
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ቀደም ሲል በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦች እንዲነሱ ይፋዊ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በሺር አል-አሳድንና የቅርብ ሰዎቻቸውን የእስላማዊ መንግሥት ቡድንን (ISIS) እንዲሁም ኢራንና አጋሮቿን የተመለከቱት ማዕቀቦች ግን ባሉበት ጸንተው እንደሚቆዩ የትራምፕ አስተዳደር አስታውቋል። 518 ሶሪያውያን ግለሰቦችና ተቋማት ከማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ እንደወጡ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።
ፕሬዚዳንቱ “ሶሪያ የተረጋጋች፣ አንድ የሆነች እንዲሁም ከራሷና ከጎረቤቶቿ ጋር ሰላም የፈጠረች እንድትሆን አሜሪካ ቁርጠኛ ድጋፍ ታደርጋለች። የአሸባሪ ድርጅቶች መጠለያ የማትሆን እና በውስጧ ለሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዋስትና የምትሰጥ ሶሪያ፣ ለአካባቢያዊ ደህንነትና ብልፅግና አጋዥ ትሆናለች” ብለዋል።
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ የፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ለሶሪያ መንግሥት የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እንዲሁም ለሀገሪቱ ልማትና መልሶ ግንባታ ወሳኝ የሆኑ አካላትን ከማዕቀብ ጫና የሚያላቅቅ ተግባር እንደሆነ አመልክቷል።
የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ ሃሰን አል-ሻይባኒ የአሜሪካን ርምጃ አወድሰዋል። “ርምጃው ለመልሶ ግንባታና ልማት ምቹ እድል ይፈጥራል። የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲያገግም በሚሠሩ ሥራዎች ላይ የተጋረጡ መሰናክሎችን ያስወግዳል። ሀገሪቱን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ክፍት ያደርጋል” ብለዋል።
የአልጀዚራው ዘጋቢ ማይክ ሃና ከዋሺንግተን ዲሲ ባሰራጨው ዘገባ፤ ሶሪያን መልሶ ለመገንባት ወሳኝ ርምጃ የሆነው ማዕቀቦቹን የማንሳቱ ውሳኔ ሰፊ ይዘትና ትርጉም እንዳለው ጠቁሟል። ርምጃው የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃ ተስፋ እንደተጣለበትም ገልጿል።
ከእዚህ በተጨማሪም የሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ሻራ “ልዩ ዓለም አቀፍ አሸባሪ” እንዲሁም አል-ሻራ የሚመሩት “ሃያት ታህሪር አል-ሻም” የተባለው ታጣቂ ቡድን (የቀድሞው “አል-ኑስራ ግንባር”) ደግሞ “የውጭ አሸባሪ ድርጅት” ተብለው ተፈርጀው የነበረበት ውሳኔ በድጋሚ እንዲታይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ማርኮ ሩቢዮ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ባለፈው ወር በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት እያደረጉ በነበሩበት ወቅት፤ ሀገራቸው ቀደም ሲል በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩ ማዕቀቦችን እንደምታነሳ መናገራቸው ይታወሳል። ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በተካሄደው የሳዑዲ-አሜሪካ ኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሶሪያ የተሻለችና ታላቅ ሀገር እንድትሆን እድል ለመስጠት ሲባል በሀገሪቱ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች እንዲነሱ ትእዛዝ አስተላልፋለሁ። ማዕቀቦች ዓላማቸውን አሳክተዋል፤ከእዚህ በኋላ አያስፈልጉም። አሁን ሶሪያ ወደ ፊት የምትጓዝበት ጊዜ ነው። ሶሪያን ወደ ሰላምና መረጋጋት እንደሚመልስ ተስፋን የሰነቀ አዲስ መንግሥት አለ” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
ከሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን እና ከቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ይህን ውሳኔ እንዲወስኑ እንዳደረጓቸው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ አሜሪካ ከሶሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ እንደምትፈልግም ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በወቅቱ ከሶሪያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት አህመድ አል-ሻራ ጋር በሪያድ በተወያዩበት ወቅት፣ አሜሪካ በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦች የምታነሳው የሶሪያ መንግሥት “የአብርሃም ስምምነት”ን በመቀበል ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመረ፣ አሸባሪ ፍልስጤማውያንን ከሀገሩ ካስወጣ እና በሰሜን ምሥራቅ ሶሪያ ለሚገኙ የእስላማዊ መንግሥት (ISIS) ማጎሪያ ማዕከላት ኃላፊነት ከወሰደ እንደሆነ ነግረዋቸው ነበር።
