
ወንጪ፡- አረንጓዴ ዐሻራ ከስንዴ ተረጂነት ለመላቀቅ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እያገዘ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማእረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ አስታወቁ።
አቶ አዲሱ በኦሮሚያ ክልል የአረንጓዴ ዐሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ትናንት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወንጪ ወረዳ ፣ ሶንቆሌ ቀበሌ ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ ለ7ኛ ዙር የሚካሄደው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እንደ ሀገር “በመትከል ማንሰራራት” እንደ ክልል ደግሞ “ የትውልድ ጥላ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚተገበር ነው። እንደ ክልል በአንድ መንደር ቢያንስ አንድ የትውልድ ጥላ እንዲኖር እየተሠራ ነው ብለዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሃሳብ አምንጪነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ጠፍተው የነበሩ ወንዞች ፣ ምንጮችና ሀይቆች ማንሰራራታቸውን የተናገሩት አቶ አዲሱ፤ እንደ አብጃታ እና ሀሮማያን የመሳሰሉ ሀይቆችን ለማሳያነት ጠቅሰዋል፤ በየአካባቢው እያገገሙ ያሉት የውሃ አካላት የመስኖ ልማትን በማስፋፋት ሀገሪቱ ከስንዴ ተረጂነት እንድትውጣ በእጅጉ እየረዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ በአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ጠቅሰው፤ በተለይም ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ አንጻር በሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
አዳዲስ የሥራ ባሕሎች እና የሥራ እድሎች ለወጣቶች እንዲፈጠሩም ማድረጉን ጠቁመው፤ በርካታ ወጣቶች ችግኝ እያፈሉ በመሸጥ፣ ፍራፍሬ በማምረት፣ ንብ በማነብ ፣ዓሳ በማርባትና እንስሳትን በማድለብ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ አረንጓዴ ዐሻራ ትልቅ መሠረት እንደሆናቸው አቶ አዲሱ አስረድተዋል።
በደን መመናመንና መጨፍጨፍ ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ተሰደው የነበሩ የዱር እንስሳትም ወደነበሩበት በመመለስ ተረጋግቶ የመኖር ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል። የመሬት መሸርሸር እና የአፈር መታጠብን መቀነስ እንዳስቻለና ከእዚህ በፊት ለእርሻ አገልግሎት ሥራ የማይውሉ ቆላማ ቦታዎችንም ወደ ሥራ ማስገባት እንዳስቻለ ተናግረዋል።
እንደ ክልል የዘንድሮውን አረንጓዴ ዐሻራ ካለፉት ጊዜዎች ለየት የሚያደርገው በሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የትውልድ ጥላ በሚል ቦታ ተለይቶ የሚለማ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ለደን ሽፋን እድገት፣ ለእንስሳት መጠለያ፣ ለመዝናኛ እና ለመሳሰሉት እንዲውል በማድረግ፤ በአንድ ሥራ በርካታ ጉዳዮችን ማከናወን ያስችላል ነው ያሉት።
አባቶቻችን ተንከባክበው ያቆዩትን የተፈጥሮ ሀብት ይኼኛውም ትውልድ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አቶ አዲሱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በክልሉ 5 ቢሊዮን ችግኞች ለተከላ እንደተዘጋጁና 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ በተለያየ ደረጃ ያሉ የክልሉ እና የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች ፣ አርሶ አደሮችና ወጣቶች ችግኝ በመትከል ተሳትፈዋል።
የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ እንደ ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ሰኔ 21 ቀን 2017 በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። እንደ ሀገር 7 ነጥብ 5 ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ይታወቃል።
በኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም