ነሐሴ ዘጠኝ ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስንዴ ሰርቆ በኩሊ አሸክሞ ወደ ቤቱ የወሰደ ወንጀለኛ ላይ የተላለፈ ፍርድን በተከታዩ ዘገባ አስነብቦ ነበር።
የሰረቀውን ስንዴ በኩሊ አሸክሞ ወደ ቤቱ የወሰደው በእስራት ተቀጣ
ባለፈው ሐምሌ 13 ቀን 1962 ዓ.ም አንድ ወንጀለኛ ተቀጥሮ ከሚሰራበት የእህል መጋዘን ግምቱ 35 ብር የሆነ አንድ ኩንታል ስንዴ ሰርቆ በኩሊ አሸክሞ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመውሰዱ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሊፈረድበት ችሏል። በተጨማሪም ግለሰቡ ከእመት ትርፌ ዕቁባ ቤት ግምቱ ሃምሳ ብር የሆነ ሬዲዮ መስረቁ ስለተረጋገጠበት ፍርድ ቤት በስምንት ወር እስራት እንዲቀጣ ሲበይንበት በኤግዚቢት የተያዙት ንብረቶች እንዲመለሱ መወሰኑን ዐቃቢ ሕግ ሻምበል ባሻ አፈወርቅ ምንተስኖት ገልጸዋል።
ነሐሴ 19 ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የተጣለበትን ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት ስርቆት በመፈጸሙ እስራት ስለተፈረደበት ወታደር ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
12 ሬዲዮኖችን የሰረቀው ወታደር የአንድ ዓመት እስራት ተፈረደበት
12 ሬዲዮኖችን የሰረቀው ወታደር ቻሞ ኮንጎ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት በአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ የማጂ አውራጃ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ፈረደ። ንብረትነታቸው የፊሊፕስ ኩባንያ የሆኑ 12 ሬዲዮኖች በካርቶኖች ተጠቅልለው ግንቦት 29 ቀን 1962 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ በበረረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤሮፕላን ተልከው ነበር። ሬዲዮኖቹ ጅማ በመውረድ ፈንታ በስህተት ማጂን አልፈው ዋሻ ወሀ ኤሮፕላን ማረፊያ ደረሱ። ወታደር ቻሞ የኤሮፕላን ማረፊያው መስመር ተቆጣጣሪ እንደመሆኑ መጠን የተሰጠውን ኃላፊነት በመዘንጋት ሬዲዮኖቹን እንደ ተጠቀለሉ ከኤሮፕሌኑ አውርዶ በመውሰድ ወደ ሌላ ሰዋራ ቦታ ደበቃቸው። ከዚያም ከሌሎች አራት ግብረ አበሮቹ ጋር በመከፋፈል ሸጠው ለመጠቀም ከደበቁበት ስፍራ ሬዲዮኖቹ ተይዘዋል።
ተከሳሹ በተደረገለት ምርመራ ጥፋተኝነቱን ከማመኑም በላይ በማስረጃም ስለተረጋገጠበት በአንድ ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበታል። እንዲሁም ሬዲዮኖቹን ተቀብለው የደበቁት አራት ግብረ አበሮቹ ሰባ ብር መቀጮ እንዲከፍሉ፣ ለመክፈል ባይችሉ በሁለት ወር እስራት እንዲቀጡ ተበይኖባቸዋል። ተሰርቀው የተያዙትም 12 ሬዲዮኖች ለባለንብረቱ ካምፓኒ እንዲመለሱ ፍርድ ቤቱ ማዘዙን የማጂ አውራጃ ፖሊስ አዛዥ መቶ አለቃ አድማሱ ብሩ አረጋግጠዋል።
የካቲት ሁለት ቀን 1964 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሁለት ብር ጉቦ በመቀበሉ ምክንያት እስራትና የገንዘብ ቅጣት ስለተላለፈበት ወታደር የሚገልጽ ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር።
ሁለት ብር ጉቦ የበላው 90 ቀን እስራትና
50 ብር ተቀጣ
ሁለት ብር ጉቦ ተቀብሏል በመባል ተከሶ የነበረው የፖሊስ ባልደረባ የ 90 ቀናት እስራትና የሃምሳ ብር ቅጣት ተበየነበት። ወታደር ነገረ ገድአ የተባለው የፖሊስ ባልደረባ ቅጣት የተወሰነበት፤ በየረርና ከረዩ አውራጃ በሸንኮራ ወረዳ ውስጥ በዘብ ስራ ላይ እንዳለ ለግል አቤቱታ የሄዱትን አቶ ዜና ወልደአምላክን አለአግባብ በማሰር ሁለት ብር ጉቦ ሲቀበል በመገኘቱ ነው።
በዚህም ምክንያት የአውራጃው ፍርድ ቤት ተከሶ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠ ሶስት ወራት ታስሮ ሃምሳ ብር መቀጫ እንዲከፍል የተበየነበት መሆኑን የአውራጃው ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ አቶ አበበ ታዬ ገልፀዋል።
ወታደሩ የተፈረደበትን ሃምሳ ብር መክፈል ባይችል ግን የአንድ ወር እስራት ተጨምሮበት በጠቅላላው አራት ወራት እንዲታሰር ተወስኗል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
የትናየት ፈሩ