‹‹ሞት ይቅር ይላሉ ሞት ቢቀር አልወድም፤
አፈሩም ድንጋዩም ከሰው ፊት አይከብድም›› ያልታወቀ ባለቅኔ…
ጎህ ቀዶ አረፋፍዷል። በጎዳናው አፋቸውን በቁራጭ ጨርቅ የሸፈኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከወዲያ ወዲህ ይራኮታሉ። ቀኑ ፀሐያማ ቢሆንም የስጋት ደመና በየሰው ፊት እንዳጠላ ለማስተዋል አይከብድም። ሰው ባይነጥፍም የቀድሞ ፒያሳ ግርማ ሞገሷ የከዳት ይመስላል። በፀጥታው ውስጥ ከወዲያ ማዶ…የአንቡላንስ ድምፅ ይሰማል። ወጪ ወራጁ ይንሾካሾካል። ይገለማመጣል…።
እጆቿ ድረስ ዘልቆ ጣቶቿን የሸፈነ ዘልዘል ያለ ሹራብ ለብሳለች። ከአፏ ከፍ፤ ከግንባሯ ወረድ ብሎ ሳሳ ያለ ሻርፕም አጣፍታለች። የተሸፋፈነችው ስስ ጨርቅ በጥቂቱም ማንነቷን የሸሸገላት ይመስላል። ጨርቋ ግን ገፅታዋን ሊደብቅላት አልቻለም። ጉልበቷ ድረስ የወረደ ጥቁር ሻማ ቁምጣ ከነጠላ ጫማ ጋር ለብሳለች። ወጣት ነች። ስታወራም ሆነ ስትራመድ ፈጠን ፈጠን ትላለች።
በእጆቿ አስር አስር ብሮችና ጥቂት ሳንቲሞች ይዛለች። ፒክ አፕ መኪና ውስጥ ካለ ወጣት ጋር እያወራች ነበር። እጆቹን ዘርግቶ በውል ለመለየት የሚከብዱ የብር ኖቶችን ዘረጋላት። ፊቷ በፈገግታ ተሞልቶ ቀልጠፍ ብላ ተቀበለችው። በድጋሚ ዞር ብላ አልተመከተችውም። አይኖቿ መቅበዝበዛቸውን ቀጠሉ። በሰከንዶች ከአጠገቡ ተሰወረች።
አገር ፍቅር ቲያትር ቤት አካባቢ ባለ አንድ ሬስቱራንት በረንዳ ላይ ነው። የመጠጥ ጠርሙስ ከፊቱ ካለ ጠረጴዛ ላይ አንድ ጎልማሳ ብቻውን ተቀምጧል። አገጩ ላይ በሁለት ቀጭን ገመዶች ከጆሮዎቹ ጋር የተያዘ የአፍ መሸፈኛ አድርጓል። በተለመደው መጣደፍ ወደእርሱ ሄደች ‹‹ባርች እስቲ አንድ ጃንቦ ግዛልኝ?›› ብላ ፍቃዱን ሳትጠይቅ ወንበሩ ላይ ዘርፈጥ ብላ ተቀመጠች። የጠመጠመችውን ሻርፕ ከፊቷ ላይ አንስታ ጭኖቿ ላይ አስቀመጠችው። ድህነትን ታግሎ ያሸነፈ ቁንጅና ተላብሳለች።
ሰውዬው ፈገግ ብሎ አስተናጋጁን በአይኑ ጠቀሰው። ሁኔታው ልጅቷን የሚያውቃት አይነት ነው። መጠጥ
መጣ። ብርጭቆ ቶሎ ቶሎ ወደ አፏ ማስጠጋቱን ተያያዘችው። ፊቷን አንዴ ፈገግ ደግሞ ጨፍገግ ታደርገዋለች። ‹‹አንድ ጃንቦ›› ብትልም ደጋግማ እየጠጣች ነው። እንደተለመደው ስታወራ ፈጠን ፈጠን ትላለች። ችኩልነቷ ተጭኗት ይሆን ሆን ብላ በድንገት ድምጿን ከፍ አድርጋ ‹‹አየህ ጭን ገልጦ አፍ ሸፍኖ አይሆንም። እዚም ሆነ እዛ የሰው ፊት ይገርፍሃል። ልዩነቱ አሁን ቀን መሆኑ ነው›› በማለት ዙሪያ ገባዋን ገልመጥመጥ እያደረገች ሳግ የተቀላቀለበት ሳቋን ለቀቀችው። ቀይ ፊቷ ቲማቲም ይመስል ጀምሯል። ሰክራ ይሆን? ወይስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምሽት ቤቶችን መዝጋት አበሳጭቷት?
ከወዲህኛው ማዶ ላይ የተቀመጡ ሁለት ወጣቶች ይንሾካሾካሉ። ወረርሽኝን ለመከላከል ተራራቁ የሚለውን የሚዲያ ጩኸት ጭርሱኑ የዘነጉት ይመስላሉ። ሰምተዋታል። ድምጿ ለነሱ ብቻ ሳይሆን ከወዲያኛው ማዶ ላለ መንገደኛም ይሰማል። አንዱ ‹‹እቺን ልጅ አየሃት? ቅድም ጨላ ስትቀፍለን የነበረችው እኮ ነች›› በማለት እንደ አዲስ ይጠይቀው ጀመር። ‹‹ገንዘብ ስትለምነን ማለቱ ይሆን?›› ፒያሳ አይደል? አራዶች ይበዙበታል መቼም!
