ሩዋንዳ (ኪኛሯን /እርጓንዳ/) ወይም በይፋ የሩዋንዳ ሪፐብሊክ በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የምትገኝ አገር ናት። ሩዋንዳ ከዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲ እና ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋር ድንበር ትጋራለች። በአገሩ ትልቁ ሃይማኖት ክርስትና ሲሆን፣ ዋናው ቋንቋ ኪኒያሩዋንዳ ነው።
ሩዋንዳ ባላት የተፈጥሮ ልምላሜና ውበት “የምድር ወገቧ ሲዊዘርላንድ” ሲያሰብላት ቆይቷል። አሁን ግን ስሟ ሲጠራ ፈጥኖ የሚታወሰው ከ800 ሺህ የማያንሱ ዜጐቿ በአጭር ጊዜ ያለቁበት የዘር ፍጅት በአሰቃቂ ገፅታው የታየባት አገር መሆኗ ነው። ለሶስት ወራት የዘለቀውና በአብዛኛው የቱትሲ ጐሣ አባላትና ለዘብተኛ ሁቱዎች የተጨፈጨፉበት መጠነ ሰፊ የዘር ፍጅት ነበር።
የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ሲሆኑ፣ ወደ ስልጣን የወጡት እ.ኤ.አ. በ2000 ላይ ነው። ሩዋንዳ በሙስና ረገድ ከአጎራባች አገራት የተሻለች ብትሆንም በሰብዓዊ መብት ረገጣ በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ትተቻለች።
‹‹እባክዎ የፕላስቲክ እቃ መያዣዎን አውሮፕላን ውስጥ እንዲተውት ይመክራሉ›› የሚለውን የካፕቴኑ (ፓይለቱ) ማስጠንቀቂያ ኪጋሊ መድረስዎን ያበስራል። ‹እንኳን ወደ ኪጋሊ ከተማ በሰላም መጡ› ከሚለው መልካም ምኞት መግለጫ ቀድሞና ጎልቶ የሚደመጠው እሱ ነው። ልመና፣ ወንጀል፣ የሱቅ በደረቴና የመንገድ ላይ ንግድ በኪጋሊ ውስጥ የማይታዩ ክስተቶች ናቸው።
የኪጋሊ ከተማ በካርታ ላይ በፍጥነት አይቶ ለመለየት ከሚቸግሩ ከተሞች ውስጥ ትመደባለች። ነገር ግን በሩዋንዳ ዋና ከተማነቷ ከፍተኛ እውቅና ያገኘች ከተማ ነች። ከ25 ዓመት በፊት የዘር ጭፍጨፋ ያስተናገደችው ከተማ በአሁኑ ወቅት ፊቷን ወደ ልማት አዙራለች። በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እቅድ መንደፍ፣ ቴክኖሎጂ ያረፈባቸው ግንባታዎች፣ የአየር ንብረት የሚጠብቁ ሥራዎችና ለቀጣይ ትውልድ የሚያገለግሉ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በኪጋሊ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚኖር ሲሆን፣ እኤአ 2024 በሶስት እጥፍ የህዝብ ቁጥሩ እንደሚጨምር ይጠበቃል። አብዛኛው ነዋሪ 25 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ሲሆኑ፣ የቀጣይ የእድገት ተሳታፊነታቸውን ለማጎልበት ተስፋ ተጥሎባቸዋል። በኪጋሊ ባህላዊ አስተሳሰቦች ተቀባይነታቸው እየቀነሰ የመጣ ሲሆን፣ በምትኩ ለውጥና ዘመናዊነት እየነገሰ መጥቷል። እኤአ 2001 እስከ 2015 የአገሪቱ ውስጥ የምርት እድገት (ጂዲፒ) በስምንት በመቶ እየጨመረ መጥቷል። እንዲሁም በአገሪቱ ፓርላማ የሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣትና የህፃናት ሞት መቀነስ አገሪቱን እየለወጣት ይገኛል።
የመሬት አቀማመጥ
የኪጋሊ ከተማ ግማሹ በተራሮች የተሸፈነና በውሃ የተከበበ በመሆኑ ለመኖሪያ የሚሆኑ ግንባታዎች ለመገንባት የግድ የፈጠራ ሥራዎች ያስፈልጓታል። እኤአ 2024 ድረስ ለማጠናቀቅ እቅድ በተያዘለት መሪ ፕላን መሰረት በከተማዋ ረጃጅም ህንጻዎች እየተገነቡ ይገኛሉ። መሪ ፕላኑ ኪጋሊ ከተማን ዘመናዊ ማድረግ የሚችል የመሰረተ ልማት ግንባታ አካቷል።
