
ርምጃው ከተወሰደ ሁለት ዓመታት ያስቆጠረ ቢሆንም፤ሰሞኑን በግብርና ምርቶች ዘርፍ የተሰጠው የደላላነት ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን የሚያወሳ መረጃ እንደ አዲስ ስሰማ የደላላን ነገር ላነሳሳው ወደድሁ። እንኳን እናቴ ሞታ ድሮም አልቅስ አልቅስ ይለኛል እንዲሉ፤ እኔም ለዓመታት ደላላ ከግብይት ሰንሰለቱ እንዲወጣ ስወተውት ኖሬ ሰሞኑን ይሄን መረጃ ስሰማ በግሌ የተደረገልኝ ያህል ነው የተደሰትሁት።
በዘርፉ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ የንግድ ሥርዓቱን የሚረብሹ በርካታ ደላላዎች አሉ። በእህል ምርት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቁም እንስሳት ዘርፍ የተሰጠው የደላላነት ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን ደላላዎች ከገበያው እንዲወጡ መደረጉንና ከ3 ሺህ በላይ ደላሎች እና አገናኞች ርምጃ እንደተወሰደባቸውም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በእዚያ ሰሞን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ በዘርፉ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ የንግድ ሥርዓቱን የሚረብሹ በርካታ ደላላዎች አሉ። ስለሆነም በእህል ምርት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቁም እንስሳት ዘርፍ የተሰጠው የደላላነት ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን፣ ይህን ተከትሎም ደላላዎች ከገበያው እንዲወጡ መደረጉን፣በቀጣይ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በገበያው የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት ይሠራል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
በተመሳሳይ በሲሚንቶ ገበያ ዘርፍ ነጻ የገበያ ሥርዓት በመዘርጋት የሲሚንቶ ዋጋ ከግማሽ በታች እንዲቀንስ መደረጉን አብራርተዋል። የሲሚንቶ ግብይት ሥርዓትን ሲረብሹ የነበሩ ደላላዎች እና በተለያዩ አካላት ስም ሲነግዱ የነበሩ ግለሰቦች ከዘርፉ እንዲወጡ መደረጋቸውን አረጋግጠዋል። የኢፌዴሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ፤ በእዚያ ሰሞን ለፓርላማ አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት አንስተዋል።ለእዚህ ይበል ለሚያሰኝ ርምጃ በልኩ እውቅና ሰጥቼ ስለ ደላላ አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳ።
ከተቀረው ዓለም የሀገራችንን የኑሮ ውድነት ለየት የሚያደርገው ማለትም ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ባሻገር እሴት የማይጨምሩ ደላሎች በገበያ ሰንሰለቱ ከማሳ እስከ ገብያ መሰግሰጋቸው፤ መንግሥትም ተገቢውን ቁጥጥርና የእርምት ርምጃ አለመውሰዱ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይፋ ባደረገው ጥናት ምርት አምራቹ ከሚሸጥበት 58 በመቶ ዋጋው ጨምሮ ሸማቹ ጋር እንዲደርስ አድርጓል።ሰሞኑን ድንች ላይ በተደረገ ጥናት ከአርሶ አደሩ በላይ ተጠቃሚው ደላላው ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ አርሶ አደሩ ሌት ተቀን ማስኖ ከሚያመርተው ድንች 60 በመቶ ትርፉን የሚወስደው ደላላ ነው።ይህ ማለት ዛሬ በሀገራችን ከሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት ድርሻው ቀላል ያልሆነው በደላሎች አማካኝነት የተፈጠረ መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል።
