መስማሚያ ጥቁምታዎች፤
አሃዱ፡- ወፈፍተኝነትን ከምን አንጻር?
በጸሐፊውና በአንባብያን መካከል የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንዲረዳ በርዕሱ ውስጥ የተጠቀሱትን ግር የሚያሰኙ አንዳንድ ሃሳቦች ቀድሜ በአጭሩ ላብራራና ላስተዋወቅ:: “ወፈፌ” የሚለውን ቃል በሀገራችን የትኛውም ክፍል ነዋሪ የሆነ ዜጋ በቋንቋው ውስጥ ጽንሰ ሃሳቡን ስለሚያገኘው እንግዳ አይሆንበትም:: የተለያዩ የአማርኛ መዛግብተ ቃላት “ወፈፌና ወፈፍተኛ” ለሚሉት ቃላት የሚከተሉትን ፍቺዎች ሰጥተዋል:: “እብድ፣ ቀዥቃዣ፣ ንክ፣ ሙር፣ ግልፍተኛ፣ አለምክንያት የሚቆጣ፣ ምክንያት የለሽ ተሟጋች ወዘተ…”::
በጥንታዊ የሀገራችን ጽሑፎችና በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ወፈፍተኛነት የሚገለጸው “የጨረቃ በሽታ” እየተባለ ነው:: የባእዱ እንግሊዘኛ Lunatic ይለዋል:: ሲተነትነውም “a person who is seen as mentally ill, dangerous, foolish, or crazy” በማለት ያብራራዋል:: ጥሩ ትርጉም ይመስለኛል::
የጥንት ሰዎች ለበሽታው መቀስቀስ ምክንያት እንደሆነ ሲገልፁ የኖሩት ከጨረቃ ጋር አያይዘው “moonstruck” በማለት ነበር:: በእኛ ቋንቋ ጥሬ ፍች እንስጠው ካልን “የጨረቃ ምች” ልንለው እንችላለን:: አርስጣጣሊስን የመሳሰሉ ጥንታዊ ፈላስፎችና የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ስለ በሽታው የሚሰጡት ትንታኔ ከሙሉ ጨረቃና ከሁለቱ ፕላኔቶች (ማርስና ሳተርን) ጋር ትይዩነታቸውን እያነጻጸሩ በመግለጽ ነው::
በዘመናዊ የአእምሮ ሕክምና ወፈፌነት የአእምሮ መቃወስ ህመም ሲሆን በበሽተኛው ላይ የሚታዩ የህመሙ ምልክቶች ከስምንት በላይ እንደሆኑ በጥናት ተረጋግጧል:: ጉዳዩ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በስፋት የማይተነተነው ቦታው ስላልሆነ ነው:: እንዲያው በጥቅሉ ወፈፌነት የአእምሮ መቃወስ ህመም ብቻ ሳይሆን “አውቆ አበድነትንም” ይጠቀልላል::
ክሌእቱ፡- ተስፈንጣሪ ፖለቲካዊ ወፈፌነት (Lunatic fringe)
እንደ እ.ኤ.አ በ1913 ዓ.ም ይህንን ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቁት ሃያ ስድስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት (ከ1901-1909) ቴዮዶር ሩዝቬልት ነበሩ:: እኒህ ሪፐብሊካን ፕሬዚዳንት ይህንን ጽንሰ ሃሳብ የተጠቀሙት የፖለቲካ ጽንፈኝነትን፣ አክራሪነትን፣ ኢምክንያታዊ አመለካከት የሚያራምዱትንና በፖለቲካ አቋማቸው ዥዋዥዌ የሚጫወቱ ግለሰቦችንና በቡድን የተደራጁ “የፖለቲካ ወፈፌዎችን” ለመግለጽ ነበር:: እንደ እነዚህ ዓይነት “መረን ለቀቅ” ፖለቲከኞች የአንድ ሀገር ፖለቲካዊ ሽክርክሪት ሰላማዊ ምህዋሩን ሳይስት እንዲጓዝ ስለማይፈልጉ ምክንያትና ሰበብ እየፈለጉ ወጀብና ነውጥ እንዲነሳ ባለመታከት እንደሚሰሩም አበክረው ገልጸዋል::
ተስፈንጣሪ የፖለቲካ ወፈፌዎች በሰላማዊ የዴሞክራሲ ምህዋር ውስጥ ተሰልፈው ነጻና ምክንያታዊ ሃሳባቸውን ከመግለጽና በመርህ ከመመራት ይልቅ “አራምባና ቆቦ” በሚዘል ኢምክንያታዊ ሙግትና በወፈፍታ ድርጊት ማተራመስን ተቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ መንቀሳቀስን ይመርጣሉ:: የፖለቲካዊ ወፈፌነታቸው መገለጫ ይህ ብቻ ሳይሆን መልኩ ብዙ ነው:: ሲያሻቸው አቋማቸውን በብዕር ሳይሆን “በሰይፍ” ለማሳመን ይሞክራሉ:: ይህ አልሆን ሲላቸው ደግሞ “መያዢያ መጨበጫ” የሌላቸውን ፖለቲካዊ ሰበዞች እየመዘዙ ግራ የማጋባት ስልት ይጠቀማሉ::
በአጭሩ ፖለቲካዊ ወፈፌነት ያለ እውቀትና ያለ ቋሚ መርህ ወላዋይነት የሚስተዋልበት ዝብርቅርቅ አቋምን የመግለጽ ህመም ነው:: ሎርድ ሶፐር (Lord Soper – ከ1903-1998) የተባሉ እንግሊዛዊ ካህን እነዚህን መሰል ወፈፌ ፖለቲከኞችን የገለጹት “የውዝግብ ወዳጆች” (the fellowship of controversy) በማለት ነበር::
ሠልስቱ፡- ሃይድ ፓርክ (Hyde Park) – “የጤናማ ወፈፌነት መናፈሻ”
ወፈፌነትና ጤናማነት የሚቃረኑ ጽንሰ ሃሳቦች መሆናቸው አልጠፋኝም:: የትርጉማቸው የተደጋጋፊነት አያዎ (አይ+አዎ= አያዎ) አንድም “አይ” አንድም “አዎ” እንዴት እንደሚባል ወደፊት አብራራለሁ:: በዚህ ርእስ ሥር ለማሳየት የምሞክረው “ዱላ የሚያቀብለውን የወፈፌ ገላጋይ” ዓይነት ሳይሆን “የወፈፌነታቸውን ምክንያት” በሥርዓት ለመግለጽ የሚሞክሩ ግለሰቦችና ቡድኖች መዋያ የሆነን አንድ የነፃ ሃሳብ መግለጫ መስክና የመናፈሻ ስፍራ በማስተዋወቅ ይሆናል::
ይህ መስክ Hyde Park በመባል ይታወቃል:: የሚገኘውም በማዕከላዊ የሎንዶን ከተማ ውስጥ ሲሆን ከአራቱ ታላላቅ የነገሥታት የመናፈሻ መስክ (Royal Parks) አንዱና ግዙፉ መናፈሻ ነው:: መናፈሻውን ያቋቋሙት ሄኒሪ ስምንተኛ የተባሉት የታላቋ እንግሊዝ ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑ፤ ዘመኑም 1536 ዓ.ም ነበር:: በወቅቱ ፓርኩ የተቋቋመው ሺህ ዘመናትን ካስቆጠረው የነገሥታቱ ቤተክርስቲያን ይዞታ ከሆነው ከዌስትሚኒስትር አቤይ መሬት ላይ ተቆርሶ ነበር::
ፓርኩ የሚገኘው ከዝነኛውና ከጥንታዊው የእንግሊዝ ነገሥታት መንበረ ሥልጣን መገለጫ ከሆነው ከበኪንግሃም ቤተመንግሥት የቅርብ ርቀት ላይ ሲሆን፤ በዚሁ ግዙፍ ፓርክ ውስጥ ለነፃ ንግግር ማካሄጃ (Free speech) የተለየው ቦታ ደግሞ (Speakers’ Corner) በመባል ይታወቃል:: ለነፃ ንግግር በተለየው በዚህ የፓርኩ ክፍል ውስጥ ማን? በምን ርዕስ? ስለ ምን ተናገረ? ማንስ በማን ላይ ምን አስተያየት ሰጠ? እንዴትስ ይህንን ሊናገር ቻለ? ወዘተ… የሚል ሳንሱረኛ በግላጭም ሆነ በስውር መንግሥታዊ የስለላ ሥራ አያካሂድበትም:: ቦታው እውነተኛ የመናገር መብት የተከበረበት “የጤነኛ ወፈፌዎች” ጥግ ነው ማለት ይቻላል:: ስለዚህ ተናጋሪዎቹን “አይ ወፈፌዎች ናቸው” ብለን ብናስባቸውም ድርጊታቸው ግን በሕግና በሥርዓት የተቃኘ “አዎ” ይበል የሚያሰኝ መሆኑን እንረዳለን::
“አያዎ”ን በሚገባ ለማብራራት:: ማንም ሰው በሰላምና በመከባበር የራሱን አትሮኖስ ዘርግቶ ወይንም የግሉን ጊዜያዊ መድረክ መድርኮ ለአላፊ አግዳሚው “ሃሳቤን ስሙልኘ፣ አቋሜን እወቁልኝ፣ እምነቴን እመኑልኝ፣ በፍልስፍናዬ ተጠመቁ፣ ብሶቴን አድምጡልኝ፣ ለኡኡታዬ ጆሯችሁን አትንፈጉ፣ ሙዚቃዬን አዳምጡልኝ፣ ቀረርቶዬን አጣጥሙልኝ፣ ሥዕሌን አድንቁልኝ፣ ድርሰቴን አንብቡልኝ ወዘተ…” በማለት ድምፁን ጮክ ብሎ በሚያሰማበት ወቅት “ማን ፈቅዶልህ ባይ” ከልካይም ሆነ ተቆጪ አይኖርበትም:: ቅብዥርዥር የወፈፌ መዘላበድንም ይሁን ደርዝ ያለውን የጨዋ ንግግር ለማዳመጥ የፈለገ ሰው ቆም ብሎ ጆሮውን መስጠት ብቻ ነው:: ይህን መሰሉ መማጠን ቁብ የማይሰጠው ተመልካች ወይንም አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ካልመሰለው ጆሮውን እያራገፈ እንደዘበት ጉዞውን ይቀጥላል እንጂ ዞር ብሎ ትዕይንቱን ለማየት ጊዜ አይሰጥም::
ፈላስፋው፣ ሃይማኖተኛው፣ ምሁሩ፣ ነካ ያደረገው፣ ብሶቱ የገነፈለበት፣ ችግር የጠበሰው፣ ጥጋብ የቀበተተው፣ ደራሲው፣ ሙዚቀኛው፣ ተዋናዩ፣ ሠዓሊው፣ ጠበቃው፣ ሰካራሙ ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል በሃይድ ፓርክ ውስጥ በሚገኘው የነፃ መድረክ ላይ ቢፈነጭ ቢያቅራራ መብቱ ነው::
“ጩኸቴን ብትሰሙ ይሄው አቤት አቤት እላለሁ፣
በደል ደርሶብኝ እጮኻለሁ – ዝያለሁ”
እያለ ቢያንጎራጉርም ሆነ፤
“ጮኬ እንዳልናገር ድምጼ ይሰልላል፣
እንዲያው ዝምታዬ እያደር ይብሳል::
ማዘን መራራትን መቼ ይረዳሉ፣
የልቤን ስናገር ሁሉም ያፌዛሉ::
