ኮሮና ቫይረስን በሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ማቆም የሚቻል አይመስልም። የስርጭት መንገዱ ከሰው ውስብስብ ባሕርይ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ማቆም የሚቻለው የተለያዩ ነገሮችን በመቀናጀት ነው። በተለይ እንደ ሕግ፤ ሥነ-ልቡና፤ ግብረገብ፤ ሥነ-ምግባር፤ ሃይማኖትና መሰል መንፈሳዊ እሴቶች በእጅጉ ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ ሳይንስ ወረርሽኙ የሚቆምበትን መንገድ ሊያሳየን ይችላል። መንገዱን ማወቅ ጠቃሚ ነገር ቢሆንም ብቻውን ዋጋ አይኖረውም። የተገኘውን መንገድ በትክክል ተግባራዊ ለማድረግ ከላይ የተጠቀሱ የዕውቀትና እምነት ዘርፎች እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው።
ይህን ወረርሽኝ ለመግታትና ለማስወገድ በመጀመሪያ የሚታሰበው ክትባትና መድኃኒት ነው። ይሁን እንጂ ወረርሽኙ ክትባትም፤ መድኃኒትም የለውም። ክትባት ወይም መድኃኒቱ እስኪገኝ ድረስ ኮሮና ቫይረስ ለመግታትና ለማጥፋት የሚከተሉትን ነገሮች አጥብቆ መከታተልና ማድረግ ያስፈልጋል። አንደኛው የባለሙያዎችንና የመንግሥትን መመሪያዎች፤ ህጎችና ደንቦችን ማክበር፤ የሃይማኖት አባቶችንና ተቋሞችን ትምህርትና ምክር አጥብቆ መከተል፤ ሶስተኛ ትክክለኛ መረጃ ማግኘትና መጠቀም፤ አራተኛ በመረጃው መሠረት ራስን ለዲስፕሊን ማስገዛት፤ አምስተኛ የግብረገብና ሥነ-ምግባር ሕግጋትን ማክበር፤ ስድስተኛ ከእምነት አንጻር የፀና አቋም መያዝ።
ዓለምን በፍጥነት ሊታደግ ስለሚችል ነገር ሲታሰብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዳለ ሆኖ ግብረገብን፤ ሥነ-ምግባርን፤ አምልኮትንና ሌሎች መንፈሳዊ እሴቶችን ከመጠቀም ውጭ ሌላ ምርጫ ያለ አይመስልም። ፀሎት ማድረግ፤ የግብረገብና የሥነ-ምግባር ሕግጋትን ማክበርና ራስን ለዲስፕሊን ማስገዛት በቀላል ማንም ሊፈፅማቸው ይችላል። በተለይ መወሰንና ማድረግ የግድ በሚሆንበት ጊዜ የግብረገብ ሕግን መጠቀም ብቸኛ ምርጫ ይሆናል። አንድ ሰው በሌላ ሰው ደህንነት ላይ ወስኖ እርምጃ መውሰድ የሚጠበቅበት ከሆነ በመጀመሪያ “እንዲህ ዓይነት ችግር በእኔ ላይ ቢደርስ ምን ይሰማኛል? ምንስ ማድረግ አለብኝ? ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት። እንዲደረግለት የሚፈልገው ነገር አለ። እርሱም መልካም ነገር ነው – መልካም ነገር ይጠቅማል፤ ያረካል፡ ያስደስታል፤ ምቾት ይሰጣል። ስለዚህ ይህ ሰው ሰዎች እንዲያደርጉለት የሚፈልገው የሚጠቅመውን፤ የሚያረካውን፤ የሚያስደስተውንና ምቾት የሚሰጠውን መልካም ነገር ነው።
በግብረገብ ኑባሬነቱ ሰው ለራሱ የሚፈልገውን መልካም ነገር ለሌላም ሰው እንዲሆን መፍቀድ ይጠበቅበታል። እንዲደረግበት የማይፈቅደው ነገር አለ። እርሱም መጥፎ ነገር ነው። መጥፎ ነገርን፤ ድርጊትን ወይም ባሕርይን የማይፈቅደው ስለሚጎዳው፤ ስለሚያሳዝነው፤ ስለማይመቸው ነው። ስለዚህ ማንም ሰው የሚጎዳውን፤ የሚያሳዝነውንና የማይመቸውን መጥፎ ነገር እንዲፈፀምበት አይፈቅድም። እርሱም ማንም ሰው እንዲያደርግበት የማይፈቅደውን መጥፎ ነገር በሌላ ሰው ላይ ማድረግ አይጠበቅበትም።
ትክክለኛ መረጃ፡- መረጃ መከታተል ዛሬ የሕይወት ጉዳይ ሆኗል። ትክክለኛ መረጃ መስጠትና መቀበል እጅግ ወሳኝ ነው። የውሸት መረጃ መቀበልና ማስተላለፍ አደጋ መፍጠር ነው። ትክክለኛ መረጃ በውል ከሚታመን ምንጭ የሚገኝ መረጃ ነው። ካልተረጋገጠ ምንጭ የሚመጣውን መረጃ ተቀብሎ ከማስተላለፍ መቆጠብ ያስፈልጋል።
ራስን ለዲስፕሊን ማስገዛት፡- ቸልተኝነትና አለመደማመጥ ለኮቪድ – 19 ጉልበት መሆን ነው። በኢትዮጵያ ቸልተኝነትና አለመደማመጥ በበርካቶች ዘንድ እንደ ጉድለትና ጥፋት የሚታዩ አይደሉም። በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ አይደለም የብዙ ሰዎች ያንድ ሰው ቸልተኝነት ራሱ ሀገርን ውድ ዋጋ ያስከፍላል። ቸልተኝነትን ማስወገድ የመፍትሔ አካል መሆን ነው፤ ቸልተኛ መሆን ግን የችግሩ አካል ለመሆን መፍቀድ ነው። የመንግሥትን፤ የእምነት አባቶችን፤ የባለሙዎችን ሕጎች፤ መመሪያዎችና ምክሮችን መጣስ ብቻ ሳይሆን ሕዝብንና ሀገርን ለአደጋ ማጋለጥ ነው። ራሱን ለዲስፕሊን ተገዢ ያደረገ ሰው “ሰው አየኝ-አላየኝ” ሳይል ሕጎችንና መመሪያዎችን አድምጦና ተቀብሎ ይተገብራል። ሁላችንም ለሀገራችና ለህዝባችን ስንል ቃል መግባት አለብን – ፈቅደንና ወደን የመፍትሔ እንጂ የችግር አካል እንዳንሆን።
የግብረገብና ሥነምግባር ሕግጋትን ማክበር፡- የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለማቆም እጃችንን ደጋግመን በሚገባ መታጠብ፤ ቢያንስ በሁለት ሜትር ያህል መራራቅ፤ አለመጨባበጥ፤ አለመተቃቀፍና ሌሎች የተከለከሉ ነገሮችን ከማድረግ መታቀብ ያስፈልጋል። እነዚህ ቫይረሱን ማቆም የሚያስችሉ መንገዶች ናቸው። የኮቪድ – 19 የግብረገብ ሕጎች ናቸው ልንል እንችላለን። “አድርጉ” የተባልነውን ማድረግ፤ “አታድርጉ” የተባልነውን አለማድረግ ነው። ለዚህ የምንጠየቀው ወጭ ወይም የምንከፍለው ዕዳ የለም፤ ከየትም የምናመጣው ወይም ለማንም የምንሰጠው አይደለም። እነዚህ በእጃችን ላይ ያሉና በአእምሮአችን ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ሃይማኖት፡- ሃይማኖቶች የሰው ልጅን ውስጣዊ ሕይወት በተስፋ በመሙላት፤ የሥነ-ልቡና ድጋፍ በመስጠት፤ ማሕበራዊ ሕይወትን በማረጋጋት፤ እኩይ አስተሳሰቦችንና ምግባሮችን በመቀነስና በማዳከም ሰዎችንና ሀገሮችን ይታደጋሉ። ዓለምን በእጅጉ እየጎዳ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ፈጣሪ እንዲያስወግደው ቤተ-እምነቶች ሁሉ በራሳቸው መንገድ ይፀልያሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብና የኮሮና ቫይረስ
ኢትዮጵያውያን በችግር ጊዜ አብሮ የመቆም ባህላቸው ጠንካራ ነው። አንዱ ሲወድቅ ሌላው ቆሞ አያይም። መውደቅን መከላከል ካልቻለ እንኳ ቆሞ ከማየት አብሮ መውደቅን የሚመርጡ ዜጎች መኖራቸው ይታመናል። ይህ የሁሉም ዜጎች ባሕርይ ነው ማለት ግን አይቻልም። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ኢትዮጵያ የሰው ቆዳ የለበሱ ጅቦችንም ፈጥራለች። ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥታዊ ሥርዓት ድረስ ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ገደብ በሌለው ራስ ወዳድነት ሀገርንና ሕዝብን የጋጡ ዜጎች ነበሩ። የተገኘውን ሁሉ ከሀገርና ከሕዝብ ቀምተው የራሳቸው ለማድረግ የጣሩ መሪዎች የነበሩትን ያህል፤ በተቃራኒው ከዚህም ከዚያም ለምነውና ለማምነው ዜጎችን ለመታደግ የሰሩ መሪዎችንም አፍርታለች – ኢትዮጵያ።