ጥናቱ በሕግና በሥርዓት ሊስተካከል በሚችል የግብይት ሰንሰለት ሸማቹ ምን ያህል ፍዳውን እያየ መሆኑንም ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከስንት ውትወታ በኋላ ሕገ ወጥ ደላላን ከግብይት ሰንሰለቱ ለማስወጣት ወደ ተግባር መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ዛሬም የግብይት ሰንሰለቱን ከደላላ ማጽዳት አልቻለም።ሆኖም ይህ ከባድ እና የባጀ ችግር ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ብቻ ወይም ለአንድ ተቋም የሚተው ጉዳይ አይደለም።የሸማቹንና የመላ የመንግሥት መዋቅርን የተቀናጀ ትብብር ይጠይቃል።ዛሬ ምስጋና ለቴክኖሎጂው ይግባውና የግብይት ሥርዓቱን በማዘመንና ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ሸማቹን በቀጥታ ከአምራቹ ማገናኘት ይቻላል።
የአርባ ምንጭን ሙዝ አምራች በቀጥታ ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት ከሸማቹም ሆነ ከአከፋፋዩ ጋር ማገናኘት ይቻላል።የከንባታን ድንች አምራችየአላባን በርበሬ፣የአድአንና የጎጃምን ጤፍ አምራች በእጅ ስልኩ ላይ በተጫነ መተግበሪያ ወይም ሌላ ቴክኖሎጂ ከሸማቹ ጋር መገናኘት ይቻላል።በነገራችን ላይ የደላላ ተጽእኖ ከገበያው አልፎ የኢኮኖሚውን ፣ የፖለቲካውንና የማህበራዊ ጉዳዩን መሠረት እየነቀነቀው ከመሆኑ ባሻገር ስውር “አራተኛው መንግሥት”እስከመሆን ደርሷል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ለመሆኑ ይህ በሠራ አካላችን የተሠራጨው፤የግብይት ሥርዓቱን የሚያተራምሰው እና ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረው “ደላላ” ምን ማለት ነው፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል፤ በ1993 ዓ.ም የአዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤” ደላላን” ገንዘብ እየተከፈለው ተፈላላጊዎችን ( ሻጭና ገዥን ፣ አከራይና ተከራይን …፤ ) አገናኘ ፣ አስማሚ ። በማለት ይተረጉመዋል። በመደለል ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው ፣ አታላይ ፣ በውሸት አግባብቶ ለማሳመን የሚሞክር፤ “ድላል”ን ደግሞ ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ በማለት ይተረጉማል።
የደስታ ተክለወልድ ዘሀገረ ወግዳ በ1970 ዓ.ም የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ፤ ደለለ ፣ አሞኘ ፣ አታለለ ፣ ሸነገለ ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ አለ፤ደላላ፣ አመልካች ፣ ጠቋሚ ድላል፣ ለጠቋሚ ፣ ላስማሚ ፣ የሚሰጥ ገንዘብ ሲል ይተረጉመዋል።ይሄኛው ትርጉም ከቀደመው ይልቅ የሀገራችንን ደላላ ቁልጭ አድርጎ ይገልጸዋል። የእንግሊዘኛውን ትርጉም ‘broker’ ስረወ ቃል ስንመለከት “brocour” ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቋንቋው አካል መሆኑን ሜሪያም ዌቢስተር የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ያወሳና ትርጉሙም ፦bro•ker : a person who helps other people to reach agreements, to make deals, or to buy and sell property (such as stocks or houses) ነው ይለናል ።
የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዘኛው መሠረታዊ ትርጉም ተቀራራቢ ቢሆንም፤ “ድለላ” ሲነሳ አብሮ ማታለል ፣ መሸንገል ፣ ማሞኘት ፣ በውሸት አግባብቶ ማሳመን የሚሉ አሉታዊ አንድምታዎች ግዘፍ ከመንሳት አልፈው “ድለላ” በተነሳ ቁጥር ቀድመው ወደ አዕምሯችን የሚመጡት እነዚህ አሉታዊ ብያኔዎች ናቸው። ከእዚህ የእኛ ሀገር ደላላ ሻጭንና ገዢን የሚያገናኝ ብቻ ሳይሆን ዋጋን፣ወደ ገበያ የሚቀርበውን መጠን፣የሚሸጥበትንጊዜ፣ስርጭቱን፣ወዘተርፈ የሚወስን ኃይል ሆኖ ወጥቷል። በሀገራችን ያለውን አብዛኛውን ደላላም ይገልታል፤ ተብሎ ይታመናል። ሆኖም እጅግ ፣ እጅግ ያነሱ በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ታማኝ ፣ ሀቀኛና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ደላሎች መኖራቸው ግን ሊዘነጋ አይገባም።
ለስሙ ነጭ ካፒታሊስት ነን።ነጻ ገበያን እንከተላለን ብንልም ገበያው በአቅርቦትና በፍላጎት ሳይሆን በደላላ መልካም ፈቃድ የሚወሰን ነው።ለመሆኑ ነጻ ገበያ ማለት ምን ማለት ነው። ነጻ ገበያ ማለት በጥቂት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ወይም ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት ገበያውን አቅርቦት እና ፍላጎትን ተከትሎ እንዲመራ መፍቀድ ማለት ነው። ነጻ ገበያ የዋጋ ጉዳይ ብቻ አይደለም።ነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ዋና ተዋናይ የሆኑት ሸማቾች እና አምራቾች/ሻጮች ሌላው ተዋናይ መንግሥት ተቀንሶ ገበያው ላይ የመወሰን መብት እንዲወስዱ የተሰጠ የውክልና አካሄድ ነው። በዜጎች መካከል ያለው የሀብት ክፍፍል ሲዛነፍም ሆነ ፍትሐዊነትን ለመጠበቅ ሲባል ገበያን ለብዙሃን ምቹነት ሲባል በመንግሥት መጎብኘቱ አይቀርም። ምክንያቱም ነጻ ገበያን ይዞ ብቅ ካለው አዳም ስሚዝ (1723-1790) ጀምሮ ላለፉት 250 ዓመታት ነጻ ገብያ በወረቀት እንጂ በተግባር አሟልቶ መተግበር የቻለ አንድም ሀገር የለም።
በዓለም የኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ ነጻ ገበያ ሥርዓት ምናባዊ ነው ተብሎ የሚተችበት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መተግበር አለመቻሉ ነው።ምክንያቱም መንግሥታት በጥቂቱም ቢሆን ገበያውን ማየት አለመቻላቸው የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ጣልቃ መግባታቸው ወደው ሳይሆን ተገደው ነው።ሀገራት በተለይ ፖለቲከኞች ነጻ ገበያ ላይ ገደብ ለማስቀመጥ የሚደፍሩበት መሠረታዊ ምክንያት የሚመነጨው ለፖለቲካል ኢኮኖሚው ደህንነት ፣ ፍትሐዊነትን ለመጠበቅ እና የሕዝብ የጋራ መጠቀሚያ ሀብቶችን ለመፍጠር ሲባል ነው።ገበያ ቸል በተባለ ቁጥር የጥቁር ገበያ መፈርጠም ፣ የብቸኛ አምራች እና አቅራቢነት/ሞኖፓል/ ባህሪ መፈጠር እንዲሁም ወደ ኢኮኖሚው ሥርዓት መግባትን ከባድ የማድረግ ልምምድ ስለሚፈጠር ነው።
ለነጻ ገበያ የቀረበ የኢኮኖሚ ሥርዓት አመክንዬ ያላቸው ሀገራት ነጻ ገበያን የግለሰቦችን ሀብት የመፍጠር ነጻነት እና የግለሰቦችን መብት ማክበር ድረስ ነው የሚተገብሩት ምክንያቱም ነጻ ገበያ የመንግሥት ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን የመንግሥት ድጎማንም ማስቀረት አለበት ስለሚል ነው። በአይነትም ሆነ በፖሊሲ ባልተደጎመ አርሶ አደር በተመጣጣኝ ዋጋ እና በገፍ ሰብል ወደ ገበያ ለማቅረብ ላደጉም ሀገራት ቀላል አይደለም። ስለ ካፒታሊዝም በተለይ “የነፃ ገበያ አቀንቃኞች የማይነግሩን 23 ቁልፍ ጉዳዮች” በሚለው ድንቅ መጽሐፉ ፕሮፌሰር ሃ ጁን ቻንግ እንደሚለው በእውነት ነፃ ገበያ የሚባል ነገር የለም There is Really No Such Thing as a Free Market ወይም ብዙ ኢኮኖሚስቶች እንደሚስማሙት No Pure Free Market Economies Actually Exist, and All Markets Are in Some Ways Constrained):: ይህ ከኢትዮጵያ እስከ አሜሪካ ገበያ ያለ ሃቅ ነው።
አስታውሱ የነጻ ገበያ መስፈርቶች በሙሉ ተተገበሩ ማለት መንግሥት የገበያ ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን ድጎማንም ማስቀረት አለበት ማለት ነው። በተለያየ መልኩ በድጎማ ሥርዓት ውስጥ የማያልፍ አምራች እና ሻጭ ለማግኘት ከባድ ነው። ለምሳሌ ፡- በሚደጎም ነዳጅ ፣በሚደጎም ውሃ፣ በሚደጎም መብራት ፣ በሚደጎም የሕዝብ መገልገያ እየተጠቀሙ የሚያመርቱ አምራቾች ሸማቾችን መግፈፍ መብታቸው ሊሆን አይችልም።
ነጻ ገበያ ነው ከፈለክ ግዛ ካልፈለህ ትተህ ሂድ፣ ከፈለኩ እሸጣለሁ ካልፈለኩ አልሸጥም ፣በገዛ ንብረቴ ዋጋ መወሰን እችላለሁ ፣ ወዘተ ማለት ነጻ ገበያ ማለት አይደለም። ሕግን ማስከበር ባለመቻል የሚመጡትም ሆነ በሕግ ያለመገዛት አዝማሚያዎች ሁሉ የነጻ ገበያነት መገለጫ አይደሉም።
ቁጥጥር የማይደረግበትና መንግሥት ጣልቃ የማይገባበት ልቅ ነጻ ገበያ ብሎ ነገር በዓለም ላይ የለም። አዎ ሙሉ በሙሉ ነጻ ገበያ ብሎ ነገር የለም ። ሁሉም ኢኮኖሚ ቁጥጥርና መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት ይደረግበታል ። በነጻ ገበያ አቀንቃኝነት በምትታወቀው አሜሪካ እንኳ ብቸኛ አምራች እና አቅራቢነትን ወይም የገበያ ሞኖፖልን ፣ የሸማቾችን መብት ለማስከበር ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የሥራ ቦታ ደህንነትን ለማረጋገጥ ነጻ ገበያው በሕግና በደንብ ልጓም ይደረግበታል። ስለሆነም በየደረጃው ያለ የመንግሥት አካል በነጻ ገበያ ስም ስድ የተለቀቀውን ገበያ ሀይ ሊለው ይገባል።
የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማገበያየት፣በየደረጃው የተሰገሰገውን ደላላ ከግብይት ሥርዓቱ በማስወጣት፤የንግድና የመኖሪያ ቤት ኪራይን በመተመንና ጣሪያ በማስቀመጥ፣ የትርፍ ሕዳግን በመወሰን፣ገበያውን ለውጭ ኩባንያዎች በመክፈት፣በሀገሪቱ ሰላምንና መረጋጋትን በማረጋገጥ፣በአጠቃላይ በግብይት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን በማስፈን አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበትና እሱን ተከትሎ የመጣውን የኑሮ ውድነት ቢያንስ ከግማሽ በላይ መቀነስ ይቻላል።ይፋዊ አኅዞች የሀገራችንን የዋጋ ግሽበት እስከ 15 በመቶ ያደርሱታል።ምንም እንኳ ሌሎች ከእዚህ በላይ ነው ቢሉንም። በግብይት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን በማስፈን ብቻ የዋጋ ግሽበቱን ቢያንስ በግማሽ መቀነስ ያስችላል።
ሌላው ሸማቹ ስለ መብቱ ግንዛቤ ኖሮት መብቱን እንዲያስከብርና በተዘዋዋሪ ደግሞ ጫናውን እንዲቀንስ የንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለሥልጣን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አውጥቶ ራሱን የቻለ ባለሥልጣን ማድረግ ይገባል።አሁን ያለበት አደረጃጀት የጥቅም ግጭት ያለበት ነውና። በሚኒስቴሩ ስር ሆኖ የንግድ ውድድርን እንዴት ሊያሳልጥና ስለሸማቹ መብት ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ሊቆም ይችላል። የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣንና ኢትዮ ቴሌኮምን በአንድ መሥሪያ ቤት እንደማደራጀት እኮ ነው።
በኢትዮጵያ የሸማች መብቶችን ለማስከበር እና ዕለት በዕለት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት ሁለገብ አካሄድንና ምላሽ ይጠይቃል።ግንዛቤን በማሳደግ ፣ የሕግ ማስፈጸሚያዎችን በማጠናከር ፣ ሥነ ምግባር ያለው የንግድ ሥራን በማስተዋወቅ እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብይት ሥርዓቱን ፍትሐዊ ፣ ታማኝ እና ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል።
የሸማቾች መብቶች በዘመነ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተሻሻሉ ሲሄዱ ፣ ባለድርሻ አካላት የሸማቾችን ጥቅም ለማስጠበቅ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማስፋፋት አበክረው ይሰራሉ፤ ይተጋሉ። እገረ መንገዴን ስለ ሸማች ምንነትና መብት ትንሽ ልበል።
“ሸማች” ማለት ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሰው የሚከፍልለት ሆኖ ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው ነው። በሕግ አወጣጥ “ሰው” የሚለው ቃል የተፈጥሮ ሰው እና በሕግ የሰውነት ሥልጣን የተሠጠው አካልን አጠቃሎ የሚይዝ ቃል ነው። በሀገራችን ሕግ መሠረት ሸማች ተደርጎ የሚቆጠረው የተፈጥሮ ሰው ብቻ ነው። በእዚህ ትርጉም መሠረት ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ጨምሮ በሕግ የሰውነት ሥልጣን የተሠጣቸው ተቋማት በሙሉ በአዋጅ ቁጥር 813 መሠረት በእዚህ ሕግ ፊት እንደ ሸማች አይቆጠሩም ማለት ነው።
