ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስን ይሻሉ። ይህ እንቅስቃሴያቸው ደግሞ የቅንጦት ብቻ ሳይሆን የግድም ጭምር ነው። በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ሊጠቀሙ የሚችሉት የተለያዩ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ሊሆን ይችላል። ለዚህ ደግሞ በተፈለገው ጊዜ እና ወደተፈለገው አቅጣጫ ሊያደርስ የሚችል ትራንስፖርት መኖር ወሳኝና የግድ ነው። ይሁንና ታዲያ የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎቱ እንደ ልብ የማይገኝና ቢገኝ እንኳ የተጨናነቀ ሲሆን ይስተዋላል፤ የዚህ መንስኤው ምንድን ነው ስንል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ አርክቴክቸር ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ኢንስቲትዩት የከተማ ልማት ኃላፊና መምህር ለሆኑት ለረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ብርሃኑ ወልደትንሳኤ ጥያቄ ባቀረብንላቸው ወቅት እንዳስረዱት፤ ሰዎች የሚንቀሳቀሱት አንዳች አገልግሎት ለማግኘት ሲፈልጉ እንጂ፣ ለቅንጦት አይደለም። በመሆኑም ትራንስፖርት የግድ አስፈላጊ ነው የሚባልበት ዋነው መነሻም ይሄው ነው።
ሰዎች የሚፈልጓቸው አገልግሎቶች ደግሞ የተለያየ ቦታ እንደመገኘታቸው መንቀሳቀስ የግድ ይሆንባቸዋል። የሚንቀሳቀሱት ደግሞ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን እንደየሚፈልጉት አገልግሎት የተለያየ ቦታ ሊሆን ይችላል። እንዲህም ሲባል ትምህርት ቤቱ፣ ቢሮው፣ ሱቁም ሆነ መዝናኛ ቦታው በአንድ ላይ አይገኝም። ስለዚህም ሰዎች ከቦታ ቦታ ብቻ ሳይሆን ወደተለያየ አቅጣጫ የግድ ይንቀሳቀሳሉ ።
ቀደም ሲል በከተሞችም አብዛኛው ጉዞ የሚደረገው በእግር ነበር። ያኔ እንዲህ እንደ አሁኑ የኢንዱስትራላይዜሽን ማደግን ተከትሎ ትራንስፖርቱም እያደገ እየተወሳሰበ አልመጣም። ከተሞች እያደጉ ሲሄዱ እንደመለጠጣቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎቱም እንደዚያው እያደገ መምጣቱ ይታወቃል። ለዚህ ደግሞ ተመጣጣኝ የሆነ ትራንስፖርት የግድ እንደሚል ይናገራሉ።
ለአብነት በዓለም ላይ በአሜሪካ የመኪና እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በአዲስ አበባም ደግሞ ሲታይ እንዲሁ የመኪና ቁጥር እየጨመረ ነው። የአዲስ አበባው ግን ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነው። እንዲያውም ከ10 በመቶ በታች ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በአዲስ አበባ እ.አ.አ በ1984 በእግር ይሄድ የነበረው ሰው 70 በመቶው እንደነበር አብነት በመጥቀስ ያብራራሉ።
በወቅቱ የመኪና ተጠቃሚው ቁጥር አምስት በመቶ ብቻ ነበር። እ.አ.አ በ2010 ላይ በእግር የሚሄደው ሰው ቁጥር 55 በመቶ ሲሆን፣ የመኪና ተጠቃሚው ደግሞ ስምንት በመቶ አካባቢ እንደነበር ይጠቅሳሉ። በአሜሪካ በአብዛኛው የሚደረገው እንቅስቃሴው በግል መኪና ነው። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ግን በአብዛኛው እንቅስቃሴ የሚደረገው በእግር ነው።
እንደ ዶክተር ብርሃኑ አነጋገር፤ በኢትዮጵያ የተሽከርካሪውን እንቅስቃሴ ማስተዋል ከተቻለ በአብዛኛው የሚበዙት አውቶቡስና ታክሲዎች ናቸው። የመንገድ መሠረተ ልማቱ ሲታይ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል። በአዲስ አበባ አጠቃላይ የመንገድ ቆዳ ስፋት ከጠቅላላው የከተማው ቆዳ ስፋት አንጻር ሲታይ ከጊዜ ወደጊዜ ጨምሯል። የአስፓልቱም ሆነ የጌጠኛ ድንጋዩ የመንገዱ ርዝመት በስፋቱ ተወስዶ የከተማው የቆዳ ስፋት በመቶኛ ሲሰላ ምን ያህል ነው የሚለው ከበለጸጉ አገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ ነበር።
ባለፉት አስርና አስራ አምስት ዓመታት በከተማዋ ላይ ከፍተኛ የመንገድ ኢንቨስትመንት ተካሂዷል ማለት ይቻላል የሚለት ዶክተሩ፣ የአዲስ አበባ መንገድ የቆዳ ስፋት በአሁኑ ወቅት ወደ 21 በመቶ መድረስ መቻሉን ያመለክታሉ። መንገድን ለመገንባት እንደ አገርም ሲታይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ነው የፈሰሰው። በአዲስ አበባም ሲታይ በየዓመቱ ለመንገድ ግንባታ የሚወጣው በጀት ከፍተኛ ነው። ለከተማዋ ቀላል ባቡር ግንባታ የተደረገው ወጪም እንዲሁ ከፍተኛ ነው።
ይሁንና ይህ ኢንቨስትመንት ተካሂዶና ከፍተኛ ወጪም ወጥቶ ከተሞች ከትራንስፖርት ችግር ነፃ ሊሆኑ አልቻሉም። ስለዚህ በከተማ እንቅስቃሴ ላይ የተለያዩ ችግሮች ይስተዋላሉ። ይህ ማለት የከተማው ትራንስፖርት ሲስተም ማለትም የከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ የመንገዱ ሲስተም፣ የእግረኞችና የብስክሌት ትራፊክ ማኔጅመንት እንዲሁም የከተማ ትራንስፖርትን የሚመለከት ኢንስቲትዩሽን ሁሉ መገለጫዎች ናቸው። የሕዝቡን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሳያሟላ ይቀራል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በዚህ ውስጥ ከቦታ ቦታ የሚደረገውን ጉዞ የሚያስተጓጉሉ ከሚባሉ ዋና ዋና ችግሮች እንደ ዓለም አቀፍ ሲታይ አንዱ የትራፊክ መጨናነቅ ነው ይላሉ፤ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) እጥረት መኖርም ሌላው መጨናነቅን የሚፈጥር ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አጥጋቢ አይደለም። አቅርቦትና ፍላጎት የተመጣጠነ አይደለም በማለት ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የትራንስፖርት ችግሮቹ የሚመነጩት አቅርቦት ከፈላጊው ጋር እኩል ባለመሆኑ ነው፤ ሌላው ደግሞ ለእግረኛ የሚሰጠውም ትኩረት አናሳ መሆን ነው።
ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፤ በእግር የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ ነዋሪ እ.አ.አ ከ2010 በኋላ ከተጠቀሰው ቁጥር ዝቅ ብሎ ከ45 እስከ 50 በመቶ ደርሶ ይሆናል፤ ነገር ግን ለዚህ እግረኛ የተሰጠው ትኩረት በጣም አነስተኛ ነው። በጥቅሉ በቂ የእግረኛ መንገድ የለም ማለት ነው። ለምሳሌ ለመኪና ነው የሚታሰበው እንጂ ለእግረኛው በቂ ትኩረት አይሰጠውም። በቂ ስፋት ብቻ ሳይሆን የእግረኛ ማቋረጫም ጭምር በቂ ትኩረት አይሰጠውም። ሌላው ቀርቶ ያሉትም የእግረኛ መንገዶች ለሌላ ጥቅም በስፋት ሲውሉ ይስተዋላሉ። ለምሳሌ የሕገ ወጥ ንግድ ማስፋፊያ ሆኗል፤ አሊያም ደግሞ መኪና ቆሞበት ይውላል ወይም የግንባታ ሥራ ይሰራበታል።
ሌላው ደግሞ ሰዎች የሆድ ሆዳቸውን ሊያወሩበት የሚችሉበት የሕዝብ አደባባዮች ራሳቸው እየጠፉ ነው የመጡት። ፊት ከመኪና መምጣት በፊት በርካታ የሕዝብ መገናኛ ቦታዎች ነበሩ፤ እነዚህ ቦታዎች ሰዎች ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን የሚያወጉባቸው ነበሩ። አሁን ግን መኪናዎች ከመጡ በኋላ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ቀርቷል። ይህን ነገር ላለማጣት ብዙ አገሮች ወደዚህ ሥርዓት ለመመለስ እየሞከሩ ነው። በተለይ የሰለጠኑ አገሮች ‹‹እንዴት አድርገን መንገዶቻችንን ከመኪና ነፃ እናወጣለን›› እያሉ ባህላዊውን ነገር ለማምጣት በመጣር ላይ ይገኛሉ። በተለይ የአውሮፓ ከተሞች በዚህ ላይ እየሰሩ ነው።
በሌላም በኩል ከትራንስፖርት ዘርፉ ጋር ተያይዞ የአየር እንዲሁም የድምጽ ብክለትን የመሳሰሉት በተለይ በእኛ አገር እንዳሉት ከተሞች ይስተዋላሉ። ሌላው ትልቁ አሳሳቢ ችግር የትራፊክ አደጋ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ በትራፊክ አደጋ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የመኪናው ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም፣ የመኪናው አደጋ ግን በጣም ከፍተኛ ነው።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉት የከተሞች ትራንስፖርት ችግሮች በጥቅሉ ሲታዩ ደግሞ የመጀመሪያ ችግር ሊባል የሚችለው የትራንስፖርት አቅርቦት በጣም አነስተኛ መሆን ነው። በዚህም የተነሳ ተደራሽነቱ በጣም አነስተኛ ነው። የትራፊክ መጨናነቁ በተለይ በትልልቆቹና በመካከለኞቹ ከተሞች እየተስተዋለ ነው። መካከለኛ ከተሞች ላይ እየተበራከቱ የመጡት ባጃጆች በከተሞች መጨናነቅ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል።
ከዚህ ቀደም ብስክሌት በስፋት የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡባቸው የነበሩ እንደ ባህርዳር፣ ሐዋሳ የመሳሰሉት የመልካምድር አቀማመጣቸው ለብስክሌት ምቹ የሆኑ ከተሞች አሁን አሁን ይህን የብስክሌት ትራንስፖርቱን ዘርፍ ቀንሰዋል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ሲባል ባጃጆች ስለመጡ ነው የሚል ነገር አለ።
ዶክተር ብርሃኑ፣ ሌላው ፖሊሲ ፍሬምዎርክ ለከተሞች ፕላንና ማኔጅመንት ብዙ ጊዜ የለም። የትራንስፖርት ፖሊሲ የግድ ያስፈልጋል ይላሉ። በተጨማሪ ደግሞ የፋይናንስ ችግር አለ። ትልቁ ችግር የከተማ ትራስፖርትን እንዴት ፋይናንስ እናድርገው የሚለው ነው። ለምሳሌ መንገድ ግንባታን በተመለከተ፤ የፋይናንሱ ጉዳይ ከከተሞቹ የገቢ አቅም በላይ ነው። ይህም በመሆኑ በመንገድ ግንባታም ሆነ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱን በማስፋፋት በኩል በተለይ እያደጉ የሚሄዱ ትንንሽ ከተሞች ላይ ትልቅ እንቅፋት ነው። አብዛኛውን ጊዜ በአገር ደረጃም እየተገነባ ያለው በብድር በሚወሰድ ገንዘብ ነው።
ሌላው ችግር ደግሞ የሰው ሀብት ሲሆን፣ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል የለም ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ የቅንጅት ነገር አይታይም። የትራንስፖርት ተቋማት ከሌሎቹ ጋር በቅንጅት ሲሰሩ እምብዛም አይስተዋልም። ስለዚህ ለተነሱ ችግሮች መፍትሄው ምን ይሆን የሚለውን በቀጣዩ ሳምንት ይዘን እንቀርባለን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2012
አስቴር ኤልያስ