‹‹አጀንዳ›› የተሰኘው የጋዜጣ አምድ ለዲሞክራሲያዊ ባህል ዕድገት የሚጫወተውን ሚና ያህል በአገራችን ብዙ ያልተጻፈበትና ጥናትና ምርምር ያልተደረገበት ገጽ ነው። በእንግሊዘኛ “Opposite editorial” ተብሎ የሚታወቀው ይህ አምድ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች የተለያየ ስያሜና ትርጓሜ ሲሰጠው ይስተዋላል። አጀንዳ፣ ነፃ አስተያየት፣ ነፃ መድረክ፣ ነፃ ሐሳብና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከዚሁ ጋዜጣ የአምዱ ስያሜ ጋር አብሮ ለመሄድ ሲባል ‹‹አጀንዳ›› የሚለው ስያሜ የእንግሊዘኛውን ‹‹Op-Ed›› ገለፃ የሚተካ ይሆናል።
የአምዱ አመጣጥና ዕድገት እንደሚያሳየው፣ ‹‹አጀንዳ›› አምድ እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም በዘመናዊ መልክ በኒወርክ ታይምስ አማካኝነት ሲጀመር የጋዜጣውን ርዕሰ አንቀፅ ይዘት የሚሞግት ተገዳዳሪ ርዕሰ አንቀፅ የሚሰፍርበት ገጽ የነበረ ሲሆን የሚገኘውም ከጋዜጣው ርዕሰ አንቀፅ በስተቀኝ ነበር። “Opposite Editori¬al” የሚለውን ስያሜ ያገኘውም ከዚሁ ከሚገኝበት ተቃራኒ ገጽ አንፃር ነው። በሂደት መገኛ ገፁና ይዘቱ ከጋዜጣው ርዕሰ አንቀፅ አንፃር ብቻ መወሰኑ እየቀረ የመጣ ስለመሆኑ አሁን ላይ በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የሚስተዋል ጉዳይ ነው።
ጋዜጠኝነት ለዲሞክራሲ ባህል መዳበር የሚጫወተው ሚና ከሚገለጽባቸው አይነተኛ መንገዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ‹‹አጀንዳ›› አምድ ነው። አምዱ የሕዝብን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች ከጋዜጣው አሳታሚ፣ ርዕሰ አንቀፅና አርታኢ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ የሚንሸራሸሩበት መድረክ ነው። ከጋዜጣው ጋር ተቋማዊ ግንኙነት የሌላቸው ፖለቲከኞች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች ተነሳሽነት ያላቸው ግለሰቦች እውቀትና ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ጽሑፎችን ለሕዝብ የሚያደርሱበት አደባባይ ተደርጎም ይታያል። በሌላ አነጋገር ‹‹አጀንዳ›› አምድ በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ፣ ለሕዝብ ጉዳዮች የቆመ፣ የሕዝብ አስተያየት መስጫ ገጽ ነው ማለት ይቻላል።
ፕሬስ መረጃዎች የሚሰራጩበት መድረክ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አስተሳሰቦችንም የሚያስተናግድ የዲሞክራሲ ማሳለጫ መሆን እንዳለበት ይታመናል። ‹‹አጀንዳ›› አምድ ከፍተኛ ተነባቢና ተጽዕኖ ፈጣሪ የጋዜጣ አምድ የመሆኑ ዋናው ምክንያት ይህ የአሳታፊነት ባህሪው ስለመሆኑ በአምዱ ላይ በሌሎች አገራት የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። የሐሳብና የርዕዮተ ዓለም ሙግቶች የሚካሄዱበት፣ ፖሊሲዎች የሚተነተኑበት፣ አዳዲስ ሐሳቦችና የምርምር ግኝቶች የሚቀርቡበት፣ ችግሮች የሚብራሩበትና የመፍትሔ አቅጣጫ የሚጠቆምበት አምድ መሆኑ የብዙዎችን ትኩረት በቀላሉ እንዲስብ አድርጎታል።
በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ‹‹አጀንዳ›› አምድን ጨምሮ ሁሉም አስተያየቶች ግልጽ የሆነ አላማና ተልዕኮ እንዲሁም ይዘትና አቀራረብ አላቸው። ከዜና ጋር በማነፃፀር የጋዜጣዊ አስተያየትን ፋይዳ አጉልተው የሚገልፁ በርካታ ናቸው። ደኒስ ፒለን የተባለ አንድ የመገናኛ ብዙሃን ኤክስፐርት እንደሚለው፣ የዜና ዘገባ በሪፖርተሩ ግለሰባዊ አድሉአዊነት ምክንያት የሚዛናዊነት ጉድለት ስለማያጣው ጉድለቱ ሊካካስ የሚችለው አስተያየቶች ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት መሆኑን ያሰምርበታል። እንደ ጆን ፒተርስ ያሉ አንዳንድ የኮሙኒኬሽን ምሑራን በበኩላቸው ከዜና ይልቅ ለአስተያየት ከፍ ያለ ዋጋ በመስጠት ሰዎች ሐቅን ከሕዝብ አስተያየት ፍርድ ቤት ደጅ ላይ ፈልገው እንዲያገኙ አጥብቀው ይመክራሉ ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም በበኩሉ በአንድ ወቅት ጋዜጣ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ ላይ ዓለምን የሚያሽከረክራት የሕዝብ አስተያየት መሆኑን ገልጾ ከሕዝብ አስተያየት በተቃራኒ የቆሙ አካላት ግን ይዋል ይደር እንጂ በማዕበሉ የመጠራረጋቸው ነገር አይቀሬ መሆኑን የዓለም ተሞክሮ ያሳያል ብሏል።
