ከአዲስ አበባ ከተማ በመነሳት ወደ ምዕራቡ የአገሪቷ ክፍል ለሚደረገው ጉዞ እንደ መውጪያ በር ሆኖ ያገለግላል። ለበርካታ ጊዜያት አገልግሎት ሲሰጥ በመቆቱም እርጅና ተጫጭኖት ቆይቷል። ከሁለት ዓመት ተኩል ወዲህ ግን እንደ አዲስ እየተሠራ የሚገኝ ቢሆንም የተለያዩ ችግሮች አጋጥመውት በተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ አልቻለም – የሳንሱሲ ታጠቅ ኬላ የመንገድ ፕሮጀክት።
በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮንስትርክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት የሴንትራል ሪጅን ቡድን መሪ አቶ ብሩክ ተክሌ እንደሚገልጹት፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እያሠራቸው ካሉ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሳንሱሲ -ታጠቅ ኬላ የመንግድ ፕሮጀክት ሲሆን፣ ህዳር 6 ቀን 2010 ዓ.ም ሥራው በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ 13 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ አሰር የተሰኘ አገር በቀል የሥራ ተቋራጭ ሥራውን ተረክቦ እየሠራ ይገኛል። የማማከሩን ሥራ ደግሞ ሂተከንና አለርት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ በጣምራ እያከናወኑት ነው።
ፕሮጀክቱ ለሁለት ተከፍሎ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል። የመጀመሪያው ከሳንሱሲ ተነስቶ እስከ 7 ኪሎ ሜትር ያህል የሚደርሰው እና በከተማ የሚያስልፈው 32 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከሰባት ኪሎ ሜትር በኋላ እስከ 11 ኪሎ ሜትር ድረስ ያለው በገጠር የሚያልፈው መንገድ ደግሞ በ21 ሜትር ስፋት እየተሠራ ይገኛል።
ከ11 ኪሎሜትር እስከ መጨረሻው ማለትም እስከ 13 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ድረስ ያለው በከተማ የሚያልፈው መንገድ ደግሞ በ32 ሜትር ስፋት እየተሠራ ይገኛል። የመንገድ ፕሮጀክቱን ለማስፈፀምም በአጠቃላይ 820 ሚሊዮን ብር ተይዟል።
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ በህዳር ወር 2010 ዓ.ም ተጀምሮ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሠርቶ በማጠናቀቅ በተያዘው የግንቦት ወር ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው በነበረው የወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት በታቀደው ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ አልተቻለም። በዚህ ጊዜም የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 90 ከመቶ ይደርሳል ተብሎ የታሰብ የነበረ ቢሆንም እስከአሁን ባለው ሂደት ማከናወን የተቻለው 40 ከመቶ ያህሉን ብቻ ነው።
መንገዱ በሚሠራበት ወሰን ክልል ወስጥ በርካታ ሰው በጥግግት የሚኖርበት፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌና የውሃ መስመሮች የሚያልፉበት በመሆኑ እና ባለስልጣኑም መንገዱን ለግንባታ ነፃ ለማድረግ ለሚመለከታቸው ሁሉ አስፈላጊውን የካሳ ክፍያ በወቅቱ ቢፈፅምም በተለያዩ ችግሮች ምክንያትና የቴሌ፣ ኤሌክትሪክና የውሃ መስመሮች በወቅቱ ባለመነሳታቸው ፕሮጀክቱ በከፍተኛ ደረጃ ተጓቷል። በተጨማሪም የመስሪያ ቦታ አለማግኘት፣ ለግንብ ሥራ የሚሆን የድንጋይ ቦታ አለማግኘትና ሌሎችም ችግሮች ለፕሮጀክቱ መዘግየት የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም ከመንገዱ መነሻ እስከ 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ድረስ በመንገዱ ቀኝ ክፍል ወሰን ማስከበር ተችሏል። ይህንንም ተከትሎ እስከአሁን ባለው ሂደት መንገዱ አስፓልት ይለብሳል ተብሎ ታቅዶ ነበር። ሆኖም በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ሥራው ከአንድ ወር በላይ ዘግይቷል። የመንገድ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ሁለት ዓመት ተኩል የሞላው ቢሆንም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተሠሩ ሥራዎች አነስተኛ በመሆናቸው ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከተያዘለት ጊዜ በላይ እየፈጀ ይገኛል።
ቡድን መሪው እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት የመንገዱ አፈፃፀም 40 ከመቶ ደርሷል። ከኪሎ ሜትር 4 ነጥብ 5 ጀምሮ እስከመንገዱ መጨረሻ ማለትም እስከ ታጠቅ ኬላ ድረስ ከሞላ ጎደል የመንገዱ አንደኛው ጎን 9 ኪሎ ሜትር አስፓልት ማልበስ ተችሏል። የመንገድ ፕሮጀክቱ ትልቁ ሥራ የትቦ ቀበራ ሲሆን፣ በመንገዱ የቀኝ ክፍል 90 ከመቶ የትቦ ቀበራ ሥራ ተከናውኗል። ከዚህ በተጓዳኝም በመጋቢት ወር አካባቢ የቡራዩ ከተማ አስተዳደር በመንገዱ ክልል ውስጥ የነበሩ የኤሌክተሪክ፣ የውሃና የቴሌ መስመሮችን በማስነሳቱ ከፕሮጀክቱ መነሻ ጀምሮ 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ድረስ ያለውን የመንገዱን የቀኝ ክፍል ሥራ ተቋራጩ የትቦ ቀበራ ሥራውን ጨርሶ የአፈር ሙሌት ሥራውን ከሞላ ጎደል አጠናቋል። እስከአሁን ባለው ሂደትም የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ አፈፃፀምም 40 ከመቶ ደርሷል።
የመንገድ ፕሮጀክቱን ቀሪ ሥራዎች በሚመለከት ከአማካሪ ድርጅቱና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በርካታ ንግግሮች ተደርገዋል። ይሁንና በርካታ የአገልግሎት መስመሮች አሁንም በመንገዱ ክልል ውስጥ ያሉ በመሆናቸው የወሰን ማስከበር ሥራው ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። በተለይም ከመንገዱ መነሻ ጀምሮ እስከ 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ድረስ ባለው የግራው የመንገዱ ክፍል ውስጥ ምንም ዓይነት የወሰን ማስከበር ሥራ አልተሠራም።
በመሆኑም የቡራዩ ከተማ አስተዳደር በራሱ እቅድ መሰረት በመጪዎቹ ሁለትና ሦስት ወራት ውስጥ የወሰን ማስከበር ሥራዎችን አጠናቆ የሚያስረክብ ከሆነ ቀሪ ሥራዎች ከዓመት በላይ የማይወስዱ በመሆናቸው መንገዱን በቀጣዩ ዓመት ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እቅድ ተይዟል። ለዚህም የወሰን ማስከበር ሥራው ከሁሉም አካላት ጋር በተቀናጀ መልኩ መሠራት ይኖርበታል።
ቡድን መሪው እንደሚሉት፤ የሳንሱሲ -ታጠቅ ኬላ የመንገድ ፕሮጀክት የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት ቢሆንም የሥራ ተቋራጩ ጠንካራ ባይሆንና የነበሩ ችግሮችን መቋቋም ባይቻል ከዚህም በላይ ችግሮች ያጋጥሙና ፕሮጀክቱም ይዘገይ ነበር። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ አፈፃፀም በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝና የአስፓልት ሥራውም በጥራት እየተከናወነ ነው።
የቡራዩ መንገድ ቀደም ሲል በአገልግሎት ብዛት ያረጀና የተበላሸ፣ ህዝቡም በጣም የተቸገረበት፣ ለትራንስፖርትም አመቺ ያልሆነና አጭር መንገድ ሆኖ ረጅም ሰዓት የሚፈጅ መንገድ የነበር መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ የዚህ መንገድ በአዲስ መልክ መሠራት በተለይ ለቡራዩ ማህበረስብ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። በአካባቢው ላይም በርከት ያሉ ፋብሪካዎች የሚገኙ ከመሆናቸው አኳያ መንገዱን በመጠቀም ለኢኮኖሚው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያግዛል ተብሎ ይገመታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
አስናቀ ፀጋዬ