ለሕዝብ ፍላጎት የመታገል የፊት መስመር ሚና
ሁሌ ተደጋግሞ እንደሚባለው ዴሞክራሲ የረጅም ጊዜ ግቦችን ያነገበና በሂደት የሚገነባ የአስተዳደር ሥርዓት ነው።ታዲያ የግንባታ ሂደቱ የመጨረሻ ግብ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ነውና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ሁሉም ዜጎች በንቃት መሳተፍና ሰላማዊ ትግል ማድረግ ግድ ይላቸዋል።በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዜጎችን በማስተባበርና ሰላማዊ ትግሉን ከፊት ሆነው በመምራት የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሂደቱ እውን እንዲሆን በማድረግ ረገድ ሚናቸው የላቀ መሆኑን የዘርፉ ልሂቃን በአንድ ድምጽ ይስማሙበታል፣ አበክረው ይመራመሩበታል፣ ይጽፉ በታልም፡፡
በአንድ ሀገር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሚና በተመለከተ «የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባርና ሚና ለዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብ ግንባታ» በሚል ርዕስ በ2008 ዓ.ም ጥናታዊ ጽሑፍ ያሳተሙት የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ተስፋዬ ሞላ ከዓላማቸው ይነሳሉ።«የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና የኅብረተሰቡን ተጨባጭ ሁኔታ በውል በማጤን ከአንድ አገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ አጠቃላይ መርሃ ግብሮችን በመንደፍና ደጋፊዎችን በማሰባሰብ የሕዝቡን ፍላጎት ለማስፈጸም የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ መታገል ነው» ይላል ጥናቱ።በአንዲት አገር ላይ ዴሞክራሲን ለማስፈንና ዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብን ለመፍጠር ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉልህ ሚና አላቸው።ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች የኅብረተሰቡን ፍላጎት በመለየት፣ በማሰባሰብና በማዋሃድና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት አባላትን በማሰባሰብ፣ በማስተማርና በማሰልጠን ዜጎች በሀገራቸው ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ስለሚያደርጉ።
ይህ ጥናት እንደሚያመላክተው ዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብ ማለት መብትና ግዴታቸውን ለይተው የሚያውቁ፣ ለነፃነታቸው የሚከራከሩ፣ በሀገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳይና በመንግሥት አሠራር ላይ በንቃት የሚሳተፉ ጠያቂና ያገባኛል የሚሉ ዜጎችን ያቀፈ ኅብረተሰብ ነው።ዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብን ለመገንባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የተለያዩ ማህበራዊ ቡድኖችን ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች መወከል፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕዝባዊ ገጽታና ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማጎልበት፣ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲደረግ መታገልና በምርጫው መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡
የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የፖሊሲ ሃሳቦችን ማፍለቅና ነባር ፖሊሲዎችም የሚሻ ሻሉበትን መንገድ መፍጠር፣ የዜጎችን የተሳትፎ ደረጃ በማሳደግ መሪዎች የሚፈጠሩበትን መድረክ ማመቻቸት፣ የመንግሠት ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብትና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ባህል እንዲዳብርና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።በተጨማሪም ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና ሕዝባዊ ማህበራትን በተሻለ ቅንጅትና ስልት እንዲደራጁ በማድረግና የመደራጀት ነፃነት እንዲኖር በማድረግ የኅብረተሰቡን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግና የመራጩን ሕዝብ ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ዴሞክራሲንና ዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ያብራራል።
ፓርቲዎቻችንና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምስረታ ትግላቸው
ከላይ በጥናቱ የተቀመጠውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማና በሕዝባዊ መንግሥት ምስረታ ወይንም በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚና ግምት ውስጥ አስገብተን የእኛን ሀገር ፖለቲካ ፓርቲዎች ለመመርመር እንሞክር።እውን ፓርቲዎቻችን ከላይ በቀረበው መንገድ በአግባቡ ሚናቸውን እየተወጡ ነውን? የሚታገሉት «የሕዝብን ፍላጎት» ለማስፈጸም ነውን? ለዴሞክራሲ ግንባታ እያበረከቱ የሚገኙት አስተዋጽኦስ ምን ያህል ነው? በእኔ ዕምነት እነዚህን መመዘኛዎች መሠረት አድርገን ፓርቲዎቻችንን ስንገመግማቸው አብዛኞቹ የሚያስቆጥሩት ነጥብ ከበቂ በታች ይሆንብኛል።እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በተቃራኒው እየተጓዙ ያሉም ይመስልኛል።ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ ሚና መብቱንና ግዴታውን ለይቶ የሚያውቅ፣ በምክንያት የሚያምን ዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብ ለመገንባት ከፊት መስመር ተሰልፎ መታገል ነው።
ይሁን እንጂ በእኛ ሀገር ከዚህ በተቃራኒው አብዛኞቹ ፓርቲዎች በጎጥና በቡድን ተደራጅተው በፍትህና በእኩልነት የሚያምን ዴሞክራሲያዊ ኅብረተሰብን በመፍጠር ፈንታ በአልቦ ድንበር የተከፋፈለ፣ በአጥንትና በሥጋ የተቧደነ፣ ራሱን ብቻ የበላይ ለማድረግ የማለ፣ የሰብዓዊነት ዓይኑን የጨፈነ ደመነፍሳዊ ኅብረተሰብ እንዲፈጠር አፍራሽ ሚና ሲጫወቱ ይስተዋላሉ።ፓርቲዎች የሚታገሉትና ሥልጣን ለመያዝ የሚሰሩት የሕዝቡን ፍላጎት ለማስፈጸም ከሆነ በእኛ ሀገር የሕዝብ ፍላጎት መቼ ተከበረ? እንደዚያ ከሆነ አሁን እንኳን ሀገር በስጋት ውስጥ ሆና ከወረርሽኝ ጋር እየተፋለመች ባለችበት ሰዓት «ምርጫው ካልተደረገ ሞቼ እገኛለሁ» ማለትን ምን አመጣው?