በሕግ የሰውነት ሥልጣን የተሠጣቸው ተቋማት፣ለማምረት ሥራ ወይም መልሶ ለመሸጥ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው፣ እንዲሁም የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎትን ያለ ክፍያ በነፃ የተቀበለ ሰው ሸማች ተደርጎ አይቆጠርም። የሸማች መብቶች በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 መሠረት ማንኛውም ሸማች የሚከተሉት መብቶች አሉት።
- ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና ዓይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት(14.1)፣
- ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት(14/2)፣
3.የዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ ያለመገደድ(14/3)፣
4.በማንኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድ እና በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራት እና የስም ማጥፋት ተግባር የመጠበቅ(14/4)፣
- የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በመግዛቱ ወይም በመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት የንግድ ዕቃዎቹን ወይም አገልግሎቶቹን ከማቅረብ ጋር ተያይዞ በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ ሻጭነት፣ በችርቻሮ ሻጭነት ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ በአቅርቦቱ የተሳተፉ ሰዎችን በተናጠል ወይም በአንድነት ካሳ እንዲከፍሉት ወይም ከእዚህ ጋር ተያያዥ መብቶችን የመጠየቅ(14/5)፣
6.ስለ ንግድ ዕቃው የተሠጡ የበለጠ የሚጠቅሙ ዋስትናዎች ወይም የሕግ ወይም የውል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣
6.1. የገዛው የንግድ ዕቃ ጉድለት ያለበት እንደሆነ ዕቃውን ከገዛበት ቀን ጀምሮ በአስራ አምስት (15) ቀን ውስጥ የንግድ ዕቃው እንዲለወጥለት ወይም ዋጋው እንዲመለስለት(20/2/ሐ)፣
6.2. የገዛው አገልግሎት ጉድለት ያለበት ከሆነ አገልግሎቱን ከገዛበት ቀን ጀምሮ በአስራ አምስት (15) ቀን ውስጥ አገልግሎቱ በድጋሚ ያለክፍያ እንዲሠጠው ወይም የአገልግሎት ክፍያው እንዲመለስለት ሻጩን የመጠየቅ(20/2/ለ)፣
6.3. ሸማቹ ጉድለት ያለበትን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመጠቀሙ ወይም ሻጩ ከላይ በተራ ቁጥር 6 የተገለጹትን ሁለት ነጥቦች በተመለከተ የቀረበለትን ጥያቄ ባለማሟላቱ ለደረሰበት ጉዳት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ካሳ እንዲከፈለው መጠየቅ መብት አለው።
7.ለገዛው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ደረሰኝ የማግኘት መብት አለው(17/1)።
የነጋዴ ግዴታዎች
- የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን ታክስና ሌሎች ሕጋዊ ክፍያዎችን ያካተተ የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልፅ በሚታይ ቦታ የማመልከት ወይም በንግድ ዕቃዎቹ ላይ መለጠፍ (አንቀፅ 15)፤
- በሚሸጣቸው የንግድ ዕቃዎች ላይ መግለጫ የመለጠፍ ወይም በተለየ ወረቀት ላይ ጽፎ ለሸማቹ መስጠት (አንቀፅ 16)፤
- መግለጫው የዕቃውን ስም፣ የተሠራበትን ሀገር፣ ክብደቱን፣ ብዛቱን፣ ጥራቱን፣ ይዘቱን፣ አጠቃቀሙን፣ የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜ …ወዘተ ያካትታል፤ (አንቀፅ 16/2 ሀ-ኀ)
