዝናሽ ተከራይ ሆነች።
የመጀመሪያ የተከራይነት ህይወትን የጀመረችው መገናኛ አካባቢ ነበር። የእርሷና የሌሎቹም ተከራዮች የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ተቆልፎበት አከራይዋ ካልፈቀደች እንጀራ አይጋገርም። ይሁንና ይህ ዝናሽ አላስከፋትም። አከራይዋ በፈቀደችበት ጊዜ እንጀራ እየጋገረች መኖር ቀጠለች። የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ከአራስነት እስከምትወጣ ተከራይነት ብዙ አልከበዳትም ነበር። ሥራ ስትጀምር ግን ተከራይነት እጅግ በጣም ከባድ ሆነባት።
የቤቱ ባለቤቶች ከቀጠረቻት ሠራተኛ ጋር መስማማት አልቻሉም። አከራዮቹ ቀድሞም ቢሆን የተከራይ ሠራተኛ እንደማይፈልጉ ገልፀው ነበር። ሥራዋን መተው አልፈለገችም። ሥራዋን ብትተውም ያለሠራተኛ ልጅ ማሳደግ እና ምግብ ማብሰል ስለሚከብዳት የግድ ሠራተኛ መቅጠር ትፈልጋለች። ስለዚህ ቤት ለመቀየር አሰበች፤ ነገር ግን ቶሎ ቤት ባለማግኘቷ ሠራተኛዋን ሸኝታ ለተወሰነ ጊዜ ከሥራ ቀረች። ለሥራዋ ቅርብ የሆነ እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ ቤት በማግኘቷ ቤቱን ለቅቃ አዲስ ያገኘችውን ቤት ተከራየች። ለልጇ መዋያ እየከፈለች የቤት ሥራውን የምትሠራላትን ልጅ ደግሞ ከጅማ ዘመዶቿ ላኩላት።
ጠዋት ልጇን ማቆያ ስታደርስ ከጅማ የመጣችዋ ልጅ
ቤት አፅድታ እንድትጠብቃት፤ ማታ ሥራ ውላና ከማቆያ ልጇን ይዛ ስትመጣ ደግሞ ልጇን እንድትይዝላት ብትፈልግም እንዳሰበችው አልሆነም። አዲሶቹ አከራዮች ልጅቷን ሱቅ ከመላክ አልፈው የእነርሱን ቤት ማስፀዳት እና ቡና ማስፈላት ጀመሩ። ዝናሽ ለአከራዮቹ ምንም ለማለት አልደፈረችም። አንድ ቀን ግን ያልጠበቀችው ነገር ተፈፀመ። ባለቤቷ ለሥራ ከአዲስ አበባ ወጥቷል። ከጅማ የመጣችዋ ልጅ ከንጋቱ 12 ሰዓት ‹‹ሽንት ቤት ልሂድ›› ብላ ሳትመለስ ቀረች። ዝናሽ ተደናግጣ ግቢው ውስጥም ሆነ ከግቢ ውጭ ብትፈልጋት ማግኘት አልቻለችም። የልጅቷን ልብስ ስትፈልግ በቤቱ ውስጥ ልብሷ የለም። ስለዚህ ቀድማ ተዘጋጅታ ልብሷን ይዛ መሄዷ ገባት። ልጅቷ ከጅማ በመምጣቷ ድርጊቱን የፈፀሙት አከራዮቿ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምታለች። ስለዚህ መጥፋቷን ፖሊስ ጣቢያ አስመዝግባ ወደ መደበኛ ህይወቷ ለመመለስ ልጇን ማቆያ አስቀምጣ ወደ ጅማ ብትደውልም ሰው ልታገኝ አልቻለችም።
ከደላላ ቤት ሠራተኛ አመጣች። ሆኖም የመጣችዋ ሠራተኛ አሁንም ከአከራዮቹ ጋር ከመቀራረብ አልፋ ሰፈር ውስጥ መላላክ እና ከባለሱቆች ጋር በመቀራረብ የቤት ውስጥ አስቤዛ ሽንኩርት፣ ስኳር እና ዘይት ሌሎችም የፍጆታ ነገሮችን አሳልፋ መስጠት ጀመረች። የአከራዮቹ አኗኗር ልቅ መሆኑ ለዝናሽ እንቅፋት ሆነባት። ከአንድ ዓመት በኋላ ልጇ በማደጉ የህፃናት ማቆያ ክፍያ እና የሠራተኛዋ ደመወዝ ስለተደራረበባት፤ ዝናሽ የቤት ሠራተኛዋ ልጅዋን ይዛ ቤት እንድትውል በማሰብ ቤት ለመቀየር ወሰነች።
