የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን (አንዳንድ ወገኖች በለውጡ ማግስት የሚካሄድ የመጀመሪያ ምርጫ እንጂ ስድስተኛ ሊባል አይገባም ሲሉ ይሞግታሉ ፤ በይዘቱም ሆነ በቅርጹ ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ ነው ብሎ በማመን፤) ሀገራዊ ምርጫ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ በተያዘለት ቀን ማለትም ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋ ካደረገ በኋላ ምክር ቤቱ ቦርዱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተወያይቶ የቦርዱን ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል::
በመሆኑም ምክር ቤቱ ምርጫውን ማካሄድ ባለመቻሉ የሚፈጠረው የሥልጣን ክፍተት ሕገ መንግሥታዊነትንና ሀገረ መንግሥቱን በሚያስጠብቅ አግባብ የመፍትሔ አማራጭ አጥንቶ እንዲያቀርብ ለሕግ ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። ኮሚቴው መንግሥት በሕገ መንግሥት ልሒቃን በገለልተኝነት በጥናት የለያቸውን አራት አማራጮች ማለትም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን ፣ እንዲሁም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ማሰጠት የሚሉትን ከመረመረ በኋላ የውሳኔ ሐሳቡን ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም ለምክር ቤቱ ያቀረበው ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም መፍትሔ እንዲሰጥበት የሚጠይቅ ነው።
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ በማለት ሲደነግግ ፣ በአንቀጽ 58(3) ላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው። የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ ይጠናቀቃል ሲል ታሳቢ ያደረገው ፣ መደበኛና ጤናማ የሆነውን ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ነው::›› በማለት ቋሚ ኮሚቴው በውሳኔ ሐሳቡ አመልክቷል።
የኮቪድ – 19 አደገኛ ወረርሽኝ ከአንደኛውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ፣ 50 ሚሊዮን ሕዝብ ጨርሶ ግማሽ ቢሊዮን ሰው የአልጋ ቁራኛ ካደረገው ከእስፓኒሽ ፍሉ (በሀገራችንም 40 ሺህ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል) ፣ ከፈንጣጣና ከጥቁሩ ሞት የከፋ መሆኑ በሳይንቲስቶች ፣ በሀኪሞችና ተጓዳኝነት ባላቸው ልሒቃን ተረጋግጧል:: ይህን አጀንዳ እየቀረጽሁ እያለ ፤ በዓለማችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ አምስት ሚሊዮን እያሻቀበ ሲሆን፤ የሟቾች ቁጥርም ደግሞ ወደ 320 ሺህ እየተጠጋ ሆኗል::
በሀገራችን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አኀዝ 317 ሲሆን፤ የሟቾቹ ቁጥር አምስት ፣ ያገገሙት ደግሞ 113 ደርሷል:: በዚህ የተነሳም በሀገርና በሕዝብ ህልውና ላይ የተደቀነ አደጋ በመሆኑ በመላው ዓለም ሊባል በሚችል ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል:: የሕዝብ እንቅስቃሴ ተገደበ ፣ ከተሞች የመናፍስት ከተማ እስኪመስሉ ጸጥ ረጭ አሉ ፣ ” ሁሉም ነገር ወደ ፀረ ኮቪድ – 19 ተባለ፣ የጤና ቀውሱ ወደ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተባባሰ ፣ የዓለም ኢኮኖሚ የጃፓንና የጀርመን የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ድምር በሚያክል መጠን አሽቆለቆለ፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ አጥ ሆኑ ፤ ሉላዊነት፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ ህብረቶች ነፈሰባቸው ፣ ሀገራት ወደ ብሔርተኝነት ዛጎል / ሼል / ተጠቀለሉ:: በዚህ የተነሳ የመንግሥት ፣ የኩባንያዎችና የዕምነት ተቋማት አሠራርና አደረጃጀት እንደ አዲስ ተበየነ:: የቅድመ ኮቪድ – 19 ዓለም ላትመለስ ተሸኘች:: የድህረ ወረርሽኟ ዓለም ገና ለአቅመ ትንባይ ባትበቃም ፍጹም የመቀየሯ ነገር የማይቀር ይመስላል:: ግና ካሁኑ መለዋወጥ ፣ መቀያየርና መገለባበጥ ከጀመሩ ሁነቶች አንዱ ምርጫ ነው::
ከ50 በላይ የአካባቢ ፣ የማሟያና ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን ጨምሮ ሕዝበ ውሳኔዎች ለሌላ ጊዜ ተራዝመዋል:: ለዚህም በሕገ መንግሥት የተደነገጉ አንቀጾችን እንዳለ የተጠቀሙ ፣ ማሻሻያ ያደረጉና ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ መስጠትን የመረጡ አሉ:: ይህን ሲያደርጉ ከተቃዋሚዎች ፣ ከልሒቃኖችና ከሚዲያዎች የተነሳ አቧራ ፣ የተደገሰ ቀውስ ፣ ክተት የተባለ አዋጅና ለጦርነት የተጎሰመ ነጋሪት የለም:: ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ አልተሟረተም:: የሽግግር መንግሥት ይቋቋም አልተባለም:: ወይም ብቸኛው የማርያም መንገድ ፖለቲካዊ መፍትሔ ነው ተብሎ አልተለፈለፈም::
ፓርቲ ፣ ስልጣን ፣ የግል ፍላጎትና የፖለቲካ ልዩነት ከሀገርና ከሕዝብ ህልውና ስለማይበልጥ:: በሀገርና በሕዝብ ህልውና ላይ አደጋ ተደቅኗል ተብሎም ሕገ መንግሥታዊነት ፣ የሕዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትነና ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ እሱን ተከትሎ ያሉ የሕግ ተዋረዶች / ሀይራርኪ ኦፍ ሎዎ / አይጣስም:: ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ጥናት አካሂዶና ከተቃዋሚዎች ጋር ከአንድም ሁለት ጊዜ ከመከረና ከዘከረ በኋላ በኮቪድ – 19 ምክንያት ለነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞለት የነበረውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳቡን ያሳወቀው:: ምክር ቤቱም ግራ ቀኙን ካስተነተነና ከመረመረ በኋላ የውሳኔ ሃሳቡ አጽድቋል:: የኢፌዴሪ መንግሥት ሦስት የተለያዩ፣ ገለልተኛና በጥናት ሒደቱ ያልተገናኙ ቡድኖችን ለይቶ ባስጠናው ጥናት ከፍ ብዬ የዘረዘርኋቸውን የመፍትሔ ሃሳቦችን ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ:: ምክር ቤቱም ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ የሚለውን መርጦ ለውሳኔ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ላከ::
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ እንዲሰጥበት ለይቶ ያቀረበው ጥያቄ ፤ ” የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል? ለሚሉት ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱ ምላሽ አለመስጠቱ የገጠመንን ችግር በመፍታት ረገድ ክፍተት አለበት የሚያስብል ነው:: በመሆኑም ከፍ ብሎ የተጠቀሱት የሕግ መንግሥቱ ድንጋጌዎች (አንቀጽ 54(1)፣ አንቀጽ 58(3) እና አንቀጽ 93 ከሕገ መንግሥቱ ዓላማና ግቦች እንዲሁም መሠረታዊ መርሆዎች ጋር በማስተሳሰርና በማገናዝብ ትርጉም እንዲሰጣቸው ፤ ” የሚል ነው ::
የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔውም ጥያቄው ትርጉም ያስፈልገዋል? ወይስ አያስፈልገውም? የሚለውን የሚዳስስና መደበኛ የጥናት አካሄድን በተከተለ አግባብ በአማርኛ የተዘጋጀ ጽሑፍ በባለሙያዎች እንዲቀርብ በደብዳቤው ጠይቋል:: በዚህ መሰረት በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ያሉ 2ኛና 3ኛ ዲግሪአቸውን ሕገ መንግሥት ላይ የሠሩ መምህራን፣ ጸሐፍት ፣ ተመራማሪዎችና አንሰላሳዮች ፤ የሕግ ባለሙያና የጠበቃዎች ማህበራት መፍትሔ ያሉትን ሃሳብ በጽሑፍ ከማቅረባቸው በላይ ባለፈው ቅዳሜና ትላንት ሰኞ የመጀመሪያውን ምዕራፍ የመሰማማትሒደት/ሒሪንግ /በአብዛኛውየኤሌክትሮኒክስና ማህበራዊሚዲያዎችበቀጥታ ለሕዝብተሰራጭቷል::ይህ በዘመናዊዋ ኢትዮጵያ የፍትሕና የሀገረ መንግሥት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ፋና ወጊ ሊባል የሚችል ነው::
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራውን የለውጥ ኃይል ከምደግፍበት 1 ሺህ 1 ምክንያቶች አንዱ በፍትሕ ተቋማት አሠራርና አደረጃጀት ላይ እየመጣ ያለ ለውጥ ነው:: ይህን ስል ሁሉም የተሟላ ነው ለማለት ሳይሆን የተቋማት ግንባታው በአስተማማኝ ጽኑ መሰረት ላይ እየተገነባ መሆኑን ለመግለጽ ነው::
ቅዳሜ ዕለት ከሸራተን አዲስ በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው ሰብሳቢ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዐዛ አሸናፊ በመሩት የመስማት ስነ ስርዓት ላይ የተናገሩት ከፍ ብዬ የጠቀስኋቸው ልሒቃን በኮቪድ – 19 ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው በመራዘሙና አሁን ሥራ ላይ ያለው መንግሥት ዘመን በወሩ የመጨረሻ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም ስለሚያበቃ የስልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር እና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ለዚህ መፍትሔ የሚሆን ግልጽ ድንጋጌ ስለሌለ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ መቅረቡ ሕገ መንግሥታዊነትን ያረጋገጠ ከመሆኑ ባሻገር የሕዝብን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ያጸና ነው ሲሉ እማኝነታቸውን ገልጸዋል::
በወረርሽኙ ሳቢያ ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት የተፈጠረባቸው ሌሎች ሀገራትም በተመሳሳይ ሁኔታ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ማንሳታቸው ተመልክቷል:: ትርጓሜ በመስጠት ሒደት ግን የሕገ መንግሥቱን አጠቃላይ አውድ በመመርመር እንጂ የትርጓሜ ጥያቄ የቀረበባቸውን አንቀጾች ብቻ ነጥሎ ለመመልከት መሞከር የተሟላ ውሳኔ ላይ አያደርስም ሲሉ አሳስበዋል:: እንዲሁም ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁ ሰዎችን ሃሳብ ከራሳቸውና በወቅቱ ከተያዙ ቃለ ጉባኤዎች መረዳት አስፈላጊ እንደሆነና በመጨረሻም ጉባኤው የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ ሌላ ክፍተት፤ ከፍ ሲልም ቀውስ ሊፈጥር ስለሚችል ያለቀለት ውሳኔን ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ተጠቁሟል::
ስለዚህ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ድረስ የተመጣበት ሒደትም ሆነ ከሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው የትርጓሜ ውሳኔ በኋላ የሚከተለው መንግሥታዊም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ አግባብ ሕገ መንግሥታዊነትን ያረጋገጠ ሰላማዊና ሕጋዊ ሒደት ነው:: ከጅምሩ የስልጣን ጥመኞችና የቆረጣ ፖለቲካ ተስፈኞች አበክረው እንዳሟረቱት የተፈጠረ ሕገ መንግሥታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ የለም:: ከዚህ አልፎ እንደ ሀገር የሕገ መንግሥታዊ ሒደቱም ሆነ የትርጓሜው አካሄድ ግልጽነት ፣ ተጠያቂነትና አሳታፊነት የተረጋገጠበትና ትልቅ ልምድ የተቀመረበት ነው ማለት ይቻላል::
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ ይጠብቅ! አሜን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)