ሳይንሱ እንደሚለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ነቅሶ በማውጣት የፖሊሲ ሃሳቦችን ማፍለቅና ነባር ፖሊሲዎችም የሚሻሻሉበትን መንገድ መፍጠር፣ የዜጎችን የተሳትፎ ደረጃ በማሳደግ መሪዎች የሚፈጠሩበትን መድረክ ማመቻቸት፣ የመንግሥት ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብትና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ባህል እንዲኖር ዘወትር ከሕዝብ ጋር በቅርበት መስራት ይጠበቅባቸዋል።ሆኖም የ «ሰላማዊ ትግል 101» መጽሐፍ ደራሲው አቶ ግርማ ሞገስ እንዳሉት፤ ከሰሞኑም በግልጽ እንደታዘብነው «የተወሰኑ የምርጫ ፓርቲዎች እንደ መስቀል ወፍ ድምጻቸው የሚሰማው ምርጫ ጥቂት ወሮች ሲቀሩት ነው፤ ሌሎች ደግሞ ከቢሯቸው ወጥተው የፖለቲካ ኃይል ምንጭ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ለመገናኘት የሚሞክሩት በመግለጫና አልፎ አልፎ በሚደረጉ የአዳራሽ ስብሰባዎች ነው»።ከዚህ የምንታዘበው አብዛኞቹ ፓርቲዎች የሚታገሉት እና ሥልጣን መያዝ የሚፈልጉት የሕዝቡን ፍላጎት ለማስፈጸም ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር መሆኑን ነው፡፡
መሪነትና የሕዝብ ወገንተኝነት የሚፈተኑበት ሰዓት
ወርቅ በሁሉም ዘንድ ተፈላጊና ተወዳጅ፣ ውድና ክቡር ከመሆኑ በፊት በብርቱ ይፈተናል፣ እቶን ውስጥ ይጣላል፣ በእሳት ይጠበሳል።ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ መከራ ተቋቁሞ፣ በፈተናው ውስጥ በጽናት ቆይቶ፣ ከባዱን ጊዜ በአሸናፊነት አልፎ፣ ይበልጥ ጠንክሮ፣ አምሮና ተውቦ በእርግጥም ሊፈለግና ሊወደድ የሚገባው የክብር ዕቃ መሆኑን እውነተኛ ወርቅ በመሆን ያረጋግጣል።ሰውም እንደዚሁ ነው።ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ፤ በደህና ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግር ጊዜም ሰው ሆኖ ካልተገኘ በትክክል ሰው መሆኑ አይታወቅም።እናም የወርቅ ወርቅነቱ የሚረጋገጠው በእሳት ተፈትኖ እንደሆነ ሁሉ የሰውም ሰውነቱ የሚለካው በችግር ቀን ይሆናል።አለበለዚያ ስላብረቀረቀና ወርቅን «ስለመሰለ» ብቻ ነሐሱም መዳቡም «ወርቅ ነኝ»፤ አስመሳዩና ሰው መሳዩ ሁሉም «እውነተኛ ሰው ነኝ» በማለት ሊያሳስት ይችላል።አሁን ላይ በእኛ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ ክፉ ጊዜን በአሸናፊነት ለማለፍ ይሄ ሁሉ ሲሆን ለወትሮው በየአደባባዩና በየሚዲያው ድምጻቸው ከሚገባው በላይ ጎልቶ የሚሰማው «ለሕዝብ እንታገላለን እና ሕዝብን እንመራለን» የሚሉ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የማሕበረሰብ አንቂ ነን ባዮች በዚህ ወሳኝ ጊዜ አገርና ሕዝብ የሚያደርጉትን የህልውና ትግል አለመቀላቀላቸው አጃኢብ አስብሏል።ለብዙዎችም «ትንግርት» ሆኗል።
በዚህ ጉዳይ ላይ በእጅጉ ከተገረሙትና ነገሩ «ትንግርት» ከሆነባቸው በችግር ቀን ካልሸሹ፣ ዘወትር ለሰብዓዊነትና ለእኩልነት በመታገል የሚታወቁ፣ ዘመናቸውን ሙሉ ለሁሉም የምትመችና የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት እየታገሉ የሚገኙት፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራችና የሰውነት አቀንቃኙ «ጥቁሩ ሰው» ኦባንግ ሜቶ ዋነኛው ናቸው።«የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት በብሔር የተደራጁ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች በስፋት ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን የት እንዳሉ አይታወቅም» የሚሉት አቶ ኦባንግ በሁኔታው በእጅጉ መገረማቸውንና ሕዝብን እንመራለን የሚሉ ፖለቲከኞች በችግር ወቅት ከሕዝብ ሸሽተው መደበቃቸው ትንግርት እንደሆነባቸው ትዝብታቸውን ይገልጻሉ።
