ከድንቅዬ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ የአክሱም ሐውልት ነው።ሐውልቱ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን፣ የመመዝገቡ ምሥ ጢርም አክሱም ቅርስንና ታሪክን አስተባብራ መያዝ በመቻሏም ጭምር ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምት ገኘዋ አክሱም፣ የጥንታዊ ሥልጣኔ ምንጭና እምብርት እንደሆነችም ይታወቃል። የአክሱም ሥርወ መንግሥት ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲመሰረት ክርስትናን እንደዋና ሃይማኖት በ4ኛው ምዕተ ዓመት የተቀበለች አገር ናት።በስልጣኔም ከሜድትራንያን አገሮች አንዷና ታላቋ እንደነበረችም ይነገራል።
በኢትዮጵያ በአክሱም ከተማ የሚ ገኝ የዓለማችን ረጅሙ ትክል የድንጋይ ሐውልት የሆነው ይህ የአክሱም ሐውልት አንድ ሺህ 700 ዓመታትን አስቆጥሯል።የ24 ሜትር ርዝመት አለው። 160 ቶን የሚመዝነው ይኽው ግዙፍ ድንጋይ፤ መሠረቱ አካባቢ ሁለት የሀሰት ብር መሣይ ፍልፍሎች አሉት። የአድዚህ ሐውልት ጌጥ ይህ ብቻ አይደለም፤ በእያንዳንዱ ጎን የመስኮት ቅርጽ የያዙ ፍልፍሎች ሲኖሩት፤ በመጨረሻው ጫፍ ላይ ደግሞ በብረት መቃን የታገዘ የግማሽ ክብ ቅርጽ የያዘ ነው።
በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንዲገነባ የተደረገው ይህ ሐውልት፣ በአክሱም ከተማ ከሌሎች መሠል ሐውልቶች ጋር እንዲቆም የተደረገው በ4ኛው ምዕተ ዓመት አካባቢ ነው። ይህም የጥንታዊ አክሱም ምን ያህል ስልጣኔ እንደነበራት ጠቋሚ ነው።
ከኩሻይቲክ የሜሮይ አገዛዝ የተወሰደ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ሐውልቶችን የማቆም ሥራ፤አሁንም ድረስ በአካባቢው ተመሳሳይ ሥራዎችን መመልከት ይቻላል። እነዚህ ሐውልቶች የሚቆሙት በመሠ ረታቸው ለሚቀበሩ ንጉሳዊ ቤተሠቦች እንደሆነም ይነገራል። በዚህም ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው መሳፍንቶች መቃብር ላይ የሚቆሙት ሐውልቶች በብዛት በተፈለፈሉ የሀሰት ብር እና መስኮቶች ያጌጡ ናቸው።
አብዛኛዎቹ ትክል ድንጋዮች በመሰረት ጥንካሬ ማነስ የወደቁ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ተጠቃሽ የሚሆነው በእርዝመቱ ተወዳዳሪ የሌለው (የ33 ሜትር ርዝማኔ ያለው) ታላቁ ሐውልት በመሬት ላይ መውደቁ ነው። በሐውልቶቹ ላይ የደረሱት ችግሮች ብዙ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ተጠቃሽ ነው።
በ1935 እ.ኤ.አ. ጣልያን ኢትዮ ጵያን በወረረችበት ጊዜ ይህን ሐውልት በጊዜው በነበረው የፋሽስት ኢጣሊያ ገዥ ትዕዛዝ መሰረት የጣልያን ወታደሮች የአክሱምን ሐውልት ከወደ ቀበት አንስተው ወደ ሮም ወስደውት እንደነበር ይታወሳል።በዚህ ጊዜ የፋሺስት አገዛዝ እንደ ጦር ምርኮ እና የሮም ግዛት መስፋፋት ምልክት አድርጎ በመውሰድ በሮም አደባባይ ላይ እንዲተከል ቢያደርግም በኢትዮ ጵያውን ጥረት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ግን ሐውልቱ ለኢትዮጵያ እንዲመለስ በመወሰኑ ወደአገሩ ተመልሶ እንደገና በቀድሞ ቦታው መተ ከሉ ይታወቃል።ጽሁፉን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎች መረጃዎችን በመውሰድ የተሰናዳ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
አስቴር ኤልያስ