ዓለም አቀፍ ስጋትና አደጋ የሆነው ኮሮና ዕለት ዕለት የስርጭትና የጉዳት አድማሱን እያሰፋ መገስገሱን ቀጥሏል። እስከትናትናው ዕለት ድረስ በዓለም ላይ አራት ሚሊዮን 374 ሺህ 888 ዜጎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 294 ሺህ 412 ያህሉ በዚሁ ሰበብ ህይወታቸውን አጥተዋል። ከቫይረሱ ተለዋዋጭ ባህሪ አንጻር በየቀኑ የሚሰሙ ግኝቶች የጥንቃቄ እርምጃዎች ተወስደው በአፋጣኝ መቆጣጣር ካልተቻለ በምድራችን ላይ አስከፊ ጉዳት እንደሚያሰከትል ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ሆኗል። ምክንያቱም የቫይረሱን ስርጭት ተቆጣጥረነዋል ባሉ ሀገራትም ላይ ዳግም መከሰቱ እየተሰማ ከመሆኑም በላይ ያገገሙ ሰዎችንም እያጠቃ ስለመሆኑ የሚያመልክቱ መረጃዎች ብቅብቅ ማለት ጀምረዋልና።
በአገራችንም ቢሆን የመጀመሪያው ተጠቂ ይፋ ከሆነበት ከመጋቢት 3/2012 ጀምሮ ዕለት ዕለት የቫይረሱ ስርጭት አድጎ እስከ ትናንትናው ዕለት ድረስ 263 ሰዎች በቫይረሱ ከመጠቃታቸውም በላይ የአምስት ሰዎች ህይወትም በዚሁ ወረርሺኝ የተነሳ ለህልፈት ተዳርጓል። በተለይም ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከሚደረጉ ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው የተጠቂዎች ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ ሲሆን በጣም አስፈሪው ነገር ደግሞ የውጪ ጉዞ ታሪክ የሌላቸውና ከለይቶ ማቆያ ውጪ የሆኑ ሰዎች ጭምር ተጠቂ መሆናቸው ነው።
ይህ እውነታ ኮሮና እጅግ ቅርብ ሆኖ መምጣቱን ለመረዳት ያስችለናል። ምን አልባትም በቅርባችን ያለ ሰው የቫይረሱ ተጠቂ ስላለመሆኑ አርግጠኛ ለመሆን አይቻልም። ስለሆነም ያለው ብቸኛ አማራጭ ከህክምና ባለሙያዎችና ከመንግስት የተሰጡንን የጥንቃቄ አርምጃዎች ያለምንም ማመንታትና መዘናጋት በጥብቅ ዲስፕሊን መፈጸም ብቻ ነው። ይህን ችላ ማለት ግን ከራስ አልፎ የሚወዱት ቤተሰብን ከዚያም ሲያልፍ አገርን እጅጉን ይጎዳል፤ ክህሊና የማይፋቅ ጸጸትንም ያስከትላል። ከዚህ አንጻር በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ሰሞኑን የሚስተዋለው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የመጠቀሙ ሁኔታ ሊበረታታ የሚገባው ነው። ይሁንና ከቫይረሱ ራስንም ሆነ ወገንን የምንታደገው ሁሉንም የጥንቃቄ እርምጃዎች ያለመሸራረፍ ስንጠቀም ብቻ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።
ኮሮና የሚያስከትለው ጉዳት በጤና ላይ ብቻ የታጠረ አይደለም። አንዳንድ ምሁራን እንደሚገልጹት ቫይረሱ በጤና ላይ ከሚያደርሰው ቀውስ ይልቅ ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጫና ዓለማችንን ብዙ ዋጋ ያስከፍላታል። ለዚህ ማሳያ የሚያደርጉት ከቫይረሱ ፈጣን ስርጭት ጋር ተያይዞ የመጣው የሰዎች ከእንቅስቃሴ መታቀብ ምርታማነትን በእጅጉ እየጎዳው ነው። አምርቶ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ከምርት ተግባሩ የራቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎቶች በመዘጋታቸው ወይም ደግሞ ሥራው በመቀዛቀዙ በበርካታ ሰራተኞች ሰርቶ ማደር ላይ አደጋ ደቅኗል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የፍጆታ ዕቃዎች እጥረትም በበርካቶች ህይወት ላይ የተደቀነ ታላቅ አደጋ ሆኗል።
ይህንን ዓለም አቀፍ ሁኔታ ቃኝተን ወደአገራችን ሁኔታ መለስ ስንል ደግሞ ከድህነት ባልተላቀቀው ኢኮኖሚያችን ላይ ኮሮና የደቀነው ስጋት አጅግ ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን። እርግጥ ነው የኮሮና ወረርሺኝ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ ፈታኝ ወቅታዊ ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው በመመከት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል። ይህንንም ተከትሎ ኢኮኖሚያችን በከፍተኛ መነቃቃት ውስጥ ከመግባቱም በላይ ትርጉም ያለውና ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ በሚያስችል ቁመና ላይ ነበርን።
ይሁንና ባልታሰበውና ባልተገመተው የኮሮና ወረርሺ ምክንያት ኢኮኖሚው ፈተና ውስጥ ወድቋል። የኤክስፖርት ምርት መቀነስ፣ የታክስ ገቢ ቀድሞ በታሰበው መልኩ ለመሰብሰብ አዳጋች መሆኑ፣ ከዓለም አቀፍ ሁኔታው ጋር ተያይዞ ገቢ ምርቶች ላይ የሚታየው መቀዛቀዝ ወዘተ የኢኮኖሚው ወቅታዊ ተግዳሮቶች ሆነዋል። ይሁንና መንግስት በአንድ በኩል የኮሮና ወርሺኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ወሳኝ ተግባራትን እየፈጸመ በሌላ በኩል ደግሞ ኢኮኖሚው አደጋ ውስጥ እንዳይወድቅ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ በመስራት ላይ ይገኛል።
በተለይም ደግሞ የአገሪቱና የአብዛኛው ህዝቧ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነው ግብርና በኮሮና ምክንያት ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስበት በከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ ጭምር እየተሰራ ያለው ሥራ ተገቢና ይበል የሚሰኝ ነው። በዘንድሮው ክረምት “አንድም የሚታረስ መሬት ጦም አያድርም” የሚለው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አባባልም ይህንኑ እውነታ የሚያረጋግጥ ነው።
ስለሆነም እንደአገርም ሆነ እነደ ህዝብ ያለን ብቸኛ አማራጭ አስፈላጊ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመፈጸም ኮሮናን መከላከልና ከዚሁ ጎን ለጎን የኢኮኖሚውን ልማት ማፋጠን ይሆናል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012