
ስፖርት በዓለም ሰላምና መረጋጋት ላይ ትልቅ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው። በተለያዩ መንገዶች የሰዎችን ግንኙነት በማጠናከር፣ መተሳሰብን በማሳደግ እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም። ስፖርት በተለይም በእርስበርስ ጦርነት ወይም በውስጣዊ ግጭቶች ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ። ስፖርት ሰዎችን ከጎሳቸው፣ ከኃይማኖታቸው እና ከፖለቲካ ልዩነታቸው ወጥተው እንዲያስቡ በማድረግ አንድ ላይ የማምጣት ኃይል አለው። በመሆኑም መተማመንን፣ መከባበርን እና መግባባትን ያዳብራል።
ስፖርትም ቢሆን ሰላም በሰፈነበት አካባቢ ብቻ ነው በነጻነት እና በደስታ ሊካሄድ የሚችለው። “ሰላም ከሌለ ፍጹም ስፖርት የለም” የሚለው አባባል እጅግ ትልቅ እውነትን ይዟል። የሰላምን ትሩፋት እና ስፖርት ሰላምን ለማስፈን ሊያደርገው የሚችለውን አስተዋጽኦ ግን አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል። ለዚህም ስፖርት በዓለም ሰላምና የተረጋጋች ሀገር እንዲኖር ምን አስተዋፅኦ ያደርጋል? የሚለውን ጠንቅቆ መገንዘብ ተገቢ ነው።
ሰላም ሲኖር ብዙ በረከቶች እና ጥቅሞች ይገኛሉ፣ በተለይም ስፖርትን በተመለከተ ተዘርዝሮ የማያልቅ ሆኖ እናገኘዋለን። የባሕል መስተጋብርን ማሳደግ አንዱና ዋነኛው መሆኑን መመልከት ይቻላል። ስፖርት ከተለያዩ የባሕልና የሀገር ዳራዎች የመጡ ሰዎችን አንድ ላይ ያመጣል። ይህም የባሕል ልዩነቶችን ለመረዳት፣ አክብሮትን ለማሳደግ እና አድልዎችን ለማስወገድ ይረዳል። በዚህም የጋራ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በቡድን ስፖርቶች ውስጥ ተሳታፊዎች የጋራ ግብን ለማሳካት አብረው ይሰራሉ። ይህም የመተባበር፣ የመተሳሰብ እና የጋራ መግባባት ስሜትን ያዳብራል። በዚህ ውስጥም ዋነኛ ተዋናይ የሆኑትን የወጣቶችን በራስ መተማመን፣ በቡድን መሥራት እና የአመራር ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ያግዛቸዋል። እነዚህ ክህሎቶች ደግሞ ለሰላማዊ ዜጋ አስፈላጊ መሰረቶች ናቸው።
ስፖርት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደ አንድ መድረክ ሆኖ ሲያገለግል በበርካታ አጋጣሚዎች አይተናል። ተሳታፊዎች በጨዋታ ሕግጋት በመመራት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መወዳደርን ይማራሉ። ይህም ማኅበራዊ ለውጥን ለማምጣት ያለው ሚና የጎላ ነው። ስፖርት በዘረኝነት፣ በፆታ ልዩነት እና በሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደ መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል የሚባለውም ከዚህ አንፃር ነው።
ሰላም ለስፖርት እድገትና ስኬት አስፈላጊ መሆኑ አያከራክርም። በተቃራኒው ስፖርት ለሰላም ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። ሰላማዊ ሁኔታዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ካለ ስጋት እንዲካሄዱ ያስችላሉ። ሰላም የገንዘብና የሀብት ድጋፍ ለስፖርት እንዲኖር ያደርጋል። ሰላም ለስፖርተኞች ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይቻለዋል።
ስፖርት በሰዎች መካከል መተሳሰብንና መከባበርን እንደሚያጎለብት እሙን ነው። ስፖርት ወጣቶችን ከጥቃትና ከብጥብጥ ይከላከላል። የተለያዩ ማኅበረሰቦችን አንድ ላይ በማምጣት የጋራ መግባባትን ይፈጥራልም። ሰላም ሲኖር ውድድሮች፣ ስልጠናዎች እና የስፖርት ዝግጅቶች ያለ ፍርሃትና ስጋት ይካሄዳሉ። ተጫዋቾችም ሆኑ ደጋፊዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው በስፖርቱ መሳተፍ ይችላሉ።
ሰላም ባለበት ሀገር የስፖርት መሠረተ ልማቶች (ስታዲየሞች፣ ማሰልጠኛ ማዕከላት) ይገነባሉ፤ በስፖርቱ ዘርፍም ኢንቨስትመንት ይጨምራል። የወጣቶች ተሳትፎም ይመነደጋል። ሰላም ወጣቶች ትምህርታቸውን እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዲያዘወትሩ ያበረታታል። ከጥፋት እና ከብጥብጥ እንዲርቁ ያደርጋል።
ሰላማዊ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ገጽታ ይኖራታል፤ ይህም ዓለም አቀፍ የስፖርት ዝግጅቶችን ለማስተናገድ እና የሀገር ስፖርተኞች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እንዲሳተፉ ያስችላል። ሰላም የአእምሮ ሰላምን ይሰጣል፤ ይህም ስፖርተኞች በአካልም ሆነ በአእምሮ ጤናማ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ለአንድነት እና ማኅበራዊ ትስስር የሚያበረክተው አስተዋፅኦም ትልቅ ነው። ስፖርት ሰላም ባለበት ሁኔታ ሕዝብን ያቀራርባል፣ የጎሳ እና የኃይማኖት ልዩነቶችን አጥብቦ አንድነትን ይፈጥራል።
ሰላም ከሌለ ፍጹም ስፖርት የለም፣ ይህ አባባል እጅግ ትክክል ነው። ሰላም በሌለበት አካባቢ የስፖርት መሠረተ ልማት ይወድማል፤ ስታዲየሞች እና ማሰልጠኛ ስፍራዎች ይጎዳሉ ወይም ለሌላ ዓላማ ይውላሉ። ስፖርተኞች ይሰደዳሉ ወይም ሕይወትን እስከ ማጣት ለሚደርስ አደጋ ይጋለጣሉ። እነዚህንም ባለፉት ዓመታት ታዝበናል።
ሰላም ከሌላ የስፖርት ውድድሮች ይቋረጣሉ፣ የሊግ ውድድሮች፣ ቻምፒዮናዎች እና ሌሎች ዝግጅቶች ይቆማሉ። በዚህም በርካታ ብሩህ ተስፋ ያላቸው ወጣቶች ተስፋ ይቆርጣሉ። ስፖርት ተስፋ የሚሰጥበት እና ሕይወትን የሚቀይርበት መንገድ መሆኑ ቀርቶ፣ ወጣቶች ወደ ሌሎች አደገኛ መንገዶች ሊያመሩ ይችላሉ። ከዚያም አልፎ የሀገር ስም ይጎዳል። ሀገር በዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነቷን ታጣለች። ስለዚህ ስፖርት እና ሰላምን እንዴት አብሮ ማስቀጠል ይቻላል? ትልቁ ጥያቄ ነው።
ስፖርትና ሰላምን ለማስቀጠል ብዙ መንገዶችን መጠቀም ይቻላል። አንዱ የስፖርት ፕሮግራሞችን በሰላም ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነው። ለዚህም የስፖርት ፕሮግራሞች እንደ መቻቻል፣ መከባበር እና ግጭት አፈታት ያሉትን እሴቶች እንዲያበረታቱ ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል።
የስፖርት ዝግጅቶችን ለሰላም ግንባታ መጠቀም፣ የስፖርት ዝግጅቶች እንደ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ያሉትን ጉዳዮች ለማስተዋወቅ መጠቀም፣የስፖርት ሰዎችን እንደ የሰላም አምባሳደር መጠቀም፣ ታዋቂ የስፖርት ሰዎች በዓለም ዙሪያ የሰላም መልእክቶችን እንዲያስተላልፉ ማድረግ፣ መንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስፖርትና በሰላም ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታት ተገቢ ነው። እነዚህ አካላትም ለስፖርት ፕሮግራሞች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና ፖሊሲዎችን በመንደፍ አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላሉ።
ስፖርት ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ያለው ፋይዳ ብሔራዊ አንድነትን ከማጠናከር የተሻገረ ነው። ለዚህ ብሔራዊ የስፖርት ቡድኖች ሲሳካላቸው የሀገር ፍቅር ስሜት ምን ያህል እንደሚጨምር፣ ሕዝብም በብሔራዊ ማንነቱ ይበልጥ እንዲኮራ ሲያደርጉ ማስተዋል ይቻላል።
ስፖርት ሰዎች ከማኅበረሰባቸው ጋር በንቃት እንዲሳተፉ በማበረታታትና በዚህም ማኅበራዊ ትስስርን ማጠንከር መቻሉ ሌላው ትልቅ በረከት ነው። መቻቻልንና መከባበርን ማሳደግም በተመሳሳይ። ስፖርት ተሳታፊዎች የሌሎችን አመለካከትና ባሕል እንዲያከብሩ ያስተምራል። የጋራ መግባባትን የመፍጠር አቅም አለው። የተለያዩ ማኅበረሰቦችን አንድ ላይ በማምጣት የጋራ መግባባትንና ትብብርን ያበረታታልና።
ስፖርት በዘር፣ በፆታና በኃይማኖት ላይ የተመሰረቱ አድልዎዎችን ለመዋጋት እንደ መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግልም ይችላል። ሰዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲወዳደሩ በማስተማር ግጭቶችን ለመፍታት አማራጭ መንገድን ያሳያል። ወጣቶችን ከጥቃትና ከአደንዛዥ እፅ መከላከልም እንዲሁ። የወጣቶች የስፖርት ተሳትፎም መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው። ወጣቶች በራሳቸው ማኅበረሰብ ውስጥ የሰላም አምባሳደር በመሆን ለሌሎች አርአያ መሆን ይችላሉና።
ስፖርት ወጣቶችን በጤናማ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ከአሉታዊ ተፅዕኖዎች ይጠብቃል። ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማምጣት ስፖርት የስፖርት ኢንዱስትሪውን በማሳደግ የሥራ እድል ይፈጥራል እንዲሁም ለሀገር እድገት አስተዋፅኦ ያደርጋል።
ስፖርት እንደ ሀገር ለዘላቂ ሰላምን ለማስጠበቅ የሰላም አምባሳደሮችን መፍጠር ይቻላል። ለዚህም ታዋቂ የስፖርት ሰዎችን መጠቀም ይገባል። እነዚህ ሰዎች በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው በመሆኑ የሰላም መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ተስማሚ ናቸውና። ለዚህም በጨዋታዎች መክፈቻ እና መዝጊያ ላይ የሰላም መልዕክቶችን ማስተላለፍ፣ የሰላም ባንዲራዎችን ማንሳት፣ የሰላም መዝሙሮችን ማጫወት፣ እነዚህ የሰላም አምባሳደሮች በስፖርት ዝግጅቶች፣ በትምህርት ቤቶችና በማኅበረሰብ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍ የሰላም መልዕክቶችን ማስተላለፍ ይችላሉ።
በዚህ ረገድ የስፖርት አሰልጣኞችና አስተዳዳሪዎች የማይናቅ ሚና አላቸው። እነዚህ ሰዎች በወጣቶች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያላቸው በመሆኑ የሰላም እሴቶችን ለማስተማር ቁልፍ ሚና መጫወት ይችላሉ። የስፖርት ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን ሚናም ትልቅ ነው። በስፖርት ሽፋን የሰላም መልዕክቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ።
ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሀገር አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ተቋርጠው መቆየታቸው ይታወቃል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው ከፀጥታ ስጋት ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑ የተሸሸገ አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሀገሪቱ ያለው ሰላም እየተሻሻለ አስተማማኝ ፀጥታ እየሰፈነ መምጣቱን ተከትሎ ለዓመታት ተቋርጠው የነበሩ እንደ መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች አይነት በርካታ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ዳግም ተጀምረው በስኬት ሲጠናቀቁ እያየን እንገኛለን። ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ይህን አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያ ከስፖርት ማግኘት ያለባትን በረከቶች አሟጣ እንድትጠቀም መበርታት አለበት።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የነበሩ የፀጥታ ችግሮች አሁንም እንዳሉ ተጋኖ ሲወራ ማየትና መስማት የተለመደ ነው። የተቋረጡ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ዳግም መጀመራቸው ግን ብዙ የሚነግረን ነገር አለ። በዋናነት እነዚህ ሀገር አቀፍ ትልልቅ ውድድሮች ካለ አንዳች የፀጥታ ስጋት በስኬት የተካሄዱት ሰላም ስላለ ነው። “ሰላም ከሌለ ፍጹም ስፖርት የለም”! (There is no perfect sport without peace) የሚባለው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
ስፖርት የሰላም መሳሪያ ነው። ሰላም ሲኖር ስፖርት ይበለጽጋል፤ ስፖርት ሲበለጽግ ደግሞ ሰላምን የማስፈን አቅሙ ይጨምራል። የስፖርት ቤተሰብ ይህንን እውነታ ተገንዝቦ ለሰላም ዘብ መቆም አለበት። በስፖርት ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ለማስፈን ትልቅ አቅም አለው። መንግሥታት፣ የስፖርት ክለቦች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎች እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በጋራ በመሥራት ስፖርት የሰላም መሣሪያ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው። እያንዳንዱ ዜጋም በስፖርት ውስጥ መልካም አርአያ በመሆን ለሰላም መረጋገጥ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል።
ልዑል ከካምቦሎጆ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም