
ባቱ፦ ባቱን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የከተማና የሀይቅ ዳርቻ የኮሪዶር ልማት እየተሠራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አህመዲን ኢስማኤል ገለጹ። አስተዳደሩ የከተማና ሀይቅ ዳርቻ ኮሪዶር መሠረተ ልማቶችን በመሥራት ለነዋሪውና ለኢንቨስተሮች ምቹ ማድረጉን ገልጸዋል።
አቶ አህመዲን ኢስማኤል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የከተማ ኮሪዶር ልማት በሁለት መልኩ እየተተገበረ ነው። አንደኛው በከተማ መሀል የሚገነባ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የሀይቅ ዳርቻ ኮሪዶር ነው። የመሀል ከተማ ኮሪዶር ልማት የእግረኛ መንገድ እና የሳይክል መንገድ እየተሠራ ነው።
እንደ ከንቲባው ማብራሪያ፤ በኮሪዶር ልማቱ በከተማዋ ከሚገነባው አረንጓዴ የማድረግ ሥራ ዋንኛው አካል ነው። በተጨማሪ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፤ አደባባይ የማስዋብ እና የመንገድ ዳር መብራቶችን የመሥራት ተግባር ዋነኛው የሥራው አካል ነው። እነዚህ ሥራዎች በከተማ መሀል የሚተገበሩ ሲሆን፤ በሀይቅ ዳርቻ ዙሪያ ደግሞ የደንበል ሀይቅን ንጽህና እና የቱሪስት መስህብነት የሚጠብቅ ፕሮጀክት ተተግብሯል።
“በአራት ሺህ ሄክታር ላይ ተመስርታ የነበረችው የባቱ ከተማ አሁን ከ21 ሺህ በላይ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አላት ያሉት ከንቲባው፤ የደንበል ሀይቅ ደግሞ 500 መቶ ስኩየር ኪሎ ሜትር (50 ሺህ ሄክታር) ስፋት ላይ ያረፈ ነው” ብለዋል፡፡
የከተማዋ ከንቲባ አቶ አህመዲን፤ የከተማው ማህበረሰብ ሃይቁን ሳይጠቀም ለረጅም ዓመታት አብረው መኖራቸውን አውስተው፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሀይቁን በንጽህና በመያዝ እና በዳርቻው ውብ የኮሪዶር ልማት በመገንባት ለጎብኚዎችና ለነዋሪው ምቹ ማድረግ ተችሏል። በዳርቻው ምንም ዓይነት የፕላስቲክና በካይ ቆሻሻ አይጣልም ነው ያሉት።
የሀይቅ ዳርቻ ኮሪዶር ልማት በመሠራቱ በቀን ከ20 ሺህ ብር እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ ይገኛል የሚሉት አቶ አህመዲን፤ ይህ ገቢ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ሲኖሩ ከ60 እስከ 70 ሺህ እንደሚደርስ ገልጸዋል።
ባቱን ከእዚህም በላይ የጎብኚዎች ምርጫ እንድትሆን እየሠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ወደ ባቱ የሚገባ የትኛውም የኢትዮጵያ እና የዓለም ሀገራት ጎብኚ ምቾቱ ተጠብቆ መዝናናት የሚችልበት ከተማ እንድትሆን እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
“የደንበል ሀይቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጣና ቀጥሎ በስፋቱ ሁለተኛ ነው” ያሉት ከንቲባው አቶ አህመዲን፤ በሀይቅ ዳርቻው በተሠራው የኮሪዶር ልማት የቱሪዝም ከተማነቷን በተጨባጭ ማሳየት ችለናል ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ ሕዝብን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነበረበት ችግር የሚያወጣ ሃሳብ ተይዞ፤ ቀድሞውኑ የነበረውን የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ፀጋ ፣ በማቀናጀትና ሃሳብ በማከል የሕዝቡን ኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
የሕዝባችን የኑሮ ዘይቤ ራሱን የቻለ የቱሪዝም መስህብ ነው የሚሉት አቶ አህመዲን፤ የባቱ ከተማ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶች እና ባሕሎች ተዋደው እና ተፋቅረው በጋራ የሚኖሩባት ነች ብለዋል።
በለውጡ ማግስት በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ 79 ባለሀብቶችን መጋበዝ እንደተቻለ የተናገሩት የባቱ ከተማ ከንቲባ፤ በኢንቨስትመንት ባቱ ትልቅ እድል ያላት ሀብታም ከተማ መሆኗን አውቀው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በሆቴል፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አድርገዋል።
ባለሀብቶች በባቱ ከተማ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ተጠቅመው በስፋት በሆስፒታሊቲ ዘርፉ ላይ ቢሰማሩ መልካም መሆኑን ገልጸዋል። የቱሪዝም ዘርፍ ከ60 እስከ 70 በመቶ ያሉትን ኢንቨስተሮች ማስተናገድ እንደሚችል ነው የተናገሩት።
“ሰላምና ጸጥታ ለሁለቱም ዘርፍ ወሳኝ ነው” ያሉት ከንቲባው አቶ አህመዲን፤ ሕዝቡ ሃያ አራት ሰዓት እና ሰባቱንም ቀናት ተደራጅቶ ከአስተዳደሩ ጋር በቅንጅት የከተማዋን ሰላም ይጠብቃል ብለዋል።
ኢንቨስተሮች መዋዕለ ንዋያቸውን ያለምንም ስጋት በከተማዋ በማዋል ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ አመልክተው፤ የከተማ አስተዳደሩ መሬት በማቅረብ፣ ቀልጣፋ አገልግሎት በቴክኖሎጂ ታግዞ እንደሚሰጥና የሰላምና ጸጥታ ሙሉ ዋስትና እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።
በዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም