በአለም ላይ በርካታ ድንቅ የሆኑና አይን የሚስቡ ኪነ ህንፃዎቸ ይገኛሉ። የህንፃዎቹ አገነባብ የተለያዩ ሁነቶችን የሚያሳዩ ሲሆን፣ በውስጣቸውም አስገራሚ ውበትን ይዘዋል። ከዚህም ውስጥ የመርከብ፣ የሳንቲም፣ ክብና ሌሎች አይነት ዲዛይኖችን ማንሳት ይቻላል። አብዛኛዎቹ የኪነ ህንፃ ውበት የያዙ ቦታዎች የሚገኙት በመካለኛው ምስራቅ አገራት ሲሆን፣ በአውሮፓና በአሜሪካም በተመሳሳይ መልኩ ውበት ያላቸው ህንፃዎች መገኘታቸው እሙን ነው።
በሌላ በኩል በአሁን ወቅት በውሃ ውስጥ የሚሰሩ ህንጻዎች እየተበራከቱ ነው። በተለይ በመካለኛው ምስራቅ አገራት በውሃ ላይ የሚሰሩ ህንፃዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። መካከለኛው ምስራቅ አገራት አብዛኛው ቦታቸው በውሃ የተያዘ በመሆኑ መሬት ለግንባታ በመጥበቧ አማራጫቸውን ወደ ውሃ ውስጥ አዙረዋል። እስቲ የተወሰኑ የውሃ ውስጥ ህንፃዎችን እንመልከት።
ዋተር ዲስክ ሆቴል
በውቅያኖስ ውስጥ የተገነባው ሆቴል የዲስክ ቅርፅ የያዘ ሲሆን፣ የተለያዩ ክንፎች አሉት። እነዚህ ክንፎች ጎብኚዎች በቅርበት የውሃ ውስጥ እንስሳትን አኗኗር እንዲያዩ አድርጓቸዋል። ይህ ቦታ የሚገኘው በዱባይ ከተማ ውስጥ ሲሆን፣ በፖሊሽ አርክቴክቶች ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ በውቅያኖስ ውስጥ ጥልቅ አድርገው ገንብተውታል። የሆቴሉ ግንባታ በሳይንስ ልብወለዳዊ ፊልም ላይ እንደሚታዩት ቴክኖሎጂዎች ውብ ተደርጎ የተሰራ ነው። ግንባታው የተጀመረው እኤአ 2012 ላይ ሲሆን፣ የህንጻው ዲዛይነሮች ንድፉን መሬት ላይ ለማውረድ ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። ግንባታውን ለማጠናቀቅ በተደረገው ጥረት ባለፈው ዓመት ላይ ሆቴሉ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የመጀመሪያው የውሃ ውስጥ አረንጓዴ ቤት
በመስታወት ውስጥ በተዘጋጀ ቤት ወይም አኳፖኒክ ውስጥ አረንጓዴ እፅዋቶችን ማሳደግ የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን በውሃ ውስጥ አረንጓዴ ቤት መገንባት ብዙ የተለመደ አይደለም።
መቀመጫውን ጣሊያን ያደረገው ድርጅት በጣሊያን በሚገኝ ኖሊ ውቅያኖች ውስጥ አምስት አረንጓዴ ቤቶችን ገንብቷል። በአሁን ወቅትም ግንባታው በእጥፍ እንዲጨምር ተደርጓል።
እያንዳንዱ አረንጓዴ ቤት ውስጥ የተለያዩ የእህል ዘሮች የሚገኙ ሲሆን፣ ባቄላ፣ እንጆሪና ሰላጣ ይጠቀሳሉ። 20 ክንድ ጥልቀት ያለው አረንጓዴ ቤቱ ተክሎቹ የሚፈልጉትን ሁሉ እንዲያገኙ ተደርጎ የተሰራ ነው። አረንጓዴ ቤቶቹ አስፈላጊ ሙቀት፣ ትክክለኛ እርጥበት እና በቂ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ እንዲያገኙ ተደርጓል። አርሶ አደሮች እንደሚናገሩት ከሆነ በውሃ ውስጥ የሚተከሉ ምግብ ነክ ነገሮች አስፈላጊውን ለም አፈር ስለሚያገኙ በፍጥነት ያድጋሉ።
የውሃ ውስጥ ፕላኔት ሆቴል
በፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የውሃ ውስጥ ሆቴል ተንቀሳቃሽ ሚሎ ሎጅ ያለው ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ ገቢ እየስገኘ የሚገኝ ቦታ ነው። ሆቴሉ
12 የእንግዳ ማረፊያ፣ ላውንጅና የማረፊያ ቦታዎች እንዲሁም ወደ ታችኛው ስፍራ የሚወስዱ አሳንስሮች ያሉት ሲሆን፣ ከታችኛው ክፍል ወደ ላይ 28 ክንድ ርዝማኔ አለው።
እስካሁን ድረስ ማንኛውም ሆቴል በውሃ ውስጥ በተገነባ ስፍራ እንግዶች እየተመላለሱ እንዲስተናገዱ ለማድረግ የደፈረ የለም። የሆቴሉ አስተዳደር ማንኛውም በውሃ ውስጥ በተሰራው መዝናኛ ስፍራ መምጣት የፈለገ ሰው ያለ አስተናጋጅ በራሱ የሚፈለገውን ነገር ማድረግ እንደሚችል አስታውቋል። በውሃ ውስጥ የተሰራው ሆቴል እንደ ቤትነት የሚያገለግል ሲሆን፣ ለሁለት ሰው ለአንድ አዳር ከሶስት ሺህ እስከ ስድስት ሺህ ዶላር ያስከፍላል።
ትልቁ የውሃ ውስጥ ሬስቶራንት
ከውቅያኖስ በታች መገኘት ከማይረሱ ትውስ ታዎች መካከል የሚቀመጥ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ
በአለም አንደኛ በሆነው የውሃ ውስጥ ሬስቶራንት መገኘት ትልቅ ስሜት አለው። በቅርቡ በሂዋዊ ደሴት ላይ የተገነባው የግማሽ ክብ /ዱም/ ቅርፅ ያለው የውሃ ውስጥ ሬስቶራንት በባህር እንስሳት ተከቦ እራት የሚቀርብበት ቦታ በመሆኑ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል።
ሰላሳ እንግዳዎችን የሚያስተናግደው ሬስቶራንቱ ከሌሎች የውሃ ውስጥ ሬስቶራንቶች በተሻለ መንገድ መስተንግዶ የሚሰጥ ነው። በሬስቶራንቱ የሚገኙት ማረፊያ ቤቶች በውቅያኖሱ ጥልቀት ላይ የተሰሩ ሲሆን፣ ለማብሰያ የሚሆኑ ቦታዎች ግን ጥበት አለበት።
ተንሳፋፊው የባህር ላይ ሆቴል
ሌላው ደግሞ በዱባይ ከተማ የሚገኘው የውሃ ላይ ሆቴል በምሽት እንግዶችን በማዝናናት ግንባር ቀደም ደረጃ ያዘው ተንሳፋፊው ሆቴል ነው። ሆቴሉ የተገነባበት መንገድ ዱባይ ከተማን ውበት ከሰጧት ህንፃዎች መካከል ይገኛል። በዱባይ ዳርቻማ አካባቢ የሚገኘው ይህ ተንሳፋፊ ሆቴል ውድ የሆኑ ጀልባዎች ያሉት ሲሆን፣ በጥልቅ መመልከት የሚያስችሉ መስኮቶችም የተዘጋጁለት ነው። አጠቃላይ በባህር ውስጥ የሚገኙ እንቅስቃሴዎችን መመልከት ያስች ላል።
ሆቴሉን ዲዛይን ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሚና ገሩት ከሆነ፤ በባህር ላይ የሚንሳፈፍ ሆቴል መገንባቱ ጠቀሜታው ለሰዎች ብቻ ሳይሆን በባህር ውስጥ ለሚኖሩ እንስሳትም ጠቀሜታ አለው። ሆቴሉ ወደታች 42 ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ አጠቃላይ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።
ማንታ የውሃ ውስጥ ሪዞርት
የማንታ አነስተኛ ቅንጡ የውሃ ውስጥ ሪዞርት የሚገኘው በታንዛንያ ፔምባ ደሴት ነው። ይህም ከአፍሪካ የመጀመሪያው የውሃ ውስጥ ሪዞርት ሆኖ ተመዝግቧል። ዲዛይኑ የተሰራው በስዊድናውያን ሲሆን፣ ሪዞርቱ ውስጥ የሚገኙት ክፍሎች ትልልቅ መስኮቶቸ አሏቸው። በሪዞርቱ አንድ ክፍል ለመከራየት ለአዳር አንድ ሺህ ሁለት መቶ ዶላር ያስከፍላል። ክፍሎቹ አጠቃላይ የባህር ውስጥ እንቅስቃሴ በሁሉም አቅጣጫ ማሳየት ይችላሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012
መርድ ክፍሉ