አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ ከተሞች ተገንብተው ለአገልግሎት ለተዘጋጁ 51አዳዲስ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ለመስጠት አስፈላጊውን የዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ጀማል ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በአገሪቱ ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የነበረውና በውጭ አገር ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በ2007ዓ.ም የተካሄደው ምደባ ያስነሳው ቅሬታ እንዳይደገም ምደባውን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ለማካሄድ ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት የሆቴሎች ደረጃ ምደባ ጥያቄ ከአዳዲስ ሆቴሎች በስፋት የቀረበለት መሆኑን አቶ ታደለ አመልክተው፤ በዚህ መሰረት በአሁኑ ወቅት የደረጃ ምደባውን ለማከናወን የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቁ ምደባውን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ለማስቀጠል እንዲቻል ከዘጠኙም ብሔራዊ ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የምዘና ባለሙያዎች እንዲሳተፉ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የተገነቡትን አዳዲስ ሆቴሎች በደረጃ የመመደብ ሥራ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ለሀገሪቱ ገጽታ ግንባታ ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ በተወዳዳሪነት ፈጥነው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማስቻል መሆኑን ያስረዱት ከፍተኛ ባለሙያው፤ በአሁኑ ወቅትም የምዘና ባለሙያዎች ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን ሥነልቦናዊ ዝግጁነት ለማረጋገጥ ተደጋጋሚ የንድፈ-ሀሳብና የተግባር ቅድመ የመሰናዶ ስልጠናዎች የወሰዱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከፍተኛ ባለሙያው እነዚሁ የምደባ ባለሙያዎች ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማድረግም ሰሞኑን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሰራቱን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት የምደባ ሥራ የሚሰራው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተገነቡና የልየታ ሥራ በተሰራባቸው 51 አዳዲስ ሆቴሎች ላይ መሆኑን፤ ባለሙያዎቹ ሆቴሎቹ በሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ድረስ በመሄድ ምዘና ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ፤ የምዘና ሂደቱ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች መካሄዱ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የተጣጣመ ለማድረግ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሊያድን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
መዛኞቹ ደረጃ መዳቢዎች ሆቴሎችን ገምግመው በሚያቀርቡት መረጃ መሠረት በልዩ ኮሚቴ ታይቶ ከፀደቀ በኋላ በውጤቱ የኮከብ ደረጃ የሚሰጣቸው መሆኑን የገለፁት ከፍተኛ ባለሙያው፤ የምዘና ቡድኑም የሚጠቀምባቸው የምዘና መሣሪያዎችና ስልቶች በጥንቃቄ ተሞልቶና በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የባለሙያ ድጋፍ ተዘጋጅቶ በአገሪቱ በጸደቀው የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብቃት መመዘኛ መስፈርቶች ተግባር ላይ የሚውል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የምዘና ሂደቱን በሚመለከት ወደፊት ለመገናኛ ብዙሃን የሚገለፅ መሆኑን የተናገሩት ከፍተኛ ባለሙያው፤ በቀጣይ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ሆቴሎች የደረጃ ምደባ ሥራ የሚከናወን ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሆቴሎችን በደረጃ መመደብ የአገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለተሻለ አድገት የሚቆምበትን አቅጣጫ እንደሚይዝ፣ ለተገልጋዩ የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥበት፣ ተመጣጣኝ ክፍያ የሚጠየቅበት እንደሚሆንና ባለሀብቱን እንደሚያበረታታ፣ ከልማቱም የተሻለ ገቢ የሚያገኝበት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
በማህሌት አብዱል