የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮና ከዚያም በፊት የግብጽ የፖለቲካ ልሂቃንና በካይሮ ቤተመንግሥት በተለያዩ ወቅቶች የገቡ የሀገሪቱ መሪዎች ለረጅም ዘመናት ለግብፅ ህዝብ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሲሰብኩ የኖሩት የተጣመ ታሪክ በሀገራቱ ህዝቦች መካከል የመተማመን መንፈስ እንዳይፈጠር ትልቁ ተግዳሮት ሆኗል።
ይህ እውነታ ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚቀባበል መልኩ በሀገሪቱ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ሳይቀር መሰረት እንዲኖረው፣ መጪው ትውልድ በእነዚህ የተጣመሙ አስተሳሰቦች ገና ከጅምሩ ሰለባ እንዲሆን በተደራጀ መልኩ ተሠርቷል እየተሠራም ነው።
ይህ የትውልዳችን ስነልቦና ሳይቀር በተሳሳተ መንገድ የመቅረጹ እውነታ በሁለቱ ሀገሮች ህዝባች መካከል ከነበረው የረጅም ዘመናት የታሪክ ትስስር አንጻር የሀገራቱ ህዝቦች በተሻለ መቀራረብና የወንድማማችነት መንፈስ ነገዎቻቸውን ከማሰብ ይልቅ በስጋትና በጠላትነት ስሜት እንዲተያዩ አድርጓቸዋል ።
ይህን ታሪካዊ ችግር ለመቅረፍ በአንድ ወቅት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከር በሀገራቱ ታሪክ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውንና ያለውን ያልተገባና ተጨባጭ መሰረት የሌለውን ያለመተማመን ስጋት ለመቅረፍ ተሞክሮ ነበረ።
ይህ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ በሀገራቱ ህዝቦች መካከል ፈጥሮት የነበረው የወንድማማችነትና ከጥርጣሬና ከስጋት የመውጣት መነሳሳት ለትዝታ ብዙም የሚደበዝዝ አይደለም። ነገሮች እንዲህ ቅርብ ናቸው የሚያስብል ተስፋ ሰጪ ክስተትም ነበር።
የግብፅ የለውጥ ኃይሎች ትግል ሰምሮ የሆስኒ ሙባረክ የስልጣን ዘመን ባበቃበት ማግስት የተስተዋለው ይህ ታሪካዊ ክስተት በአንድ በኩል ፣ በሌላበኩል የለውጥ ኃይሉ የነበረውን ያለመተማመንን የስጋት መንፈስ ለመስበር የሄደበት ረጅም መንገድ በሀገራቱ ህዝቦች መካከል ፈጥሮት የነበረው አዲስ ተስፋ ትልቅ ፣ በእርግጥም ትልቅ ነበር።
የግብፅ ወንድሞቻችን ቀናነት በካይሮና በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ የለውጥ ተስፋን ሰንቆ ማስተዋል የተቻለበትን ታሪካዊ አጋጣሚ ፈጥሯል። በርግጥም በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረው የለውጥ መንፈስ ያልተገቡ ታሪካዊ ስጋቶችን መሻገር የሚችል አቅም የፈጠረም መስሎ ነበር።
ሁኔታው መልኩን የቀየረው ለውጡን ተከትሎ ካይሮ ቤተመንግሥት የገቡት የሀገሪቱ ፖለቲከኞች አሁንም የውስጥ ችግሮቻቸውን ለማርገብና ተቀባይነታቸውን ለማሳደግ የዓባይና የህዳሴ ግድብ ግንባታ በማንሳት የፖለቲካ ጊዜ የአደጋ መውጫ አድርገው የመጠቀማቸው እውነታ ነው።
እውነታው እንደታሰበው የአደጋ ጊዜ መውጫ መሆን ባይችልም የተሄደበት እርቀት ግን አስደንጋጭና በርግጥም አሳሳቢ እንደነበር ለማሰብ አይከብድም። የጦርነትና የጦርነት ነጋሪት ከፍ ባለ ድምፅ የተጎሸመበት፣ ፊከራ የበዛበት ነበር፡፡
ጉዳዩ በራሱ የፈጠረው እውነታ ስላልነበረ ከዚያ ሁሉ ፉከራና ቀረርቶ በኋላ፣ ነገሩ የነበረ አስካይመስል ድረስ ሁኔታዎች መልካቸውን ቀይረው ሌላ ዝማሬና ሌላ ዜማ ሲሰማ ተስተውሏል። ነገሩ እንደቀደሙት ተመሳሳይ ታሪካዊ አጋጣሚዎች በመጣበት ቅጽበት ተመልሶ በኖ ጠፍቷል። እውነታውን በአግባቡ ለሚያውቁት ነገሩ ፈገግ የሚየሰኝ ቢሆንም በግብፅ ሕዝብ ላይ ዘርቶት የሄደው ያልተገባ ዘር ግን ቀላል አልነበረም፤ አልሆነም።
ስለወንድማማችነት፣ ስለአዲስ ታሪካዊ የግንኙነት ምዕራፍ መከፈት ብዙ ብዙ የተነገረውና የሰማው የግብፅ ህዝብ፣ የሰማው ተስፋ ሰጪ ድምፅ ከጆሮው ሳይጠፋ የተነገረውን ተስፋ እንኳን አጣጥሞ ሳይጨርሰው የተፈጠረው ክስተት ለማመን የከበደ እንደሚሆን ለማንም ስሜት ላለው ፍጡር ሩቅ አይሆንም።
ከቤተ መንግሥት ተሳናባቹ ፖለቲከኛ ከገባበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት የፈጠረው ይህ ስሜት ሳይደርቅ ወደ ቤተ መንግሥት የመጣው ሌላኛው ባለተራ የውስጥ ፖለቲካው የተረጋጋ ሲመስል አሮጌዎቹን የተሳሳቱ ትርክቶች ሊያድሱ የሚችሉ ቋንቋዎችን ይዞ ብቅ ቢልም ሁኔታው ብዙም መጓዝ አልቻለም።
የሀገራቱ ህዝቦች የሚፈልጉትን በመተማመን ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነትን ለማምጣት የሚያስችል አቅም መፍጠር አልቻለም። እንደተለመደው የግብፅን ህዝብ የለውጥ መንፈስ ተሸክሞ መጓዝ የሚችል ስርዓት መምጣት ባለመቻሉ ዳግም የዓባይና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግብፅ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኗል። የአሁን ከቀደሙት የሚለየው አጀንዳውን ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ብቻ ነው።
የአባይ ወንዝና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በዚህ ወቅት የግብፅ የፖለቲካ ትኩሳት ቴርሞ ሜትር መሆኑ አዲስ ክስተት አይደለም። ቀደም ሲል እንደነበረው በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ኃይል የግብፅ ህዝብ የሚፈልገውን መስጠት ስላልቻለ አሁንም የአባይ ወንዝንና የታላቁ ህዳሴ ግድብን አጀንዳ አድርጎ ጊዜ መግዣ እያደረገ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ ትናንትም ይሁን ዛሬ ድንገት ነገም የአባይ ወንዝም ሆነ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በራሱ በሀገራቱ መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል አቅም የለውም።
የግብፅ የፖለቲካ ልሂቃንና የቤተመንግሥት ሰዎች ሀገራዊ ህዝባዊ የለውጥ ፍላጎቶችን ማሳካት ባልቻሉበት ሁኔታና የህዝባቸውን የለውጥ መንፈስ በሌላ የስጋት መንፈስ ለመቀልበስ የሚጠቀሙበት ትናንትም ከትናንት በስቲያም የነበረውና ድንገትም ከእነዚህ ቀናት ስህተት መማር ካልቻሉ ነገም ተመልሶ ሊመጣ የሚችል የህዝቦችን ተስፋ የሚነጥቅ እርግማን ነው።
ችግሩ ለዘለቄታው ሊፈታ የሚችለው የግብፅ የፖለቲካ ልሂቃንና የቤተመንግሥት ሰዎች በቅንነት የህዝባቸውን የለውጥ ፈላጊነት መንፈስ በአግባቡ ተረድተው ህዝቡን የሚመጥን የፖለቲካ ስርዓት መገንባት ሲችሉ ብቻ ነው። እስከዚያ የዓባይ ወንዝና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከፖለቲካ አጣብቂኝ የመውጫ ካርድ ሆኖ ማገልገሉ አይቀርም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2012