ንፁህና አረንጓዴ
ኪጋሊ ከአፍሪካ ከሚገኙ ከተሞች በንፅህናና ምንም አይነት አደጋ የማይከሰትባት ከተማ ስትሆን ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሁሉም ህብረተሰብ በወር አንዴ ከተማውን ያፀዳል። በፅዳት ዘመቻው ላይ ሁሉም ህዝብ የመሳተፍ ግዴታ አለበት። እኤአ 2008 ጀምሮ የላስቲክ እቃ መያዣዎች በከተማዋ ጥቅም ላይ ማዋል እንደማይቻል ከተነገረ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ መጥቷል። በሩዋንዳ አረንጓዴ ልማት ከተነደፈ በኋላም ኪጋሊ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ እየሰራች ባለችው ሥራ ከፍተኛ እውቅና ተችሯታል። የአረንጓዴ ልማትን የሚያሳየው ፓርክ በእኤአ 2018 ለህዝብ ክፍት መደረጉ ይታወሳል።
ትምህርትና ቴክኖሎጂ
ኪጋሊ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ የፈጠራ ሥራዎች የሚበዙባት ከተማ ነች። የሩዋንዳ መንግሥት እኤአ 2016 ጀምሮ የ‹4 ጂ ላይት› ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ሁሉም ዜጋ እንዲጠቀም አስችሏል። የዓለም ባንክ ባወጣው ዘገባ መሰረት፤ በአፍሪካ ከሚገኙ ከተሞች ኪጋሊ የንግድ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሁለተኛዋ ቀላል ከተማ መሆኗን ጠቅሷል። ኪጋሊን የፈጠራ ማዕከል የማድረግ ሥራው እስከተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይህ እንቅስቃሴ ሩዋንዳን በእውቀት ላይ የተመሰረተ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ያደርጋታል። የሩዋንዳ መንግሥት የያዘው የትምህርትና የቴክኖሎጂ ማስፋፋት ሥራ እኤአ 1994 የነበረውን አራት ሺህ የተማሪዎች ቁጥር እኤአ 2016 ላይ 86 ሺህ እንዲደርስ አድርጎታል።
የፈጠራ ሥራዎች ማዕከል
ማንኛውም ሰው የፈጠራ ሥራ ሲያከናውን ሰፋ ያለ ቦታና የሚሞክርበት ገንዘብ ያስፈልገዋል። ለዚህም በኪጋሊ እኤአ 2016 ላይ የፈጠራ ሥራዎች የሚከናወኑበት ማዕከል እንዲከፈት ተደርጓል። በዚህ ማዕከል አዳዲስ የፈጠራ ሀርድ ዌር ምርቶችና ኤሌክትሮኒክስ የሆኑ እቃዎች በሰዎች ተሰርተዋል። የዚህ ማዕከል ጠቀሜታ በሀርድዌርና በሶፍትዌር አዳዲስ ፈጠራ ያላቸው ሩዋንዳውያን ቦታ አግኝተው እንዲሰሩ አድርጓል። በተጨማሪም ሩዋንዳውያን የፈጠራ ሰዎች በዓለም እንዲታወቁም በር ከፍቷል።
የትራንስፖርት መሰረተ ልማት
በኪጋሊ በአብዛኛዎቹ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙት አውቶቡስ ነው። የከተማ አውቶቡሱ ብዙ ቦታዎች የሚያዳርስ በመሆኑ በውስጡ የዋይፋይ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጓል። እጅግ ፅዱ የሆነችው ኪጋሊ መንገዶቿ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት ከተሞች በትራፊክ መጨናነቅ የተወጠሩ አይደሉም። ብስክሌት ነጂዎች ሳይቀሩ ሄልሜት ኮፊያ እንዲያደርጉ ህጉ ያዛል። የትራፊክ ፍሰቱ ስርዓት ባለው መልኩ ሲፈስ ይታያል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
መርድ ክፍሉ