ዛሬ ግንቦት ስምንት ነው። በደርግ ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተደረገበት። ትናንት ደግሞ ግንቦት ሰባት ነበር። ግርግር ተፈጥሮበት የነበረው የ1997 ዓ.ም ምርጫ የተደረገበትና በስሙም ፓርቲ የተቋቋመበት። የፊታችን ሐሙስ ደግሞ ግንቦት 13 ነው። የደርግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም አገር ለቀው ወደ ዝምባቡዌ የተሰደዱበት። የሳምንቱ ሐሙስ ደግሞ ግንቦት 20 ነው። የደርግ ሥርዓት ተገርስሶ ኢህአዴግ አገሪቱን የተቆጣጠረበት ዕለት።
ግንቦትና የካቲት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳል። ልዩነታቸው፤ የካቲት የውጭ ጠላት ድል የተደረገበት ስለሆነ በአንድነት ይከበራል። የግንቦት ወር ታሪኮች አሁንም አከራካሪና ብሽሽቅ ያለባቸው ናቸው። በነገራችን ላይ የካቲት ወር የአገር ውስጥ የግጭት ታሪክም ያለው ነው። የህወሃት የምስረታ በዓልና ራሱ የደርግ አብዮት በየካቲት ወር ውስጥ የሚነገሩ ናቸው።
የግንቦት ወር ታሪክን ከሌሎች የሚለየው የቅርብ ዘመን መሆኑ ነው። ከላይ የጠቀስኳቸውን የግንቦት ወር ክስተቶች በሙሉ በህወሃት ያሉ ሰዎች የሚያውቋቸው ናቸው። የ30 እና የ15 ዓመታት ታሪክ ነው ያላቸው። ሰዎች በመኖር የሚያውቁት ታሪክ ስለሆነ ነው አከራካሪነቱ የበዛው። መቶ እና ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩት በታሪክ ድርሳናት ብቻ ስለሆነ የሚታወቁ ብዙም ሲኮነኑ አይሰማም። በእርግጥ በእነርሱ ላይም ክርክሮች አሉ። ቢሆንም ግን እንደ ግንቦት ክስተቶች አይሆንም።
‹‹ታሪክ በባለሙያዎች ይጻፍ›› የሚባለው ለዚህ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪክ በባለሙያዎች ሳይሆን በፖለቲከኞች እየተጻፈ ነው። በፖለቲከኞች የሚጻፍ ታሪክ ደግሞ ሚዛናዊነቱ አጠራጣሪ ነው። የግል ስሜታቸው ያሸንፋቸዋል። ከወቅታዊ ብሽሽቅ ተነስተው ይጽፋሉ፤ ይህ መጽሐፍ ታሪክ ሆኖ ይቀመጣል። መጻሕፍቱም የሚጻፉት በአንድ ጀንበር ነው። ዛሬ አንድ አገራዊ ስክተት ቢከሰት በሦስት ወይም አራት ቀን ውስጥ መጽሐፍ ሆኖ ይወጣል። ወራትና ዓመታት በመውሰድ ሰፊ ጥናት የሚደረግበትን ጉዳይ ‹‹የምንትሱ ምሥጢር›› ተብሎ መጽሐፍ ሆኖ ይወጣል። አሁን ላይ ያለ ሰው እውነታውን ቢረዳም እየቆየ ሲሄድ ግን የተዛባ ታሪክ ያስተላልፋል።
የኢህአዴግ ታሪክ በታሪክ ባለሙያዎች አልተጻፈም። በእርግጥ አንዳንድ የታሪክ ባለሙያዎች (ለምሳሌ ፍስሐ ያዜ) እንደሚሉት፤ በማስተዳደር ላይ ያለ መንግስት ዜና እንጂ ታሪክ አይባልም። ማንም እያየው ስለሆነ ማለት ነው። የታሪክ ባለሙያዎች በዚህ ወቅት የተሰሩ ዘገባዎችንና ሰነዶችን ሰብስበው ይጽፋሉ ማለት ነው።
