ወጣት ነስረዲን ጀማል፣ ተወልዶ ያደገው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስልጤ ዞን ሌራ አካባቢ በአያቱ ቤት ነው። ወጣቱ፣ በ2001 ዓ.ም የአራተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ አዲስ አበባ ሲገባ፤ ጫት ቤት የመሥራት ፍላጎት አልነበረውም። ነገር ግን አራት ኪሎ አካባቢ 12 ቀበሌ ጫት ይሸጡ የነበሩ አጎቱ ቤት በመቀመጡ፤ በማይፈልገው የአጎቱ የጫት ሥራ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ተገደደ።
አጎቱ የነስረዲንን ጉልበት ለመዱ። እንዲለያቸው አልፈቀዱም። ነስረዲን ግን አንድ ሰው አብዝቶ የመከረውን በማስተዋሉ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ፤ ‹‹ጫት ከሚሸጡም ሆነ ጫት ከሚቅሙ ሰዎች ካልራቅኩ ህይወቴ ሙሉ ለሙሉ ይበላሻል›› በማለት አጎቱ በሚሠሩበት በቅርብ ርቀት በእዚያው በአራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አካባቢ የሊስትሮ ዕቃዎችን ገዝቶ ጫማ መጥረግ ጀመረ። በዚህ ተግባሩ አጎቱ አኮረፉ። ቤታቸው አላሳድርም ከማለታቸው ባሻገር ‹‹ተመልሰህ ከኔ ጋር መሥራት አለብህ›› እያሉ ሲያገኙት እየደበደቡ፤ ማሰቃየት ጀመሩ። ወጣቱ ግን በዚያው በአራት ኪሎ አካባቢ ጫማ በመጥረግ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ።
ነስረዲንን የገፉት አጎቱ ትምህርት ለማስተማር እንኳ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እና ያለደመወዝ ማሠራታቸው እንዲሁም ሥራው ለተሻለ ህይወት ከማነሳሳት ይልቅ ቀጣይ ህይወቱንም የሚያበለሽ በመሆኑ የፈለገውን ዕርምጃ ሲወስድ ስለማደሪያው አላሰበም ነበር። በልጅነቱ ለብቻው ኑሮን ለመጋፈጥ የቆረጠው ነስረዲን፤ ህይወት እንደፈለጋት አልጋ በአልጋ አልሆነችለትም። ማደሪያ አጣ። ቤት ለመከራየት አቅሙ አልፈቀደም። ስለዚህ ማደሪያውን በረንዳ አድርጎ፤ ከአጎቱ ሸሽቶ ቦታ ቀይሮ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መዝናኛ ክበብ በር አካባቢ ተቀምጦ ጫማ ማሳመሩን ተያያዘው። የታክሲ ረዳቶች ተባብረውት ጎዳና ላይ ከእነርሱ ጋር በማደሩ ጓደኛ አፈራ።
በጫማ ጠረጋው እና በትህትናው ተወዳጅነትን ያተረፈው ነስረዲን፣ የአካባቢው ሰዎች ይደግፉታል። በቅርብ ርቀት ያሉ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትን የሚጠብቁ ፌዴራል ፖሊሶችም ጫማ እያስጠረጉ ያበረታቱታል። አጎትየው ግን እዚያ ድረስ እየመጡ የሚሠራበትን ዕቃ ሦስት ጊዜ አስዘረፉት። በመጨረሻ ሲደበድቡት የተመለከቱት ፌዴራል ፖሊሶች አጎትየውን ሁለተኛ ያንን እንዳያደርጉ አስጠንቅቀው ገላገሏቸው።
