የኮሮናን ወረርሽኝ ለመከላከል ሰብዓዊነት ካሰባሰ ባቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እስከ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ከቤተሰብ እስከ ግለሰብ፣ ከደሃ እስከ ሐብታም ንቅናቄውን ያልተቀላቀለ፣ የመሪውን ጥሪ ያልተቀበለ፣ የድርሻውን ለማበርከት ደፋ ቀና ያላለ በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር በማህበረሰብ ረገድ ማግኘት ይቸግራል። ከተመለከትናቸው የቅድመ መከላከል በርካታ የበጎነት ተግባሮች አጃኢብ(ወይ ግሩም) ያሰኘንን ልንነግራችሁ ወደናል።
ወላጆቹን በሞት ካጣበት ከአራት አመቱ ጀምሮ ያደገው በ‹‹ኤስ ኦ ኤስ›› ሕጻናት ማሳደጊያ ነው።የድርጅቱን እንክብካቤ ከእናት ውለታ አያሳንሰውም። ሕጻናት በበጎ አድራጎት ድርጅቶች በኩል ሲያድጉ ሊገጥሙ የሚችሉ የሕይወት ውጣ ውረዶችን አጣጥሞ ያውቃቸዋል። ድጋፍ በሚፈልጉበት በዚህ የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ባንዣበበት ጊዜ ቀርቶ በሰላሙ ጊዜም ቢሆን ብዙ የማይደፈኑ የፍላጎት ቀዳዳዎች መኖራቸውን ሲያስታውስ ልቡ በሐዘን ይሰበራል። ፈተናዎች ሳይበግሩት በእነዚህ ቀዳዳዎች ሾልኮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባት ችሏል።ከዚያ ወዲህ ባለፈባቸው መንገዶች እየመጡ ላሉ አያሌ ሕጻናት ልምድ እንካችሁ ይላል። ወረርሽኝ በሽታም ሆነ ሌሎች የችግር ክምሮች ታልፈው ለአላማ መብቃት እንደሚቻል የመንፈስ ብርታትን ከተሞክሮው እንዲቀስሙ ይመክራል።
ሌላም የሕይወት ገጠመኝን አስተናግዷል።የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ጊዜ የተካሄደው የ1997 ዓ.ም ምርጫ ግርግር ለእሱ ጦስ ያስከተለ ነበር፤ አዲስ አበባ ሜክሲኮ ኒያላ አካባቢ በተፈጠረ የመኪና አደጋ ተጎድቷል፤ እስከ ውጪ አገር ድረስ ከባድ የሕክምና ሂደቶችን አልፎ በዊልቸር የሚንቀሳቀስ መንፈሰ ጠንካራና ልበ ሩህሩህ ሰው እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ሰው ወጣት ኃይለሚካኤል ዋስይሁን ይባላል። የልደታ ብርሃን ከብሎክ አንድ እስከ 14 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤቶች ኃላ/የተ/የኅ/ሥ/ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ነው።ትናንት እርሱ በሕጻናት ማሳደጊያ በበጎ ሰዎች ጥረት አሳልፏል።ዛሬ እርሱ ለወገኖቹ መድረስን የዜግነት ግዴታው አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡
አቶ ኃይለሚካኤል፣ በአለም ላይ ጥላሸት ያጠላው የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያም መከሰቱን ተከትሎ በአቅመ ደካሞችና የእለት ጉርስ በሚቸግራቸው ዜጎች ላይ በሽታው ከባድ ችግሮች እንዳያስከትል ዜጎች እንደየአቅማቸው በመርዳዳት እንዲረባረቡ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።