ኮሮና ቫይረስ ያመጣውን አደጋ እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም በቤት ኪራይ ዙሪያ ችግር የፈጠሩ ሰዎች፤ ሸቀጦችንና የፍጆታ ዕቃዎችን ዋጋ የሰቀሉ፤ ተፈላጊና መሠረታዊ የሆኑ ሸቀጦችን የደበቁ፤ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ከተለያዩ ባዕድ ነገሮች ጋር እየደበላለቁና የመጠቀሚያ ጊዜ የተላለፈባቸውን ነገሮች የሚሸጡና ሌሎች መሰል ፀያፍ ድርጊቶችን የፈፀሙ ዜጎች ተስተውለዋል። ኮሮና ቫይረስ በቻይና ተከስቶ በፍጥነት መሰራጨት ከጀመረና በተለይ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ በሀገራችን በቤት ኪራይ ዙሪያ የተነሳውን ውዝግብ ለማሳያ ብቻ እናነሳለን።
አንዳንድ ሰዎችና ቤተሰቦች “ኮሮና ቫይረስን ታመጡብናላችሁ” ብለው ተከራዮችን ቤት እንዲለቁላቸው ጠይቀዋል የሚል መረጃ በቅብብሎሽ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲተላለፍ ነበር። ይህ ለብዙዎች አስደንጋጭ ነው። ከመቸውም ይበልጥ በጋራ ቆመን የወረርሸኑን አቅም መስበር በሚገባበት ጊዜ ተከራዮችን ሂዱልን ማለት ከሕግም፤ ከሞራልም፤ ከሃይማኖትና ከዜግነትም አንጻር የሚከብድ ነው። የሰው ልጆችን የተፈታተኑና የሚፈታተኑ ብዙ ነገሮች አሉ። አንዱ ያልታሰበ፤ ፈጽሞ ያልተገመተ ችግር ሲከሰት የሚፈጠር ፈተና ነው። ዛሬ ኮሮና ቫይረስ ለሰው ልጆች ሁሉ ባልታሰበ ጊዜና መንገድ የተከሰተ አደጋ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለማችንን አሽመደመዳት።
በዚህ ምክንያት የዓለም ሕዝብ ግዙፍ በሆነ የፍርሃት ድባብ ውስጥ ነው። ሕይወት ነውና እንፈራለን። አንዳንዶቻችን ከምንም በላይ ለራሳችን እንፈራለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ ለቤተሰባችን፤ ለልጆቻችን፤ ለዘመዶቻችን፤ ከዚያም አልፎ ባጠቃላይ ለሀገር፤ ለሕዝብና ለዓለማችን ስንል እንፈራለን። ይህ ተገቢ ፍርሃት ነው። ተገቢ የሆነ ፍርሃት ያለውን ያህል ተገቢ ያልሆነ ፍርሃትም አለ። በሌሎች ምክንያት ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ ወገንን ወዳልታሰበ አደጋ የመግፋት ጉዳይ የሚፈጠረው አግባብ ባልሆነ ፍርሃት ነው። ከላይ የተጠቀሰው የአከራይ – ተከራይ ጉዳይ በዚህ ዓይን መታየት ይችላል። በዚህ የመከራ ጊዜ ቤት ልቀቅልኝ ማለት ማንም ሰው እንዲደረግበት የማይፈቅደውን መጥፎ ነገር ወገኑ በሆነው ሌላ ሰው ላይ እንዲደረግ መፍቀድ ስለሆነ ከሞራል አንጻር የማይገባ ወይም የማይታሰብ ነው።
መግፋት በምንም መለኪያ የሚደገፍ አይደለም። ፍርሃትን መቋቋም ደግሞ ከሰው ሰው ይለያል። አንዳንዱ ቀደም ሲል ያልነበረውን ባሕርይ ወዲያው ያሳያል – ይረበሻል፤ ይሸበራል፤ ይበሳጫል፤ ይጨናነቃል ወዘተ. ይህ የፍርሃት ስሜቱን በምክንያት መቆጣጠር በማይችል ሰው ላይ የሚታይ ነው። አንዳንዱ ፍርሃትን በምክንያት ይቆጣጠራል። በምክንያት የፍርሃት ስሜቱን መቆጣጠር የሚችል ሰው ራሱን ያረጋጋል፤ ነገሮችን ያመዛዝናል። ከውሳኔ የሚደርሰውና እርምጃ የሚወስደው አውጥቶና አውርዶ፤ ጥቅምና ጉዳትን፤ ትርፍና ኪሳራን፤ መልካምና መጥፎውን ለይቶ ነው። አንዳንድ አካራዮች ተከራዮቻቸውን በዚህ የጭንቅ ሰዓት ቤት ልቀቁልን ብለው መጠየቃቸው በፍርሃት ምክንያት ሊሆን ይችላል።
በእርግጥ በአካራዮችም ሆነ በተከራዮች በኩል ሊታዩ የሚችሉ ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ለማንኛውም ከሕግም ሆነ ከማሕበራዊ ደንቦች፤ ከግብረገብና ሥነ-ምግባር መርህዎች አንጻር ፍጹም የሚነቀፍ እንጂ የሚደገፍ አይደለም። የሰው ስብዕና የሚፈተነው በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ነው። ምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ በማይኖርበት ጊዜ ሁሉም ሰው ያው ሰው ነው። ጦርነት በሌለበት ቦታ ማን ጀግና፤ ማን ፈሪ እንደሆነ መለያት ያስቸግራል። የሰው መልካምነት፤ ደግነት፤ ቅንነት፤ ርህሩህነት፤ አስተዋይነት ወዘተ የሚታወቀው በእንዲህ ዓይነት የመከራ ጊዜ ነው። በዚህ ፈታኝ ጊዜ ሰው ሰብአዊ ለሆነ ሰው ርህራሄን ማሳየት አለበት። “አለሁልህ፤ ከጎንህ ነኝ፤ አብረን ነን፤ ተጋግዘን፤ ተደማምጠን፤ ያለንን ተካፍለን ፈተናውን እናልፋለን” የሚባባሉበት ጊዜ ነው።
ቤትን በሰላም ጊዜ አከራይቶ የመከራ ቀን ልቀቅልኝ ማለት ነውር ነው። ይህ የሞራል ኃላፊቱን የመወጣት ብቃት ወይም አቅም የሌለው ሰው ድርጊት ነው። የጭንቅ ቀን ሁሉም ሰው ለማንኛውም ሰው ሕይወትና ደህንነት የኃላፊነት ስሜት ሊኖረው ይገባል፤ ሁሉም ሰው ለእያንዳንዱ፤ እያንዳንዱም ሰው ለሁሉም ሰው መቆም አለበት። የሚያዋጣው መገፋፋትና መጨካከን ሳይሆን መተዛዘንና መረዳዳት፤ መደማመጥና መቻቻል ነው። ሰው ለሰው መድኃኒት የሚሆንበት እውነተኛ ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።
በሁለት ነገሮች ምክንያት አከራይ ተከራይን ቤት ልቀቅልኝ ሊል ይችላል። ለራስ ወይም ለቤተሰብ ብዙ ከመጨነቅ አንድ ሊሆን ይችላል። ይህ ከላይ እንደተጠቀሰው ፍርሃትን በምክንያት መቆጣጠር ካለመቻል የሚመጣ ነው። የተከራዮች ባሕርይ አስቸጋሪነት ሌላው ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ተከራዮች የሚገኙበት መስመርና ያላቸው ባሕርይም መታየት አለበት። አንዳንዶቹ የግብረገብ መርህዎችን የማያውቁና የማያከብሩ፤ ዲስፕሊን የሌላቸው፤ እንዳስፈለገንና እንዳሰኘን መሆን መብታችን ነው የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ። መልካም ስብዕና የሌላቸው፤ የመፍትሔ አካል ለመሆን የማይፈቅዱ፤ በራሳቸው የግል ጉዳይ ላይ የተጠመዱ፤ ያለ ሰዓት ወጥተው የሚገቡ፤ ጠጥተውና ተሳክረው የሚያስቸግሩ፤ በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ፤ አፍ ለአፍ ገጥመው ጫት የሚቅሙና ሌሎች መሰል ችግሮች ያሉባቸው ዜጎች ለኮሮና ቫይረስ ጥቃት በቀላሉ የሚጋለጡ ናቸው። ካለው ጊዜ አንጻር የእነዚህ ተከራዮች ባሕሪ እጅግ አሳሳቢ ነው።