በጊዜው ምንም እንኳ ነስረዲን በረንዳ አዳሪ ቢሆንም የትምህርት ፍላጎት ስለነበረው ቀን ሊስትሮ እየሠራ ማታ እየተማረ ህይወቱን መግፋት ቀጠለ። ገንዘብ አጠራቅሞ ከታክሲ ረዳት ጓደኛው ጋር ለሁለት በ250 ብር ግንፍሌ አካባቢ በደባልነት ለመኖር ቤት ተከራየ። ከህይወት ጋር ግብ ግብ ቢገጥምም ለማሸነፍ የሚያደርገውን ትግል አከራዮቹ የበለጠ ፈታኝ አደረጉበት። አከራዮች ሳሎን እየኖሩ ነስረዲን እና ጓደኛው በደባልነት ጓዳውን ተከራይተው ሲያድሩ፤ ገንዘብ ለማሥቀመጥ ይቸገር ነበር። ባንክ እንዳያስቀምጥ መታወቂያ የለውም። በቤቱ ደብቆ ሲያስቀምጥ አካራዮቹ የጫት እና የሲጋራ ሱሰኞች ስለነበሩ ገንዘብ እየሰረቁ ሲያሰቃዩት፤ ነስረዲን ከእነ ጓደኛው ከአንድ ዓመት በኋላ ቤቱን ለቆ ወጣ።
ካዛንቺስ መናኸሪያ አካባቢ ሌላ አንድ የታክሲ ረዳት ልጅ ጨምረው ለሦስት 550 ብር ቤት ተከራዩ። ቤቱን የተከራዩት በአንድ ሰው ስም ሲሆን፤ ሁለቱ ተደብቀው እየገቡ እና እየወጡ የተወሰኑ ወራትን አሳለፉ። የቤት ኪራይ ገንዘብ ክፍያ ጊዜ ሲደርስ የታክሲ ረዳቶቹ ይጠፋሉ። አከራዮቹም የተከራዮቹን ቁጥር ሲያውቁ ዋጋ ይጨምራሉ። ነስረዲን ከጋራ ኑሮ የሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ለብቻው ሽሮሜዳ አካባቢ በ350 ብር ቤት ተከራየ።
‹‹ለብቻ መከራየት የተሻለ የደህንነት ስሜት ቢኖረውም ገንዘብን የሚፈጅ በመሆኑ ሰዎች እንዳያድጉ ያደርጋል›› በማለት የሚናገረው ነስረዲን፤ ቀድሞ በ350 ብር የተከራያት ቤት ቀስ በቀስ ዋጋዋ 1ሺህ ብር ደረሰ። ያንን ቤት ለቆ ቢወጣም የቤት ኪራይ ዋጋ እየጨመረ አንድ አልጋ ለምታዘረጋ ቤት በወር ሁለት ሺህ ብር እየከፈለ አንድ ዓመት አስቆጠረ።
ቀድሞም በረንዳ ላይ እያደረ ትምህርቱን እንደአዲስ በአፄ ናኦድ ትምህርት ቤት ከአንደኛ ክፍል የጀመረው ነስረዲን፤ አራተኛ ክፍል ሲደርስ እየሩሳሌም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ እስከ ሰባተኛ ክፍል ተምሯል። አሁንም በዚያው ትምህርቱን የቀጠለ ሲሆን፣ በአካባቢው ያሉት ሰዎች ትህትናው እና ትጋቱ ስለሚያስደስታቸው ይደግፉታል።
ነስረዲን ወዳጆቹ አነስተኛ የላሜራ መደርደሪያ አሠርተውለት ጋዜጣ መሸጥ ጀመረ። ትምህርቱን እየቀጠለ ስለነገው ብዙ ነገር እያሰበ ኑሮውን የዕለት ገቢው ላይ መሰረት ያደረገው ነስረዲን፣ የጫማ ጠራጊነት ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ትቶ ጋዜጣ እየገዛ እና ወረቀት እየሰበሰበ ከጓደኛው ጋር እየተጫረተ በመሸጥ ገቢውን አሳደገ። የቤት ኪራይ ያንገላታው ነስረዲን የኑሮን ሸክም የምትጋራ የህይወት አጋር ፈለገ። በሦስት ሺህ ብር የተሻለ ቤት ተከራይቶ ከሁለት ወር በፊት ትዳር መሰረተ።
‹‹መፅሐፍ ማንበብ በጣም እወዳለሁ›› የሚለው ነስረዲን፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ሥራውን ያቀዛቀዘበት በመሆኑ መፅሐፍ በማንበብ ጊዜውን እያሳለፈ ይገኛል። ባለቤቱም ሥራ መሥራት ብትችልም የኮቪድ ወረርሽኝን ፈርቶ ከቤት እንድትወጣ ባለመፈለጉ ጠቅላላ ወጪውን መሸፈን የእርሱ ግዴታ ሆኗል። በሚያገኘው የዕለት ገቢ የቤት ወጪ እና የቤት ኪራይ ክፍያን ማከናወን ከባድ መሆኑን ይናገራል። በዚያ ላይ ሥራውን አሳድጎ ትልልቅ ጨረታዎች ላይ ለመሳተፍ ገንዘብ ማጠራቀም ይፈልግ የነበረ ቢሆንም፤ ወረርሽኙ ዕቅዱን አስተጓጉሎበታል። አሁን ግን የዕለት ገቢው ተቀዛቅዞ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በመድረሱ ስለቤት ኪራይ ብቻ መጨነቅ ጀምሯል።