በዚህ መነሻነትና በማህበሩ አባላት ነዋሪዎች አነሳሽነት ለቀለብና ለሕክምና አገልግሎት ይውል ዘንድ በአይነትና በገንዘብ ያሰባሰቡትን ለማስረከብ በግንቦት ልደታ ማግስት ከባልደረቦቹ ጋር ስለናት በጎ አድራጎት ድርጅት ቀዬ ሳር ቤት ተገኝቷል። የማህበሩ አባላት ከእለት ጉርሳቸው እየቀነሱ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ማሳለጫ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባለፈ በዚህ የችግር ጊዜ ለወገናቸው መድረስ እንዳለባቸው በመወሰን ማሰባሰባቸውን አስረድቷል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት ኮማንደር ባህሩ እና ኢንስፔክተር አብይ በተባበሯቸው የድምጽ ማጉያ ሞንታርቦ በመቀስቀስ በአጭር ጊዜ 60 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ በማሰባሰባቸው ተደስቷል።በመሆኑም ከኮሮና ወረርሽኙ መከላከል በተጨማሪ ለሕዳሴው ግድብና ለልብ ሕሙማን የሚሆን አስተዋጽኦ በቅንጅት እንደሚሰሩ በአባላቱ ላይ ያሳደረውን እምነት ተናግሯል።
የመልካምነትን እና የበጎነትን ዋጋ ከእሱ በላይ አይቶ ያደገ አለመኖሩን የገለጸው አቶ ኃይለሚካኤል፣እናት አባት የወለዷቸውን ልጆች የማሳደግ ግዴታዎች አሉባቸው፤ ነገርግን ሕጻናት ማሳደጊያዎች ሰው የመሆን የአስተሳሰብ ልዕልና አስገድዷቸው ባልወለዷቸው ልጆች በርካታ ፈተናዎች ይከፍላሉ፤ ከወደቁበት አንስተው ለወግ ለማዕረግ ያበቃሉ፤ የኮሮና ወረርሽኙ ደግሞ ልፋታቸውን እጥፍ ድርብ ያደርግባቸዋል፤ ሥለሆነም በዚህ ወቅት ከጎናቸው ሆኖ ከሚደርሱባቸው ችግሮች መከላከልና መደገፍ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
የልደታ ብርሃን ከብሎክ አንድ እስከ 14 ኮንዶሚኒየም ነዎሪዎች ማህበር ዋና ሰብሳቢ አቶ በለጠ ተሾመ በበኩላቸው፣ ድጋፉ ከማህበሩ አባላት በፈቃደኝነት የተሰበሰበ ነው። ወረርሽኙ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት አሻራን ከማሳረፍ የሚቆጠር ነው።በመሆኑም ወረርሽኙ በሕጻናት ማሳደጊያዎች ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ እነዚህን ሁኔታዎች በመደጋገፍ ማለፍ እንዲቻል የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሆነ ገልጸዋል።
ከነዋሪው ማህበረሰብ የተበረከተ በአይነት 18 ሺህ 745 የሚሆን ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ፣ ዱቄት፣ ሳሙና፣ ዘይትና ስኳር የተሰበሰበ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ ደግሞ 38 ሺህ 389 ብር በመሰብሰብ ለስለናት በጎ አድራጎት ድርጅት አስረክበዋል።
የስለናት በጎ አድራጎት ድርጅት አስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ ካሳሁን ከበደ እንዳሉት፣ በ1994 ዓ.ም በኤች አይ ቪ ወረርሽ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት በየቦታው ተጥለው በሚገኙበት ጊዜ ችግሩን ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ለማቃለል የተቋቋመ እንደሆነ አስረድቷል።ድርጅቱ አሁን ላይ በአምስት ሕጻናት ተኮር እና በሁለት ሴት ተኮር በሰባት አጠቃላይ ፕሮግራሞች ላይ እየሰራ ይገኛል።
የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ አገልግሎት ይሰጣል። በማህበረሰቡ ውስጥ ከወላጆቻቸው ጋር የሚገኙ ለችግር የተጋለጡ ሕጻናት ለምግብና ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎች እንዲሆን በወር 360 ብር ይሰጣል፤ ከወላጆቻቸው የተለያዩ ሕጻናትን መልሶ እንዲቀላቀሉ ያደርጋል።ለ20 ተማሪዎች ቤት ተከራይቶ ሙሉ ወጪ በማሟላት ይረዳል።በተቋሙ ውስጥ ከ32 በላይ ሕጻናት ይንከባከባል።የአካልና የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸውን 12 ሕጻናት ይንከባከባል።በአዲስ አበባ ከ105 በላይ ሕጻናት እናቶቻቸውን በማጠናከር የትምህርት ግብዓት ያግዛል።ሻሸመኔ 50 የሚሆኑ ሕጻናትን ይረዳል።ከ45 በላይ ሰራተኞች እና 17 ሞግዚቶችን ይዞ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ ሳይኖረው ከማህበረሰቡ በሚያገኘው ድጋፍ የተመሰረተ እንደሆነ ተናግረዋል።በመሆኑም በኮሮና ወረርሽኙ ምክንያት ለሕጻናቱ ደሕንነት ሲባል የሚጎበኝ አካል የለም። ከበጎ አድራጊዎች በሚገኙ የምግብ፣ የንጽሕና መጠበቂያ እና ሌሎች ድጋፎች እየቀጠለ እንደሆነ ገልጸው፤ ለተበረከተላቸው ስጦታ በሕጻናቱ ስም በማመስገን እንዲህ አይነት በሰብዓዊነት የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሕጻናትን ጤና ከወረርሽኙ በምን መልኩ እየጠበቃችሁ ነው? በሚል ላነሳንላቸው ሲመልሱ በሽታውን ለመከላከል የሚሰራው ስራ ከሰራተኞች ይጀምራል።በፊት ተመላልሰው የሚሰሩትን አሁን ላይ በፈረቃ ለ15 ቀናት ያህል ሰራተኞች እዚሁ ሆነው በመንከባከብ ላይ ናቸው፡፡ሌላው የድርጅቱ ሰራተኛ ለወር ያህል እዚሁ በመሆን ስራውን እየሰራ ነው።ይህ ሁኔታ በምልልስ የሚፈጠር ችግርን ይቀንሳል።ከልጆች ጋር የሚኖረው ንክኪ እንዲቀነስ ተደርጓል።የሚጎበኛቸውና ድጋፍ የሚያደርገው ማህበረሰብ ከሕጻናት ጋር አይገናኝም።በድጋፍ የሚገኙ ማስኮችና ሳኒታይዘሮች በተገቢው እንዲገለገሉባቸው ይደረጋል ሲሉ የሚደረጉ የመከላከል ስራዎችን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት ሕጻናቱን ሰዎች ከመካከላቸው በመገኘት አቅፈው በመሳም ድጋፍ የሚያደርጉላቸው በመሆኑ አሁን ላይ ይህ ሁኔታ ሲቀር በሕጻናቱ ላይ የሚስተዋሉ የስነልቦናና የጤና እክሎች ይኖሩ ይሆን? በሚል ላነሳንላቸው ሐሳብ፤ አሁን ላይ ከትምህርት ቤትም ቀርተው በግቢ ብቻ እየዋሉ በመሆኑ አልፎ አልፎ የሚታዩ ስሜቶች አሉ።የመኪና ድምጽ ሲሰሙ ለማየት የመፈለግ ሁኔታዎች ይታያሉ።በመሆኑም በመምከርና በጨዋታ ችግሩ ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው ይደረጋል ሲሉ ተናገረዋል፡፡
ድሮ ብዙ የማይታወቀው ድርጅት ወረርሽኙ በፈጠረው አጋጣሚ በማህበረሰቡና በመንግስት አካላት የመጎብኘትና የድጋፍ አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን አቶ ካሳሁን በመልካም አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንዳች አዲስ ጉዳይ ለዓለም ማህበረሰብ የሚያበረክት ሳይሆን እንደማይቀር የዘርፉ አጥኝዎች ይተነትናሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
ሙሐመድ ሁሴን