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የታሪክ መዛባት የሚከሰተው። የታሪክ ፀሐፊዎች የሚጽፉት በወቅቱ ከተሰነዱ ሰነዶች ነው። ከዘመነ ኢህአዴግ ወዲህ ግን አራምባና ቆቦ የሆኑ ነገሮች በዝተዋል። ከፓርቲዎች መብዛት ጋር ተያይዞ ፖለቲከኞች የተለያየ መጽሐፍ ጽፈዋል። አንዱ የጻፈውን ለማስተባበል ሌላው ይጽፋል፤ የአንዱን ለማራከስ ሌላኛው ይጽፋል። እውነታው የት ጋ እንዳለ አይታወቅም። ጋዜጦችና መጽሔቶችም እንደዚሁ ናቸው። አንድ አይነት ክስተት፤ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች የተለያየ ይሆናል። አሃዛዊ መረጃ ካለውም፤ አንዱ ላይ 100፤ ሌላው ላይ 200፤ ሌላው ላይ 50 ሊሆን ይችላል።
ታሪክ የድርጊቱ ተዋናይ በነበሩ ሰዎች ቢጻፍ ፀሐፊዎች አንደኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭ ይሆኑ ነበር፤ ዳሩ ምን ዋጋ አለው ይሄም ችግር አለበት። በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው ባለሥልጣናት መጽሐፍ የሚጽፉት ሲባረሩ ወይም ከሥልጣን ሲወርዱ ነው። የሚጽፉትም ሲዋኙበት የነበረውን ሥርዓት ለማውገዝ ነው። ከሥርዓቱ አኩርፈው የወጡ ሰዎች ከስሜት ነፃ ይሆናሉ ብሎ ለማመን ያስቸግራል። የሚጠቀሟቸው ቃላት ራሱ ስሜታዊነታቸውን ይገልጻሉ። ‹‹ሰይጣን፣ ሆዳም፣ ከርሳም፣ አራጅ… ›› የሚሉ ቃላትን ይጠቀማሉ። የዚያን ሰው ወይም ድርጅት ጥፋት ለመግለጽ ሁነቱን ወይም አሃዛዊ መረጃውን ማስቀመጥ ነው። እነዚህን ቃላት ከተጠቀሙ የጥላቻ እንደሆነ ያስታውቃል።
ከዚህ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ ቅዱስ በማድረግ አብዝቶ ማቆለጳጰስ ነው። ሲሰሩበት የነበረውን ሥርዓት ቅዱስ በማድረግ ተቀናቃኞቹን ደግሞ ያራክሳሉ። አንዳንድ ጊዜ ከሚባለው ከሚሰማው ውጭ የሆነ ነገር ሲጽፉ ደግሞ ከእውነታው ጋር ይጋጫል። ለምሳሌ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ‹‹ትግላችን›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ስለታጠቅ ጦር በሚያወራው ምዕራፍ ውስጥ የጠቀሱት አንድ አንቀጽ በህይወት ካሉ ሰዎች ከሚሰማው ውጭ ነው። ኮሎኔል መንግስቱ እንደገለጹት፤ ወታደር ሲመለመል በራሳቸው በወጣቶቹ ፈቃድ ብቻ ነበር። እናትና አባቶች እንደሚሉት ግን በግዳጅ ነበር። በራሳቸው ፈቃድ የገቡ ቢኖሩም ኮሎኔል መንግስቱ ግን ግዳጅ እንደሌለ ገልጸዋል። እንዲያውም ብዛታቸው ከሚፈለገው በላይ ሆኖ እየለመንን ነው የመለስናቸው ብለዋል። ምናልባት በሶማሊያ ወረራ ወቅት ብቻ ካልሆነ በስተቀር ይሄ የሚሆን አይመስልም።
እንግዲህ መሪዎች ራሳቸው ሲጽፉም ይሄ ችግር አለ ማለት ነው። የኢህአዴግ ሰዎችም ሲጽፉና ሲናገሩ እንዲሁ ነው። የደርግን ሥርዓት ሰይጣናዊ አድርገው ይስሉታል። የኢህአዴግ ተቃዋሚዎችም ስለኢህአዴግ ሲጽፉ ተመሳሳይ ይሆናል። ራሳቸው አገር ገንቢ፣ ሌላውን ደግሞ አገር አፍራሽ ያድርጉታል። እንዲህ አይነት መበሻሸቅ ነው ታሪክን የሚያዛባ። እንግዲህ ይሄው መበሻሻቁ በራሱ ታሪክ ይሆናል ማለት ነው።
የግንቦት ታሪክ የአገር ውስጥ ብሽሽቅ ታሪክ ነው። የደርግና የኢህአዴግ ጦርነት የአንድ አገር ህዝቦች ጦርነት ነው። አባዱላ ገመዳ ‹‹60 ዓመታት›› ብለው በጻፉት መጽሐፋቸው ‹‹የወንድማማች ጦርነት›› ይሉታል። በነገራችን ላይ አባዱላ በዚህ መጽሐፋቸው የጻፉት የራሳቸውንና የኢህአዴግን የትግል ታሪክ እንጂ ደርግን አረመኔ የሚል አይደለም። እንዲያውም አንድ የገለጹት ነገር አለ። የተማረከ የደርግ ወታደር ካለ ምንም አይነት ጉዳት እንዳይደርስበት ስምምነት አላቸው። ምክንያታቸው ደግሞ ወንድማማቾች ነን የሚል ነው። ምናልባት ይሄ የጦርነት ህግም ሊሆን ይችላል፤ በሌላ በኩል ‹‹ወንድማማች ነን ካሉ ለምን ተዋጉ?›› ያሰኛል።
እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ነገር ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምም ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ክንውኖች የሚያደንቁትን አልሸሸጉም። ለምሳሌ ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት የነበራቸውን ጥረትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መመስረታቸውን እንደ ታሪካዊ ስኬት ጠቅሰውታል። አቶ መለስ ዜናዊም ስለኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ተጠይቀው ‹‹መንግስቱ ሰው በላ ቢሆንም የአገር ፍቅሩንና ጀግንነቱን ግን አልክድም›› ብለዋል።
ከአገሪቱ መሪዎችና ሌሎች ባለሥልጣናት በተጨማሪ ደግሞ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል የተጻፉና የተነገሩም አይታጡም። ለምሳሌ ግንቦት ሰባት ራሱን ችሎ መጽሐፍ ተጽፎለታል። ፀሐፊው የኢህአፓ መሥራች አቶ ክፍሉ ታደሰ ናቸው። ‹‹ግንቦት 7›› የተሰኘው ይህ የክፍሉ ታደሰ መጽሐፍ ግላዊ ስሜትና ትንታኔ የለውም። የአጻጻፍ ስልቱም እንደሌሎች የታሪክ መጻሕፍት አይደለም። ቀጥታ ዘገባ ነው የሚመስለው። የነበሩ ሁነቶችና ክስተቶችን ነው የሚናገረው። የተጠቀሱት ሁነቶች እውነት ናቸው ወይስ ሀሰት የሚለው እንዳለ ሆኖ እንዲህ ከግላዊ ስሜት የፀዳ መሆኑ ግን ጥሩ ያሰኘዋል። የግንቦት ሰባት ክስተት በታሪክ መሰነዱ ደግሞ አስፈላጊ ነው። የታሪክ መጽሐፍ ሁሉ እንዲህ መሆን አለበት ማለት ግን አይደለም። ፀሐፊው የታሪክ ባለሙያ ከሆኑ የራሳቸውን እይታና ትንታኔ ይጨምሩበታል።
ወደ ግንቦታዊ ክስተቶች እንሂድ። ግንቦት ሰባት እና ግንቦት 20 ከታሪክነት ይልቅ ገና በዜናነት ደረጃ ላይ ስላሉ እንለፋቸው። በዛሬዋ ቀን ግንቦት ስምንት 1981 ዓ.ም የነበረውን ክስተት የታሪክ ድርሳናትና የበይነ መረብ መረጃዎች እንዲህ ያስታውሱታል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ ተግባራዊ ሙከራ የተደረገው በ1981 ዓ.ም ቢሆንም የመፈንቅለ መንግሥት ሃሳቡ ከተጠነሰሰ ግን ቆይቷል። የድርጊቱ ዋነኛ ጠንሳሾችና ጀማሪዎች የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ እና ከአየር ኃይል አዛዥነት ተሽረው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ናቸው። ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለጉብኝት ወደ ምስራቅ ጀርመን ሄደዋል። በዕለቱ የመጨረሻውን የአድማ ስብሳባ ለማድረግ የተመረጠው ቦታም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ነበር።