ነስረዲን፣ አከራዮቹ በቤት ኪራይ ላይ ጥገኛ መሆናቸውን በቅርብ ጊዜ በመግባቱ ለማረጋገጥ ቢቸገርም፤ አካራዮቹ አንድ ቀን እንኳን ሲያልፍ የኪራይ ገንዘብ የሚጠይቋቸው በመሆኑ ችግሩ ቢባባስ ‹‹የዋጋ ቅናሽ ያደርጉልኛል ወይም ለተወሰነ ጊዜ የቤት ኪራይ ክፍያ ነፃ ይሆንልኛል›› ብሎ እንደማይገምት ነግሮናል።
ሌላው እንደነስረዲን ሁሉ ገቢያቸው በዕለት ተዕለት ሥራ ላይ ተመስርቶ ቤት ተከራይተው ከሚኖሩት መካከል አቶ እርሻ ስራቶ አንዱ ናቸው። አቶ እርሻም ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከጉራጌ ዞን ከወልቂጤ አካባቢ የመጡ ሲሆን፣ ልባሽ (የተለበሰ ልብስ) ከጨረታ ገበያ በመግዛት አሳጥበው እና አስተኩሰው ስድስት ኪሎ አካባቢ የሰንበት ቀን ገበያ (ሰንደይ ማርኬት) ጎዳና ላይ ይነግዳሉ።
ኮቪድ 19 ኢትዮጵያ ውስጥ ተገኘ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ንክኪ ያለበት የጨረታ ገበያ በመቆሙ፤ የእነርሱም ንግድ ለአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል። በእነዚህ ጊዜያትም የዕለት ገቢያቸውን ለማግኘት ተቸገሩ። ሁለት ልጆቻቸውን እና ሥራ የሌላቸው ባለቤታቸውን ቀለብ እና የሚኖሩበትን የቤት ኪራይ ለሁለት ወር መክፈል የቻሉት ያስቀመጡት ገንዘብ በመኖሩ እና የቤተሰብ ዕርዳታ ተጨምሮበት ነበር።
‹‹አከራዮቼ የሚተዳደሩት በቤት ኪራዩ ነው። ያም ሆኖ በ2 ሺህ 400 ብር የተከራየነውን ቤት ኮሮና ከመጣ በኋላ ‹400 ብሩን አትክፈል› በማለት የተወሰነ ትብብር አድርገውልኛል›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ እርሻ፣ ምንም እንኳ ጨረታ ላይ ለመግዛትም ባይሆን ያገኙትን ልብስ ተራርቀው እንዲሸጡ የረፍት ቀን ገበያ የተፈቀደ በመሆኑ፤ ከአስራ አምስት ቀን ወዲህ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ይገልፃሉ። ነገር ግን የዕለት ገቢያቸው መቀነሱን፤ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ እና ወረርሽኙ ከተባባሰ የቤተሰባቸው ህይወት የሚያሳስባቸው መሆኑን ነግረውናል።
ሁለቱም በዕለት ገቢ ላይ ኖሯቸውን የመሰረቱት ሰዎች እንደሚናገሩት፤ ገበያቸው ቀንሷል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ እና ከተባባሰ ሁኔታው የበለጠ አስቸጋሪ የሚሆንባቸው በመሆኑ ስጋት ውስጥ ገብተዋል። በተለይ የቤት ኪራይ ክፍያው ጉዳይ ይበልጥ አሳስቧቸዋል። ነገር ግን ነገ የተሻለ ይሆናል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ነግረውናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
ምህረት ሞገስ