«መሪነት የሚታየው በችግር ጊዜ ቢሆንም እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች ግን ‹ እንወክለዋለን › ከሚሉት ሕዝብ ጋር እንኳን ሲቀርቡ አይታዩም» በማለት አቶ ኦባንግ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ «የሠርግ ቀን የሕዝብ ወኪሎችን» አስመሳይነት ይናገራሉ።እንደ እርሳቸው መስለዋቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሂደት ፍጻሜው ሥልጣን መያዝ ቢሆንም ሥልጣን የሚገኘው ሕዝብ ሲኖር መሆኑን ተረድተው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ሕዝቡን ለማዳን ሊረባረቡ የሚገባ መሆኑን ያመላከቱት ድርጅቶቹ ቢያንስ እንኳን «እንወክልሃለን» ለሚሉት ብሔር ሕዝቡ ከበሽታው ራሱን እንዲጠብቅና የሚችሉትን በማድረግ እንዲያግዙ ተማጽነዋቸዋል።ከዚህ በፊት ሕዝቡን ለማግኘት ይጠቀሙባቸው የነበሩ መገናኛ ብዙኃንም በዚህ የችግር ወቅት ለበጎ ነገር እንዲጠቀሙባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።«እነዚህ ድርጅቶች የሚያስተላልፉት መልዕክት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሕዝብን ለመከፋፈል ሳይሆን ሕዝብን ለማቀራረብ፣ ሕዝቦችን ለማስተባበርና ለመተባበር፣ የሚያራርቅ ሳይሆን ሕዝቡን የሚያቀራርብ፣ ለክፉ ሳይሆን ለበጎ ነገር፣ በአጠቃላይ ሕዝብን ለማዳን የሚያግዝ መሆን አለበት፤ ለዚህም የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ጠላት የሆነውን ይህንን ወረርሽኝ ለመግታት እንደ ሰው አብሮ መቆም ያሻል» የሚል ሰናይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለሕዝብ አንቂዎችና ታጋዮች የቀረበ
የሕዝብ ጥያቄ
ቀደም ሲል ዓለማችንን የገጠማት ችግር ወደ እኛ ሳይ መጣ፣ አስፈሪው ወረርሽኝ እኛንም በፍርሃት ሳያስቀምጠን፣ ሀገር ኮሮና በቀሰቀሰው ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ሳትገባ ከሠላም እጦት በቀር ሁሉም ሠላም ነበር።ሰላምም ያጣው ሕዝቡ ነው እንጂ «የሕዝቡ ታጋዮች» አልነበሩም።ሕዝቡ ነው እንጂ እነርሱማ ሠርግ ላይ ነበሩ።«የሚታገሉለት» ሕዝብ ሰላሙን ያጣ ነበር እንጂ እነርሱማ በየቀኑ ትግል ላይ ነበሩ።
“አክቲቪስቶች ሃያ አራት ሰዓት “አክቲቭ” ሆነው “ሕዝባቸውን” ያነቁ ማለቴ ያጠቁ ነበር።ፖለቲከኛ ነን ባዮች ሃያ አራት ሰዓት “ለሕዝባቸው” ይታገሉ ነበር።በየቀኑ “ሊያጠቃህ የሚፈልገውን ሁሉ ልናጠፋልህ፣ ከጥቃት ልንከላከልህ፣ ቋንቋህን፣ ባህልህን፣ ማንነትህን ልናስከብርልህ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል መብትህን ልናረጋግጥልህ፣ ከመዋጥ ልንታደግህ… አይዞህ፣ አለንልህ” እያሉ “ይታገሉለት” ነበር ሕዝባቸውን።ሲመቻቸው በአካል እየሰበሰቡ፣ አለያም በሚዲያ ሁሌም “ከሕዝባቸው” ጎን ይቆሙ ነበር።አሁን ግን ያ ሁሉ ነገር የለም።ሃገርና ሕዝብ ችግር ከገጠማቸው ወዲህ እኒያ ትጉህ “አክቲቪስቶች” እና “ፖለቲከኞች” “ከሕዝባቸው” ጎን የሉም።እንደ በፊቱ “ለሕዝባቸው ጥቅም” ሲጮኹ አይሰሙም።ኧረ “ታጋዮቻችንን” ምን ነካብን? ሕዝብ እኮ ችግር ውስጥ ነው።በመልካሙ ጊዜ ሃያ አራት ሰዓት አብረውን የሚኖሩ፣ ያለ እኛ የማይሆንላቸው ችግር ባይገጥመን እንኳን ችግር እየፈጠሩ “አለንላችሁ” የሚሉን “ተቆርቋሪዎቻችን” የት ገቡ፣ ምን ዋጣቸው? ምነው ዛሬ እኛ ያልፈጠርነው ችግር ሲፈጠርብን “ታጋዮቻችን” አለሁ አላሉን? ምነው በችግር ቀን ከጎናችን አልቆሙ?
ለሕዝብ መታገል ሲባል?
