
ጅግጅጋ፦ በሶማሌ ክልል ባለፉት ሰባት ዓመታት በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት 57 ቢሊዮን 19 ሚሊዮን 9333 ሺህ 256 ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል መመዝገቡን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ። የዲያስፖራው ተሳትፎ 4 ቢሊዮን 851 ሚሊዮን 490 ሺህ 348 ብር መሆኑን ጠቆመ ።
የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ ረሽድ አብዲሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በሶማሌ ክልል ባለፉት ሰባት ዓመታት በተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል።
በእነዚህ ዓመታት 24 ቢሊዮን 571 ሚሊዮን 730 ሺህ 468 ብር ለማስመዝገብ መታቀዱን አስታውሰው፤ የኢንቨስትመንት ልማቱን ለማሳደግ በተፈጠሩ ሥራዎች 57 ቢሊዮን 19 ሚሊዮን 9333 ሺህ 256 ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል ተመዝግቧል ብለዋል። ከአጠቃላይ ኢንቨስትመንቱ የዲያስፖራ ተሳትፎ 4 ቢሊዮን 851 ሚሊዮን 490 ሺህ 348 ብር የሚጠጋ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቢሮው በዲያስፖራ ማስተባበር ዘርፍ በኩል በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙትን የክልሉ ተወላጆችን በማስተባበርና በማቀናጀት በክልሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴው ላይ እንዲሳተፉ ሰፊ ሥራ መሥራቱን አመልክተዋል።
እንደ አቶ አሕመድ ገለጻ፤ በክልሉ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ይታይ የነበረውን ክፍተት በመለየት፣ በመገምገም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የኢንቨስትመንት መስኮችን በመለየት፣ ኢንቨስትመንት ልማቱን ለማሳደግ በትኩረት መሠራቱ፣ በክልሉ የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ አስችሏል።
በሁሉም ዘርፍ 150 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት 200 ፕሮጀክቶች እንዲሁም 70 ፕሮጀክቶች በዝግጅት ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ባለሀብቶች ፕሮጀክቶቻቸውን እንዲያስፋፉና እንዲያሳድጉ በተደረገ ድጋፍና ክትትል መሠረት ለ765 ፕሮጀክቶች በኢንዱስትሪ፣ ሆቴል፣ ኮንስትራክሽን እና አገልግሎት ዘርፍ የማበረታቻ አገልግሎት መሰጠቱን አመላክተዋል።
ከተመዘገቡት ፕሮጀክቶች ለ 35 ሺህ 981 ቋሚ እና 45 ሺህ 615 ጊዚያዊ የሥራ እድል፣ በድምሩ ለ78 ሺህ 533 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል።
በክልሉ የኢንቨስትመንት ልማት አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ቢሮው የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ያሉት ኃላፊው፤ ቢሮው ለውጡን ተከትሎና መንግሥት ለግሉ ሴክተር የሰጠውን ልዩ ትኩረት ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን በስፋት መሥራቱን አስታውቀዋል። ከእዚህ በተጨማሪም ባለሀብቱ ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዲገባና እንዲያለማ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ጭምር በመሄድ የፕሮሞሽን ሥራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል።
በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከዓመት ወደ ዓመት እየተሻሻለ እና ሊታይ በሚችል መልኩ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ቢሮው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተፈጠረውን መነቃቃት ለማስቀጠል ከሁሉም ባለድርሻ ተቋማት እና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም