የኮሮና ቫይረስ በዓለም ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ እጅግ በርካታ የሰው ልጆችን ህይወት ቀጥፏል፤ በርካታዎችም የቫይረሱ ሰለባና ተጠቂ ሆነዋል። አሁንም ቢሆን የቫይረሱ ስርጭት በፍጥነት በመስፋፋት የዓለም ሀገራትን እያዳረሰይገኛል። በሰው ልጆች ላይ እያሳደረ ካለው የጤና ቀውስ ባሻገር በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህ የሆኑ ችግሮች በመፍጠር ሰዎችን ለከፋ ችግር እየዳረገ ይገኛል።
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ሳይከሰት በፊትና ከተከሰተም በኋላ ስርጭቱ እንዳይስፋፋና የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ለመከላከል የሚረዱ የተለያዩ የዝግጅትና የጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በመንግስት የተለያዩ የለይቶ ማቆያ ማዕከላትና አስፈላጊው የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችንና መሳሪያዎችን በማሟላትና ለክልሎች ሳይቀር በማከፋፈል የማዘጋጀትና የህክምና ተቋማትን አቅም የማጠናከር ስራዎች ተሰርተዋል።
ቫይረሱን በመከላከል ረገድ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች ሳይቀር ኅብረተሰቡን ከበሽታው ለመታደግና ለጥንቃቄ የሚረዱ የእጅ ማስታጠቢያ ማሽኖችን ፤ የተለያዩ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ፤ የእጅ ጓንቶች እንዲሁም የተለያዩ ለህክምናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በብዛት በማምረትና በማከፋፈል የበኩላቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ።
የቫይረሱ ስርጭት ለመግታት እየተወሰዱ ባሉ የጥንቃቄ ርምጃዎች ከሚከሰቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ባሻገር አካባቢ ላይ የሚያስከትሉት ተጽፅኖ ቀላል የሚባል አይደለም። በሀገራችን ቆሻሻን ለመቆጣጣር የሚያስችል ጠንካራ ሥርዓት አለመኖር ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ የህክምና ቁሳቁሶች የአወጋድ ችግሮች የሚያስከትሉት ጉዳት እጅግ ጉልህ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከህክምና ተቋማት የሚመነጭ ቆሻሻ አያያዝ ደረጃ፤ ከምንጩ ከመቀነስ ጀምሮ ለይቶ ማከማቸት እና ጉዳት እንዳያስከትል ሆኖ መምከን ወይም መወገድ ይኖርበታል። ምንም እንኳን ኮቪድ-19 ከቆሻሻ ማስወገጃ ወይም ማከማቻ ቦታ ወደ ሰው ወይም ሌሎች እንስሳት መተላለፉን የሚያሳይ የጥናት ማስረጃዎች ባይኖርም፤ ቫይረሱ በአየር ላይ የሚቆይባቸውን ጊዜያት መነሻ በማድረግ ምናልባትም የዜጎችን ህይወት የሚያሳጣ ሊሆን ስለሚችል ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
ለቫይረሱ መከላከያ ሲባል የህክምና ተቋማትና ባለሙያዎች እንዲሁም ህብረተሰቡ የሚጠቀሙባቸው በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች በተለያየ መጠን እና ብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። ከዚህም በላይ የቫይረሱ ስርጭት ከፍ እያለና እየተሰፋፋ የሚሄድ ከሆነ የህክምና ቁሳቁሶች አጠቃቀም ይጨምራል። ይህንንም ተከትሎ ወትሮውንም ደካማ የነበረውን የህክምና ቁሳቁሶች የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓታችን ይፈትነዋል። የቆሻሻ መሰብሰቢያ፣ ማጓጓዥ፣ ማከሚያ እና ማስወገጃ ወይም ማምከኛ ግብዓቶችን ማዘጋጀት የቆሻሻ አወጋገድ፣ ስርዓታችን ላይ ለውጥ ለማድረግ ከወዲሁ አጽኖት ተሰጥቶት መታሰብ ያለበት ጉዳይ መሆኑን ያመላክታል።
ለመሆኑ ቫይረሱን ከመከላከል ጎን ለጎን አካባቢን ለብክለት ሊዳረጉ የሚችሉ አደገኛ ቆሻሻን በጥንቃቄ በማስወገድ አካባቢን ከብክለት በመታደግ ረገድ በመንግስት በኩል እስካሁን ምን እየተሰራ ነው? ወደ ፊትስ ምን ለመስራት ታቅዷል። በዚሁ ሀሳብ ዙሪያ የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደረቅና አደገኛ ቆሻሻ ህግ ተቀባይነት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ ጋር ቆይታ አድርገናል።
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፡- ማንኛውም ለህክምና አገልግሎት የሚውል ቁሳቁስ ተገቢው ጥቅም ለመስጠት አገልግሎት ላይ ከዋለ በኋላ በጥንቃቄ ካልተወገድ በአጭር ወይም በረጅም ጊዜ ሊከስት የሚችል የራሱ የሆነ የአካባቢ ብክለት ችግር ያስከትላል። በአሁኑ ወቅት ከኮቪዲ 19 ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ ቫይረሱን ለመከላከል የምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች በተለይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችና የእጅ ጓንቶች በብዛትና በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። እነዚህን ቁሳቁሶች ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በጤና ተቋማት ህክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች እንዲሁም በርካታ ህብረተሰቡ ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።
የህክምና ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ ከአደገኛ ቆሻሻ ጋር የሚመደቡ በመሆኑ በአያያዝም ሆነ አወጋገድ ረገድ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ናቸው። እነዚህ ቁሳቁሶች አንድም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በጥንቃቄ ተሰብስበው ካልተወገዱ በቀር እንደገና በሌሎች ሰዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፤ በዚህም ለቫይረሱ ስርጭትና መስፋፋት እንደ አንድ መንስኤ ሊሆን ይችላሉ ። በተመሳሳይም እነዚህ ቁሳቁሶች መሬት ላይ በሚጣሉበት ፤ ከቆሻሻ ጋር ተወግደው በሚቃጠሉበት ወይም ወደ ውሃማ አካላት በሚጣሉበት ጊዜ የአካባቢ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የአካባቢ ብክለት ስንል አንድ አካባቢ ተፈጥሮዊ በሆነ ሁኔታ ሊሰጥ የሚችላቸውን አገልግሎቶች የብዘኃ ህይወት አገልግሎቶች ሊሆን ይችላል ፤ አጠቃላይ የሰው ልጅና ሌሎች በዚያ አካባቢ ላይ ሊያገኙ የሚችሉ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች፤ እንዳያገኙ የሚያደርግ የበካይ ነገሮች ወደ አካባቢ ( ወደ አየር፤ ውሃ፤ አፈር ወይም መሬት ) መለቀቅ የሚያካትት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ፤ እነዚህ ነገሮች ሲለቀቁ በካይ ነገሮች ተለቀቁ እንደሚባል ያስረዳሉ። በእነዚህ በካይ ነገሮች አማካይነት ደግሞ ጉዳት ሲደርስ ወይም አካባቢው ተገቢውን የብዘኃ ህይወት አገልግሎት መስጠት ሲያቅተው ወይንም መስጠት ሳይችል ሲቀር ፤ አካባቢው ተበከለ ወይም ጉዳት ደረሰበት ማለት እንደሚቻል አብራርተዋል።
እያንዳንዱ ሰው ዕለት ተዕለት በሚያደርገው እንቅስቃሴ፤ ምግብ ለማዘጋጀት እጅ ለመታጠብ ወይም ሌሎች የኑሮ ሂደቶችን ለመተግበር በሚደረግ ሂደት ውስጥ ቆሻሻ ያመነጫል የሚሉት አቶ ግርማ ፤ ይህ ቆሻሻ በተገቢ ሁኔታ ተሰብስቦ እስካልተወገድ ድረስ ውሃን ከመበከሉም በላይ ሲቃጠልና ሲወገድ በአየር ወይም በአፈር ላይ ጉዳት ያደርሳል ፤ አፈር ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥም ሊያደርግ ይችላል። አሁን ላይ እንደሚታየው ደግሞ በከተሞች መግቢያና መውጫ ላይ ቆሻሻ ሲጣል አካባቢው መስብዕነቱን ወይም ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንዲያጣ በማድረግ ሊቀይረው ወይም ሙሉ ለሙሉ ሊያጠፋው ስለሚችል ተገቢው የስነምህዳር ዋጋ እንዳያገኝ ሊያደርገው ይችላል። ይህ የአካባቢ ብክለት አንዱ አስረጂ እንደሆነ ይጠቁማሉ ።
ከኮቪዲ 19 ለመከላከል ጥቅም ላይ ከሚውሉት የመከላከያና የህክምና ቁሳቁሶችን አኳያ በአጠቃላይ ሊከሰት የሚችል አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ወይም ለመከላከል የሚያስችል የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅና የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ 1090 /2010 ተብሎ የሚጠራ አዋጅ መኖሩ አስታውሰው። ይህ አዋጅ አጠቃላይ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ሊደርስ የሚችልን ተጽዕኖ በመከላከል በኢኮኖሚው እና በማህበራዊ ላይ የሚያደርሱት ችግሮች ማስቀረት የሚችሉ እርምጃዎችን አካትቶ የያዘ ነው። ከዚህ ውስጥም አደገኛ ቆሻሻን ሊያመነጩ የሚችሉ ተቋማት ተገቢ የሆነ የመሰብሰብ፤ በጊዜያዊነት የማከማቸት፡ የማጓጓዝ፤ የማከምና የማስወገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፤ ኮሚሽኑ በአዋጁ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር መሠረት በማድረግ ሦስት ዋናዋና ተግባራት አከናውኗል። የመጀመሪያው ፤ የህክምና ተቋማት እነዚህ አደገኛ ቆሻሻዎች በአግባቡ መሰብሰቡን፤ በጊዜያዊነት መከማቸቱን ፤ ማጓጓዝና መወገዱን መቻላቸው ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ባሉ ጤና ተቋማት የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች እየተሰራ ነው። ህግ ተላልፎ የተገኘ ወይም በአግባቡ ያልሰበሰበ ፤ ያከማቸና ያላስወገድ ተቋም ሲገኝ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት የህክምና ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙት በህክምና ተቋማት ብቻ አለመሆናቸው የገለጹት ኃላፊው፤ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እያንዳንዱ ሰው በተለይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል። ነገር ግን አወጋገድ ላይ እጅግ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው በመሆኑ ፤ ሲወገድ ለሌላ ሰው ጠንቅ እንዳይሆን በየቦታው እንዳይጣልና በአግባቡ እንዲወገድ ለማድረግ በርካታ ሚዲያዎችን በመጠቀም የግንዛቤ ማስፋት ስራዎች መሰራቱንም ይጠቁማሉ። ከባለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮም በተለያዩ መገናኛ ብዘኃን በመጠቀም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር በመተባባር መልዕክቶችን ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ሦስተኛውና ረዘም ያለ ጊዜን የሚወስደው ህጎቹን በደንብ መሬት ላይ አውርዶ ለመተግበር የሚያስችል የአስራር ስርዓቶችን በደንብ የመዘርጋት ጉዳይ ነው። አንድ የጤና ተቋም ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተፈጠረ ካለው የቆሻሻ ብዛትና ተለያይነት አንጻር፣ ምን ምን እርምጃዎች መውስድ አለበት የሚል ዝርዝር የአሰራር ስርዓቶች እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፤ እነዚህ ቁሳቁሶች በስፋት ጥቅም ላይ በሚውሉበት አካባቢም፤ ጥቅም ላይ የሚያውሉ ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው በሚለው ላይም እየተሰራ ነው። በአጠቃላይ እንደነዚህ አይነት ቴክኒካል ነገሮችን መመለስ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት እየተዘጋጀ ነው። ህግ የማስከበር ስራና ህዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ፤ ሌሎች ተከታታይ የሆኑ የአሰራር ስርዓቶችን የማሻሻል ስራ ከአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እንዲሁም ከክልል የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት ጋር በመሆን በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
እስካሁን ህጉን የተላለፉና ከሚፈለገው መመሪያ ውጪ የሆኑ ተቋማት ባለመኖራቸው የተቀጡ ወይም አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደባቸው የሉም የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ የህክምና ተቋማት የተሻለ ጥንቃቄ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፤ ስጋት የሚሆነው በተለይ የቫይረሱ ስርጭት አሁን ካለው በላይ በጣም የሚሰፋ ከሆነ እና ጥቅም ላይ የሚውሉት ቁሳቁሶችና ተቋማት ውስጥ የሚገለገለው የሰው መጠንና ከበዛ፤ ምናልባት አሁን ላይ ያለን አቅም ቆሻሻን የሚመነጨውን በአግባቡ ለማስተናገድ አይችል ይሆናል እንጂ አሁን ላይ ባለን አቅም ተቋማቱ ጥሩ የሆነ ጥንቃቄ እያደረጉ ነው ይላሉ።
በተለይ ከአስገዳጅ አዋጅ ጋር በተያያዘ አብዛኛው ሰዎች የሚጠቀሙትን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ቁሳቁስ በየቦታው ተጥሎ ማየት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ ፤ ህብረተሰቡን የማስተማሩና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንዳለ ሆኖ፤ በየከተሞቻችን ቆሻሻን ቤት ለቤት እየሰበሰቡ ያሉ ማህበራት ራሳቸውን እንዲጠብቁ የሚያደርግ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለብን ያስገነዝባል። በተለይ የጽዳት አስተዳደርና ቆሻሻ አያያዝ ላይ የሚስሩ ተቋማት ተጨማሪ እርምጃዎች መውስድና ባገኙት አጋጣሚ ህብረተሰቡን ማስተማሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ይህን ለመስራት የሚያስችል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ የከተማ አስተዳደሮች በጉዳዩ ዙሪያ በትኩረት እንዲሰሩ በማድረግ ፤ ተጨማሪ ጥንቃቄን ህብረተሰቡ እንዲወሰድ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
ህብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አገልግሎቱን ከጨረሰ በኋላ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የማስወገድ ሃላፊነቱን በመወጣት፤ በዘርፉ የሚሰሩ ሰራተኞች የስራ ላይ ደህንነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ ርምጃዎችን መውሰድና መተግበር ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የመንግስትም ሆነ የህብረተሰቡ ትኩረት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን በስፋት መውስድ ላይ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በተቋማት ሆነ በግለሰብ ደረጃ የምናስወገዳቸው ቆሻሻዎች ሌላ የስጋት ምንጭ እንዳይሆኑ በመስራት ፤ በተለይ ጠንካራ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች መውስድ ያስፈልጋል ይላሉ። ለቫይረሱ መከላከያ የምንጠቀማቸው ቁሳቁሶች አንዳንድ አካባቢ ላይ እየወደቁ በስፋት ይታያሉ። ይህንን ደግሞ እንስሳቶቻችንን፤ ውሃችንን አልፎም ደግሞ ቆሻሻ በክፍት ቦታ በሚቃጠልበት ወቅት መልሶ ተጨማሪ የሆነ ጫና በአካባቢ ላይ የሚያሳድር ይሆናል ብለዋል።
በመጨረሻም ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚጠቀምባቸውን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎች በየቦታው መጣል ለጤናም ሆነ ለአካባቢ ጠንቅ መሆኑን መገንዘብ አለበት። እነዚህ ቁሳቁሶች በአግባቡ በማስወገድ የራሱን ኃላፊነት በመወጣት ቫይረሱን ለመከላከል እለት ከዕለት የሚያደርገውን ጥንቃቄ ማጠናከርና የአካባቢውንም ንጽህና ለመጠበቅ ማሰብ አለበት ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2012
ወርቅነሽ ደምሰው