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ፣ የምድር ጦር ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ኃይሉ ገብረሚካኤል፣ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል አምሃ ደስታ፣ የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ፣ የፖሊስ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ወርቁ ዘውዴ፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል አብዱላሂ ዑመር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ፣ የሀገር መከላ ከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል አበራ አበበ፣ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መኮንን ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ትርፌ፣ የጦር ኃይሎች አካዳሚ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ አበበ፣ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የእቅድና ፕሮግራም መምሪያ ኃላፊ ኮሞዶር ኃይሌ ወልደማርያም እና ሌሎች የጦሩ አባላት ከመከላከያ ሚኒስትሩ ቢሮ አጠገብ ባለው አነስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰቡ።
ተሳታፊዎቹ ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አልነበሩም። ከየጦርክፍሎች የተውጣጡ ሌሎች ሰዎችም አሉበት። መፈንቅለ መንግስቱን ለማድረግ ተሰብስበው የነበሩት እነዚህ የጦር ጀኔራሎች አለመግባባት ተፈጥሮ እዚያው እርስርሳቸው ሊጨፋጨፉ እንደነበርም ይነገራል። ስብሰባውን ረግጠው የወጡም አልጠፉም።
የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ በሊቀ መንበሩ ሸኝት ላይ ያልተገኙ የጦር አዛዦች ሁኔታ ጥርጣሬ ውስጥ ስለከተታቸው (ሙከራው አዝጋሚ ቢሆንም የቆየ ስለነበር) አዛዦቹን የሚከታተል ቡድን አደራጅተው ስለነበር እያንዳንዱን ድርጊት ይከታተሉ ነበር። ጉዳዩ የመፈንቅለ መንግሥት አድማ መሆኑን ሲያረጋግጡም ነገሩን የሊቀ መንበሩ ቀኝ እጅ ለነበሩት ለሻለቃ መንግሥቱ ገመቹና ለሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን አሳወቋቸው። በዚህ ጊዜ ለመፈንቅለ መንግስት ጠንሳሾች ሽምግልና ቢላክም ‹‹ሽምግልናም ድርድርም አያስፈልግም›› ብለው ተናገሩ። ይሁን እንጂ በጠንሳሾች አለመግባባት፣ በእቅድና አፈፃፀም ስህተት መፈንቅለ መንግስቱ ከሸፈ። ‹‹አብዮት ልጆቿን ትበላለች›› ቀጥሎ እነዚህ የጦር ጄኔራሎች የአብዮት ሰለባ ሆኑ።
ምን ዋጋ አለው! ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ከግንቦት ስምንቱ መፈንቅለ መንግስት ቢተርፉም ከግንቦት 13ቱ (ከሁለት ዓመታት በኋላ) መፈንቅለ መንግስት ሊተርፉ አልቻሉም።
ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት በወታደራዊ አገዛዝ ያስተዳደሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ለ17 ዓመታት ሲፋለማቸው የነበረው የኢህአዴግ ጦር አዲስ አበባ ሲቃረብ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም አገር ለቀው ሸሹ። ወዲያውም በዚያኑ ዕለት ሌፍተናንት ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሰየሙ።
ከ1983 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ተቃዋሚው የኢህአዴግ ሰራዊትም ወደ አዲስ አበባ በአሸናፊነት ገሰገሰ። የጦር ጥቃት እንደተጠጋቸው የተረዱት ኮሎኔል መንግስቱ ‹‹እምንሞተውም እምንኖረውም እዚሁ አገራችን ላይ ነው›› ቢሉም ይሄን ቃላቸውን ለማጠፍ ተገደዋል።
ኮሎኔል መንግስቱ የሚበሩበት አውሮፕላን እንዲዘጋጀላቸው ምክንያቱ በብላቴን ወታደራዊ ማስልጠኛ ወታደራዊ ስልጠና በማድረግ ላይ የነበሩትን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እጐበኛለሁ በሚል ሰበብ ነበር። ከብላቴና ወደ አስመራ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በሚል ሀሳብ አውሮፕላኗ ነዳጅ እንድትሞላ አዘዙ። ረፋድ ላይም በረራቸውን ጀመሩ። ሆኖም ግን በአየር ላይ እንዳሉ አውሮፕላኑ ወደ ናይሮቢ እንዲበር አብራሪውን አስገደዱት። አብራሪው፣ ለኬንያ በረራ እንዳልተዘጋጀ የኬንያ ካርታ እንደሌለው እና መብረር እንደማይችል ቢያሳውቅም ኮሎኔሉ ግን ‹‹በግድ ትሄዳታለህ›› ብለው አቅጣጫውን ለውጦ እንዲበር አስገደዱት። ናይሮቢ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁለተኛ ፀሐፊ ተቀበሏቸው፤ በዚያው የስደተኝነት ኑሩዋቸውን ወደሚገፉበት ወደ ዝምባቡዌ ሀራሬ ከአምስት አጃቢዎቻቸው ጋር አይሮኘላን ለውጠው ሾለኩ። በኋላ ግን የዝምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እንዳረጋገጡት ኮሎኔል መንግሥቱ ከአገር የሸሹት በተጠና እቅድ እንደነበር ተነግሯል።
የግንቦት ወር ታሪክ የደርግ እና የኢህአዴግ ነው። የግንቦት ሰባቱ ከደርግ ጋር ባይገናኝም ከኢህአዴግ ጋር ይገናኛል። ኢትዮጵያን ለውጭ ጠላት የሚያጋልጣት እንዲህ አይነት የአገር ውስጥ ጦርነት ነው። ይሄን ደግሞ ራሳቸው መንግስቱ ኃይለማርያምም ያምናሉ። በ‹‹ትግላችን›› መጽሐፋቸው ደጋግመው ጠቅሰውታል። ይሄን እያወቁ ግን ሥርዓታቸው አምባገነን ነበር (እርሳቸው ነኝ ባይሉም)። እርግጥ ነው የዚያድ ባሬን ወረራ በድል ተወጥተዋል። ይሄ አኩሪ ሥራቸው በዚያ አምባገነን አገዛዛቸው ውስጥ እንኳን አስመስግኗቸዋል።
የፖለቲከኞች የግል አጀንዳ፣ የአኩራፊ ባለሥልጣናት የጥላቻ አስተያየት እና የራሳቸውን አስተዳደራዊ ሥርዓት ብቻ የሚያንቆለጳጵሱ ሰዎች የሚጽፉት፤ እውነታን ያዛባልና ታሪክ በባለሙያዎች ይጻፍ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
ዋለልኝ አየለ