በማለት ከጥላሁን ገሠሠ የተዋሰውን ዜማ እያቅራራ ቢውል እንኳ ተተናኳይም ሆነ ልሰርህ ባይ የፀጥታ ሠራተኛ በዙሪያው ዝር አይልም:: እርግጥ ነው መብቱ ገደቡን ጥሶ የሌላን ሰው ክብር ልንካ ማለት በፍጹም የሚደፍሩት ድርጊት አይደለም:: የግለሰቦችን ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ የሚረግጥ “ዱታ ነኝ ባይ” እብሪተኛ ከተስተዋለና ለጸጥታው ክፍል ሪፖርት ከደረሰው ሕጉ በሚፈቅደው ሥርዓት ምላሽ መሰጠቱ የሚቀር አይደለም::
አርባዕቱ፡- ለሀገሬ የምመኘው “ የሃይድ ፓርክ” ዓይነት
በየዘመናቱ ሀገሬ የፖለቲካ ወፈፌዎች ድህነት አጥቅቷት አያውቅም:: ድፍረት ካልሆነ በስተቀር ምናልባትም በፖለቲካው ወፈፌነት ዓይነትና ብዛት በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ውስጥ ለመመዝገብ ብንወዳደር እጃችን እየተሳመ በአንደኝነት ሳይጨ በጨብልን የሚቀር አይመስለኝም:: ዞር ብለን ያለፉትን ስልሳ ዓመታት የታሪካችንን ገጾች ብናገላብጥ እንኳ በርካታ በወፈፌነት (Lunatic fringe) የተደመደሙ ክስተቶችን ለማስታወስ አንቸገርም:: ዛሬም ቢሆን የሀገራችንን አየር እየበከለ ያለው ከወፈፌ ፖለቲከኞች ነን ባዮች አንደበት እየወጣ የሚሰነፍጠው ትንፋግ ከማስነጠስ መቼ ፋታ እንደሚሰጠን ለመተንበይ ያዳግታል::
አንዳንድ “ፖለቲከኞቻችን” ትናንት ከተቸከሉበት ቦታ ሳይነቃነቁ እዚያው እንደቆሙ የዛሬን ጀንበር ወደ ኋላ ጎትተው ለመሳብ ሙከራ ሲያደርጉ እየታዘብን ነው:: የእነዚህ ወፈፌ “ፖለቲከኞች” ቋንቋ፣ አመለካከለት፣ የሙግት ዘዬ፣ ለበጣዊ ምጸታቸውና የጃኬታቸውን የቀለም ዓይነት እንኳ ሳይለውጡ እዚያው እንደነበሩ አሉ:: በእነርሱ ዐይን ትውልዱ የቀለለ ነው:: ቋንቋቸው በእኛ ጊዜ ሁሉ ቀረ ይሉት ዓይነት ነው:: ታሪካቸው በ“ታስሬና ተገርፌ” የደመቀ ነው:: ኑሯቸውና ያኗኗር ዘይቤያቸው “ያው በገሌ” ይሉት ዓይነት ነው:: የራሳቸውን ኑሮ እንኳን ለመለወጥ በስንፍናና በአቅም እጦት ሲማቅቁ ኖረው ሰበቡን “እንዲህ የሆንኩት ለሕዝቤ ዲሞክራሲ ስታገል ነው” በማለት ይሸነግሉናል፤ ሆ! እያልን ስንከተላቸውም በውስጣቸው እያፌዙ ዞር በማለት ምላሳቸውን ያወጡብናል:: እነዚህ ተቀዳሚ ደረጃ ላይ የሚቀመጡ ወፈፌ ፖለቲከኞች (Lunatic political personnel) የሚባሉ ዓይነቶች ናቸው::
አንዳንዶች ደግሞ በመሸ በነጋ ቁጥር በሥልጣን ቅዠት ባንነው እየተነሱ በቅዥብርብር አመለካከታቸው እንድንከተላቸው ሰማይ ይቧጥጣሉ:: አንዳንዶችም እንኳን ለእኛ ለተራ ዜጎች ቀርቶ ለራሳቸውም በማይገባቸው ምኞት ታብተው ሕዝቡ የእነርሱ እስረኛ እንዲሆን ይፈልጋሉ:: አንዳንዶች ከአንዱ ፓርቲ ወደ ሌላኛው ፓርቲ እየተገላበጡ በማረርና በማሳረር ተክነው የፖለቲካ ወፈፌነታቸውን የዕለት እንጀራ መሸመቻ አቁማዳ ሲያደርጉ ይስተዋላል:: ሁሉንም “አንዳንዶች” እንዘርዝር ብንል ተግባራቸው ያጥወለውለናል እንጂ ገበናቸው ደጅ ስለተሰጣ ገላልጦ ማየቱ የሚከብድ አይሆንም:: ነገራችንን በምሳሌ እናጎላምሰው::
