ምንም እንኳን በሀገራችንም ሆነ በውጭ ሀገር የፖለቲካ ፈላስፋዎች ዘንድ የባህር ዛፍ ፖለቲካ የሚባል ነገር ባንሰማም ወይም ተፅፎ ባናይም የህወሀት የፖለቲካ መርህ ከአንደኛው የባህር ዛፍ ጠባይ ጋር ስለሚመሳሰል የህወሀትን የፖለቲካ አካሄድ የባህር ዛፍ ፖለቲካ ብየዋለሁ። ለምን ብሎ ለሚጠይቅ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አመክንዮ ማየት ተገቢ ይመስለኛል። እንደሚታወቀው በትላልቅም ሆነ በትናንሽ የሀገር በቀል ዛፎች ስር እና ዙሪያቸው የተለያዩ እፅዋት እና የተለያዩ የሳር አይነቶች በብዛት በቅለው ይገኛሉ፤ ይኖራሉም። ነገር ግን የባህር ዛፍን ጠባይ በምንመለከትበት ጊዜ አንዱ እና ዋነኛው የባህር ዛፍ መለያ ጠባዩ ከራሱ የባህር ዛፍ ዝርያ ውጭ ሌሎች ዛፎችን እና የተለያዩ የሳር አይነቶች በአጠቃላይ በዙሪያው ወይም በስሩ እንዲኖሩ አለመፍቀዱ ነው። በመሆኑም ህወሀት ልክ እንደ ባህር ዛፍ ከእኔ እና ከመሰሎቼ ውጭ ማንም፤ ማንም በአጠገቤም ሆነ በዙሪያየ እንዲኖሩ አልፈቅድም በማለት የፖለቲካ ሽብልቋን በመጠቀምና እና የፖለቲካ ልቃቂቷን በመተብተብ ከህወሀት እና መሰሎቿ ውጭ ያሉ ሀይላትን የተለያዩ መርዛማ ስሞችን ከፊትና ከኋላ እንደ ቀንድ እና ጅራት በመለጠፍ ፤ በመቀጣጠል ስታሳድድ ፣ ስታስር ኖራለች። ይህ አልበቃ ብሏት አሁንም ከእኔ ውጭ የምትለውን ሀሳዊ መሲህነቷን እና ሞገደኛነቷን ቀጥላበታለች። ስለሆነም ይህ እኔ እና መሰሎቼ ብቻ በሀገሬቱ ስራችንን አስረዝመን ቅጠላችንን አንዠርገን እንኑርን የህወሀት ፖለቲካ የባህር ዛፍ ፖለቲካ ብየዋለሁ።
ከባህር ዛፍ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ አሁን አንድ ወቅታዊ ችግር መፈጠሩን ማየት ተገቢ ይሆናል። ይህም ምንድን ነው በህወሀት መራሹ የተዘጋጀውና ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ አላሳተፈም እየተባለ የሚተቸው የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ሲረቀቅ በወቅቱ የነበሩ ምሁራንን ለይስሙላ ያሳተፈ ቢሆንም ከተፅኖ ውጭ ነበር ማለት ግን አልነበረም። በመሆኑም “የሹክሹክታ ጋብቻ ለፍች ያስቸግራል” እንዲሉ አሁን ያለው ህገ መንግስት በሚረቀቅበት ወቅት ምሁራን ቢሳተፉም የተሳተፉት ምሁራን የወያኔን ፖለቲካዊ ፍላጎት ሚጎራበጡ አልነበሩም። የወያኔን ፖለቲካ ይጎራብጣሉ ተብለው የታሰቡት ምሁራን ቀድመው ሀገራዊ ጉዳዮችን መከወን እንዳይችሉ ከፊሎቹ ከሀገር መባረር፣ ከፊሎች ደግሞ ለእስርመዳረግ እና የቀሩት ደግሞ ከስራ የመታገድ ዕጣ ደርሶባቸዋል። ስለሆነም ሁሉንም የሚመለከታቸውን ምሁራንን እና የሀገሪቱን ህዝቦች ያላሳተፈ (ገሸሽ ያደረገ) ህገ መንግስት በመሆኑም የህገ መንግስቱ የማርቀቅ ሂደት የሹክሹክታ ጋብቻ አይነት ነበር። በመሆኑም ህገ መንግስቱ ሊረሱ (ሊገደፉ) የማይገባቸው አንዳንድ ጉድለቶች ያሉበት ነው። ከነዚህም መካከል ሰሞኑን የገጠመንን ችግር ማየት በቂ ነው። በእርግጥ ፍጹም እንከን የሌለው ህገ መንግስት በየትኛውም ሀገር አይኖርም። ነገር ግን ሀገር በችግር ውስጥ ስትሆን ምርጫ ምን መምሰል አለበት የሚለውን ጉዳይ ህወሀት በበላይነት እየመራችው በተዘጋጀው ህገ መንግስት ላይ አልሰፈረም። ስለዚህ ይህንን ጉዳይ ረቂቅ ህገመንግስቱ ላይ አለማስፈር የማን ችግር ነው ? መልሱ ቀላል ነው። ይህም የህወሀት እና በረቂቁ የተሳተፉ አካላት ችግር ነው። ስለሆነም ራሳቸው ህወሀቶች ለፈጠሩት ችግር አሁን ያለው መንግስት ለችግሩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረቡ ምን ላይ ነው ሀጢያቱ?