ስለ እውነት አገር ችግር ውስጥ በገባችበት፣ ሕዝብ ጭንቀት ውስጥ ባለበት በዚህ የፈተና ሰዓት “የሕዝብ ተቆርቋሪዎች” ከሕዝብ የራቁበት፣ የጠፉበት ምስጢሩ ምን ይሆን? ከላይ ጥናታዊና ሳይንሳዊ ማስረጃዎች በመነሳት ለሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች ዓለም አቀፍ የደህንነት ስጋት በሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ሀገርና ሕዝብ ችግር ውስጥ በገቡበት በዚህ ፈታኝ ሰዓት ከመድረክ የራቁበት ምክንያት የሚታገሉት በትክክል ለሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም መሳካት ባለመሆኑ እንድል ያስገድደኛል።
በእርግጥም የሰው እውነተኛ ማንነቱ በችግር ጊዜ ይገለጣል።ከእነርሱ በስተቀር የደህንነትና የሰላም ስጋት በሌለበት፣ ለጊዜውም ቢሆን እነርሱን ብቻ ሰላም ለማድረግ(ሰላምን የሚያሳጣ የኋላ ኋላ ሰላም ማጣቱ ስለማይቀር) በሕዝብ ስም የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደድ “እንታገልልሃለን” በማለት በሰላሙ ጊዜ ሌት ተቀን ይጮሁ የነበሩ “አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች” ችግር ሲመጣ ተደበቁ።
የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሕጋዊና ይፋዊ ኃላፊነት ከተጣለበት መንግሥት በላይ ራሳቸውን በተጨማሪ መንግሥትነት በመሾም በሰላሙ ጊዜ 90 ጊዜ “ሕዝቤ”፣ “ሕዝቤ” እያሉ ሕዝብን ሲያደናቁሩና ሲያናቁሩ ይውሉ የነበሩ “የሕዝብ ተቆርቋሪዎች” አሁን ላይ ሕዝቡ ችግር ሲገጥመው በጣት ከሚቆጠሩት ከአንዳንድ እውነተኛ የክፉ ቀን የሕዝብ ልጆች በቀር አብዛኞቹ ኮሮና ከመጣ ወዲህ ሕዝቡን ጥለው ሸሽተዋል።
ይህም የሚያመላክተው ለሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ወገኖች ወትሮም ቢሆን ይታገሉ የነበሩት ለጥቅማቸው እንጂ ለሕዝባቸው አለመሆኑን ነው።እናም አስመሳዮቹ አሁን ላይ የጠፉበት ምክንያት ጊዜውን ጠብቆ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ እንጂ ድሮም የነበረ ነው ማለት ይቻላል።ይኸውም እነዚህ የሠርግ ቀን አርበኞች በችግር ጊዜ የመጥፋታቸው ዋነኛው ምክንያት ሕዝብን በተለያየ መንገድ ከፋፍለው ለጥቅማቸው ሲሉ “ለጥቅምህ እንታገልልሃለን” የሚሉትን የራሳቸውን “ሕዝብ” ፈጥረው በሕዝብ የሚነግዱ “የሕዝብ ነጋዴዎች” እንጂ “የሕዝብ ታጋዮች” አለመሆናቸውን ያሳብቃል፡፡
ይህ ወቅታዊ የፖለቲከኞቻችንና የሕዝባዊ አንቂዎቻችን ሁኔታ በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕዝብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉን በአንድ ወቅት በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጠይቀናቸው የነበረው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ውሂበእግዜር ፈረደ ያሉትን ያስታውሰኛል።“ከመሠረቱ በእኛ ሀገር ያለው ፖለቲካ የሕዝብን ፍላጎትና ጥቅም መሠረት ያላደረገ በመሆኑ የፖለቲካ ነጋዴ እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ የለም” ነበር ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ።እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከሕዝብ ጋር የማይገናኙበት ዋነኛው ምክንያትም ዓላማና መርኋቸው ከሕዝብ ያልመነጨ በመሆኑ ሕዝቡን ለመቅረብና ለመግባባት ስለሚያዳግታቸው ነው።ስለሆነም መርኋቸው የፖለቲካ ሥልጣንና ገንዘብ ለማጋበስ በመሆኑ ሥራቸው በፖለቲካ ስም መነገድ ነው።ሕዝቡን አያውቁትም፣ እርሱም አያውቃቸውም፡፡
የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ያደረገ በሕዝብ ቅቡልነት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በፓርቲና በምርጫ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ አሰፍናለሁ ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው።ቀጣዩ ምርጫም ከዚህ የተለየ አይደለም።እንዲያውም አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ በሀገሪቱ ያለውን ግጭት የበለጠ ሊያባብሰውና አገሪቱን ወደባሰ ቀውስ ሊከታት ይችላል በማለት ነበር ያስጠነቀቁት የፖለቲካ ምሁሩ።
እነሆ ምሁሩ እንዳሉት በችግር ጊዜ ሲሆን “ሕዝቤ” ከሚሉት መነገጃ መሣሪያቸው አርባ ክንድ ርቀው፣ ድምጻቸውን አጥፍተው ሲጠባበቁ የነበሩት ፖለቲከኞቻችንና ፓርቲዎቻቸው ይኸው የጥቅምና የሥልጣን ነገር ሲሆን ከተደበቁበት ዋሻ ወጥተው አለቅጥ ይጮኹ ጀምረዋል።የሚያሳዝነው ደግሞ አሁንም ሳያፍሩ የሕዝቡ አሳቢና ተቆርቋሪ ሆነው መምጣታቸው ነው።ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው፣ ለሕዝብ ማሰብም እንደዚህ አይደለም፣ የእውነተኛ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ተግባርም ይህ አይደለም፡፡
ጥቂት ወገናዊ ምክረ ሃሳብ እንደ መውጫ
ለሕዝብ የምትታገሉ ፓርቲዎቻችን ቆም ብላችሁ ራሳችሁን እንድታዩ፣ መንገዳችሁን እንድትመረምሩ፣ አገርና ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ እንድትሰሩና በትክክልም የሕዝብን ፍላጎት የማስፈጸም ታላቅ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ከመተቸት ባሻገር መፍትሔ ይሆናል ብለን የምናስበውን ወገናዊ ምክረ ሃሳብም ለማመላከት እንሞክራለን።ስህተትን ማመን ብልህነት ነው፣ ከስህተት መመለስ ደግሞ ታላቅነት ነው።እናም ከስህተታችሁ ተመለሱ፣ ዶክተር አብይ እንዳሏችሁ ቁጥራችሁን ቀንሱ፣ ለሰማንያው ብሔር ከመቶ ዘጠኝ አትለፉ፣ የሰማንያው ብሔር የጋራ ማንነት ሰው ነውና በሰውነት ብትደራጁ አንዳችሁ ለሁሉም ትበቃላችሁ።
እንደ ኦባንግ ሜቶ “ሰው ነኝ” በሉ።በማንነቱ ይደራጅ እያላችሁ ሰውን ማንነቱን አታሳጡት።የፖለቲካ ንግዳችሁን አቁማችሁ በትክክል የሕዝብን ፍላጎት አውቃችሁ ሀገርና ሕዝብን ለሚጠቅም ነገር ታገሉ።ከዚህ ቀደምም ደጋግመን እንዳልነው ፖለቲካ የራስ ጥቅም ማሳደጃ፣ ሕዝብም መነገጃ አይደለም።ጥርሳችሁን ነቅላችሁ ያደጋችሁበትን የነ ኒኮሎ ማኪያቬሌን “ሁሉንም ነገር ለራስ” የሴራና የጥፋት ዲያቢሎሳዊ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን እዚያው ማኪያቬሌ በበቀለበት በጣሊያን ሀገር “ፖለቲካ ማለት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የራስን ጥቅም የሚሰዉበት ቅዱስ ሳይንስ ነው” በሚል ሀገርና ሕዝብን የሚያስቀድመውን የነ ማርከስ ቱሊየስ ሲሴሮ ሰናይ የፖለቲካ እሳቤም ተማሩ።
“ሕዝቤ” እያላችሁ ለራሳችሁ አትሩጡ።እነሆ ለሕዝብ ከሆነ ሕዝብ ችግር ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት እናንተ የት አላችሁ? ነው ወይስ ክፉ ጠላቱን ለመመከት ልዩነቱን ሁሉ ወደ ጎን ትቶ ሕዝቡ አንድ ላይ ስለቆመ፣ እናንተ እንደምታደርጉት ካልተከፋፈለ አንድነቱን ከጠበቀ በእናንተ ዘንድ ሕዝብ ሊባል አይችልም? አንድነት አንድ ዓይነትነት ባይሆንም ኅብረት ኃይል ነውና አንድነት ለዘላለም ይኑር! እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ዓለሙን ሁሉ ይማር! ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
ይበል ካሳ