ይሁን እንጂ በኮሮና ወረርሽኝ ጊዜ ለራስ ማሰብንና ለሌላ ማሰብን ለያይቶ ማየት ያስቸግራል። ለራስ መጠንቀቅ ማለት ለሌላም መጠንቀቅ፤ ለሌላ መጠንቀቅ ማለት ለራስም መጠንቀቅ ማለት ነው። ለራሱ የማይጠነቀቅ ሰው ለሌላው ይጠነቀቃል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። ሰው በአካልም በነፍስም አንድ የሆነበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። በኮሮና ዘመን ተከራይን ቤት ልቀቀኝ ማለት በሌሊት ከቤት አውጥቶ ለጅብ የማቀበል ያህል ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ እያንዳንዱ ሰው የመፍትሔ እንጂ የችግር አካል መሆን አይጠበቅበትም። ለሁሉም ሰው ማሰብና መጠንቀቅ አለብን። አድርጉ የተባልነውን በማድረግና አታድርጉ የተባልነውን ባለማድረግ የሀገርን ከባድ ሸክም፤ የሕዝብን፤ የመንግስትንና የባለሙያዎችን ውስብስብ ኃላፊነትና ጭንቀት መጋራት የሞራልና የዜግነት ግዴታ ነው። ለሚነገረንና ለምንጠየቀው ማንኛውም ነገር ዋጋ መስጠት አለብን። ነገሮችን በመናቅ እንዳንተላለቅ። በዘመነ ኮቪድ-19 ነፃነቴ ነው፤ መብቴ ነው የግል ጉዳዬ ነው የምንለው ነገር ብዙ የለም። ገደብ ተጥሎብናል – መፈንጨትና መወራጨት አንችልም። መንግሥት አይደለም ገደብ የጣለብን – ኮሮና ቫይረስ ነው። ቫይረሱ ከመምጣቱ በፊት የትም በዋለው እጃችን የፈለግነውን ነገር መንካት እንችል ነበር። ዛሬ ይኸን ማድረግ የኤሌክትሪክ ገመድ የመጨበጥ ያህል አደጋ ሆኗል።
ይሁን እንጂ እነዚህን ኢ-ግብረገባዊና ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የህዝብ፤ የመንግሥት፤ የሚዲያና የበጎ ፈቃደኛ ዜጋ ድምፅ ከጫፍ እስከ ጫፍ ከማስተጋባቱ በላይ በጎ አድራጊ ዜጎች፤ ተቋሞች፤ ኩባኒያዎች፤ ባንኮች፤ ወጣቶች በመረባረብ ከላይ የጠቃቀስናቸውን መጥፎ አዝማሚያዎች አርግበውታል። ግብረገባዊነትና ሥነ-ምግባራዊነት አቆጥቁጦ ኢ-ግብረገብነትና ኢ-ሥነ ምግባርነት ከፊታችን የደቀኑትን መጥፎ አደጋዎች ገፈውልናል። ከወጣቶች እስከ አዛውንቶች፤ ከተራ ዜጎች እስከ ከፍተኛ የሀገር ባለሥልጣናት፤ ከግለሰብ እስከ ተቋማት-ኩባኒያዎች፤ ባንኮች፤ ድርጅቶችና መንግሥታዊ አካላት ሁሉ ያካተተ የበጎ ፍቃድና እርዳታ እንቅስቃሴዎች ተደረጉ። እጅግ ብዙ የአልባሳትና የመጠለያ፤ የምግብና የገንዘብ፤ የአስቤዛና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ተደረጉ። በዚህ ረገድ የተደረገው ርብርብ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለወገኖቻቸው የሚቆረቆሩ ወይም የሚቆጩ ደጋጎች መሆናቸውን አስመስክረዋል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ምክንያት በአካል ነው ተራራቁ የተባልነው እንጂ በመንፈስና በሐሳብ አትቀራረቡ አልተባልንም። በሰላም ጊዜ አከራይቶት በአንዲህ ዓይነት የጭንቀት ጊዜ ልቀቅልኝ ማለት በጣም ነውር ነው። እንዲህ ባዩ የሞራል ኃላፊነት የማይሰማው ሊሆን ይችላል።
ውድ አንባቢዎች በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ ሃሳቤን አካፍላችኋሁ፤ መልካም ሳምንት።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
ጠና ደዎ(ፒ.ኤች.ዲ)