ይህ በእንዲህ እንዳለ ህወሀትም ”ከሞተች ሚስቴ ምን አለኝ ከአማቴ” እያለች ትገኛለች ። ማለትም እኔ ከፌዴራል መንግስቱ ስልጣን ከተነሳሁማ ስለ ኢትዮጵያ ምንስ ቢሆን ምን አገባኝ አይነት አካሄድን የመረጠች ይመስላል። በአሁኑ ወቅትም ህወሀት በትግራይ ክልል ሁለተናዊ ጉዳዮች ላይ የፌደራል መንግስት ምንም ሥልጣን እንደሌለው በማስመሰል በክልሉ እኔ ብቻ ተካይ ነቃይ ነኝ እያለች ትገኛለች። ለዚህም ዋና ማሳያው የፌደራል መንግስት በተከሰተው ዓለምአቀፋዊ ችግር ምክንያት ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ሲገልፅ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ህዝብም ያለውን ችግር ተገንዝቦ ምርጫ መካሄድ የለበትም ሲል ህወሀት ግን ምርጫው ካልተካሄደ ገመድ ባንገቴ ስትል እያየን ነውና። ለዚህ ደግሞ መከራከሪያ አድርጋ ያቀረበችው ራሷ አንድም ቀን አክብራው የማታውቀውን ህገ መንግስት ነው። ከዚህ በፊትም ህወሀት በፌዴራል መንግስት ላይ በነበረችበት ጊዜ ምሁራንን ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ፣ ጋዜጠኞችንና የሲቪክ ማህበራትን ስታሰቃይ፤ ስትገድል፤ ስታስር እና ስታሳድድ ሁሌም የምትለው ነገር አለ። ይህም ህገ መንግስቱን ጥሰዋል ፣ ህገ መንግስቱን ለመናድ ሞክረዋል ወዘተ። ግን እስከ መቼ ነው ህወሀት በህገ መንግስቱን በመንተራስ መተወን የምታቆመው? እደግመዋለሁ ! ግን እስከ መቼ ነው ህወሀት በህገ መንግስቱን በመንተራስ መተወን የምታቆመው?
እውነት ለመናገር ህወሀት ስለዴሞክራያዊ አስተዳደር የማውራት ሞራል አላት? አንድ ፈረስ ያለመዋዦ (ያለመደላድል) ለተደጋጋሚ ጊዜ እቃ ከተጫነ የፈረሱ የጀርባ ቁስል ሊድን በማይችልበት ሁኔታ እንደሚቆስል እሙን ነው። ህወሀትም ልክ ያለመዋዦ (ያለመደላድል) እቃ እንደተጫነ ፈረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይም እያመረቀዘ በቀላሉ የማያሽር መንፈሳዊና ቁሳዊ ቁስል አቁስለው አልፈዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የህወሀትን ፍላጎት ባማከለና የህዝቡን ፍላጎት በዘነጋ በተደጋጋሚ በሚወጡ ህጎች ነው።
አሁን ደግሞ ህወሀት እራሷን ለትግራይ ህዝብ ህብስተ መና ለማስመሰል በፕሮፓጋንዳ ወፍጮዋ ፕሮፓጋንዳዋን እየሸረከተች ትገኛለች። እንዴት ግን አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከእኔ ውጪ አንተን ሊወክልህ የሚችል ሌላ አካል ሊኖር አይችልም። የሚለውን ህዝብ እንዲህ በፕሮፓጋንዳ ብቻ እየሸነገለ ሊያቆየው የሚችለው? እዚህ ላይ ህወሀትን የተወሰኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ እፈልጋለሁ። አንደኛ – የትግራይን ህዝብ ትክክለኛ ጥያቄ ወይም ፍላጎት በሚገባ ታውቁታላችሁ? ሁለተኛ- እንታገልልሀለን ለምትሉት የትግራይ ህዝብን መብት ለማስከበር እንመጥናለን ብላችሁ ታስባላችሁ? ሶስተኛ ለዴሞክራሲያዊ ትግል ምን ያህል ዝግጁ ናችሁ? ሁሉንም ጥያቄዎች አዎ እናደርጋለን ብላችሁ ለማጭበርበር እንደምትሞክሩ እርግጠኛ ነኝ። ህወሀት አሁን በሀገራችን ላይ እያደረገች ያለው ነገር የበሰለ የፖለቲካ አካሄድ ሳይሆን የሀገር ክህደት ሴራ ላይ ያለች ይመስለኛል። ምክንያቱም እኔ ያላልኩት እና እኔ ብቻ የፈለኩት ካልሆነ ሀገር እንደ ሀገር ለመቀጠል ያስቸግራል ብሎ በየሚዲያው መለፈፍ የፖለቲካ ብስለት ስላልሆነ።
በመጨረሻም “ከቅርብ የወደቀ ከስብራት ይድናል” እንዲሉ ህወሀትም ሆናችሁ ህወሀታዊ አስተሳሰብ እና ግብር ያላችሁ አካላት አሁን ኢትዮጵያ ላይ ያለው ነገር በመመካከር እና በመወያየት የሚፈታ ስለሆነ ሌላ ችግር ተፈጥሮ ሀገራችን ወደ ጥልቅ ጉድጓድ እንዳትገባ የሀገራችንን ወቅታዊ ችግር እና የህዝቦቿን የልብ ትርታ ያገናዘበ ምክክር ብታደርጉ ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
በአሸብር ሀይሉ