እርግጥ ነው ዓለምን ከሚያንቀጠቅጡ ቃላት ተርታ የማይጠፉትን ደሀ(ነት)፣ ልማት፣ እርዳታ፣ ልገሳ/ለጋሽ አገራት፣ ሰብአዊ መብት፣ ፈንድ፣ ብድር፣ ድጋፍ፣ ዩኤስኤይድ፣ ቻይናኤይድ፣ የካናዳ ስንዴ፣ ወጪ/ገቢ (Import/Export) ወዘተ የሚያስታውስ ሰው ምን ያህል የአገራት ዓለም አቀፍ ግንኙነት በተወሰኑ ገዥ ቃላት ላይ እንደተንጠለጠለ ሳይዘገይ ይረዳል። በተለይ ጉዳዩን ወደ ታዳጊ አገራት ለመለሰው ከእነ ሀቲቱ ቁልጭ የማለቱ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው።
በዚህ በንግድ/እርዳታ፣ እነዚህን ተገን ባደረጉና ኑሯቸውን በእነዚሁ ስር የሚገፉ ወገኖችን በተመለከተ ያልተባለ ነገር አለ ለማለት ቢከብድም ከእነዛ መካከል ሚዛን የሚደፉት ግን በጣም ጥቂት ሲሆኑ አንዱም የግራሀም ሀንኮክ “Lords of Poverty: The Power, Prestige, and Corruption of the International Aid Business.” መጽሐፍ ነው፡፡
እንደ አንድ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኘ መጽሐፍ የሀንኮክን እናንሳ እንጂ ከዚያ በፊት የኛው ሰው በዚሁ ጉዳይ ላይ ከጊዜው በቀደመ መልኩ አብዝቶ የተናገረ፣ የተነተነና ያስገነዘበ ሰው ያለ ሲሆን እሱም በ1956 “ምልክአም ሰይፈ ነበልባል” ሥራው “ለብድርና እርዳታ ስንል የአካልና የመንፈስ ነፃነታችንን መሸጥ የለብንም” ያለው ነው። አቤ ጉበኛ በዚህ መጽሐፉ “ልቦለድ ፃፈ” ከማለት ይልቅ “ፖሊሲ አረቀቀ” ማለቱ ይቀላልና የደራሲውን ሙሉ ሰብእና ስናደንቅ ዛሬ “መንግሥት ለመሆን እየገሰገስኩ ነው” የሚሉና ወደ 150 የተጠጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንዲት የማንነታቸው ገላጭ ማኒፌስቶ እንኳ የሌላቸው መሆኑን በመታዘብ ነው። ደሞም እኮ ካንዳንድ ደካማ ፖሊሲዎች “ምልክአም ሰይፈ ነበልባል” በእጅጉ እንደሚሻል መናገር “ከአቤ የወገነ” አስብሎ እንደሱ የሚያስከስስ አይሆንምና “የተሻለ” መሆኑን መናገር ተገቢ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንሰማው ሚጢጢዬ ጭምጭምታ በዚሁ “Trade and Aid” ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን፤ ከማጠንጠንም ባለፈ በ”Sino-French rela¬tions” ወይም “Franco-Chinese relations” ስያሜው በሚታወቀው የፈረንሳይና ቻይና ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ደቅኖ መገኘቱና፤ የዚህም መሽከርከሪያ ምህዋሩ አፍሪካ መሆኗ ነው።
እንደሚታወቀው የአገራት (መልካምም ይሁን አይሁን) ግንኙነት መመስረቻ ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው። ሃይማኖት ሊሆን ይችላል፣ ጦርነት ሊሆን ይችላል፣ ንግድ (እንደ ጥንቱ ሲራራ ነጋዴ)፣ ድንበርተኝነት፣ ርእዮተ ዓለም፣ እርዳታ መስጠት/መቀበል፣ ብዙ ናቸው። ለዛሬ ሲኖ-ፈረንሳይን ጠቅሰናልና በዚያው ላይ ብቻ እናተኩር።
ቻይናን የገጠማት ፈተና ይህ ብቻም አልነበረም፤ “The Eight-Nation Alliance” በሚባል በሚታወቀው ጥምረትና ጦርነት ስምንት አገራት (ዩኤስኤ፣, ግሬት ብሪቴን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ አውስትሮ-ሀንጋሪ፣ ጣሊያን፣ ሩሲያ፣ እና ጃፓን) ከበው የቀጠቀጧት ሲሆን ተቋቁማቸው እዚህ የደረሰች አገር ነች (ልክ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት እኛን ገጥሞን እንደነበረው ማለት ነው)። ዛሬ ደግሞ ኮሮና። ወደ ፈረንሳይ እንምጣ።
የፈረንሳይ ታሪክ እንደሌሎች ኃያላን ሁሉ ታሪኳ እንደ ነጠላ ቁጨት ዘርፈ-ብዙ ነው። በቅኝ ግዛት ጉድፍ ውስጥ አለችበት፣ በሥልጣኔም ሆነ ገቢ/ወጪ ንግድ እንደዚያው። የፈላስፎች አገር መሆኗ ስሟን እንደሚያስጠራው ሁሉ በፖለቲካ-ኢኮኖሚውም ስማቸው ከሚጠሩትም ጎን ነች። በመሆኑም ፈረንሳይ ሁሉም ጋር አለች፤ ለየት የሚያደርጋት አንድ ነገር ቢኖር ከአፍሪካና ቀኝ ገዥነት ጉድፏ ጋር በተያያዘ ያለው ሲሆን፤ ይህም ከቻይና ጋር “Trade and aid” ወደ “Trade or aid” እየተዛወረና አተካሮን እየፈጠረ መሆኑን እንየው።
ምንም እንኳን ጉዳዩ የግል አረዳድ ቢሆንም ነገሩ እንዲህ ነው። ቀደም ባለው በዘመነ ቅኝ ግዛት ከአንድና ሁለት አገራት በስተቀር የአፍሪካ አገራት በኃያላኑ ቅርምት ስር ወድቀው፤ ቅርጫው ተከፋፍሎ ነጮቹም የየድርሻቸውን የያዙ ሲሆን አንዷም ባለ አንበሳ ድርሻዋ ፈረንሳይ ነበረች። በመሆኗም ከቅርጫው የደረሳትን በደረሳት መሠረት ተረከበች፤ እነሆ ዛሬም ድረስ የዳቦ ስማቸውና መለዮአቸው “ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገራት” (Francophone countries) ነው። ይህም የአገራቱን ማንነት ከመሠረቱ ከመናድም ባለፈ የትምህርት ፖሊሲያቸውን ጭምር በመቆጣጠር አፍሪካዊ የሆነ ግን ደግሞ በማንነቱ ፈረንሳዊ የሆነ፤ ለቀኝ ተገዥነት ራሱን አሳምኖ የሰጠ … ትውልድ በመፍጠር እስካሁን ዘልቋል። ፈረንሳይም በዚሁ በመተማመን ተደላድላ ተቀምጣ ኖራለች። አሁንስ? ጥያቄው ይሄ ነው።
በ2050 ቋንቋዋ ዓለምን ያጥለቀልቀዋል ተብሎ የተተነበየላት ቻይና ወደ አፍሪካ ከገባች ሰንበትበት እያለች ነው። ከነችግሯም ቢሆን ለአፍሪካውያን በዓይን ገላጭነት፣ ስሜት ቀስቃሽና ቆስቋሽነት፣ ለጋሽና አበዳሪነት፣ አሰልጣኝና አልሚነት ወዘተ ሥራዋን እየሰራችና በ«መላዋ» አፍሪካ ክንፏን እየዘረጋች ትገኛለች። ይህ ደግሞ በብዙዎች፤ ኃያሏን ዩኤስኤ ጨምሮ አልተወደደላትም። በተለይ አሁን የቻይና በአፍሪካ ማህፀን ውስጥ እንደልብ የመሆኗ፤ አፍሪካውያኑ ያላዩትን የመሠረተ ልማት አውታሮችና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማየት ጉድ እንዲሉ የማድረጓ ጉዳይ ከማንም በላይ ፈረንሳይን (በይፋ ባትናገረውም) እያሳሰበ የሚገኝ ሲሆን፤ የአሳሳቢነቱ መነሻም «ነባሩን ግዛቴን ልታነቃንቀው፣ የተረጋጋውን የሕዝቡን ለፈረንሳይ የማደር ስሜቱን በመናጥ ልትቀለብሰው፣ ከፈረንሳይ ሰራሽነት ማንነቱ ወደ ተፈጥሯዊ አፍሪካዊነቱ እንዲመለስ ልታደርገው፣ ከተረጂነት ወደ ራስን መቻልና ሰርቶ መኖር ባህል ልታመጣው፣ በ”Trade and aid” ስም ከቁጥጥሯ ስር ልታወጣው… ነው» የሚል ነው፡፡ አሁን አሁን «ጉዳዩ ምንድነው?» ወደሚል ጥያቄና የቻይና- አፍሪካን ትስስር “Trade and aid” ወይስ “Trade or aid” ወደሚል ሙግትና ውዝግብ እያዘነበለ፤ የፈረንሳይ ስጋት እያየለ፣ የቻይና የተጋገረ ዝምታ እየጠነከረ መምጣት ላይ ነው።
በእርግጥ ነገሩ ውስጥ ውስጡን እየተብላላ የሚገኝ፣ የ«ፈረንሳይኛ ተናጋሪ»ዎቹም ፍላጎት ጉራማይሌ እየሆነ በመምጣት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለይ የመሪዎች ልብ ለቻይና ክፍት መሆኑ፤ ከፈረንሳይ ጡረታ፣ ድጎማ፣ እርዳታዎችንና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ከሚያገኙት በስተቀር ለፈረንሳይ ያላቸው ፍቅር እንደድሮው አለመሆኑ ሁሉ ተዳምረው ፈረንሳይን ሆደ ባሻ እያደረጋት መሆኑ ገና ባፍ ያልተነገረ የሆድ ህመም ከሆነባት ጊዜው ቀላል አይደለም። ይህንንም እየገለፀችው የምትገኘው የያዘቻቸውን አገራት ምሁራን በተለያዩ ዘዴዎች ለመያዝ እያደረገችው ካለው ጥረት አኳያ ሲሆን እስካሁን «ተሳክቶላታል» የሚል መረጃ የሚሰጥ አንድም ምልክት የለም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቻይና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በመያዝና ወደ እራሷ በማምጣቱ ረገድ ፈረንሳይን በመቦነሷ ነው የሚሉ ገደምዳሜ መረጃዎች እዚህም እዚያ ይሰማሉ/ይታያሉ። በተለይ እስከ ዛሬ ምንም ሳትሰራበት ተዘናግታ የቆየችበትና ምራቅ የሚያስውጠው የአፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ከእጇ እየወጣ የመሄዱ ጉዳይ ለፈረንሳይ አይውጡት፣ አይተፉት የሆነ ውስጣዊ ሆድ ቁርጠት በቀዳሚና ግዙፍ ምክንያትነት መጠቀስ ከጀመሩ መሰነባበታቸውን የውስጥ ለውስጥ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባጭሩ በአሁኑ ሰዓት ቻይና በግዛቶቹ እየገነነች፣ እየተወደደች፣ እየተንሰራፋችና የተፈጥሮ ሀብትን ሥራ ላይ በማዋሏ እየተደነቀችና እየተወደሰች ስትገኝ፤ ባንፃሩ ፈረንሳይ ከ«ፈረንሳይኛ ተናጋሪ አገራት» ጋር የጋራ ቋንቋ፤ የጋራ የቀድሞና አሁን ጦር አባላት፣ ፈረንሳይ የተማሩ የእነዚሁ አገራት ምሁራን ጋር ያላት ግንኙነት ብቻ እንደተከበረ ያለ ይመስላል። ይህ እስካሁን ያለው ነው፤ የወደፊቱን አብረን የምናየው ይሆናል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
ግርማ መንግሥቴ