እንደ ሀገር የመጣችበትን መንገድ ስንቃኝ የከፍታና የቁልቁሉት መንገዶችን እናገኛለን።እነዚህ መንገዶች አንድም የውጭ ሃይሎች ጫና፣ በሌላም በኩል የመንግስታትና የህዝቦቿ ድክመትና ጥንካሬ ውጤቶች ናቸው።
የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአብዛኛው የተገነባችው በሃይልና በጉልበት ነው።በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣት በተደረጉ ጦርነቶች በርካታ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረቶችም ወድመዋል።
ለምሳሌ አፄ ቴዎድሮስ ቀደም ሲል የነበረው የዘመነ መሳፍንት እንዲያበቃ ለማድረግ ባደረጉት ጦርነት አሁን ላለችው ኢትዮጵያ እውን መሆን የራሳቸው ሚና ተጫውተዋል።ከዚያ በኋም ቢሆን በተለይ በአፄ ሚኒልክ ዘመን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራፍ ሰፊ ዘመቻዎች ተካሂደዋል።በነዚህ ዘመቻዎችም አወንታዊና አሉታዊ አስተያየቶች ይነሳሉ፡፡
በአፄ ሃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን አንድ ማዕከላዊ መንግስት ቢኖርም በተለያዩ ምክንያቶች የዜጎች መብቶች ያልተረጋገጡ በመሆኑ የዜጎች ቅሬታና ግጭት እዚህም እዚያ እንደነበሩ ይታወሳል።በተለይ ለዘውዳዊው ቤተሰብ ብቻ የወገነው የዘመኑ መንግስት ቀስ በቀስ ድሃው ማህበረሰብ በመንግስት ላይ እንዲያምጽ አደረገ።ይህ ደግሞ እየዋለ እያደር ለመንግስቱ መውደቅ መንስኤ መሆን ችሏል፡፡
በደርግ ዘመንም ቢሆን በአገራዊ አንድነት ስም የተለያዩ የህረተሰብ ክፍሎችን ያገለለ ብቻ ሳይሆን ፍፁም አምባገነናዊ በመሆኑ ዜጎች ከአመፅ ውጭ የሆኑበት አንድም ቀን አልነበረም።በዚህም የተነሳ ለ17 አመታት የዘለቀ የርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከርማ አገር ከእድገት ይልቅ ቁልቁል፤ ስትንሸራተት ቆይታለች፡፡
እነሆ በኢህአዴግ የ27 አመታት ጉዞም ቢሆን መንግስት ያለንን መተማመን በማጥፋት ዕርስ በርስ እንድንፋጅና ሰላም እንዳይኖር ከማድረግ የዘለለ የረባ ለውጥ ሳይመጣ ቆይቷል።ይባስ ብሎም የህብረተሰቡ ሃገራዊ ስሜት ተቀዛቅዞ በአካባቢና በጎጥ ማሰብና መሳሳብ የበዛበት ዘመን ሆነ።ያለፉት ሁለት አመታም ይኸው ቀደም ብሎ የተዘራን ሰብል እንደ ሀገር እየታጨደ ያለበት ወቅት ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ሂደቶች ታዲያ ስለአገራዊ ፍቅር ወጥ አቋም እንዳይኖረን በማድረግ አገራዊ ፍቅር እንዲቀዛቀዝ ያደረጉበት ነባራዊ ሁኔታ ፈጥረዋል።አገራዊ ፍቅር ያላዳበረና በዚህም የጋራ መግባባት ላይ ያልደረሰ ህዝብና መንግስት ደግሞ ባንዳዎችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በውጭ ሃይሎች የተፈተነችባቸው በርካታ ወቅቶች ነበሩ።ከነዚህ መካካል በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በየቦታው ባቆጠቆጡ የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎች ሀገርን የመውረር ጥረቶች እንደነበሩ ይታወሳል።ለዚህ ደግሞ ከጣልያን፤ ከእንግሊዝ፣ ከሶማሊያ፣ከደርቡሾች፣ ከግብጽና ከሌሎችም ሃገሮች ጋር የተደረጉ ግጭቶችና ጦርነቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡
በነዚህ የግጭት ወቅቶች ታዲያ መላ ኢትዮጵያውያን ወራሪዎቹን ሃይሎች ለመፋለም በአንድነት መቆማቸው የሚታወስ ነው።ያም ሆኖ ግን አልፎ አልፎ አገራቸውን በመክዳት ከጠላት ሃይል ጋር የተሰለፉና የወገንን ጦር እስከመውጋት የደረሱ ባንዳዎች እንደነበሩ ታሪክ ያስታውሰናል።ለዚህ ደግሞ በተለይ በጣልያን ጦርነት ወቅት የነበሩ ባንዳዎችን ማንሳት ይቻላል።
በዚህ ዙሪያ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ሚኒልክ” በሚለው መፅፋቸው ላይ እንደጠቀሱት በጣልያን ጦርነት ወቅት ከጣልያን ጦር ጋር በማበር የኢትዮጵያን ጦር ፊትለፊት እስከመግጠም የደረሱ ባንዳዎች ነበሩ።ለአብነትም የአድዋ ጦርነት አንዱ አካል በነበረው የአምባአላጌ ውግያ የጀነራል ቶዚሊ ጦር ዋና ቀኝና ግራ ክንፍ መሪዎች ኢትዮጵያኖች ነበሩ። ሁለቱም ከራስ መንገሻና ከራስ አሉላ ጋር ተጣልተው ነው ከጣልያን ጋር ያበሩት። በዓድዋ ውጊያ ላይ የተሳተፉ የመጀመሪያ ባንዶች ናቸው ።
በጣሊያን ዘመን አገርን ከወረራ ለማዳን አርበኛው በዱር በገደሉ ሲዋጋ ህዝቡም ህይወቱን ሲሰዋ ጥቂት ሰዎች ግን ለጣሊያን በባንዳነት አድረው ክህደታቸውን በግልጽ ያሳዩ ነበር። የነዚህን አድር ባዮች ተግባር የሚያውቁት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በቅኔ ሸንቆጥ ያደርጓቸው እንደነበር ይነገራል። ታዲያ አንድ ቀን ንጉሡ በተገኙበት የዒላማ ተኩስ ላይ በፊት በባንዳነት የሚታወቅና ቤተ መንግስት አካባቢ የሚመላለስ ሰው በመጀመሪያው ጥይት አልሞ ይመታል። ይህ ሰው በጠላት ወረራ ወቅት ባንዳ እንደነበረ የሚያውቁት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ «ወይ ጉድ ባንዴ ቡን አረጋት» ሲሉ በቀልድ ባንዳነቱን እንደነገሩት ይነገራል ።
በርግጥ የባንዳነት እንቅስቃሴና በየዘመኑ ባንዳ ማነው የሚለው ሃሳብ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ለማለት ያስቸግራል።ለምሳሌ በ1928 ጣልያን ኢትዮጵያን ዳግም በወረረችበት ወቅት በርካታ የውስጥ አርበኞች የመኖራቸውን ያህል ቁጥራቸው በርከት ያለ ባንዳዎችም እንደነበሩ ይነገራል።ከነፃነት በኋላ ታዲያ “የለም እኔ ለአገር ነው የታገልኩት፤ አንተ ባንዳ ነህ፣ወዘተ” የሚሉ አተካራዎች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳዶቹ በአገራቸው የውስጥ ችግር ምክንያት ከጠላት ጋር በመሰለፍ አገራቸውን እንደወጉ ይነገራል።ለምሳሌ በደርግ ዘመን ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራት ጦርነት አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ከአገራቸው በተቃራኒ በመቆም ሉኣላዊነትን የሚጋፋ ተግባር ፈጽመዋል።
ያም ሆኖ ግን በአገራቸው ውስጥ ከመንግስት ፍላጎት በተቃራኒ በመቆም ወይም ከሌሎች ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ሰላማዊ ትግል ውስጥ ገብተው የሚታገሉ ሃይሎችን በዚህ የባንዳነት መፈረጅ ተገቢ አይደለም።አሁን አሁን በአንዳዶቹ ላይ የሚስተዋለው ይህ ነው።ለምሳሌ ከነሱ ፍላጎትና የትግል መስመር ውጭ በመሆናቸው የባንዳነት ስም የሚለጠፍባቸው አንዳንድ ወገኖችና ግለሰቦች አሉ።ይህ ደግሞ ለነፃነት የሚደረግ ትግል እንጂ ባንዳነት ሊባል አይችልም፡፡
በአንፃሩ ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተነሳ ከግብጽ ጋር ቅራኔ ውስጥ መሆኗ ይታወሳል።ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ከግብፅ ጎን በመሰለፍ ይህንን ታሪካዊ የልማት ስራ ለማደናቀፍ የሚጥሩ ሃይሎች እንዳሉም ይነገራል።መንግስትም በግልፅ እነዚህ ሃይሎች እነማን እንደሆኑ በይፋ ባይገልፅም በዚህ ተግባር የተሰለፉ ሀይሎች መኖራቸውን ይገልጻል።ይህ እውን ከሆነ ግን አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ታሪክ የሚወቅሳቸው በመሆኑ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል።
አገራችን በአንድ በኩል በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት የጦርነትና የትንኮሳ አዝማሚያ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት በዚህ መልኩ ከነዚህ ሃይሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማድማትና የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ወይም አገሪቱን ለማተራመስ የሚጥሩ ሃይሎች ካሉ ግን ከዚህ ድርጊታቸው ራሳቸውን ሊያቅቡ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
ውቤ ከልደታ