አንድ፡- “መንበረ ሥልጣኑ ወደ እኔ ካልዞረ ሀገር “ሀገር አትሆንም”፤ ሕዝቡም ተረጋግቶ አይኖርም::” እያሉ በኢሕጋዊነት መንጨርጨርና ጦር ለመስበቅ ነጋሪት ማስጎሰም “የጸና ወፈፌነት” ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል?
ሁለት፡- በኮቪድ 19 ክፉ ወረርሽኝ ሰበብ “የፖለቲካውን የሥልጣን ማረጋገጫ ምርጫ ማራዘሚያ” በተመለከተ የሕግ ምሁራንና ተመራማሪዎች በሕገ መንግሥቱ አንቅፅ አተረጓጎም ላይ በንቃት እየተወያዩና እየተከራከሩ ወደ አንድ ሀገራዊ መግባባት ለመድረስ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት “የሽግግር መንግሥት ካልተቋቋመና ለእኛም ዳረጎታችን ካልተቆነጠረልን በስተቀር ሞተን እንገኛለን” ብሎ መወራጨትና የህሊናን ጨርቅ እስከ መጣል መድረስ “የከፋ ወፈፌነት” እንጂ ሌላ ምን ይባላል?
ሦስት፡- ለፌዴራልም ሆነ ለክልል ፓርቲነት ተገቢውን መስፈርት ማሟላት ተስኗቸው በምርጫ ቦርዱ “ቀይ ብዕር” የመሠረዝ ዱላ ሲሰነዘርባቸው “ኡ! ኡ! ያዙኝ ልቀቁኝ” ብሎ መንፈራገጥና አቅል መሳት የፖለቲካ ኤፕሊፕሲ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ወካይ ቃል መግለጽ እንደምን ይቻላል?
አራት፡- ሀገር በክፉ ቸነፈር መጠቃቷ ሳያንስ ማኅበራዊና ብሔራዊ መረጋጋት እንዳይኖር አቅዶ በመንቀሳቀስ ልማትን መቃወምና ሰላምን ለማናጋት ሕዝብን ወደ ከፋ ግጭት ለመግፋት መሞከር የጠገገው ቁስል እንዲያመረቅዝ በጨረቃ ብርሃን ሳይቀር ሤራ መጎንጎኑ የወፈፌነት ስብዕና (Lunatic personality) እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ ግራ መጋባቱን ሊያጦዙ የሚሞክሩ ግራ ገቦችን ለመቋቋም የሚቻለው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ከወፈፌ አንደበታቸውና ድርጊታቸው የሚወጣውን መርዝ በማምከንና ከእኩይ ድርጊታቸው ራስን በመጠበቅ እንደሆነ እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ ጸሐፊው አጥብቆ ያምናል:: ስለሆነም መንግሥት ጆሮ የሚሰጠውና የሚያደምጠው ከሆነ ጸሐፊው ዳግላስ አንድ የቢቸግር ምክረ ሃሳብ መለገስ ይወዳል::
ከአዲስ አበባ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች መካከል በሸራተን ሆቴል አካባቢ እየተገነባ ያለው የሕዝብ ፓርክ በጉጉት ከሚጠበቁትና በግዙፍነቱ ተስፋ ከተጣለባቸው ሀገራዊ ትሩፋቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታመናል:: በዚህ የሕዝብ መናፈሻ ፓርክ ውስጥ የፖለቲካ ወፈፌዎቻችን እንደ ሃይድ ፓርክ እንደፈለጉ የሚፈነጩበት “የነፃ ማበጃ” Speakers’ Corner ተወስኖ ቢዘጋጅላቸው ለእኛም ሆነ ለተከታዩ ትውልድም ትንሽ እረፍት አይሰጠንም ይሆን? ልክ የሎንዶኑ ሃይድ ፓርክ ለበኪንግሃም ቤተመንግሥት ቅርብ እንደሆነው ሁሉ የሸራተኑ የሕዝብ ፓርክም የፖለቲካ ወፈፌዎች ለሚያብዱለትና ለሚቋምጡለት የአራት ኪሎ ቤተመንግሥት በቅርብ ርቀት ላይ ስለሚገኝ ቢያንስ በዓይን ፍቅር እንኳ ወድቀው እፎይታ ሊያገኙ ስለሚችሉ ጉዳዩ አጥብቆ ቢታሰብበት አይከፋም::
ያለበለዚያ ግን ባገኙት ሚዲያ ሁሉ ብቅ እያሉ “ስመ ዲሞክራሲን በማመካኘት” በሕዝብ ቁስል ላይ ጥዝጣዜ በሚጨምር በወፈፍታ ድርጊታቸው ግራ እያጋቡ እንዳያደነቁሩን ለእኛ ለተራ ዜጎች ጥበቃ ሊደረግልን ይገባል:: ለመሆኑ ስለ ስንቱ አስበን እንዘልቀዋለን?
ኮቪድ 19 ከቤት ኮድኩዶ ቢያውለንም “ቀን እስኪያልፍ ያለፋል” በማለት ለመጽናናት እየሞከርን ነው:: ከወዲህ የህዳሴ ግድባችንን በክፉ የሚያዩ አይኖች እንዲታወሩና የሚመኩበት ጉልበታቸው ቄጤማ እንዲሆንና ትምክህታቸው እንዲመክን እንደየእምነታችን ፈጣሪን እየተማፀንን ከጉድለታችንም ለግድባችን ድጋፋችንን እያደረግን እንገኛለን:: ከወዲያ ነገን ስናስብ ድኅረ ኮሮና ምን ዓይነት ሀገራዊ ተስፋና ስጋት ይዞ ይመጣ ይሆን? እያልን መጨነቃችን አልቀረም:: ይህ ሁሉ ሸክም ሳያንሰን እንደምን አቅላቸውን በሳቱ ወፈፌ ፖለቲከኞች እየታመስን እንኑር::
መንግሥታችን ሆይ! ጆሮህ እንደኛ በተለያዩ ውጥረቶች “ጭው እንዳለብህ” ብንረዳም ከእነዚህ ወፈፌ ፖለቲከኞች ድርጊት ሳትታክት ዘብ እንድትቆምልን እንማጸናለን:: ከአሸባሪ ድርጊታቸውና ልፍለፋቸውም አደብ እንድታስገዛልን አቤት እንላለን:: “ዲሞክራሲን” ሰበብ እያደረጉ አያምሱን፤ ጤናችንንም አይግፈፉ:: ለመሆኑ በዚህ መዘዘኛ የቴክኖሎጂ የትስስር መረብ የሚረጨው የመርዝ ሽታ መንግሥትን አልሰነፈጠውም ይሆን? “ሆድ ይፍጀው!” ከማለት ውጭ ምን ማለት ይቻላል::
“ኧረ ምረር ምረር መረር እንደ ቅል፣
ስላልኮመጠጠ ስላልመረረ ነው ዱባ ሚቀቀል::” በማለት የሀገሬ ቀረርቶኛ አንጎራጎረ ይባላል:: ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)