የትራምፕ ውሳኔ ለአሜሪካና ሶሪያ ግንኙነት አስደናቂ ርምጃ ቢሆንም፤ “የአብርሃም ስምምነት”ን ተቀብሎ ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመጀመር ጉዳይ ለሶሪያ መንግሥት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ እንደሚሆንበት ተንታኞች ገልጸዋል። በተለይም ሶሪያ “የአብርሃም ስምምነት”ን እንድትቀበልና ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት እንድትመሰርት የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ የፍልስጤማውያንን ጥያቄና ጥቅም የሚክድ በመሆኑ ቅድመ ሁኔታው ለአረባዊቷ ሶሪያ እጅግ ከባድ ጥያቄ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በሶሪያ የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት በሺር አል-አሳድ መንግሥት ይፈጽማቸዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ሀገሪቱ በአሜሪካና በአውሮፓ ኅብረት ከባድ የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች ተጥለውባታል። ማዕቀቦቹ የሶሪያ ምጣኔ ሀብት ክፉኛ እንዲዳከም አድርገውታል።
ሶሪያ ለ14 ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት አሰቃቂ ውድመትን አስተናግዳለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ሶሪያ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረችበት የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ለመመለስ ከ50 ዓመታት በላይ ይፈጅባታል። የመልሶ ግንባታውን ሥራ ለማፋጠን ብዙ ኢንቨስትመንት ትፈልጋለች። ከአስር ሶሪያውያን መካከል ዘጠኙ በድህነት ውስጥ ይገኛሉ። የሀገሪቱ ጥቅል ሀገራዊ ምርት (GDP) ጦርነቱ ሲጀመር ከነበረው ዋጋ በእጥፍ አሽቆልቁሏል። የሀገሪቱ የሰብዓዊ ልማት አሃዝ እ.አ.አ በ1990 ከተመዘገበው ያነሰ ሆኗል። በ14 ዓመቱ ጦርነት ያጣችው ጥቅል ሀገራዊ ምርትም 800 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል።
በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረት በጦርነት የደቀቀችውን ሶሪያን መልሶ ግንባታዋን ለማገዝ በሀገሪቱ ላይ ጥሏቸው የነበሩትን የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች እንደሚያነሳ ባለፈው ወር አስታውቋል። ከእዚህ በተጨማሪም ኅብረቱ ባለፈው የካቲት ወርም በሶሪያ ወሳኝ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ላይ ጥሏቸው ከነበሩት ማዕቀቦች መካከል አንዳንዶቹን ማንሳቱን አስታውቋል። ብሪታኒያም በ12 የሶሪያ መንግሥት ተቋማት ላይ ጥላቸው የነበሩትን ማዕቀቦች ማንሳቷን ባለፈው ሚያዝያ አሳውቃለች ።
ሶሪያን ለ24 ዓመታት ከመሩት በሺር አል-አሳድ እጅ ሥልጣን ነጥቆ ሀገሪቱን ለማስተዳደር እየሞከረ የሚገኘው የሶሪያ የሽግግር መንግሥት፤ ምዕራባውያን በበሺር አል-አሳድ የሥልጣን ዓመታት በሶሪያ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች እንዲያነሱ ደጋግሞ እየጠየቀ ይገኛል። የሽግግር መንግሥቱ በጦርነት የወደመችውን ሀገር ለመገንባት የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዲፕሎማሲ የማደስና የማጠንከር ፍላጎት አለው። ሀብታሞቹ የባህረ ሰላጤው ሀገራትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በሀገሪቱ የመልሶ ግንባታ ተግባር ላይ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው ይፈልጋል።
የአሜሪካና የአውሮፓ ማዕቀቦች መነሳታቸውም የሶሪያ ምጣኔ ሀብት ከገባበት አዘቅት ወጥቶ እንዲያገግም በማድረግ ረገድ ቀላል የማይባል ድርሻ ይኖረዋል። የማዕቀቦቹ መነሳት በማዕቀቦቹ ምክንያት በሶሪያ ከርዳታና ከኢንቨስትመንት ታቅበው የቆዩት ሀብታሞቹ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ለሶሪያ መልሶ ግንባታ በጎ አስተዋጽኦ በሚኖራቸው የኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ያስችላቸዋል። አሜሪካና አውሮፓ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው በመሆኑ ማዕቀቦቻቸውን ማንሳታቸው ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከሶሪያ ጋር የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማከናወን ያስችለዋል ሲሉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም