ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከተመሰረተች እነሆ በቅጡ የማይታወቁ በሺዎች የሚቆጠሩ (ግማሹ 3 ሺህ ግማሹ 2 ሺህ ሌላው ደግሞ 6ሺህ አመታትን ይቆጥራሉ) ምእተ አመታትን አስቆጥራለች። በነዚህ ዓመታቶች የተበታተኑ መዋቅራዊ ሂደቶች፣ ለጠላት በር ከፍቶ ጠላት ከገባ በኋላ በመደራጀትም ይሁን በመደናገጥ የውጪ ወራሪዎችን ድል ነስተናል። እንደ ህዝብ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በብዙ ነገሮች ስምምነት ቢኖረንም በአንዳንድ ጉዳዮች ስምምነት ስለሌለን ብቻ የኛ የሆኑ ብዙ ነገሮቻችንን አሳልፈን ለሌሎች ሰጥተናል፣ የኛ ያልሆኑ ነገሮችን በእብሪትና በጉልበት ወርሰናል።
ለምሳሌ ባነሳው የምህንድስናና የስነቅርስ እንዲሁም ስነ ቅርፃቅርፅ ላይ ያለን ግጭት ጉልበታችንን እና ጥረታችንን ለሌሎች አሳልፈን በመስጠት ስንነታረክ ከርመናል። የአክሱምን ሀውልት፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት ማነው የሰራው ብለህ ስትጠይቅ ግሪኮች ናቸው፤ አረቦች ናቸው፤ ቱርኮች ናቸው እና የመሳሰሉ የራስን ታሪክ አሳልፎ በደግነትም ይሁን በዳተኝነት ለሌሎች መስጠት እንደምሳሌ ማንሳቱ በቂ ነው፡፡ የጀጎል ግንብ አመጣጥ ሲነሳ የሀረር አሚሮችን ዋጋ እንደመስጠት ሙሉ በሙሉ ለቱርኮች ጠቅልሎ ማስረከብ የተለመደ ነገር ነው፡፡
በሀገራችን የታሪክ አጻጻፍ ውስጥ ከፍተኛ የሚዛን መዛባት ስለነበረና ስላለ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ እንደውም ለዚች ሀገር እንደ ሀገር መቀጠል ምክንያት የሆኑ ብዙ ብሄሮች በቁማቸው እስከነ ገድላቸው ተቀብረዋል፡፡ በርግጥ ታሪካችንን የሚሰንድ የምሁራን መዳራሻ አልነበረንም፤ መጻፍና ማንበብ ከጀመርን ወዲህ ደግሞ እውቀትን የመቆጣጠር ወይም ሞኖፖሊ ኦፍ ኖውሌጅ እንደነበር ይነገራል፡፡ በርግጥ አሁን ያለችንን ቁንጽል የታሪክ ማህደር ያለ ቤተ-ክርስቲያን አይታሰብም ነበር ስለሆነም የአንበሳውን ድርሻ ትይዛለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እስከ ችግሮቿ ባትኖር ኖሮ ሀገራችን ምን እንደነበረች እንኳን በቅጡ ለመገንዘብ ይቸግረን ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ብዙም አሻሚ አይደለም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እራሷ ተዋህዶ እስከሆነችበት ጊዜ ድረስ በፖለቲካ የተወጠረች ስለነበር ሃይማኖታዊ ቀኖናዋን እንኳን በቅጡ እንድትፈፅም እድል አልሰጧትም ነበር። ከተዋሀደችም ቦኋላ ፅፋ ያስረከበችን ነገሮች አሁንም ከፖለቲካው ጫና ያልወጣ ነበር።
የህዝብን ታሪክ እንደመፃፍ የግለሰብ ታሪኮችን፣ መዋእለ ነገስታትን ማለቴ ነው እንድትጽፍ ተገዳለች። በተወሰነ መልኩ ደግሞ የፖለቲካው ማዕከል ስለነበረች፤ አንድ አንዶች” በማዛባቱ “ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አላት ብለው ይከሷታል፡፡ ያም ሆኖ ግን አስተምራለችና ይህም ትልቅ ነገር ነውና ልትመሰገን ይገባል።
በርግጥ ይህ ሁሉ እውቀትን በበላይነት የመቆጣጠር ስራ ሲሰራ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከቀለም ትምህርት ጾሙን እንዳያድር አረብኛ የማይተካ ሚና ነበረው፡፡ በተለይ በወሎና በምስራቁ የሀገራችን ክፍሎች በደጋው የማይታወቁ ወይም በትንሹ የተቀመሱ ጽንሰ ሀሳቦች እንደ ፍቅህ ወይም ህግ፤ ባይዕ ወይም ግዢና ሽያጭ፤ ኢኮኖሚክስ፤ የህክምና ጽንሰ ሀሳቦች፤ የአለም ታሪክ በተለይ ደግሞ የኢስላሙ አለም የፖለቲካና የሃይማኖታዊ ብሎም የማህበራዊ ታሪኮች በመድረሳዎችና በከለዋች እና ዛውያዎች በሚገባ በለውህ እና በሌሎች መሳሪያዎች ተሰንዷል ቁርዓን እና ሀዲስ ተሸምድዷል። ሆኖም ትኩረታቸው የንግድና ሃይማኖት አካሄዶች ላይ ብቻ የተገደበ ስለነበር የፖለቲካ ጫናው ብዙም አልነበረም በተለይ ከ13ኛው ክ/ዘ ወዲህ ከፖለቲካ ነጻ ነበር፡፡
ይህን ያክል ቤተ እምነቶቹን ካመሰገንኳቸው ዘንዳ ወደ ቀጣዩ ዋና ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ከላይ የተመለከትናቸው አራማባና ቆቦ የሆኑ ጉዳዮች ማለትም የእምነቱ፣ የታሪኩ፣ የፖለቲካውና ማህበራዊው ብሎም መዋእለንዋያዊው ጉዳዮች ለምን አስፈለገ አንዱን ማድማት አይሻልም ነበር እንዴ የሚል ትክክለኛ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ይህ ለኔም ጥያቄ ስለሆነ አልመልሰውም ግን አንድ መልስ መሳይ መልስ አለኝ።
አሁንም በዚሁ ዝቅጠት ውስጥ ስላለን ያለፍንበት ሆኖ ለታሪክ ጸሃፍት ብቻ የሚተው ሳይሆን ማደግ በነበረብን ልክ ማደግ ባላመቻላችን፣ አንድን አመት እንደ ህዝብ አንድ ሺህ ጊዜ እየኖርን ስለ ሆነ እና የተለያዩ ሺህ አመታትን ስላባከንን፣ ሕዝባችን ተመሳሳይ የረሃብና የእርዛት ዘመናትን እየደጋገመ በርሃብ ጠኔ እየተቆላ ምርትና ምርታማነትን እንደማሳደግ፣ ጥሩ የሆነውን ታሪካችንን ወስደን ከመጥፎው እየተማርን እንደ ህዝብ እና እንደ ሀገር ማለፍ ሲገባን የሄደውም የመጣውም የሚያስበው ሥልጣን ብቻ መሆኑን በተመለከተ በትንሹ ላስታውስ፡፡
ይህን የማደርገውም ሁሉም የራሱን ድርሻ በማበርከት ሳይመሽብን በተባበረና በተጋገዘ እጅ የበኩሉን እንዲወጣ ለማመላከት ያክል ሲሆን የማያስማሙን ነገሮች እንዳሉ ሁሌም ማስታወስ፤ ነገር ግን አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ሚዛን የሚደፉ መሆናቸውንም ለማስገንዘብ ያክል ይረዳኝ ዘንድ ነው፡፡ እነዚህ እንደ ቀላል ነገር የምናያቸው ነገሮች ተዳምረው በአግባቡ መጠቀም ባላመቻላችን እና ትምህርት አለመውሰዳችን አንዱም አንዳችን ለሌላቸውን እውቅናን መስጠት ስላልቻልን አሁንም ምንዥላቶቻችን በተጋደሉት ጉዳዮች ላይ ነን ‹‹የሃውልት ይነቀል ሃውልት ይተከል›› ትውልድ አሁንም ይችን ሀገር ለሌላ አደጋ እንዳያጋልጣት የሚል ስጋት አለኝ፡፡
ለዚህ ሁሉ ሀገራዊ ውጣውረዶች መነሻው ታሪካችን በተለይ የፖለቲካ ታሪካችን ነው የሚል እምነት አለኝ። ዘመናዊው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አራት ዋና ዋና ደረጃዎችን አልፏል ማለት ይከብደኛል። ምክንያቱም እየተደጋገሙ ስላሉ። እነዚህን ዘመናት በቅደም ተከተል ሳይሆን በዘፈቀደ ባጭሩ እንደሚከተለው አቀርባለሁኝ።
አንደኛው ዘመነ መሳፍንት ሲሆን በዚህ ጊዜ ሀገሪቱ በነዚህ መሳፍንት የስልጣን ጥማት የተነሳ መቶ አመታትን ወደ ኋላ ተሽከርክራ ለቀጣዮቹ ፖለቲከኞች ከባድ የቤት ስራ ሆናለች። አሁንም የዘመነ መሳፍንት አይነት አዝማሚያዎች በየሰፈሩ እየተስተዋሉ እናያለን።
ሁለተኛው የነገስታት ዘመን ነው፡፡ ይህም ዘመን እንደ ዘመነ መሳፍንቱ ሁሉ ከፍተኛ ውዝግብ የነበረበትና የሸዋ፣ የአዳል፣ የጎዣም፣ የጅማ፣ የትግራይ እና ሌሎች አካባቢዎች መካከል ግጭት እና ግጭት የተስተዋለበት ዘመን ነው። እንደ ሀገር አሁንም ከዚህ ያተረፍነው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ሶስተኛው የንጉስ ነገስታት ወቅት ሲሆን ይህ ‹‹የገብር አልገብርም›› ፍጥጫ የበዛበት፣ ህዝቡ ማንነቱን ያጣበትና የተወዛገበበት ወቅት ነበር። በዚህ ዘመን ከሌሎቹ ዘመናት በተለየ መልኩ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንደ ሌሎቹ ሀገራት ሁሉ በውድም ይሁን በግድ ቅርፅ የያዘችበትና ሁላችንም ተቀብለን መኖር የጀመርንበት ዘመን ነው። ( ያልተቀበሉ እንዳሉ ልብ ይለዋል) ይህ እንደ ህዝብና ሀገር ከፍተኛ የሽግግር ወቅት /turning point/ነው።
በዚህ ዘመን እንደ ሀገር በአለም ላይ ገናና ድሎችን አስመዝግበናል፣ ዓለም አውቆናል ብቻ ሳይሆን የውስጥ ልዩነቶቻችን ሳይበግሩን ለዓለም ህዝብ አንድነትን አስተምረናል። ወደ ሀገር ውስጥ ስንመለስ ግን አብዛኛው በዓለም ህዝብ ዘንድ የምንታወቅባቸው ጉዳዮች በአስመሳይነት የተሞሉ እኛ ራሳችን እንደ ህዝብ ያልተስማማንባቸው ነገሮች ናቸው። በዚህ ዘመን የህዝቦች ማንነት ጠፍቷል፣ ከፍተኛ የመሬት ወረራዎችና መስፋፋቶች ተደርገዋል፤ ባህልና ቋንቋዎች ተጨፍልቀዋል፤ ዕምነቶች ለመቀጫ መነሻ ምክንያት ሆነዋል። ከባባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች /GRAND VIOLATION OF HUMAN RIGHTS/ ተካሄዷል።
የመጨረሻው የደርግን አምባገነን ጨምሮ አሁን እስካለንበት «የብልፅግና» ዘመን ድረስ ያለው ነው። ይህ ዘመን ከሌሎቹ የሚለይበት እጅግ ብዙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አሉት። ከእነዚህም አንዱ ‹የመድብለ ፓርቲ› ስርዓት ሲሆን ሌላው በየጊዜው ምርጫ ማካሄድ ነው (አምባገነንም ቢሆን)። እነዚህ ሁለቱ ኩነቶች የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ቁልፍ ጉዳዮች ከመሆናቸውም ባሻገር የሀገርና የህዝብን ቀጣይ ዕጣ ፈንታን የሚወስኑ ነገሮች ናቸው። በሀገራችን የ2012ቱን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ብዙ አስተያየቶች፣ ውዝግቦችና ትንታኔዎች፣ ብሎም ግርግሮች እየተፈጠሩ ነው። እየተደረገ ያለውን ወከባና ሁካታን ስንመለከት አሁንም እንደወትሮው የሀገራችን ፖለቲካ ከፍተኛ የስልጣን ጥማት፣ ለወንበር እንጂ ለህዝብ የተዘጋጀ ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን። ይህን ደፍሬ እንድናገር የሚያደርጉኝ ብዙ ምክንያቶች አሉኝ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የአዳም ዘር ፍሬዎችን ፈጅቶ በሚሊዮኖች ያሚቆጠሩትን ደግሞ ለሞት ኮንትራት በተፈራረመበት በዚህ ወቅት በተለይ የፖለቲካው ልሂቃን የሚያደርጉት ትርጉም አልባ እና መርህ የለሽ ክርክር ሀገራችንና ሕዝባችንን የማይችሉት ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ከፍተኛ ስጋት አለኝ። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ወንበር ላይ ‹‹ፊጥ›› ለማለት ሩጫ በፍፁም ያልተገባ ነው የሚል እምነት አለኝ። ሀገር ለመለወጥና የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል በመጀመሪያ በምክንያትና በአመክንዮ ተነጋግሮ መተማመንና መስማማት ይቀድማል፡፡
ምርጫን ተወዳድሮ ለማሸነፍ ሳይሆን ተወነጃጅሎ ለማሸነፍ የሚደረገው ጥረት ‹ሲሉ ሰምታ ዶሮ ታንቃ ሞተች› እንዲሉ የሌሎች ሀገራት ፖለቲከኞች የሚያደርጉትን ብሽሽቅ ወደ ሀገራችን ለማምጣት መሞከር በእውነቱ የህዝባችን ችግር አልገባንም ማለት ነው ያስብላል። በቀን ሶስቴ በልቶ የማያድረውን ህዝብ እርሻህን ትተህ ወሬ ፈትል እኔን ደግፍ እኔን ተንከባከበኝ፣ ሀሳብህን ትተህ እኔ በቀደድኩልህ ቦይ እንደ ጅረት ፍሰስ ማለት በራሱ ጉድ ነው።
በፖለቲካው አለም የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ለመንግስትና ህዝብ ትልቅ ግብዓት ይሆናሉ። የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል ጥረት ያደርጋሉ። የፖሊሲ ክፍተቶችን ይከታተላሉ አመላካች አቅጣጫዎችን ይጠቁማሉ። መንግስት ጥሩ ሲሰራ የማመስገን አፋቸው አይታሰርም መንግስት ሲያጠፋም አፋቸው በትንሽ የግል ጥቅም አይሎገምም፡፡ ይህ በኛ ቤት ሲታይ ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ሀገሪቱ ሀላፊነት የሚሰማው መንግስት ይኑራት፤ በበሽታው ላይ የእጅ የበላይነት ይኑረን ከዚያ ወደ ምርጫና ስልጣን እንመጣለን የምርጫና ፓርቲዎች ጉዳይ ዝርዝሩን በሌላ ጽሁፍ ሌላ ጊዜ እመለስበታለው፡፡
አቶ ሙሳ አደም በጅግጂጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሰተኛ ዲግሪ ተማሪም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በሰብሳቢነት እየመሩ ያሉ ሰው ሲሆኑ የአፋር ህዝብ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ክፍል ሀላፊ በመሆንም ያገለግላሉ፡፡ ለማንኛውም አስተያየት በኢሜይል አድራሻ mussaadem83@gmail.com በኩል ማቀበል ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2012
ሙሳ አደም