ለነጋዴ የተከለከሉ ድርጊቶች (አንቀጽ 22)
- የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ስላላቸው ጥራት ወይም መጠን ወይም ብዛት ወይም ተቀባይነት ወይም ምንጭ ወይም ባህርይ ወይም ውሁድ ወይም ጥቅም የተሳሳተ መረጃ መስጠት(22/1)፤
2.የንግድ ዕቃዎች ስለአዲስነታቸው ወይም ስለሞዴላቸው ወይም አገልግሎታቸው የቀነሰ ወይም የተለወጡ ወይም እንደገና የተሠሩ ወይም በአምራቹ እንዲሰበሰቡ የተባሉ ወይም ያገለገሉ ስለመሆናቸው በትክክል አለመግለጽ(22/2)፤
- የሌላውን ነጋዴ የንግድ ዕቃዎች በአሳሳች ሁኔታ መግለጽ (22/3)፤
- የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን በማስታወቂያ እንደተነገረላቸው አለመሸጥ ወይም ማስታወቂያው የመጠን ውሱንነት መኖሩን ካልገለጹ በስተቀር ሸማቾች በሚፈልጉት መጠን ልክ አለመሸጥ (22/4)፤
- ስለዋጋ ቅናሽ ሀሰተኛ ወይም አሳሳች መረጃ ማስተላለፍ(22/5)
- የሸማቹን መብት የሚጠብቅ ባልሆነ ምክንያት የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን አልሸጥም ማለት(22/12)፤
- የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን በንግድ መደብሩ ውስጥ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥ(22/14)፤
- ከሽያጭ ጋር በተያያዘ የተገባ የዋስትና ግዴታን አለመወጣት(22/7)፤
- የንግድ ዕቃ የሚያስፈልገው ጥገና ወይም የሚተኩ ክፍሎች እንደማያስፈልጉት አድርጎ ማቅረብ(22/8)
- የንግድ ዕቃዎች የተሠሩበትን ሀገር አሳስቶ መግለጽ(22/15)፤
- በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልዎ መፈጸም(22/16)፤
- ማንኛውንም አገልግሎት የመስጠት ሥራን በንግድ ሥራው ከሚታወቀው ደረጃ በታች ወይም ባልተሟላ ሁኔታ መስጠት 922/9)፤
- በግብይት ወቅት ማንኛውንም የማጭበርበር ወይም የማደናገር ተግባር መፈፀም(22/11)፤
- ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን የንግድ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች ያለደረጃ ማህተም ለሽያጭ ማቅረብ (22/13)፤
- አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ የንግድ ዕቃ አብሮ እንዲገዛ ማስገደድ(22/17)፤
- ሕገ ወጥ በሆነ ማንኛውም የመለኪያ መሣሪያ መጠቀም(22/18)፤
17.ለሰው ጤናና ደህንነት አደገኛ የሆነ፣ ምንጩ ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃው የወረደ፣ ወይም የተመረዘ፣ አገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ ወይም ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ የንግድ ዕቃዎችን ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ(22/10)፤
- አንድ ሸማች አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት በመግዛቱ ወይም የገንዘብ መዋጮ በማድረጉ እና በሸማቹ አሻሻጭነት ከእሱ ቀጥሎ ሌሎች ሸማቾች የንግድ ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን የሚገዙ ወይም የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ ወይም በሽያጭ ስልቱ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ በሸማቾቹ ቁጥር ልክ ተጨማሪ የገንዘብ ወይም የዓይነት ጥቅም እንደሚያገኝ የሚገልጽ ፒራሚዳዊ የሽያጭ ስልት ተግባራዊ ማድረግ(22/6)፤ከላይ ከተጠቀሱት መብቶች ውስጥ ያልተከበረ ካለ ግብይቱን በፈጸሙበት አካባቢ ለሚገኝ ንግድ ቢሮ ወይም ለፖሊስ በማቅረብ በሕግ ምላሽ እንዲሰጥዎ ያድርጉ።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 22 ቀን 2017 ዓ.ም