ጓደኛው መለስ አድርጎ ‹‹እረስተሃት ነው ከተድላ ቤት አጠገብ እንደውም ከፎክላንድ ወደዚህ ስትመጣ ያለው ናይት ክለብ እዛኮ ነው የምትሰራው›› በማለት ወሬውን ያሞቅለት ጀመር። ወጣት ነች፣ ቆንጆ ነች… ሌላም ሌላም እያሉ ‹‹ሰርታ መብላት አለባት›› የሚል ፍርደ ገምድል አርቲ ቡርቲ መተርተር ጀመሩ።
ጀርባዋን የከበዳት ነው የምትመስለው። ፊቷ ደም እንደመሰለ ነው። እጆቿ ጠርሙሱን እንደጨበጡ ናቸው። የሌሊቱን በቀን እየካሰች አይነት ነገር። ሆኖም መቅበጥበጧን አቁማለች። ሱሱ ነበር እንዴ ያቅበዘበዛት? አብሯት ያለው ሰው ያዳምጣታል። ወሬዋን የወደደው ይመስላል። አሁን ድምጿ ዝቅ ስላለ የምትለው ግን አይሰማም። ከበረንዳው ከአንዱ ጥግ ከተሰቀለ ስፒከር ላይ ግን እሷን የወከለች የምትመስል ወጣት ከለስላሳ ሙዚቃ ጋር ብሶት በጎነተለው ድምፅና ሳግ ታነበንባለች። የሚገርም ነው። ከስፒከሩ የሚወጣ ሳይሆን ቆንጆዋ ልጅ የጃንቦውን ብርጭቆ እንደ ድምፅ ማጉያ ተጠቅማ ማህበረሰቡን የምትወቅስ ነበር የሚመስለው። እንዲህ እያለች…
‹‹ያው መቼም እኔም እንደ ሰው፤ አንዳንዴ! አንዳንዴ! ብቻ ህሊናዬን እውነት ሲያምረው…ሰብሰብ ብዬ የማስበው። ቀድሞስ ቢሆን ለኔ ቢጤ፤ ለኔ ቢጤ! የህይዋን ዘር ማን መስክሮ ሊናገር። እኔው ከራሴው ስከራከር ያው መቼም እንደሰው፤ የሃቅ እርሃብ ነብሴን ሲያከው፤ ልቤ ልቤን የሚሞግተው። እውነትስ ‹ምንትስ› ማን ነው? ኧረ ማነው?…›› የምትል ይመስላል።
ምሽት ገላዋን ብትሸጥ፤ የሰው ፊት ገርፏት። ዛሬ ተፈጥሮም እንደደላቸው እንደ አንዳንዶቹ ቆጠረቻት። የኖረችው ኑረት እርሱም ከመኖር ተመዝግቦ ‹‹ጭንሽን፣ አፍሽን አፍኚ›› በሚል ደምራ ሸነቆጠቻት። ከበረንዳው ላይ ነች። መጠጥ አሁንም አሁንም ይመጣል። በአንድ እጇ ቀደም የሰበሰበችውን የብር ኖቶች፤ በአንደኛው ደግሞ የጃንቦ ጠርሙሷን ጨብጣ፣ ገፅታዋን አንዴ ፈገግ አንድ ጊዜ ደግሞ ጨፍገግ እያደረገች ከጋባዧ ታወጋለች።
ወጣቶቹም ያንሾካሽካሉ ‹‹የሚገርምህ እኮ ማታ ሲከለከል በቀን መንገድ ላይ መቆም ሁሉ ጀምረዋል። ጭር ያለ ቦታ ይቆማሉ። ወይ ደግሞ እሷም ለምን እንደ ጓደኞቿ አትሰራም? ከምትለምን›› እያሉ…እሷ ግን አትሰማቸውም። ጀርባዋን እንደሰጠቻቸው ነች። ፊቷ ግን እንደቀላ ነው። የሚሉትን እየሰማች በድምፅ ማጉያ በረንዳው ላይ ባለው ስፒከር ‹‹ለፍርዳቸው›› በምላሹ የምትሟገት ይመስላል።
… ነገሬ ከልብ ያልወጣ ነውና ለህዝብ፤ ለማንም ያልተገለጠ እውነት አለኝ። ከቶ የናንተን ፍርድ ከመጤፍ የማይቆጥር። ስለዚህ አንዳንዴ ብቻ፤ አልፎ አልፎ ብቻ! ለአንድ አፍታ ሃሳቤም ስጋዬም አርፎ መንፈሴም ሲያገኝ እፎይታ። ‹‹ምንትሶች›› ለምትሉኝ የለኝም ፀጥታ…ከዚያ ከሌት ውጣ ውረድ፤ ከቀን መኝታው ድብታ ጋር ሲነፅር፤ የዛሬው የኔ ቢጤነቴ አንድ ነው…እያለች
‹‹አያችሁ ጭን ገልጦ አፍ ሸፍኖ አይሆንም። እዚም ሆነ እዛ የሰው ፊት ይገርፍሃል። ልዩነቱ ልመናው ቀን መሆኑ ነው››…በእውቀቱ ስዩም ደግሞ እንዲህ ይላል… ወፈፌ ቀን አልፎ እብድ ቀን ሲመጣ፤
ማልቀስ አመፅ ሲሆን በሸንጎ የሚያስቀጣ።
እንባዬን የት ላርገው፤
ወዴት ልሸሸገው? (የማለዳ ድባብ)…
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2012
ዳግም ከበደ
‹‹አየህ ጭን ገልጦ አፍ ሸፍኖ አይሆንም…››