ፍርሀት እና ስጋት በብዙ መንገድ ሊፈጠር ይችላል ። አንድም ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳች ሲያጋጥሙ ፣ እነሱ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት በማሰብ እና በማሰላሰል ፤ ከዚህም ባለፈ ስለ አንድ ነገር ትክክለኛ እና ተገቢ መረጃ ካለማግኘት ፤ የመረጃ እጥረቱ በራሱ የሚፈጥረው የእውቀት ክፍተት የሚፈጥረው ፍርሀት ነው ። ፍርሀት ሰወኛ ነው ፣ የሰውነትም አንዱ ማሳያ ነው።
አደጋ የሚሆነው ግን ፍርሀቱ ደረጃውን አልፎ በራሱ የችግር ምንጪ መሆን ሲጀምር ነው ። ይህ ሁኔታ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ድረስ ሊሄድ የሚችል ፤ሊያስከትል የሚችለውም ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። በዚህ ችግር ውስጥ ያለፉ ና የሚያልፉ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን እና ማህበረሰቦችን ዓለም በተለያዩ ወቅቶች አስተናግዳለች።
ችግሩ በአብዛኛው ለተሳሳቱ አላማዎች ተብለው በሚሰራጩ የተሳሳቱ ስጋትና ፍርሃትን ፈጣሪ መረጃዎች ምክንያት ነው ። እነዚህ መረጃዎች በተደራጀ እና በተጠና መልኩ የሚዘጋጁ ፤ የሚፈለገውን ውጤት እስኪያመጡ ድረስ በስፋት የሚሰራጩ ከመሆናቸው የተነሳ በአንድ ወቅት እውነት የሆኑ ያህል እውነት ሆነው ተቀባይነት የሚያገኙበት አጋጣሚ ሰፊ ነው ።
በአባይ ወንዝ እና በወንዙ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያም ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም ። በአባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ከዘመናት ጀምሮ የግብጽ የፖለቲካ ልሂቃን እያራመዱት ያለው የተሳሳተ አካሄድ ፤ለዚህም እንዲረዳቸው የሚያመነጩት መረጃ የግብጽን ህዝብ በዘመናት ሁሉ በውሃው ዙሪያ ስጋት እንዲያድርበትና ከዚህ ስጋት በመነሳትም ሁሌም ቢሆን ጥሩ እንቅልፍ እንዳይተኛ አድርጎታል።
በአንድ በኩል እውነተኛ የሆነውን (በሳይንስ የተደገፈውን) የአባይ ወንዝ የተፋሰስ እውነታ፣ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ ሀገራት ህዝቦችን እውነተኛ ማንነትን በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ ያላቸውን አስተሳሰብ፤ አስተሳሰቡ የተገዛበትን መርህ በማጣመም የግብጽ ህዝብ በሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ህዝቦች ላይ መተማመን እንዳይኖራቸው አድርጎታል።
ከዚህም በላይ በወንዝ ውሃ ጉዳይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የችግሩ መፍቻ ብቸኛ መንገድ የሃይል አማራጭ ስለመሆኑ በማመን ፈጥኖ ወደ ፉከራና ቀረርቶ መሄድ ቀላሉ መንገድ ተደርጎ እንዲታይ አድርጎታል። ይህ እውነታ የግብጽ ህዝብ ከተሰበከው የስጋት ስብከት አንጻር ፤ ጉዳዩን ከህልውና ጋር በማስተሳሰር የተፈጠረ በመሆኑ ብዙም ግር አያሰኝም ።
በዚህ አይነት ፍርሃት ውስጥ ያለን ማህበረሰብ ከፍርሃቱ ነጻ ማውጣት የሚቻለው አንድም እራሱ ፍርሃቱ ከተጨባጭ አውነታ የመነጨ ነው ወይስ አይደለም ? ብሎ የፍርሃቱን ምንጭ በአግባቡ ጊዜ ወስዶ ለማጥናትና ለመረዳት የሚያስችል ተነሳሽነት ሲፈጠር ነው ። ፍርሃቱን በተጨባጭ መረጃ (እውቀት) ማምከን ሲቻል ነው። ይህ የሚጀምረው ደግሞ የአባ ወንዝ ውሃ ለተፋሰሱ ሀገራት ምናቸው ነው ? ተስማምተውና ተባብረው ቢያለሙት ያንሳቸዋል ወይ —ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ሲሞከር ነው ።
አሁን ካለው ተጨባጭ እውነታ የግብጽ ህዝብ ይህንን ለማድረግ እድሉ ያለው አይመስልም። በአንድ በኩል የግብጽ የፖለቲካ ሊሂቃን እና የቤተመንግስት ሰዎች የአባይ ውሃን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ አቅም አድርገው እየተጠቀሙበት መሆኑ ፤ ለዚህም ሲባል በህዝቡ ላይ እየተጫነ ያለው የስጋት መረጃ በጣም ሰፊና በዘመናት መካከል ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለ የመጣ መሆኑ ፤ነገሩን ያከብዱታል። ከዚህ ይልቅ ቀላሉና አሻጋሪ የሚሆነው የጀመርነውን የታላቁን የህዳሴ ግድብ ስራን ተረባርበን መጨረስ ነው።
የታላቁን የህዳሴ ግድብ የምንጨርስበት ፍጥነት የግብጽ ህዝብ በዘመናት የተጫነበትን የስጋት መረጃ ከንቱነት ለማሳየት ያለ አንድ አማራጭ ነው ። ግድቡን ጨርሰን ወደ ስራ ስንገባ በርግጥም በዘመናት እንደተነገራቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለግብጽ ህዝብ ስጋት አለመሆናቸው ፤ እንዲያውም የወንዙ ውሃ ከምናስበውና ከምንገምተው በላይ የትብብርና የወዳጅነት መሰረት መሆን እንደሚችል ማመን የሚያስችላቸው ተጨባጭ ማሳያ ይሆናል።
የግድቡ ፈጥኖ ማለቅ ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አዲስ የመተማመንና የ ወዳጅነት ከዛም ባለፈ የአፍሪካዊ ወንድማማችነት ታሪካዊ ምእራፍ መክፈት የሚያስችል ነው ። የግብጽ የፖለቲካ ሊሂቃንና የቤተመንግስት ሰዎች የቱን ያህል ሕዛባቸውን ባልተገባ መረጃ ያልተገባ የስጋት ሕይወት ውስጥ ከተውት እንደነበር የግብጽ ህዝብ አይኑን ከፍቶ እንዲያይ እድል የሚሰጥ ነው።
የግብጽ ወንድሞቻችንን ከዘመናት የስጋትና የፍርሃት ህይወት ነጻ የማውጣት ታሪካዊ ሃላፊነት በእኛ እጅ ነው ፤ ይህንን ሃላፊነት ለመወጣት ኑ የህዳሴውን ግድብ እንጨርስ ።
ለግብጻውያን ግድቡ ከግድብ በላይ ነጻ አውጪ ነው !
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2012