በአገሪቱ ከሚገኙ እምነቶች መካከል የክርስትናና የእስልምና እምነቶች ቀደምትና ዳጎስ ያለ ታሪክ ያላቸው ናቸው። እምነቶቹ ወደ አገር ውስጥ ገብተው መስፋፋት ከጀመሩ አንስቶ በተለያየ ቦታ የእምነት ተቋማቶቻቸውን ገንብተዋል። በተለያዩ ጊዜያት የተገነቡት ማምለኪያ ቦታዎች ታሪካዊ በመሆናቸው በዓለም ቅርስነት እስከመመዝገብ ደርሰዋል። የማምለኪያ ስፍራዎቹና ግንባታዎቹ ሲሠሩ የራሳቸው የሆነ ምክንያት አላቸው። ቤተክርስትያንም ሆነ መስጂድ ሲታነጽ በዋናነት መሰረት የሚያደርጉት የእምነቱን አስተምሮ ነው።
የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያት ዘመን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑና ሌሎች ታሪካዊ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ክርስትና እምነት ሆኖ በኤጲስ ቆጶስ ደረጃ መመራት የጀመረው በአራተኛው ክፍለ ዘመን በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይተረካል። ይኸውም የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ አባ ፍሬሚናጦስን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አድርጎ የሾመው በዘመነ አብርሃና አፅብሃ ጊዜ እንደሆነ ነው የሚነገረው።
የቤተክርስትያን አስተናነጽን በተመለከተ በአገሪቱ የተለመዱና እንደ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም የማይነቀፉ ሦስት ዓይነት አሠራሮች አሉ። ዋሻ፣ ሰቀላማ (ምኵራብ) ቤተ ንጉሥ (ክብ) ናቸው። ዋሻ የሚባለው በሰው ሥራም ሆነ በተፈጥሮ የሚገኝ ሲሆን፣ ልክና መጠኑ እንዲህ ነው ተብሎ ላይነገር ይችላል። የውስጥ አሠራሩም ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ሁሉ ላያሟላም ይችላል። የተወሰደው ከአዳም ጀምሮ የተነሱ አበው እግዚአብሔርን ለማገልገል እንዲህ ዓይነት ቦታዎችን ይጠቀሙ ነበርና ከዚያ የተወረሰ ነው:: የዋሻ ቤተክርስቲያን አሠራር (በመጋረጃ የተከፈለ) ሲሆን፣ ራሱን ችሎ በዘመነ ሐዲስ መናንያን በበረሃ የሚገለገሉበት ቤተክርስትያን ነው።
የዋሻ ቤተክርስቲያን በሩ አንድ ብቻ ነው። ቅኔ ማህሌት ፣ ቅድስትና መቅደሱም የሚለየው በመጋረጃ ብቻ ነው። ቅዱስ ላሊበላ ያሠራቸው አብያተ ክርስቲያናት አንዳንዶቹ ዋሻዎች ናቸው። የዋሻ ቤተክርስቲያን ጉልላት የለውም የመቅደሱም በር አንድ ነው።
ሌላኛው የቤተክርስትያን አሠራር ሰቀላማ ቅርጽ ያለው ነው። የተወሰደውም ከጥንቱ የሙሴ ድንኳን ጀምሮ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ምኵራባትና እንዲሁም ከታላቁ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ነው። ቤተ ክርስቲያን በአራቱም የዓለም ማዕዘናት የምትሠራ መሆኑን ለመግለጥ ባለአራት ማዕዘን አድርገው ይሠሩት ነበር:: የአሠራሩ ይዘትን በተመለከተ የአራት ማዕዘን ቅርፅ (የምኩራብ ዓይነቱ) የተወረሠው ከአይሁድ ምኩራብና በዘመነ ክርስትናም የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት እሌኒ በኢየሩሳሌም ካሠራችው ቤተክርስቲያን የተቀዳ እንደሆነም ይነገራል።
ወደ ሦስተኛው የቤተ ክርስቲያን የአሠራር ዓይነት ስንመጣ ክብ (ቤተ ንጉሥ) ተብሎ ይጠራል:: በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በጣም የሚደገፈው የአሠራር ዓይነት ይህ ነው። ምክንያቱም ሦስቱንም ፆታ ምዕመናን(ካህናት፣ወንዶችና ሴቶች) በየነገዳቸው ለይቶ በማስቀመጡ ረገድ ከሦስቱም የቤተ ክርስቲያን ዓይነቶች የተሻለ ነው ተብሎ ይታሰባል። ክብ ቅርፅ ባለሦስት ዙሪያ ክፍል (ቤተ ንጉሥ) ዙሪያ ክብ አሠራር (ቤተንጉሥ) ውስጡ በሦስት ግድግዳ የተከፈለ ሲሆን፣ ስያሜው የተወረሰው ከግብሩ ከሚሰጠው አገልግሎት ነው። ሁለተኛው ቅርጽ ዙሪያው ክብ ነው። ቤተንጉሥ ቅርጽ ይባላል። በግድግዳ ከሦስት ይከፈላል። የመጀመሪያው ዙሪያ ቅኔ ማህሌት ይባላል። ሁለተኛው ቅድስት ይባላል። ሦስተኛው መቅደስ ይባላል።
እንደ ዜና መዋዕለ ነጋሽ ታሪክ ከሆነ፤ ከአረብ ምድር የመጡት 15 የአረብ እንግዶች እምነታቸውን በነፃነት ያመልኩ ዘንድ ፈቃድ የተሰጣቸው በ615 ዓ.ም ነው። ይህንንም ፈቃድ የሰጠውን ንጉሥ ለመዘከር አል ነጃሺ መስጂድ ተገነባ። መስጂድ ማለት የሰጋጆች ቦታ የሚለውን ለመግለጽ የተቀመጠ እንደሆነ ይነገራል። በተጨማሪም የእምነቱ ተከታዮች የሚሰባሰቡበት ቦታም ሊባል ይችላል። በእስልምና የተለያዩ የእምነቱ ስርዓቶች ያሉ ሲሆን፣ በተለይ በዓርብ ቀን ብዛት ያላቸው አማኞች ተሰባስበው አብረው የሚሰግዱበት ለአብነት ይጠቀሳል።
የመጀመሪያው መስጂድ ግንባታ ዲዛይን የተወሰደው በመዲና ከሚገኘው የነብዩ መሀመድ መኖሪያ ግቢ መሆኑ ይነገራል። የመስጂድ አሠራር በየጊዜው እየተቀያየረ የመጣ ሲሆን፣ አብዛኛው አሠራር ሰፊ ክፍት ቦታ ያለው፣ የተዘረጋ ጣሪያ ያለው፣ ምሂራብና ምንባር የያዘ እንዲሁም የፀሎት ማድረጊያ ማማ የተሠራለት ነው። ምሂራብ ግማሽ ክብ ሲሆን፣ ፀሎቱን የሚመራው ኢማም የሚቆምበት ስፍራ ነው።
የሚሂራብ አቅጣጫም ወደ መካ የሚያመለክት ነው። ምኒባር ደግሞ በሚራብ በቀኝ በኩል የሚገኝ ሲሆን፣ ፀሎትና ትምህርት የሚሰጥበት ስፍራ ነው። በቀድሞ ጊዜ የእስልምና መሪዎች ቆመው ንግግር የሚያደርጉት በሚንባር ነው። በተጨማሪም በሚራብ አቅራቢያ ማቁሱራህ የሚባል ሳጥን መሳይ ስክሪን ይገኛል። ይህ የሚያመለክተው ፈጣሪ ወይም አላህን ነው። ምንጣፍና መጋረጃዎች የመስጂዱ ወለል ላይ የሚነጠፉ ሲሆን፣ በፀሎትና በስግደት ወቅት የእምነቱ ተከታዮች ኢማሙን ተከትለው ስግደት ያከናውናሉ።
ምናሬት(ረጅም ማማ) የመስጂድ የዲዛይን አሠራር ሲሆን፣ ረጅም ማማ በመሥራት በቀን አምስት ጊዜ ጸሎት በሚደረግበት ወቅት ፀሎት የሚመራው ሰው የሚቆምበት ስፍራ ነው። ማማው ሁልጊዜ ከመስጂዱ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በተጨማሪም ክፍት የሆነ ቦታ ይተውለታል። ነበዩ መሀመድ የእምነቱን ተከታዮች ለፀሎት በጠሩበት ወቅት በመስጂድ ከፍታ ቦታ ላይ በተደረገ ፀሎት ነበር። የቀድሞ ፀሎት ማድረጊያ ማማ የሚገኘው በሰሜን አፍሪካ ቱኒዝያ ውስጥ ሲሆን፣ አል ቋይራዋን ይባላል። የተገነባውም እኤአ ከ724 እስከ 727 እንደሆነ ይገመታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
መርድ ክፍሉ