በእኛ አገር ደረጃ ‹‹አጀንዳ›› አምድ መቼና በማን እንደተጀመረ የተጠና ነገር ባይኖርም አገራችን ባሳለፈቻቸው የሽግግር ወቅቶች ብቅ ብለው ድርግም ያሉ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ይነገራል። አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ሥልጣን እንደመጡ አካባቢ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› የተባለው ጋዜጣ ተራማጅ ያላቸውን አስተያየቶች የሚስተናገድበት የምሑራን ገጽ ፈጥሮ ነበር። በሌላ በኩል ደርግ ወደ ሥልጣን እንደ መጣ ለተወሰነ ዓመታት ፖለቲከኞች፣ ምሑራንና ተማሪዎች የመሬት አስተዳደርን ጨምሮ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሐሳብና የርዕዮተ ዓለም ክርክር የሚያደርጉበት ገጽ በመንግሥት ጋዜጦች ላይ እንደነበር ይታወቃል። ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን እንደመጣም በተመሳሳይ መልኩ ጋዜጦች የተለያዩ ነፃ አስተያየቶችን የሚስተናገዱበት ዕድል ተፈጥሮላቸው እንደነበር የሚታወስ ነው። ሁሉም ሙከራዎች ነፃ የህዝብ አስተያየት መንሸራሸሪያ የጋዜጣ አምድ ጅማሮ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።
‹‹አጀንዳ›› አምድ የተለያዩ ሐሳቦችን ከማስተናገድ ይልቅ የተወሰኑ ድምጾችን ብቻ ለማጉላት የሚውልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በተለይ ዴሞክራሲ ባልዳበረበትና የሐሳብ ብዝሃነት በማይበረታታበት አገራት አምዱን ለፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ጥቅም ብቻ ማዋል የተለመደ ነው። ለምሳሌ በአገራችን ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት የዚህ ጋዜጣ ‹‹አጀንዳ›› አምድ የኢህአዴግ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ብቻ የሚስተናገዱበትና ለሌላው በሩ ዝግ የሆነ አምድ እንደነበር አሊ የሚባል አይደለም። ለስሙ ‹‹ነፃ አምድ›› ይባል እንጂ ከሚዲያ አሠራርና ከጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር ያፈነገጡ አሠራሮችን ሲያስተናግድ እንደነበር ተደጋግሞ ተገልጿል። የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች በ2009 ዓ.ም አገር ጥለው እንደተሰደዱ በአሜሪካ ድምጽ ላይ ቀርበው የተናገሩት ነገር ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው። መንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአስር ጊዜ በላይ አዲስ ነገር ጋዜጣን የተመለከቱ ጽሑፎች በ‹‹አጀንዳ አምድ›› ሥር አውጥቶ እንደነበር አስታውሰው ሁሉም ጽሑፎች በነፃ አስተያየት ስም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የጻፏቸውና ለቀጣይ እርምጃቸው ምክንያታዊ መደላድል የሚፈጥሩ ውንጀላዎችና ስም ማጥፋቶች እንደነበሩ ገልፀዋል።
ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን አምዱ በሩን ለተለያዩ አስተያየቶች ክፍት ያደረገ ይመስላል። ጋዜጣውንም ሆነ አምዱን ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር ጋር በማያያዝ፣ ግለሰቦች በአምዱ ሥር ለመስተናገድ እምብዛም ሲጣጣሩ ባይታይም በጎ መሻሻሎች እንዳሉ ግን የማይካድ ሃቅ ነው። ከአለፈው ጊዜያት አሠራር አንፃር አሁን ላይ አምዱ ነፃ ወጥቷል ማለት ይቻላል። በዚህ አምድ ሥር ህዝባዊና አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ መጻፍ፣ መወያየት፣ መከራከር ወቅቱም አምዱም የሚጠይቀው ጉዳይ ነው::
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
(በለው አንለይ – batlast@gmail.com)