‹‹የቤት ኪራይ ዋጋው የተሻለ ነው›› በሚል ወደ ተነገረለት ፈረንሳይ አካባቢ ሁለት ክፍል ቤት በተመጣጣኝ ዋጋ አግኝታ ተከራየች። እዛ ግቢ ለጊዜው አከራዮቹ ጠበቅ ያሉ በመሆናቸው የተሻለ ሆነ። ነገር ግን በአከራዮቹ ግቢ ትዳር የመሰረተች እና ሦስት ልጅ ያሏት የአከራዮቹ ልጅ በመኖሯ፤ አልፎ አልፎ እርሷ የምትፈጥረው ጫና ዝናሽን ያሳስባት ነበር። የአከራይዋ የልጅ ልጆች ከእሷ ልጅ ጋር ሲጫወቱ በተለይ ሁለቱ ትልልቅ በመሆናቸው አልፎ አልፎ የዝናሽን ልጅ ይመቱታል። የቤት ሠራተኛዋን ‹‹ልጁን አትልቀቂ፤ ከእነርሱ ጋር አይገናኝ›› ብትላትም እርሷ ግን ልጁ
ሲያለቅስባት ትለቀዋለች። ዝናሽ ያንን ችላ ማሳለፍ ለመደች። ልጇም አብሯቸው የሚጫወቱት ልጆች ከእርሱ ይበልጠ ነበርና የበታችነቱን ተቀብሎ ተለማምጦ መዋል ቻለ።
በፈረንሳይ አካባቢ በተደጋጋሚ ውሃ ይጠፋል። አንዳንዴ ውሃው ሳይመጣ ከአስራ አምስት ቀን በላይ ይቆያል። ግቢው ውስጥ ሌሎች ተከራዮችም አሉ። ውሃው ሲመጣ ብዙ ጊዜ አከራይዋ ከቀዱ በኋላ የሴትየዋ ልጅ ትቀዳለች። ለሁለቱም ቤተሰብ የሚሆን ውሃ ተቀድቶ፤ በተጨማሪ ታንከር ከሞላ በኋላ ተከራይ በተራ ይቀዳል። ስለዚህ እነዝናሽ ውሃ ሳይቀዱ ውሃው ተመልሶ ይሄዳል። በዚህ ምክንያት ዝናሽ ውሃ በአህያ ታስቀዳለች። እየቆየች ስትሄድ ተስፋ ቆርጣ ሙሉ ለሙሉ ከግቢው ውሃ መቅዳት አቁማ፤ በአህያ እያስጫነች ልብስ ማጠብም ሆነ ማሳጠብ እና ለፈለገችው ጉዳይ መጠቀም ቀጠለች። በዚህ አንዳንዴ በወር ከ200 እስከ 300 ብር የምታወጣበት አጋጣሚ ነበር። ያም ሆኖ አልከፋትም። ሁለተኛ ልጅ ወለደች። ልጆቿን ሌላ ሠራተኛ ቀጥራ ማሳደግ ቀጠለች።
ሁለተኛዋ ልጅ ሴት በመሆኗ አከራዩዋም ሴት የልጅ ልጅ ስለሌላቸው ሁሉም ሳይከፋው እየተቀባበላት አንድ ዓመት አስቆጠረች። በቤቱን ከተከራየች ሁለት ዓመታት ተቆጠሩ። ነገር ግን ከአከራዮቿ ጋር የሚያቃቅራት ጉዳይ አልጠፋም። የአከራዮቹ ሠራተኛ ትበጠብጣት ያዘች። የእርሷ ቤት ልብስ ታጥቦ ሲሰጣ፤ ሠራተኛዋ ውሻ ትፈታለች። ውሻው ሲፈታ ደግሞ እጅግ ሃይለኛ እና ሰው የሚተናኮል ነው። እየዘለለ የተሰጣውን ልብስ እያወረደ ይቦጫጭቃል። የእርሷ እና የልጆቿ ልብሶች በውሻው ተቀዳደዱ። ዝናሽ እንባ አውጥታ አለቀሰች። ምናልባት ከእርሷ ሠራተኛ ጋር አልተግባቡ ይሆናል ብላ በማሰብ የእርሷን ሠራተኛ ሸኝታ ሌላ ቀጠረች። ነገር ግን ችግሩ አልተቃለለም። አከራዮቹ ፊታቸውን ባያጠቁሩም፤ ሠራተኛዋ ግን ሰበብ ፈልጋ ልጁን መምታት፤ ዝናሽም ሆነች የዝናሽ ባለቤት ሲያልፍ በአሽሙር መሳደብ ሥራዋ አደረገችው።
