የኢትዮጵያን የኋላ ታሪክ ስንመለከት ወጣ ገባ ሆኖ እናገኘዋለን።በአንድ በኩል ዛሬም ድረስ ሚስጢሩ ያልተገለጠ የስልጣኔ ማማ በሌላ በኩል ደግሞ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ረሃብ መገለጫዎቻን የሆኑበት የታሪክ ገፅ ይገኛል፡፡
እነዚህ የተለያዩ የአገራችን ገጽታዎች የውጭ ሃይሎች ሴራና ተንኮል ቢኖርበትም በአብዛኛው ግን የውስጣችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ናቸው።በተለይ በየዘመኑ ያሳለፍናቸው የርስ በርስ ግጭቶችና የፖለቲካ አለመረጋጋት ተገቢውን እድገት እንዳናስመዘግብ እንቅፋ እንደነበሩ ይጠቀሳሉ፡፡
ካለፉት ሃምሳ አመታት ወዲህ የነበረውን የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ብቻ እንኳን ብንመለከት በአብዛኛው የርስ በርስ ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት ከድህነት እንዳንወጣ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
ያም ሆኖ ግን በተለያዩ ወቅቶች ዴሞክራሲዊ ስርኣትን ለመገንባትና ከዚህ ጋር ተያይዞም አገራዊ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ወርቃማ እድሎችም ነበሩ።ለምሳሌ በ1966 አብዮቱ ሲፈነዳ ደርግ በመጀመሪያ ያሳየው የዴሞክራሲ መንገድ ብሩህ ነበር።በ1983ም ኢህአዴግ ወደስልጣን ሲመጣ በርካታ የፖለቲካ ሃሎችን በማሳተፍ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ ፍንጭ ሰጥቷል።በወቅቱ እስከ ሽግግር መንግስቱ ድረስ የታዩ ለውጦችና የሚዲያውም ነፃነት የዚሁ ማሳያዎች ነበሩ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በ1997 ብቅ ብሎ የጠፉው የዴሞክራሲ ወጋገን ብዙዎችን ያስቆጨ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
በተለይ በ1997 ዓ.ም ኢህአዴግ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጎልበት በያዘው አቅጣጫ መሰረት በቅድመ ምርጫ ወቅት የተፈጠረው ሰፊ ምህዳና ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች የተፈጠሩበት፣ በዚህም በርካታ ዜጎች ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እውን መሆን የተነቃቁበት ወቅት እንደነበር ምሁራን በቁጭት ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ መንግስት በተለይ ሚዲያውን ነፃ በማድረግና ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሰፊ የአየር ሰዓት በመስጠት እያንዳንዱ ተፎካካሪ ፓርቲ በእድሉ ተጠቅሞ ዓላማውንና ፕሮግራሙን ለህብረተሰቡ እንዲያስተዋውቅ እድል በመስጠቱ ዜጎች የተሻለ የፖለቲካ ግንዛቤ ያገኙበት ሰፊ ምህዳር ተፈጥሮ ነበር።ነገር ግን ገዢው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህን የህዝብ መነቃቃትና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከመጠቀም ይልቅ ስልጣንን ዋነኛ ዓላማቸው በማድረጋቸው እድሉ ሊመክን ችሏል፡፡
በወቅቱ ለተበላሸው እድል ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ ፓቲዎችም ጭምር ናቸው።በወቅቱ አንዳንድ አካላት ገዢው ፓርቲ ቀድሞውኑ ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እንዳልነበር ሲገልጹ፤ ከፊሎቹ ደግሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስልጣን ካላገኘን “ሞተን እንገኛለን” በሚል በፈጠሩት ግርግርና አካሄድ እድሉ መበላሸቱን ይተቻሉ።ያም ሆኖ ግን በመጨረሻ የተፈጠረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል በሚፈለገው ልክ ብርሃን ሳያበራ ድርግም ብሎ ጠፍቷል፡፡
በርካታ ምሁራ እንደሚያነሱት እንዲህ አይነት እድሎች ዳግም ባለፉት ሁለት አመታት ተገኝተዋል።በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት መጪውን ምርጫ ፍትሃዊና ፍፁም ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ቃል ገብቶ እየሰራ ይገኛል።ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ሃይሎችን ጭምር በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ እድሉን በማመቻቸትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶችን ያለገደብ በማስከበርና በማክበር ያሳየው መንገድ ትልቅ ማሳያ ነው።ይህ በህዝቦች ትግል የተገኘ የዴሞክራሲ መንገድ በአጭሩ እንዳይቀጭ ግን ከወዲሁ ማሰብና ዳግም ስህተት ላለመፍጠር መስራት የዜጎች፣ የሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችና የመንግስት ሀላፊነት ነው፡፡
መንግስት በመጪው ነሃሴ ይህንን ምርጫ እውን በማድረግ ዴሞክራሲውን ሙሉ ለማድረግ ቀጠሮ ቢይዝም በተፈጠረው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መከናወን አልቻለም።ወረርሽኙን መቆጣጠር ስንችልና ምርጫውን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች ሲሟሉ ለአመታት ብልጭ እያለ ሲጠፋ የነበረውን የዴሞክራሲ መንገድ እውን ለማድረግ ቁርጠኝነቱን ደጋግሞ እያስታወቀ ነው።የተፈጠረውን መልካም እድል ዳግም እንዳይበላሽ አማራጮችን አስቀምጦ እየሰራ ነው።
አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን ከመስመር በወጣ መንገድ የተገኘውን እድል የሚያጨልምና መልካም እድሎችን ዳግም የሚያከስም የፀብ አጫሪ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ይታያል።ይህንን ሁኔታ በማረም ይህ በእጃችን ያለ ታሪካዊ አጋጣሚ ሳይበላሽ በአግባቡ በመጠቀም በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመትከል ለእድገታችን ዘላቂ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባ ሁላችንም በጋራ እንረባረብ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012