አልፎ አልፎ አከራይዋም በሆነው ባልሆነው መቆጣት ጀመሩ። ባለቤቷም ሆነ እርሷ ሌሎቹም ተከራዮች ከ3 ሰዓት በኋላ አምሽተው ግቢ መግባት አይችሉም። ከመሸባቸው
ውጭ ማደር ግዴታ ነው። ዋናው ቤት ለግቢያ መግቢያ በር ቅርብ ሲሆን፣ የተከራዮቹ ቤት ግን ወደጓሮ በመሆኑ ሩቅ ነው። በሩን ባለቤቶቹ ከቆለፉ በኋላ ወደ ግቢ መግባት አይቻልም። ግቢው ሊሾ ቢሆንም ልብስ ሲታጠብ ጊቢው ውስጥ ውሃ ጠብ ማድረግ አይፈቀድም። ያ ሁሉ ሆኖ ዝናሽ በጥንቃቄ ለመኖር ስትል ከግቢው ከመውጣት ብላ ከነጭራሹ ሠራተኛ ላለመቅጠር ወሰነች። ልጆቿን ታላቁን ትምህርት ቤት ታናሽየዋን ማቆያ እያስቀመጠች ሥራ ብትውልም በተለይ ከአከራዮቹ ሠራተኛ ጋር መቻቻል ከባድ ሆነ። አንድ ቀን ከባድ ነገር ተፈጠረ።
ሠራተኛዋ የግቢው መግቢያ በር አካባቢ ልብስ ታጥባለች። የዝናሽ ባለቤት ለሥራ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ስለነበር ከሥራ መግቢያ ሰዓት ቀድሞ መጥቶ በር ያንኳኳል። ሠራተኛዋ በቀዳዳ አይታ አልከፈተችም። ዝናሽ ከሥራ አልገባችም። ደጋግሞ ሲያንኳኳ ከጓሮ ሰው ሰምቶ በሩ ተከፈተለት። በር የከፈተችዋ ሴት ለሠራተኛዋ ‹‹ምናለ ይህን ያህል እያንኳኳ እዚህ ሆነሽ በር ብትከፍቺ›› ስትላት፤ የአከራዮቹ ሠራተኛ በር አለመክፈት መብቷ እንደሆነ ገልፃ እርሱን የሚመለከት ስድብ ተሳደበች። የዝናሽ ባለቤት ስድቡ ጆሮ ውስጥ ገባ፤ ራሱን መቆጣጠር ስላቃተው የያዘውን ጥሎ ተንደረደሮ የአከራዮቹን ሠራተኛ ደበደባት። ጩኸቷን ስታቀልጥ ሰው ተሰበሰበ። ተባብረው ያዙት፤ ፖሊስ መጥቶ እርሷ ወደ ሆስፒታል እርሱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ።
ዝናሽ ጉዳዩን ስትሰማ ፈራች፤ ወደ ቤት ሳትገባ ቤት አፈላልጋ በከፍተኛ ዋጋ በዛው ዕለት ሙሉ ግቢ ተከራየች። እርሷ ልጆቿን ሌላ ሰው ቤት አሳድራ፤ ሌሊት ዕቃዋን ስታዘጋጅ ቆይታ መኪና ጠርታ በጠዋት ቤቱን ለቀቀች። ባሏም ተፈቶ ጉዳዩ በሽምግልና እንዲያልቅ ተደረገ። ዝናሽ አሁን ምንም እንኳ ውድ ቢሆንም ሙሉ ግቢ ተከራይታ እየኖረች ነው።
ዝናሽ፣ በእርግጥ አከራይ ሆና ዘመናትን አሳልፋለች። መሬት በአካፋ ተዝቆ የሚመጣ ቢሆን ያንን ባደረገች፤ ነገር ግን አይሆንም። አሁን እርሷ ተከራይ እንደሆነችው ሁሉ አከራዮች በአንድ አጋጣሚ ተከራይ የሚሆንበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ በመተሳሰብ የማንም መብት ሳይነካ፤ ማንም ሳይበደል ለመኖር መሞከር የተሻለ ይሆናል ትላለች።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012
ምህረት ሞገስ